መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ በጥቅምትና በግንቦት እንደምታካሂድ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት የግንቦቱ ርክበ ካህናት ትንሣኤ በዋለ ከ፳፭ኛው ቀን ጀምሮ ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በጸሎት የተጀመረ ሲሆን ግንቦት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በብፀዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመክፈቻ ንግግር ተጀምሯል፡፡ እኛም ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን መልእክት ቀጥለን እናቀርባለን፡-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፬ኛ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትየጵያ፣
- ብፀዕ አቡነ ያሬድ፣
- ብፀዕ አቡነ ዮሴፍ፣
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡-
የምሕረት አባት፣ የሰላም አለቃ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ስላደረሰን፣ በስሙ ልንወያይም ስላበቃን ክብርና ምስጋና ሁሉን ለሚችል ለኃያሉ አምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡
“ወተጸመዱ ለጸሎት ኵሎ ጊዜ በእንተ ኵሎሙ ቅዱሳን፡- ስለ ቅዱሳን ሁሉ ዘወትር ለጸሎት የተጠመዳችሁ ሁኑ” (ኤፌ.፮፥፲፰)
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኘን የቤተ ክርስቲያናችንና የሃይማኖታችን ቁልፍ የግንኙነት መሣሪያ ጸሎት እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር በሁሉ ያለና የሚገኝ ምሉእ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል፣ ያያልም፣ ነገሮች ከመሆናቸው ወይም ከመታሰባቸው በፊት ሳይቀር ድንበርና ወሰን በሌለው ዕውቀቱ ያውቃል፡፡ ይሁንና ቢያውቅም ለፍጡራን ሁሉ በተለይም አእምሮና ለብዎ ላላቸው መላእክትና ሰዎች የተሰጣቸውን ብሩህ አእምሮ ተጠቅመው የሚበጃቸውን በራሳቸው እንዲመርጡና እንዲወስኑ ፍጹም ነፃነትን አጎናጽፏቸዋል፡፡
ሰዎችም ሆኑ መላእክት ይህንን ነፃነት ተጠቅመው ያለ ምንም ተፅዕኖ ሲወስኑ በውሳኔአቸው ላይ እግዚአብሔር ተፅዕኖ አያደርግም፡፡
ውሳኔአቸውን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት ግን ይጠይቃል፣ ዳኝነትም ይሰጣል፡፡ የመላእክትም ሆነ የሰዎች ውድቀት ሊከሰት የቻለው በዚህ ነፃ ምርጫና ውሳኔ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረን እውነት ነው፡፡ ዛሬም በዓለም እየሆነ ያለው ይኸው እውነት ነው፡፡
ሰው የከፋ ኃጠአትን ለመፈጸም ሲሮጥ ምክርና ትምህርት ከመስጠት ባለፈ እግዚአብሔር በነገሩ ጣልቃ ገብቶ ሲያስቆም አናይም፡፡
“አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ፣ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቃድከ፡- እሳትንና ውኃ አቅርቤልሃለሁ፤ እጅህን ወደፈለግኸው ክተት” የሚለውም ይህንን እውነታ ያመለክታል፡፡
ከዚህ አንጻር ሰው መከራዎችንና ፈተናዎችን እየሳበና እየጎተተ የሚያመጣቸው በራሱ ነፃ ምርጫና ውሳኔ እንጂ በሌላ ተጽእኖ እንዳይደለ እናስተውላለን፡፡
የርኩሳን መናፍስት ተፀዕኖ እንዳለ የምናይበት ጊዜ ቢኖር እንኳ መግቢያቸው የሰው ነፃ ዝንባሌ እንደሆነ በአዳምን ሔዋን ያየነው እውነት ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ደግሞ ሰዎች በሌሎች ምክንያቶች ሲፈተኑና መከራ ላይ ሲወድቁ የምናየው እውነት ነው፤ ከዚህም አኳያ በቃየን ምክንያት አቤል ሕይወቱን ሲያጣ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ከወደቁ በኋላ በራሳቸው ምርጫና ውሳኔ ወይም በሌላ ወገን ግፊት ፈተና ላይ ሲወድቁ እናያለን፡፡
- ብፀዕ ወቅዱስ አባታችን፣
- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
የምንኖርባት ዓለመ ሰብእ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ምን ጊዜም ከመከራን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ይህ የማይቀር ነገር መሆኑን የሚያውቅ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን መርሕ ቢኖር፡- “ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፡- ማለትም ወደ ፈተና እንእንዳትገቡ ትግታችሁ ጸልዩ” የሚለው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችንን ተከትሎ ዘወትር ስለ ቅዱሳን እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡
ከዚህ አንጻር ከመከራና ከፈተና ለመዳን የተሰጠን የመዳኛ ስልት ተግቶ መጸለይ ነው፤ ስንጸልይም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለቅዱሳን ሁሉ ተግተን ዘወትር መጸለይ እንዳለብን ተነግሮናል፤ ኃላፊነትም አለብን፡፡
ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ አንጽታ ስለቀደሰቻቸው ምእመናን ልጆቿ ዘወትር ስትጸልይ የምትኖረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ስለሆኑ ምእመናን ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለሙ ሁሉ ማለትም ስለ ሰማዩ፣ ስለ ምድሩም፣ ስለ እንስሳቱም በአጠቃላይ ስለ ፍጥረት ሁሉ ትጸልያለች፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሀገራችን፣ በሕዝባችንና በደመ ክርስቶስ በተቀደሱ ክርስቲያን ልጆቻችን ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ ስለሆነ ከምን ጊዜም በላይ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጸልይ፣ ልናለቅስና ልናዝን ይገባናል፡፡
ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች፣ ምእመናንና ምእመናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲጸናባቸው ቅዱስ ሲኖዶስን በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ይህንን የፈተና ጊዜ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠባሳ ታሪክ መሆኑ አይቀርም፤ በእግዚአብሔርም ተጠያቂነትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ምእመናን ልጆቻችንም በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጠ በጣም መጠንቀቅ አለብን፡፡
ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጎዱ ለሚገኙት ምእመናንና ምእመናት እንደዚሁም በአጠቃላይ ያለ ፍትሕ እየተጎዱ ለሚገኙ ሰዎች መፍትሔ አምጪ አካል ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡ ይህንንም ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠው የጥበቃ ኃላፊነት መሠረት በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስ ማለትም መጠለያ፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና መድኃኒት በማቅረብ ሊያከናውነው ይገባል፡፡ ይህ መሰሉ ቅዱስ ተግባር ለቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ነገር ሳይሆን ስታደርገው የነበረና አሁንም እያደረገችው የሚገኝ ነው፡፡ የአሁኑ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የችግሩ ክብደትና ውስብስብነት ማየሉ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሕልም አለ ተብሎ መተኛት እንደማይቀር ሁሉ ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ዓቅምን በማየት የምእመናንን ትብብርና እገዛ በመጠየቅ፣ እንደዚሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናትና ልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከራውንና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል፤ ለዚህም የዛሬ ሠላሳ ዓመት ገደማ የነበረው ዓይነት አሠራር ዘርግተን ብንሠራ ሰውን ከረሃብ እልቂት ማዳን እንችላለን፡፡
ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ዙሪያ በሰፊው መክሮበት ውሳኔ እንዲያሳልፍ በዚህ የመክፈቻ ጉባኤ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡
በመጨረሻም፡-
ለመንግሥትም ሆነ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንደዚሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምንፈልገው የአደራ መልእክት ቢኖር፣ የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ሲባል አስፈላጊ የሆነ ዋጋ መክፍል እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ ዋስትና ያለው ሰላም በሀገራችን ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነት መፈጸም ሲችሉ ነው፡፡
ስለሆነም ይህ ለነገ የማይባል፣ የህልውናችን ጥያቄ መልስ መሆኑን አውቀን ሁላችንም በዚህ መልካም ሥራ እንድንተባበር በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላለፋለን፡፡
እግዚአብሔር የተባረከ የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ