ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ጌታችን ምሥጢረ ቊርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ በወንጌልም እንደተጻፈው ፋሲካውን የሚያከብሩበት ቀን ሲደርስ ጌታ ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሒዳችሁ ፋሲካን እንበላ ዘንድ አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም በየት እንድናዘጋጅልህ ትወዳለህ አሉት? ወደ ከተማ ገብታችሁ የውኃ ማድጋ የሚሸከም ስምዖን የተባለ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደ ገባበት ቤት እርሱን ተከተሉት፤ መምህር ከደቀ መዛሙርቶቼ ጋር ፋሲካ የሚያደርግበት አዳራሽ ወዴት ነው ይልሃል? በሉት እርሱ የተነጠፈውንና ታላቁን አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም ፋሲካን አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም ወደ ተላኩበት ከተማ ገብተው አልዓዛርን የውኃ ማድጋ ተሸክሞ አገኙት፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ለስምዖን ጌታ በቤቱ ፋሲካን ሊያዘጋጅ መሻቱ እንደሆነ ነገሩት፤ እርሱም የፍጥረታት ጌታ በቤቱ ሊመጣ እንዳለ አስቦ ተደሰተ፤ ወደ ሚስቱ አክሮሲናም ሔዶ ይህ አልዓዛርን ከሞት ያስነሳ እኔንም በኃጢአቴ ይቅር ይለኛል፤ ያነጻኝ ዘንድ ከሐዋርያት ጋር በቤታችን ይመጣል አላት፤ አክሮሲናም እጅግ ተደሰተች፡፡

ጌታችንም ጊዜው ሲደርስ ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከጌታ እግር ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው፡፡ ይሁዳ ግን ይህን ሰዓት አልነበረም፤ ውጪ ከሻጭና ለዋጭ ጋር ገንዘብ ሲደራደር ነበር፤ ስምዖንም ለሚስቱ አክሮሲና ጌታና ሐዋርያት የሚገቡበት በእግራቸው የሚረግጡት ምንጣፍ እንድታነጥፍ አዘዛት፡፡ አክሮሲና ግን የጌታን መልክ አታውቀውም ነበር፤ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ሲጸልዩ አይታ ‹‹ከእናንተ ውስጥ መምህሩ ማነው›› አለቻቸው፤እነርሱም ዝም አሉ፤ መልከ መልካም ወደ ሆነውና የጌታ ወዳጅ ወደሆነው ዮሐንስ ተመልክታ እርሱ ይሆን አለች፤ ጴጥሮስ ግን ቀበል አድርጎ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከውስጠኛው ክፍል ቆሞ ይጸልያል፤ ጌታ እርሱ ነው›› አላት፡፡ እርሷም ገብታ ሰገደችለት፤ ይሁዳም በመጨረሻ ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ አለው፡፡ በር ጠባቂውም እለእስክንድሮስም የተነጠፈውን እስካጥፍ ጠብቅ ብሎ ዘለፈው፤ ልብሱንም አንስቶ አስገባው፤ /ግብረ ሕማማት ፭፻፹፫-፫፻፹፭/፡፡

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል (ማቴ. ፳፮፥፯-፲፫)፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም የታዘዘውን ለሕዝቡ ነገረ፤ ዅሉም እንደ ታዘዙት ፈጸሙ፡፡ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ መቅሠፍት ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብጻውያንን ቤት በሞተ በኵር ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ አልፏል፡፡ ፋሲካ መባሉም ይህን ምሥጢር ለማስታወስ ነው (ዘፀ. ፲፪፥፩-፳)፡፡

በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች አገር እንደ መኾኗ ይህን ሥርዓት ትፈጽም ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ‹ፋሲካ› ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ጌታችን በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ ምሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስም ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን ‹ፋሲካችን› እንለዋን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱)፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ስያሜዎች

 ጸሎተ ሐሙስ

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ ያደረሱበትን መከራ በማሰብ የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ሆሳዕና ማግስት ጀምሮ ሰሙነ ሕማማትን በሐዘን፣ በጸሎትና በስግደት ታሳልፈዋለች፡፡ ለቀናቱንም የተለያየ ስያሜ ሰጥታ ሥርዓቱን ታከናውናለች፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  • ሰኞ፡– አንጽሆተ ቤተ መቅደስ(በቤተ መቅደስ ሲሸጡና ሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት) ፣ እንዲሁም አምላክ ሲሆን የእኛን ሥጋ ተዋሕዷልና ተራበ፡፡ ለምልማ ከነበረችው በለስ ፍሬ ይበላ ዘንድ ጎበኛት ነገር ግን ፍሬ አጣባት፡፡ በለሷንም ረገማት፡፡ ስለዚህም መርገመ በለስ ተባለ፡፡
  • ማክሰኞ:የጥያቄ ቀን፣ የትምህርት ቀን
  • ረቡዕ፡- የምክር ቀን (አይሁድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉት ዘንድ የተማከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን ነው፡፡ ይሁዳም በሰላሣ ብር አሳልፎ ሊሰጣቸው የተስማማበት ቀን ነው፡፡

 ጸሎተ ሐሙስ

ስለ ሦስቱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ይህን ያህል ካልን ጽሁፋችንን ጸሎተ ሐሙስ ላይ ትኩረት አድርገን እንቀጥላለን፡-

ጸሎተ ሐሙስን ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምስጢር ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣ የነፃነት ሐሙስ እየተባለም ይጠራል፡፡

ሕጽበተ ሐሙስ

ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ “ሕጽበተ ሐሙስ” ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን” ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምሥጢር ቀን

ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን” ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ

መድኃኒታችን ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ይህ ዕለት “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ “ኪዳን” ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ሆነ ሐሙስ “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ

ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ሆነ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ ባሮች ሳይሆን ወዳጆች ተብለን በክርስቶስ ተጠርተናልና፡፡

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሆሉ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፬፥፲፮ የሚገኘውን ሰፊ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎችም ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ያካትታሉ፡፡ ጌታችን እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ ለደቀ መዛርቱ ምሥጢሩን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲቻለው በሰፊ ማብራርያ እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን ከዚህ እንማራለን፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠውም በዚሁ ዕለት ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ነው (ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፰)፡፡

በጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደ ተለመደው ይከናወናሉ፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ሕጽበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ሕጽበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፡-

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲሆን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

የሰሙነ ሕማማት ዕለታት

ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ስለ ተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት ስለሚነገርበት ቅዱስ ሳምንት ይባላል፡፡ በተጨማሪም የመጨረሻ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመኾኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ግብረ ሕማማት መጽሐፍ እንዲሁም ከሌሎች ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ባዘጋጀው መዝሙር ያመሰግናሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ መኾኑ ይነገራል፡፡ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም

 ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ. ፶፫፥፬-፲፪)፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መኾኑን በማሰብ፤ ከማንኛውም የሥጋ ሥራ በመታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር ሰሙነ ሕማማትን እናከብራለን፡፡ ብድራትን የማያስቀረው አምላካችን እግዚአብሔር መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎናልና፡፡

በሕማማት ሳምንት ውስጥ ከሚገኙት ዕለታት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (ሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሰኞ

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አንደኛ፡- ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ፡- ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡

ፍሬ ያልተገኘባት ዕፀ በለስን ረግሟል፡

በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ በማግሥቱ ተራበ የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም ይላል(ኢሳ.፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበር፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፡-የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው” ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ ተራበ  ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በርግጥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባር ፍሬ የፈለገ መኾኑን ለማጠየቅተራበ ተባለ፡፡

በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› ብሏል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ ርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሦኩሰ

ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው” ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ እርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል “ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ይለናልና እግዚአብሔር

ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡የሰው ልጅ

ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?” ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡

 የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከቤተ መቅደስ አስወጥቷል፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ አይሁድ የጸሎት ቤት የሆነውን ቤተ መቅደሱ የገበያ አደባባይ አድርገውት አገኘ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አይሁድ ያደረጉትን የማይገባ ሥራ ያስወግድ ዘንድ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ አስወጣ፡፡ “በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ፣ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” እንዲል(ማቴ.፳፩፥፲፪-፲፫)፡፡

 ማክሰኞ

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ የትምህርት ቀን ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማር. ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ ሉቃ. ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰)፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑም ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲሆኑ፣ ጥያቄውም፡- “በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ?

ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?” የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን መድድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀናቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡

ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን በራሴ ሥልጣን ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡ ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው

ወይስ ከምድር?” ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ከሰማይ ነው ቢሉት” ለምን አላመናችሁበትም?” እንዳይላቸው፤ከሰው ነው ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡

ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?” በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ዓለም የሚወደው የገዛ

ወገኑን ነው” የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

 ረቡዕ

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፡-

አንደኛ፡- የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ  ተማክረዋል፤ ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡ ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡

ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ምን ትሰጡኛላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ”  በማለት ጌታችንን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል (ማቴ.፳፮፥፲፭)፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ አሰምቶ ነበር፡፡

ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” በማለት ያቀረበው አሳብአዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮)፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ሁሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡

ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን ርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው ተብሎ እንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?” ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም ብቻ በመያዝ እምነታቸውን፣ በገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳውያን ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡ስምዐ ተዋሕዶ ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት

ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ በተለይም አእሩግና ሕፃናት “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም” በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ “ሆሼዕናህ” የሚል ትርጉም ሲኖረው “እባክህ አሁን   አድን” ማለት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ “ኦ እግዚኦ አድኅንሶ፤ ኦ እግዚኦ ሠርሕሶ፤ ብሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው” እያለም ዘምሯል፡፡ (መዝ.፩፻፲፯፥፳፭-፳፮)፡፡  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መነሻ በማድረግ ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ሰጥታ ታከብረዋለች፡፡ ስያሜውንም ያገኘው በዕለቱ ከሚዘመረው መዝሙር ነው፡፡

ዕለቱን በተመለከተ የተለያዩ ምሳሌዎች ይመሰላሉ፡-

የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/፡-

ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫም ነው፡፡ እናታችን ሣራ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ በእርግና ዘመኗ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የጎበኛትን አምላክ ለማመስገንና የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ጠይቀዋታል፡፡

የዮዲት አሦራውያንን ድል ማድረግ፡-

የአሦር ንጉስ ናቡከደነፆር እስራኤልን ለመውረር፣ ሀገሪቱንም ለማጥፋትና ለመበርበር ተነሣ፤ የጦር ቢትወደዱን ሆሎፎርኒስን ልኮ ያጠፋቸው ዘንድ ወሰነ፡፡ ሆሎፎርኒስም የጌታውን ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ሀገሪቷንም ይበዘብዛት ዘንድ ሠራዊቱን አስከትሎ በእስራኤል ላይ ዘመተ፡፡

ዮዲትም ወሬውን በሰማች ጊዜ በራሷ ላይ አመድ ነስንሳ፣ ማቅ ለብሳ ጸለየች፡፡ ጸሎቷንም በጨረሰች ጊዜ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች፤ ጌጣ ጌጦችዋንም አጥልቃ ወደ ሆሎፎርኒስ ቀረበች፡፡ በደም ግባቷም ተማረከ፣ ግብዣም አደረገላት፡፡ ከመጠን በላይ ጠጥቷልና ራሱን በሳተ ጊዜ በራሱ ሰይፍ አንገቱን ቆረጠች፤ በግንብ ጫፍ ላይ እንዲሰቅሉትም አደረገች፤ አሦራውያንም በሽንፈት ተመለሱ፡፡

የእስራኤል ሴቶችም ዝናዋን ሰምተዋልና “ያይዋትና ይመርቋትም ዘንድ ወደ እርሷ ሮጠው ተሰበሰቡ፤ ታላቅ በዓልንም አደረጉላት፤ ዘንባበውንም በእጇ ያዘች፤ ከእርሷ ጋር ላሉት ሴቶች ሰጠች፡፡ በሕዝቡም ፊት ሴቶችን ሁሉ እየመራች በዝማሬ ሄደች፤ የእስራኤልም አርበኞች ሁሉ የጦር መሣሪያቸውን ከዘንባባ ጋር ይዘው እየዘመሩ ተከተሏት” እንዲል፡፡ (ዮዲ. ፲፭፥፲፩-፲፬)፡፡

በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ሆኖ ሕፃናትና አእሩግ “ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል” (የማቴ. ወንጌል አንድምታ) እያሉ ዘንባባ ይዘው ሲዘምሩ ኦሪትንና ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ግን “መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ብለውታል፡፡ ጌታችንም መልሶ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ሲል መልሶላቸዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ “እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡” እንዲል (ዘካ.፱፡፱)፡፡

ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲል በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ተጉዟል፡፡ (ማቴ.፳፩፥፬፤ ማር.፲፩፥፩-፲፤ሉቃ.፲፱፡፳፷-፵፤ ዮሐ.፲፪፤፲፭)፡፡

፩. አህያዋና ውርንጫዋ፡- 

በዚህ ዓለም አህያ ለሸክም የሚያገለግል፣ የተናቀ፣ ነገር ግን ትሑት የሆነ እንስሳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አህያ እንደ በቅሎ ሰጋር እንደ ፈረስ ፈጣን አይደለም። በአህያ የተቀመጠ ሰውም አሳድዶ አይዝም፤ ጋልቦ ሮጦም አያመልጥም። ተሸክሞ እንኳን በዱላ እየተደበደበ አህያ ጌታውን በቅንነት ያገለግላል። ጌታችን በዚህች ትኁት በሆነችው አህያ መገለጡ በትኁታን ለማደሩ ምሳሌ ነው።

ጌታችን የተቀመጠባቸው አህዮች አንደኛዪቱ ጭነት የለመደች ውርንጫይቱ ደግሞ ገና ያልለመደች ናት። አህያይቱ የኦሪት ምሳሌ ስትሆን ቀንበር መሸከም መቻሏ ሕገ ኦሪትን መጠበቅ የለመዱ የእስራኤል ዘሥጋ፣ ውርንጫዪቱ ደግሞ ቀንበር መሸከም የማትችል ስትሆን የአሕዛብ ምሳሌ ናት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሁለቱም ተቀምጦባቸዋል። አህያይቱ ቀንበር መሸክም የለመደች እንደሆነች ሁሉ ኦሪትም ሕግ ናትና፤ ውርንጫይቱ ቀንበር መሸክም ያልለመደች እንደሆነች ወንጌልም ያልተለመደች ሕግ ናትና፡፡ (ወንጌል አንድምታ)፡፡

ልብስ:- 

ደቀ መዛሙርቱ አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ከታሰረችበት ቦታ ፈትተው እንዳመጡለት በዚያ የነበሩት ሰዎች ልብሳቸውን በአህያዪቱና በውርንጫዪቱ ጀርባ ጎዘጎዙ፤ አህያዪቱ ተራምዳ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ ልብሳቸውን አነጠፉ። ይኽም ምሳሌ ነው። ልብስ የውስጥ ገመናን ሸፋኝ ነው። አንተ ገመናችንን ከታች ነህ ሲሉ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት። በሌላ በኩልም ልብስ ክብር ነው፤ ያንን የሚያስከብረውን ልብስ አነጠፉለት። ክብራችን አንተ ነህ ሲሉ ክብራቸውን ዝቅ አደረጉለት። እግዚአብሔር በረድኤት ሲያድርብን ይንቁን ያንገላቱን የነበሩት ሁሉ ያክብሩናል። ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ መከራ ተፈራርቆባቸዋል። ዓለም ትቢያና ጉድፍ አድርጓቸዋል። ይኹን እንጂ በሃይማኖታቸው ጽናት በምግባራቸው ቅናት እግዚአብሔር አድሮባቸው ሁሉ ያከብራቸዋል። አስጨናቂዎቻቸውን ሳይቀር ይገዙላቸዋል።

ጌታችን በቤተ መቅደስ፡-

 ሕዝቡም በብዙ ምስጋናና እልልታ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ እያነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ ይልቁንም ሽንገላ ከሌለበት ከሕፃናት አፍ የሚፈልቀው ምስጋና እየቀረበለት በልዩ ግርማ ጌታችን በኢየሩሳሌም አደባባይ አቋርጦ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር በሥጋ ተገልጦ እየተመላለሰ ባገለገለባቸው ዓመታት ውስጥ ከተቆጣባቸው ጥቂት ጊዜያት አንዱ በሆሳዕና ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገባ ነው። የጸሎት ቤት የሆነችውን የእግዚአብሔር ቤት አይሁድ የገበያ ቦታ የቅሚያና የዝርፊያ አደባባይ አደረጓት። በዚህም ትሑቱ ጌታ ተቆጣ። በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን አስወጣቸው። ወንበራቸውን ገለበጠው። ቤቱን ቀደሰው። “ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል” እንዲል ቅዱስ ዳዊት። አነፃው፤ ለየው፤ አከበረው፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ይኽን ቤት ነገረ ምፅአቱን ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበት ወቅት ትቶት ሄዶ ነበር። “ጌታችን ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ” እንዲል ቅዱስ ማቴዎስ። የሆሳዕና ዕለት ግን ለሐዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲሆን ነጋዴዎቹን አጭበርባሪዎቹን አውጥቶ አጽድቶ ሰጠን። በዚያም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ “በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም” ተብሎ እንደ ተጻፈው። ማቴ ፳፩፣ ፲፬።

የሊቃነ ካህናትና የጸሐፍት መቆጣት፡-

የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ክቡር በሆነ ምስጋና መመስገን፣ የቤተ መቅደሱ በክርስቶስ መጽዳትና ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ሊቃነ ካህናትንና ጸሐፍቱን አላስደሰታቸውም። በክፋትና በተንኮል ካባ እንደተጀቦኑ ጻድቃን መስለው ለዘመናት ትሑትና የዋህ የሆነውን ሕዝበ እግዚአብሔር ሲያታልሉ የነበሩት እነዚህ አካላት በጽድቁ ክፋታቸውን የሚገልጥባቸው የክርስቶስ በክብር መገለጥ እንዲሁም መመስገን አስቆጣቸው። የእርሱ መገለጥና መመስገን እነርሱን የሚያሳንስ ክፋታቸውን የሚገልጥ መሆኑን ተረዱት። ጌታችን በወንጌል “ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም (ዮሐ. ፫፣፳)” እንዳለው ሆነባቸው።

ትቶአቸው ሄደ፡-

የታሰሩትን ፈትቶ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ፣ ቤተ መቅደሱንም ባርኮ ፈውስ በረከት አሳድሮበት፣ ተመስግኖበት ለዘላለምም የሚመሰገንበት መሆኑን ለተቃወሙት አስረድቶ ሲያበቃ “ትቶአቸው ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ። በዚያም አደረ፡፡” ክህነታቸውም አለፈች። ያላቸውን ክብር፣ ሀብት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅንና ትሑት ልቡና ለነበራቸው ለሐዋርያት ተሰጠች።

በአጠቃላይ በዓለ ሆሳዕና በዚህን ቀን አህዮቹ ከጌታችን የተላኩላቸውን ፈቺዎቻቸውን (ደቀ መዛሙርቱን) አላስቸገሯቸውም። እንደ ልቧ መቦረቅ የምትወድ ውርንጫ እንኳን አደብ ገዝታ ፈቺዎቿን ተከትላ ሄደች። እኛስ? ከታሰርንበት የክፋትና የኃጢአት ሁሉ ማሰርያ መች ይሆን የምንፈታው?  እንግዲህ እንደዚያን ዕለት ሰዎች ልብሳችንን ሳይሆን ልባችንን፣ የዛፍ ቅርንጫፍ ሳይሆን ራሳችንን በጌታችንና የእርሱ እውነተኛ አገልጋዮች በሆኑ በቅዱሳኑ ፊት ዝቅ እናድርግ። ለዚህም የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን። አሜን።

ደብረ ዘይት

መ/ር በትረ ማርያም አበባው

ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ፣ የወይራ ዛፍ የሚበዛበት ተራራ ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ሲሰጥ አምስተኛውን እሑድ ደብረ ዘይት ብሎታል። በዚህም ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱና ምልክቶቹ ለቅዱሳን ሐዋርያት ነግሯቸዋል።

በዚህ የዐቢይ ጾም አምስተኛው እሑድ ላይ በስፋት የሚነገረውና በሥርዓተ ማኅሌቱም የሚቆመው ዳግም ምጽአትን የሚያወሳ ጉዳይ ነው። “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ እንተ ባሕቲቶሙ ወይቤልዎ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንት ተአምሪሁ ለምጽአትከ ወለኅልቀተ ዓለም፤ ያን ጊዜ ጌታ በደብረ ዘይት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፡- ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠይቀውታል። (ማቴ. ፳፬፣፫)

 ምጽአት ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ የትርጓሜ ስልት ምጽአት እንደ ጊዜ ግብሩ ይተረጎማል፡፡ ለምሳሌ፡- “እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ” (መዝ. ፵፱፣፩) የሚለውን ብንመለከት በሦስት መንገድ ሲተረጎም እናገኘወለን፡፡ አንደኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል ረድኤት ይሰጣል ተብሎ ይተረጎማል። ሁለተኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል የማይታየው ረቂቁ አምላክ ሥጋን ተዋሕዶ ይታያል ማለት ነው። ሦስተኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል ዓለምን ለማሳለፍ በኃጥኣን ሊፈርድባቸው ለጻድቃን ሊፈርድላቸው ይመጣል ማለት ነው።

ከምጽአት በፊት የሚታዩ ምልክቶች

. ብዙዎች በሐሰት እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉ (ማቴ. ፳፬፭ )፡-

ይህን የመሰለ በዓፄ ዘድንግል ዘመነ መንግሥት በአማራ ሳይንት እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበር። ንጉሡም “እስመ ይትነሥኡ ሐሳውያነ መሲሕ፣ ወሐሳውያነ ነቢያት፣ ወይገብሩ ተአምራተ ወመንክራተ ዐበይተ ለአስሕቶ፤ ሐሳውያን ነቢያት፣ ሐሳውያን መምህራን ይነሳሉ፤ ሰውን ያስቱ ዘንድ ጽኑ ጽኑ ተአምራትን ያደርጋሉ።” እንዲል (ማቴ. ፳፬፣፳፬) ድፍረት የተሞላበትን ትምህርቱንና ሐሳዊነቱን ተረድተው አስገድለውታል፡፡

ተአምርን ኃጥኣንም ጻድቃንም ሊያደርጉት ይችላሉ። በሙሴ ዘመን የነበሩ ጠንቋዮችም ተአምር ሠርተዋል። ሊቀ ነቢያት ሙሴም ተአምር ሠርቷል።

ስለዚህ ተአምር ብቻ ዓይተን አንከተልም። መንፈሳዊ ሕይወቱ በምልአት ተጠንቶ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ ከሆነ አስተምህሮውም ትክክል ከሆነ እንጂ ተአምር ብቻ ስላደረገ አንድ ሰው ትክክል ነው አይባልም። እንግዲህ በድፍረት እኔ ክርስቶስ ነኝ የሚል ሐሳዊ መሲሕ እንደሚመጣ፣ የክርስቶስ ያልሆኑ ነገር ግን የክርስቶስ ነን ብለው የሚመጡ ሐሰተኛ መምህራንም እንደሚነሡ ይነግረናል።

. ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል (ማቴ. ፳፬፯)፡-

አንዱ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ ይጠላዋል፤ አንዱ መንግሥት ሌላውን መንግሥት ይጠላዋል። ይህማ ቀድሞስ ነበረ አይደለምን ቢሉ በዝቶ ይደረጋል ማለት ነው።

. ረኀብ፣ ቸነፈር ይመጣል (ማቴ. ፳፬፱)፡-

ያን ጊዜ ለጸዋትወ መከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገርፏችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ ይጠሏችኋል። በእኔ ስም ስላመናችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ይህ ለጊዜው ለቅዱሳን ሐዋርያት የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው ግን እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ክርስቲያኖች ነው።

. ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይስታሉ (ማቴ. ፳፬፲)፡-

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “ሃይማኖት አንዲት ናት” (ኤፌ. ፬፣፬)፡፡  ይህ ሆኖ ሳለ ግን ሰይጣን በዘራው ኑፋቄ፣ ከመጻሕፍት ያላገኙትን፣ ከመምህር ያልተማሩትን፣ በልብ ወለድና በመሰለኝ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል እንደ ቃሉ ሳይሆን ለራሳቸው ስሜት እንዲስማማ እየተረጎሙ ብዙዎች ከአንዲቱና ርትዕት ከሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል። ብዙዎች በሃይማኖታቸው ይስታሉ በማለት በሃይማኖት የሚጸኑት ጥቂቶች መሆናቸውን ይነግረናል።

. ፍቅር ትቀዘቅዛለች (ማቴ. ፳፬፲፪)፡-

የሕገ እግዚአብሔር ፍጻሜው ፍቅር ነው። ሕግጋት በሙሉ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ተብለው ይከፈላሉ። የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫው ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅ ነው። “ዘያፈቅረኒ ይዕቀብ ቃልየ፤ የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቅ” ብሏል (ዮሐ. ፲፬፣፳፪)፡፡ የፍቅረ ቢጽ መገለጫው ደግሞ ሊደረግብን የማንፈልገውን እና ለእኛ የማንመኘውን በሌላው አለማድረግና አለመመኘት ሲሆን ለእኛ ሊደረግልን የምንፈንገውንና የምንመኘውን ደግሞ ለሌላውም ማድረግና መመኘት ነው። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ዘሌ.፲፱፣፲፰ ይላልና”።

በመጨረሻው ዘመን ግን ፍቅር ትቀዘቅዛለች። ራስ ወዳድነት ይበዛል ማለት ነው። “ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት። ወይከውኑ ሰብእ መፍቀርያነ ርእሶሙ ባሕቲቶሙ ወመፍቀርያነ ፈጊዕ ወንዋይ፤ በመጨረሻው ዘመን ክፉ ዘመናት እንደሚመጡ ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ ይሆናሉ። ገንዘብን ወዳጅ ይሆናሉ” ተብሏል። (፪ኛ ጢሞ .፫፣፩-፫)፡፡

ምጽአት መቼ ይሆናል?

ዳግም ምጽአት መቼ እንደሚሆን አይታወቅም። ምጽአት መቼ እንደሚሆን የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ “ወበእንተሰ ይእቲ ዕለት ወኪያሃ ሰዓት አልቦ ዘየአምራ፤ ያችን ሰዓት ያችን ዕለት የሚያውቃት የለም፡፡” (ማቴ. ፳፬፣፴፮) እንዲል የሰው ልጅ ምጽአት መቼ እንደሚሆን ሰለማያውቅ መልካም ሥራን እየሠራ ተግቶ እንዲጠብቅ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ በኋላም “ድልዋኒክሙ ሀልው፤ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ብሎናል። ስለዚህ ንስሓ ገብተን፣ ሥጋውን ደሙን እየተቀበልን መልካም ሥራን እየሠራን ፈጣሪያችንን እንጠብቀው።

ፍርድ በምጽአት

መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በምጽአት “ለሁሉ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ” (መዝ. ፷፪፥፲፪)  ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባው እንደ ሥራው ፍርድ የሚሰጥ ያን ጊዜ ነው። “አሜሃ ይብሎሙ ንጉሥ ለእለ በየማኑ ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ ለአቡየ ትረሱ መንግሥተ ሰማያት ዘድልው ለክሙ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም፤ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥተ ሰማያትን ውረሱ” በማለት መልካም ሥራ የሠሩትን በቀኙ ያቆማቸዋል። (ማቴ. ፳፭፣፴፬)።

ሕይወታቸውን በከንቱ ያሳለፉ፣ ከመልካም ሥራ ርቀው ሲቀጥፉና ሲበድሉ፣ ለክፉም ሲተባበሩ ለነበሩት ኃጥኣን ደግሞ “ሑሩ እምኔየ ርጉማን ውስተ እሳት ዘለዓለም ዘድልው ለሰይጣን ወለመላእክቲሁ፤ እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደተዘጋጀው የዘለዓለም እሳት ሒዱ” ይላቸዋል፤ በግራውም ያቆማቸዋል።

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለእያንዳንዱ የዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ሰጥታ የምታስተምር ሲሆን አምስተኛውን የዐቢይ ጾም ሰንበት ደብረ ዘይት (ዕለተ ምጽአት) በማለት ሰይማዋለች፡፡ በዕለቱም ከዋዜማው ጀምሮ የሚዜመው ዜማ፣ የሚነበቡት ምንባባት፣ የሚሰበከው ስብከት ሁሉ ዕለቱን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

ደም መለገስ ይቻላል?

የክርስትና ሕይወት መሠረቱ ፍቅር ነው፡፡ የክርስቲያኖች የእምነታቸውን መሠረት የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ በመስጠት ፍቅሩን  ገልጦልናል፡፡ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት፤ ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም“ (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) በማለት የፍቅርን ተእዛዛት ሰጥቶናል፡፡

ፍቅር የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ “በወንድማማቾች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤  የምትፈራሩም ሁኑ፣ እርስ በርሳችሁ ተከባባሩ“ እንዲል(ሮሜ. ፲፪፥፲)፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያት በሥራና በቃል ፍቅርን የሰበኩት፤ ስለ ፍቅር እስከ ሞት የደረሱት፡፡

በመሆኑም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሁሉ የፍቅርን ሕግ ልንፈጽም ፍቅራችንን ለሌሎች ልንሰጥ ይገባል፡፡ “…የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመርምር እላለሁ፡፡ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሃ ሆነ” (፪ቆሮ ፰–፱) ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት ክርስቲያኖች ሀብታም፣ ደሀ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ወገን፣ ጠላት ሳይሉ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍጹም የሆነ ፍቅራቸው ሊያሳዩ ይገባል፡፡ ይህም ፍቅር ተእዛዘ እግዚአብሔርን ሚዛኑ  አድርጎ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ ልዩነት የሚፈጸም ነው፡፡ ሰዎች ደም የሚለግሱትም ይህን መሠረት  በማድረግ ለወገኖቻቸው ያላቸውን ፍቅር  በዚሁ ይገልጡታልና ፡፡

ክርስቲያኖች ከፍቅር የተነሣ እንኳን ደማችንን ሕይወታችንንም ልንሰጥ ይገባል፡፡ እንዲያውም  ደም መስጠት በሕይወት እያለን ካለን እንደማካፈል ስለሆነም ታላቅ የክርስቲያንነት መገለጫ ነው፡፡ በእኛ መሥዋዕትነት የሌሎች ሕይወት የሚተርፍ ከሆነ ሕይወታችንንም እስከ መስጠት  ልንደርስ ያስፈልጋልና፡፡

በእኛ መሥዋዕትነት የአንድ ሰው ሕይወት ከሞት ተርፎ ለንስሓ እንዲበቃ ማድረግ ለሰማያዊ ክብር የሚያበቃ ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ደም መለገስ የክርስትና ትምህርት ውጤትም  ነው፡፡

ደማችንን የምንለግሰውም ለምናውቃቸው ሰዎች ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለእኛ እግዚአብሔር ጤናውን ከሰጠን እግዚአብሔር የሰጠንን ያለ ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ልናደርግ ይገባናልና፡፡ ይህ ሲባል ግን ደም የምንለግስበት ዓላማ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓላማው በፍቅር የሰውን ልጅ ሕይወት ማዳን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከዚያ ውጪ መሸጥ መለወጥ አይገባም፡፡ በተረፈ እኛም በታመምንና በተቸገርን ሰዓት ደም ተቀባዮች እስከ መሆን እንደምንደርስ መዘንጋት የለብንም፡፡ ይሁን እንጂ ከሰው ብድርን አገኛለሁ ብለን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋን ለማግኘት ደማችንን ብንሰጥ ለጋሶች ያሰኘናል፡፡ ከሥርዓተ ቤተ ክስቲያን አንጻርም ትርፍ ለማግኘት፣ ለዝና፣ … ወዘተ እስከ አላደረግነውና በፍቅርና በቸርነት ከፈጸምነው የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም፡፡

ምንጭምሥጢሬን ላካፍላችሁ ፳፻፬ ዓም፤ ቁጥር ፩.፪.እና ፫  ገጽ-፩፻፷፱

በእኔ ውስጥ ያሉ ተኩላዎች

ብፁዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

የወጣቶች ጉዳይ ሊቀ ጳጳስ

   ዲ/ን በረከት አዝመራው እንደተረጎመው

ክፍል ሁለት

በኃጢአት የጎሰቆለ አእምሮ እንደ ተኩላ

አእምሮ /Mind/ በኃጢአት ጨልሟል፡፡ በዚህ ጨለማነት ምክንያት ብሩህ ካልሆነውና ከጨለመው አእምሮ የወጡ ብዙ ፍልስፍናዎችና የእምነት መጣመሞች /deviation/ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔርን መካድ መርሑ የሆነው አቴይዝም /atheison/፤ እግዚአብሔር መኖሩን የሚያምነው ነገር ግን ከእርሱ ጋር መገናኘትን የማይፈልገው በዚህ መርሑም “በሰማይ ያለህ አባታችን ሆይ፣ አንፈልግህምና በዚያው ቆይ” የሚለው ኤግዚሰተንሻሊዝም /Existentialism/፤ ሁሉም ነገር /ወንበሩም ድንጋዩም/ የእግዚአብሔር የአካል  ክፍል እንደሆነ የሚናገረው ፓንትይዝም /pantheism/ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አእምሮ የጨለመው በኃጢአት ነው፡፡ አእምሮ ብሩህ ሲሆን ግን እግዚአብሔርን እናውቀዋለን፤ በመኖሩም በሁሉም እየሠራ እንደሆነ እንረዳለን፤ ወደ ዘለዓለማዊው መንግሥት የሚመራን እውነተኛው አምላክ እርሱ እንደሆነ እናውቃለን፡፡

በቅርቡ አንድ ታሪክ በኢንተርኔት አንብቤአለሁ፡፡ የተወሰኑ ልጃገረዶችን በክፍሏ የምታስተምር መምህርት ወደ አትክልት ቦታ ወሰደቻቸው፡፡ ከእነዚህ ወጣት ልጃገረዶች አንዷን ”ከጓደኞችሽ ፊት ሆነሽ መልሽልኝ፤ ይህ ዛፍ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች

“ያ ሕንፃስ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች፡፡

“እግዚአብሔርንስ ታይዋለሽ?”

“አላየውም” ልጅቷ መለሰች፡፡

መምህሯም “ስለዚህ እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም” አለች፡፡

ሌሎች ልጆች በመደናገጥ ላይ ሳሉ አንዷ ልጅ ተነሥታ “መምህር ዛፉ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች፡፡

“ወፎችስ ይታዩሻል?”

መምህሯም “አዎ” አለች፡፡

“ሰማዩስ ይታይሻል?” አለች ተማሪዋ ወደ ሰማይ እያየች፡፡

“አዎ” አለች መምህሯ፡፡

ተማሪዋ ጥያቄዋን ቀጠለች፡፡ “አእምሮሽን ታይዋለሽ?” ስትል ጠየቀች

“አላየውም” ብላ መለሰች መምህሯ፡፡

ተማሪዋም መምህሯን እየተመለከተች “ስለዚህ መምህር አእምሮ የለሽም” አለቻት፡፡

በብሩህና በጨለምተኛ አእምሮ መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማየትና መንካት ምን ልዩነት ይፈጥር ይሆን? የቴሌቪዥን ሞገድን ማየት እንችላለን? ኤሌክትሪክንስን መንካት እንችላለን? ስለዚህ የሉም ማለት ነውን?

ብሩሃን ልንሆን ይገባል፣ ብሩህነትም ሊገኝ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች በመታነጽ ነው፡፡

ዲያብሎስ በተለያየ መንገድ ዕውቀትና ጥበብ ያለን በማስመሰል ያታልለናል፤ እውነተኛው አብርሆት /Enlightmet/ ያለው ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ በዳዊት መዝሙር “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብሏል፡፡ አንተ ብሩህ ነህ /Enlightened/ ከሆንክ ሌሎችን ብሩሃን ማድረግ ለመንገዳቸው ብርሃን መስጠት ይቻልሃል፡፡ ይህም በሥራህ፣ በዘመዶችህ እና በጓደኞችህ ሁሉ ይሆናል፡፡

የሥጋ ምኞት እንደ ተኩላ

ሥጋ ተኩላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሥጋ ነፍስን፣ ነፍስም ሥጋን እንደሚዋጉ እና እርስ በእርሳቸው እንደሚቀዋወሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ይህ ከክርስቶስ መምጣት በፊት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ክርስቶስ ግን ይህን የሥጋ ኃጢአት ዝንባሌ በእኛ ውስጥ ያሸንፈዋል፤ እንቆጣጠረውም ዘንድ ኃይል ይሰጠናል፡፡ በእርግጥ ኃጢአት እንደተመረዘ ማር ይጣፍጣል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ያለች ነፍስ ግን ኃጢአትን መከላከልና መተው ይቻላታል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጻፈ በክርስቶስ “የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ /ኃጢአትን/ ትረግጣለች” እንደተባለ፡፡

በኢንተርኔት የሙሰራጭ የዝሙት /pornographic/ ፊልሞችን ጨምሮ ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባችሁ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንደ ተርታ ነገር እየተለመደ ሲሄድ ዝሙት በሁሉም ቦታ የሚገኝ ተገቢ /normal/ እና ቅቡል /accepted/ እየሆነ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ ወደ በለጠ ጥማት ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ በሥጋ ፍላጎት እየተመሩ በዝሙት ከመውደቅ መታቀብ ሕገ እግዚአብሔርን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ሥጋህን ጨዋማ ውሃ ከሰጠኸው ሁሌም ሳይረካ ሲጠማ ይኖራል፡፡ በክርስትና ግን እስከ ጋብቻ ድረስ በንጽሕና መቆየት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ያለበትን ቅዱስ ጋብቻ በእግዚአብሔር ቅድስና ሆነን ራሳችን በንጹሕ የጋብቻና የግንኙነት ቅዱስ ሕይወት እንመራ ዘንድ ይገባናል፡፡

በሥጋ የምትኖሩ ከሆነ በሥጋችሁም ትሞታላችሁ፡፡ ድል አድራጊ ሊያደርግህ የሚችል ብቸኛው አማራጭ ግን መንፈሳዊነት ነው፡፡ በመንፈስ ስትኖር በእርካታና በደስታ ትኖራለህ፡፡ በጭንቀትና በጾታዊ ፍላጎት /sexual desire/ መካከል ጥብቅ ግንኙነት አለ፡፡ በእግዚአብሔር ታምነህና ደስ ተሰኝተህ የምትኖር ከሆ ግን ከዚህ ጭንቀትና በዚህም ከሚመጣው ተገቢ ያልሆነ የሥጋ ፈቃድና ምኞት ነጻ ትሆናለህ፡፡ በጭንቀትና በስህተት፣ በአስቸጋሪ ነገሮች በተከበበ ሕይወት የምትኖር ከሆነ ምንም ይሁን ምን ደስታን የምታገኝበት መንገድ መፈልገህ አይቀርም፡፡ ከኃጢአት የሚመጣው ደስታ ጊዜአዊና ወዲያው ደግሞ የበደለኝነት እና ጸጸት ስሜት የሚያስከትል በመሆኑ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ደስታ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በእኛ ያደረገው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነውና፡፡ ይህ ደስታ በሕይወታችን የምንረካበት፣ የኃጢአትና የምኞት መንገዶችን እንዳንፈልግ በማድረግ ሁል ጊዜ በርካታ ያኖረናል፡፡ ለዘለዓለማዊ ሕይወትም እንድንበቃ ያደርገናል፡፡

ለማጠቃለል እነዚህን ተኩላዎች ለመከላከል በዚህ መንገድ እንዝመት

  • እኔነት /Ego/፡- በሕይወታችን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እናድርግ እኛነታችን ግን ዝቅ ይበል፡፡
  • አእምሮ /Mind/፡- በእግዚአብሔር ቃል አእምሯችንን ብሩህ እናድርግ
  • ሥጋ /Flesh/፡- የክፉ ምኞት ደስታዎችን ከመፈለግ ተቆጥበን “የወይን ወለላን እስክንረግጥ” ድረስ የደስታ እርካታን የምናገኝበትን መንፈሳዊነትን ለማግኘት እንታገል፡፡

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“በእኔ ውስጥ ያሉ ተኩላዎች”

ብፁዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

የወጣቶች ጉዳይ ሊቀ ጳጳስ

   ዲ/ን በረከት አዝመራው እንደተረጎመው

ክፍል አንድ

እየተነጋገርንበት ያለው ርእስ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በውጭና በውስጥ ያሉብንን ተግዳሮቶች እንዴት መዋጋት እንዳለብን የሚያመልክት ነው፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በእኛ ውስጥ እና ከእኛ ውጭ ያሉ “ተኩላዎች” ናቸው፡፡ እኛ እንደ በጎች ነን፤ ውስጣዊውንና ውጫዊውን ሕይወታችንን እየተፈታተኑ ሊናጠቁ የሚሞክሩት ደግሞ ተኩላዎች ናቸው።

የዛሬው ትምህርት ስለ ውስጣዊ ተኩላዎች ነው፡፡ እነዚህም በሕይወታችን የሚታዩ ውስጣዊ ተቃርኖዎችና ጠላቶች ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና ዘለዓለማዊ የሕይወት ጉዟችን በትክክለኛው አቅጣጫ እንጓዝ ዘንድ ይህንን ርእስ ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ ሁሉን ብናገኝ ዘለዓለማዊነታችንን ግን ብናጣ ምን ይጠቅመናል? ስለዚህ ዘለዓለማዊነትን እንድናገኝ አጥብቀን መሥራትና በሕይወታችን ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ እንደምታዩት ዓለም ትለዋወጣለች፤ ስለዚህ እውነታ ሊሆን የሚችለው የማይለወጠው ዘለዓለማዊነት ነው፡፡ ዓለምና ክብሯም ያልፋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ዓለም ሕይወት አሻግረን ፊታችን ያለውን ልንመለከት ግድ ይለናል፡፡፡ ቁሳዊውን ዓለም ብቻ የሚያስቡ ሰዎች ግን ታላቅ ስህተት ፈጽመዋል፡፡ ወሰንና መጨረሻ ከሌለው ከዘለዓለማዊው ዓለም ከእግዚአብሔር መንግሥት ይልቅ በውስኑ ዓለም ባክነው ይቀራሉና፡፡

የተፈጠርነው በእኛ ውስጥና ውጪ ካሉ ተኩላዎች ጋር አይደለም፡፡ እነዚህ በኃጢአት የሚመጡ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳምንና ሐዋንን ሲፈጥር ያለ እነዚህ ተኩላዎች ነው፡፡ እነርሱ በኤደን ገነት የእግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መኖር እየተሰማቸው ከእርሱ ጋር ይኖሩ ነበር፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከዕፀ በለስ በስተቀር በገነት ውስጥ ካለው ዛፍ ሁሉ ይበሉም ነበር፡፡ የተፈቀደውም ጉዞ ሲደርሱ ከዕፀ ሕይወትም መብላቸው አይቀርም ነበር፡፡ እነርሱ ግን የተለየ ምርጫ መረጡ፡፡ በእርግጥ በዚህ ውሳኔአቸው ብዙም አንጸጸትበትም፡፡ ለድኅነት ታሪክ እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ የሚኖርበትን ነገር ፈጥሯልና እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው በመሆኑ የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን ጠርቶናል፡፡ እነሆ አሁን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እስክንደርስ ድረስም ሁሉ ከፍ ከፍ የምንል ሆነናል፡፡

ስንፈጠር የተፈጠርነው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፡፡ በጥበብና በአእምሮ ቅድስና በምንላቸው በፍቅር፤ በመንፈስና በምግባራት፣ በነፃነትና ነፃ ፈቃድ እንዲሁም በዘለዓለም ሕይወታችን እግዚአብሔርን የምንመስል ሆነናል፡፡ ሆኖም አዳምና ሔዋን ነፃነታቸውን ያለ አግባብ በተጠቀሙበት ጊዜ ከዕውቀት ዛፍ በሉ፤ ኃጢአትን በሠሩ ጊዜ ብሩህ አእምሯቸውን ማጣት ጀመሩ፡፡ ነፃነት ወደ አዳምና ሔዋን ውድቀት አመራ፤ ፈተና ከዲያብሎስ መጣ፤ ከኤደን ገነትም መውጣትም በእግዚአብሔር ተደረገ፡፡

በወደቀው ሰብእናቸው ለዘለዓለም እንዳይኖሩ በማሰብ ከሕይወት ዛፍ እንዳይበሉ በፍርዱ ከኤደን አስወጣቸው፡፡ ለዘለዓለም እንዲኖሩ ቢፈልግም ከድኅነት በኋላ መሆን ነበረበት፡፡ ስለዚህም ከመንግሥቱ ተለይተን እንዳንቀር ገነት ከእርሱ ጋር እንኖር ዘንድ ድኅነትን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡

ስለዚህ የተኩላዎቹ ፈጣሪዎች እኛ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ሁሉን ከፈጠረ በኋላ ሁሉም መልካም ነበርና ሰውንም ከፈጠረ በኋላ “በጣም መልካም” ብሏልና፡፡ ተኩላዎቹ ማደግ የጀመሩት በእኛ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ የውስጥ ተኩላዎች ምንድን ናቸው?

የመጀመሪያው ክፉ እኔነት ነው፡፡ ሁለተኛው የኃጢአት ሕግ የተጠናወተው አእምሮ ነው፡፡ ይህ አእምሮ እንደዚህ እንዲሆን ባይፈጠርም በኃጢአት ከጨለመ በኋላ እንደዚህ ሆነ፡፡ ሦስተኛው ሥጋችን ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋ በራሱ ችግር እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡ ተኩላ የሚያደርገው በውስጣችን የሚኖረው ኃጢአት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዐይን መልካምም ክፉም ነገር ሊያይ ይችላል፡፡ መንፈሳዊ እድገታችንና አኗኗራችንን የሚያሰናክሉት ሦስት የውስጥ ተኩላዎች እንዚህ ናቸው፡፡

የክፉ እኔነት ተኩላ /Ego/

እኔነት እንዴት ተኩላ ሊሆን ይችላል? እኔነት/Ego/ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ተለይተን በራሳችን ውስጥ ታጥረን በትዕቢት፤ በከንቱ ውዳሴና በራስ ወዳድነት እንድንያዝ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ከሚለው መልእክት በተቃራኒ በራሳችን ብቁ እንደሆንን እና አግዚአብሔር ሳያስፈልገን ሁሉን ማድረግ እንደምንችል እንድናምን ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን “ሁሉን እችላለሁ” ብሎ አላቆመም፤ እነዚህን ማድረግ የሚችል በእግዚአብሔር መሆኑን ዐውቋል፡፡ እኔነት የተጠናወተው ሰው በሕይወቱ ያሉትን መልካም ነገሮች ከእግዚአብሔር ጋር ማዛመድ አይፈልግም፡፡ ክፉ እኔነት/Ego/ በኤደን ገነት የኃጢአቶች ምንጭ ነበር፡፡ ዲያብሎስ የወደቀው እንደ እግዚአብሔር  ሊሆን በመፈለጉ ነውና፡፡ አዳምና ሔዋንም በእባቡ የተታለሉት እንደ እግዚአብሔር መሆን ፈልገው ነው፡፡

እግዚአብሔር በሕይወትህ ሲኖር መንፈስህ ከፍ ከፍ ይላል፤ እኔነትህ ግን ዝቅ ዝቅ ይላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ “እርሱ ሊበዛ እኔ ግን ላንስ ይገባል” እንዳለ በሕይወትህ የእግዚአብሔር ቦታ ከጨመረ እኔነትህ /Ego/ እየቀነሰ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሕይወታችን የምንፈልገውም ለዚህ ነው፡፡ በንስሓ፣ በቍርባን፣ በጸሎት፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት፣ በጾም፣ በስግደት እና በምሥጋና እግዚአብሔር በውስጣችን ያድራል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው በማንኛውም ግንኙነት ወደ ላይ የተዘረጋ መስመር እንመሠርታለን፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ወደ ውስጥ እንዘረጋለን እርሱም እኔነት /Ego/ ነው፡፡

ምድራዊው ገጽታ ደግሞ ሥጋዊነት ነው፡፡ ወደ ላይ እንመለከት ዘንድ ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ “ልባችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” የሚለን እኛም “ከመንፈስህ ጋር ነው” ብለን የምንመልሰው ይህንን ነው፡፡ መፍትሔአችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱን በውስጣችን ልንይዝ ይገባል፡፡ ይህንን ምሳሌ ተመልከቱ፡፡ ልብን በጎነ ሦስት/Triangle/ ብንመስለው /በእርግጥም ልብ ሦስት ጎን ቅርጽ አለው፤ ዓለምን በጎነ ሦስቱ /Triangle/ ዙሪያ በተሳለ ክብ ቅርጽ ብንወክላት፣ ውስጥ ያሉት ማዕዘናት በምንም ተአምር በክቡ ሊሞሉ አይችሉም፡፡ ጎነ ሦስት የሆነውን ልብ ለመሙላት በሦስትነት የሚኖረው እግዚአብሔር ያስፈልጋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ፍቅር ግን ልቡናህን በደስታ፣ በቅድስና፣ በጥበብ እና በዘለዓለማዊነት ይመላዋል፡፡ እንድትኖር ወደተፈጠርክለት የእግዚአብሔር አምሳልነት ይመልስሃል፡፡

የክፉ እኔነትን /Ego/ ውጥንቅጥ ለመፍታት እግዚአብሔር ፍቅር፣ አምልኮቱ በልቡናህ ውስጥ ማደግ አለበት፣ በዚህ ጊዜ ክፉ እኔነትህ ይቀንሳልና፡፡

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም

ይቆየን፡፡

ዘረኝነት፤ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው

ክፍልሦስት

ከዘረኝነት ጠባይ ለመራቅ ወጣቶች ምን ማድረግ አለባቸው?

ሥጋዊ ማንነትንና ክርስትናን መለየት

በማነንት ጉዳይ ብዙ ክርክሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምድራዊው ማንነት በሰዎች መንፈስ የተገነባ ሲሆን ሰማያዊው ማንነት ደግሞ በመስቀል ላይ የተገነባ ነው ይላሉ፡፡ ምድራዊ ማንነት ሙሉ በመሉ ሰው ሠራሽ ነው ብሎ መቀበል ቢከብድም ኃላፊ ጠፊ መሆኑ ግን አያጠራጥርም፡፡ በምድራዊው ማንነት ውስጥ በተፈጥሯዊ ሂደት የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፤ በጊዜ ሂደት በመማር ወይም በመላመድ የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ጾታን፣ የቆዳ ቀለምን፤ አካላዊ ቁመና የመሳሰሉትን በተፈጥሮ የምንወርሳቸው ማንነቶች ናቸው፡፡ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ በአጠቃላይ የሰዎች የአኗኗር ዘዬ ከማኅበረሰብ የሚወረሱ ማንነቶች ናቸው፡፡ ግለሰቦችን ወይም ማኅበረሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸው ማንነት ይኖራል፤ የሚለያቸው ማንነትም ይኖራል፡፡

አንድ የሚያደርጉንም ሆነ ልዩ የሚያደርጉን ሥጋዊ ማንነቶች ከሃይማኖታችን ዓላማ ወይም እሳቤ ጋር እስካልተጋጩ ድረስ አክብሮና ተቀብሎ መኖር ሰላማዊና ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ ግጭት ወይም አለመግባባት የሚፈጠረው የራስን አድንቆ የሌላውን ማንቋሸሽ ሲጀመር እንዲሁም የእኔን ማንነት ካልተቀበልክ ብሎ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጫና ለማሳደር መሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ከእግዚአብሔር መንግሥት ሊለየን ይችላል፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል፡፡ (ማቴ. ፯፥፲፪)

በመሆኑም የሌሎች ወንድሞቻችንን ማንነት አክብረን በሰላም መኖር ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ምድራዊ ማንነት ቢኖረውም ከክርስትናው ሊበልጥበት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ማንነት በምድር የሚቀርና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ማንነት ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በፍርድ ቀን የምንጠየቀው የምንናገረውን ቋንቋ ወይም የምንከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም ደግሞ የኖርንበትን ማኅበረሰባዊ ባህል አይደለም፡፡ ስለ ሠራነው መልካም ሥራ እንጂ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለም ስንኖር የማንነታችን ሚዛን ሊሆን የሚገባው ክርስትናችን ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ተራ ነገር ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “በዚህ በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሧት፣ ለምኞቱም እሺ አትበሉት፡፡ ለእግዚአብሔር ራሳችሁን መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት” ይላል፡፡ (ሮሜ ፮፥፲፪)፡፡  ስለሆነም ክርስቲያን ወጣቶች ፖለቲከኞችና የጎሳ አቀንቃኝ ቡድኖች ለራሳቸው ጥቅም በሚቀይሱት የጥፋት መነገድ ተጠልፎ ላለመግባት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡

በወጣትነት ዘመን እንደ ዜጋ ለሀገርና ለማኅበረሰብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደ ሃይማኖት ሰው ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ መትጋት እንጂ ለሥጋም ለነፍስም በማይበጅ ሐሳብ መጠመድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ለሕሊና መኖር

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ “ብፁዓን ነጹሐነ ልብ” በሚለው መጽሐፋቸው “የሃይማኖት ሰው መሆን የሚቻለው መጀመሪያ በሕሊናችን ማዘዝ ስንችል ነው” ይላሉ፡፡ ሕሊና የመፈተሸ፣ የመመርመር፣ የመምረጥ፣ የአመክንዮ ችሎታ አለው፡፡ ሕሊና የእውነት ሚዛን ነው፡፡ ሊባንዮስ የሚባል በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ የታወቀ ፈላስፋ ነበር፡፡ በዘመኑ የምርምር መስክ እጅግ የተራቀቁ ተማሪዎችን ስላፈራ ከነዚህ ለየትኛው የመምህርነት መንበሩን እንደሚያወርስ ቢጠይቁት “ለዮሐንስ ነበር ወደ ክርስትና ተሻገረ እንጂ” ብሎ መለሰ ይባላል፡፡

ዮሐንስ የተባለው ትልቁ የቤተ ክርስቲያችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ታላቁ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕሊናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ ይላል፡፡ ሕሊናን ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ከተራው፣ ከሚለያየው፣ ከሚከፋፍለው አስተሳሰብ፣ ከደሴቱ ከሥርቻው ወደ ኮረብታው ወደ ተራራው ውጡ፤ ወደ ሰማይም ቀና በሉ፤ ተገቢ ቦታችሁን ዐውቃችሁ በዚያ ቁሙ፣ የእውነት ቃል የደግነት ዜና ስሙ፤ አዳምጡም፤ ማለት ነው፡፡ እኛ ሕያውያን ፍጥረታት መሆናችንን ስናስብ የሚለያየንና የሚከፋፍለን አጀንዳ ሁሉ ተራና የማይጠቅም ሐሳብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኃላፊና ቁሳዊ በሆነ አጀንዳ ልቡናችን ከባዘነ ግን ከሕሊና በታች እንሆናለን፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ በንቃት መሳተፍ

በአገራችን በማንነት ላይ የተመሠረተ ግጭት በስፋት የሚስተዋለው ክርስቲያኖች ከፖለቲካና ከውሳኔ ሰጪነት በመራቃቸው ነው፡፡ ክርስቲያን ሲባል የስም ክርስቲያን ሳይሆን ለእውነት የቆመውንና ለእውነት የሚተጋውን ማለታችን ነው፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ለፍትሕና ለሰው ልጅ እኩልነት ይተጉና ፍርድ ጎደለ ደኃ ተበደለ ብለው የሚሠሩ እንደነበር በልዩ ልዩ የታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ ለራሳቸው ዜጋ ይቅርና ለወራሪ ጠላት እንኳ የሚራሩ እንደነበር በታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

ኢትዮጵያውያን በግብረ ገብነት እንዲታወቁ ያደረጋቸው በዋናነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረው የሰው ልጅ ይራራ ዘንድ ግድ ይለዋልና፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያን ይመሩና ያስተዳድሩ የነበሩ ነገሥታት ሁሉ እንከን አልነበራቸውም ማለት እንዳልሆነ ልገነዘብ ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ቢሳተፉ ዛሬ ላይ የምናስተውላቸው መለያየቶች ባልተፈጠሩ ነበር፡፡

ምክንያቱም ዳዊት ደስታ ኦርቶዶክሳውያን እና ፖለቲካ በሚለው መጽሐፉ ከገጽ ፩፻፫ ጀምሮ እንደገለጠው ክርስቲያኖች በፖለቲካው በንቃት ቢሳተፉ ዴሚክራሲ ይሠፍናል፤ የፖለቲካ መረጋጋት ይመጣል፤ አገርን ከመፍረስና ከመበታተን መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያኖች በሀገራቸው በክፉ መሪዎች አንዳይሞቱና ለስደትና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያንም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ተከብሮ በነጻነት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚተጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን መከላከል ይቻላል፤ ብልሹ አሠራር እንዳይኖርና ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፤ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የምንመኘውን መልካም ተግባር መፈጸም ይቻላል፤ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በሰውነቱ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የሥጋም ሆነ የነፍስ ድህነትን ለማስወገድ ዕድል መፍጠር ይቻላል፤ ዛሬ ላይ የምናስተውለው የጎሳ ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻላል፤ ወዘተ፡፡ ነገር ግን አቅምና ችሎታ ያላቸው ክርስቲያኖች በራሳቸውና በውጫዊ ምክንያቶች ከፖለቲካው በመራቃቸው ከላይ የተዘረዘሩትን በጎ ተግባራት ማከናወን አልተቻለም፡፡ ዛሬም ቢሆን አልረፈድምና ወጣቶች በፖለቲካው በንቃት በመሳተፍ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን ከአጥፊዎች ለመታደግ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው 

ክፍል ሁለት

የዘረኝነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?

አንዳንድ የዓለማችን ሀገራት እየተባባሰ የመጣውን የዘር ጥላቻ ለማስወገድ በሕግ አስደግፈው ቢሠሩም ዘርን ወይም ማንነትን መሠረት ያደረ ጥላቻንና መድሎን ማስቀረት አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ ሠለጠኑ በሚባሉት አገራት ሳይቀር የዘረኝነትን ጠባይ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልቻሉም፡፡ የዘረኝነት እሳቤ በአገራችን መቼ እንደገባ በትክክል ባይታወቅም በሰነድ የተደገፈ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ፲፱፻፷ዎቹ ጀምሮ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ሕዝቦች ባለቤት በመሆኗ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ማንነትን የፖለቲካ ማእከላቸው በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ማንነትን መሠረት ያደረገ አለመግባባት ወይም ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡

በሀገራችን በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ግጭት አሁን ባለበት ደረጃ ባይሆንም በታሪክ አጋጣሚ በተለያየ ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት መዋቅር የተደገፈና በማንነት ላይ የተመሠረተ መገፋፋት እየተባባሰ የመጣው ከዐለፉት ሠላሳና ዐርባ ዐመታት ወዲህ ነው፡፡

ስለ ዘረኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው” በማለት ይገልጻል፡፡  እንዲሁም ከሊቀ ነቢያት ሙሴ መጻሕፍት መካከል “አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት” የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ዘሩ አንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው፡፡ (ሐዋ. ፲፯፥፳፮፣ ዘፍ. ፫፥፳፣ ፩፥፳፰)

በመሆኑም አዳምና ሔዋን ለመላው የሰው ዘር አባትና እናት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የኖኅ ዘመን ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት የጥፋት ውሃ መጥቶ በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ባጠፋ ጊዜ ኖኅና ቤተሰቡ ከመጣው የጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የኖኅ ልጆች እንደሆንን መረዳት እንችላለን፡፡ (ዘፍ.፱፥፲፰)

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ በማለት ክርስቲያኖች ገንዘብ ሊያደርጉት የሚገባውን ማንነት አስተምሯቸዋል፡፡፣ ማቴ. ፳፫፥፰)

ከምንም በላይ ክርስቲያኖች ለአንድነት ይተጉ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ ሆኖ አስተምሮናል (ዮሐ. ፲፯፥፳)፡፡ አንድነትንና አብሮነትን አጥብቆ የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክት “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ሆናችሁ ኑሩ” በማለት ክርስቲያኖች ከመከፋፈልና ከመለያየት ሐሳብ እንዲርቁ አስተምሯል፡፡(፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲)

ይኸው ሐዋርያ በመልእክቱ “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳሁም ብልቶች ናችሁ” በማለት ክርስቲያኖች በክርስቶስ አንድ እንደሆንን ይመሰክራል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፲፪፤፳፯)፡፡ በአጠቃላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት የምንማረው መለያየትን ሳይሆን አንድነትን፣ ጠላትነትን ሳይሆን ወንድማማችነትን፣ ጥልን ሳይሆን ሰላምን፣ ራስ ወዳድነትን ሳይሆን መተሳሰብን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን ነው፡፡

ዘረኝነትና የክርስትና ሕይወት አብረው መሄድ ይችላሉን?

ለዚህ ጥያቄ መልሱ አብረው አይሄዱም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው ስንፍና አምላክን እስከመካድ ያደርሳል(መዝ. ፲፫፥፩)፡፡ ዘረኝነት ስንፍና ነው፡፡ ዘረኝነት ሃይማኖትን እስከ መካድ ያደርሳል፡፡ ዘረኝነት ከግብረ ገብነት ያፈነገጠ ጠባይ ነው፡፡ ከግብረገብነት የወጣ ሰው ደግሞ ለምኞቱ ድንበር የለውም፡፡ በዘረኝት የተለከፈ ሰውም ለጥፋቱ ዳርቻ የለውም፡፡ ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ሲሆን ዘረኝነት ደግሞ ሰይጣንን ወይም ዲያብሎስን መምሰል ነው፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩)

ክርስትና አንድነትንና ፍቅርን ይሰብካል፤ ዘረኝነት ደግሞ መለያየትንና ጥላቻን ይደሰኩራል፤ ክርስትና ባልእንጀራን እንደ ራስ መውደድን ያስተምራል፤ ዘረኝነት ደግሞ ባልንጀራን መግደልን ማሳደድን ይሰብካል፡፡ ክርስትና “የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ፤ ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፡፡ እርስ በእርሳችሁም በአንድ ሐሳብ ተስማሙ በማለት ያስተምራል፡፡(ሮሜ. ፲፪፡፲፮) ዘረኝነት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ በቀልን ጠላትነትን ይሰብካል፡፡ ስለሆነም ዘረኝነትን ልንርቀው የሚገባ ክፉ ጠባይ ነው፡፡

ይቆየን፡፡

ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው

ክፍል አንድ

መግቢያ

እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የወጣትነት ዘመን የሽግግር ዘመን ነው፡፡ ይህ ሽግግር በሁለት ይመደባል፡፡ አንደኛው ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት የሚሸገጋሩበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከቤተሰብ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል የሚሸጋገሩበት ዘመን ነው፡፡ ይህ የሽግግር ዘመን ወጣቶች ጊዜያቸውን በማስተዋል ከመሩት ለፍሬ የሚበቁበት በማስተዋል ካልመሩት ደግሞ ለጥፋትና ለውድቀት የሚደራጉበት ጊዜ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ስለ ወጣትነት ዘመን ሲናገሩ “በአበባ ውስጥ የፍሬ እንቡጥ ለመያዝ መጀመሪያ የአትክልቱ አያያዝ ደንበኛ ሆኖ ሲገኝ ይጠቅማል፡፡ ወጣትም ከፍሬ ለመድረስ የሚችለው በወጣትነቱ በሠራው ሥነ ምግባር ነው፡፡ ወጣት ሰውነቱን በቆሻሻ ምግባር ያቆራመደው እንደሆነ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ያቀደውም ነገር ከመንገድ ይመለሳል፡፡ መንፈሳዊ ዕድል እንዲያውም አይታሰብም” ይላሉ፡፡ (ሥነ ምግባር ገጽ ፶፫)

በአጠቃላይ የወጣትነት ጊዜ ለቀጣይ የዕድሜ ዘመናት መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ በማስተዋል መጓዝን የሚጠይቅ ነው፡፡ ወጣቶች በዘመናቸው ልዩ ልዩ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ተግዳሮቶችም አንዱ ዘረኝት ነው፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ወጥነት ያለው ትርጕም ለመስጠት አስቸጋሪ ከሆኑ ቃላት አንዱ ዘር ወይም በእንግሊዝኛው (Race) የሚባለው ነው፡፡ በተለይም ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔር ወዘተ የሚሉ ቃላት በተለያዩ አገራት የተለያየ ትርጕምና ይዘት ሊኖራቸው ስለሚችል ተመሳሳይ ግንዛቤ ለመያዝ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ለአብነት አንዳንድ ሰዎች ከቅርብ ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የሚታየው የሕዝብ አለመረጋጋትና ቀውስ ምንጩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀር ዘርን ወይም ጎሳን ወይም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ ፖለቲከኞችም ይሁን የፖለቲካ ተንታኞች ይህን ይበሉ እንጂ አሁን ላይ ያለው የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት መንግሥታዊ መዋቅሩ በዘር፣ ወይም በጎሳ፣ ወይም ደግሞ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው አይልም፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፮ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥት አንጻር ከተመለከትነው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለብቻው ነጥሎ በዘር፣ ወይም በቋንቋ፣ ወይም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ነው እንደማይል አንብቦ መረዳት ይቻላል፡፡ ታዲያ መንግሥታዊ አወቃቀሩ በዘር ላይ ወይም በጎሳ ወይም በቋንቋ ላይ ነው የተመሠረተው የሚለው አባባል ምንጩ ምን ይሆን? ለሚለው መላምት ከመስጠት የዘለለ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

እርግጥ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች ሕገ መንግሥቱን በራሳቸው አረዳድና ፍላጎት በመተረጎም ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፤ በሃይማኖታቸው በአጠቃላይ በማንነታቸው ምክንያት በደል ሊደርስባቸው ይችላል እንጂ የሀገራችን ሕገ መንግሥት ዘረኝነትን አያበረታታም፡፡ እንዲያውም “ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑንና ማንኛውም ሰው በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው” ተብሎ በአንቀጽ ፳፭ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ የሰው ልጅ እኩልነትን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሕግ ባለሙያዮች የበለጠ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ በግርድፉ መረዳት የምንችለው ጉዳይ ቢኖር ግለሰቦችና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ከሕግ በአፈነገጠ መንገድ በመጓዝ ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያዩ አጀንዳዎችን በማቀበል አፍራሽ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተጠቀሰውና ምናልባትም የዘረኝነት ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው “ማንነት” የሚለው ቃል ነው፡፡ ማንነት የሚለው ቃል ደግሞ የብዙ ጥቃቅን ማንነቶች ድምር ውጤት እንጂ በቀጥታ ዘርን ብቻ አያመለክትም፡፡ ለምሳሌ ጾታ ራሱን የቻለ ማንነት ነው፣ የቆዳ ቀለም አንድ ማንነት ነው፤ሃይማኖት አንድ ማንነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አንድ ማንነት ነው፣ ቋንቋ አንድ ማንነት ነው፣ ወጣትነት ወይም ጎልማሳነት ወይም እርግና ሌላኛው ማንነት ነው፣ ወዘተ፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉት ማንነቶች በአንድ ሰው ጥቅል ማንነት ላይ ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ዘር የሚለውን ቃል በዋናነት ሁለት መገለጫዎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በግልጽ የሚታይና ከሌላው ማኅበረሰብ ሊለይ የሚችል የአካል ወይም የቆዳ ቀለም ልዩነት ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጅ ጥቁርና ነጭ ተብሎ እንደሚከፋፈለው ዓይነት በግልጽ ሊታይ የሚችል አካላዊ መለያ ሊኖር ይገባል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የእገሌ ዘር አባል ነን ብለው ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረሰብ አግልለው የራሳቸውን ማኅበረሰብ የፈጠሩና ከብዙኃኑ ማኅበረሰብ ራሳቸውን ያገለሉ ከሆነ ዘር የሚለውን መስፈርት ሊያሟሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ዘር የማንነት አካል ሊሆን ይችላል እንጂ ማንነትን ሙሉ ለሙሉ ሊተካ አይችልም ማለት ነው፡፡

በአንጻሩ ጎሳ ማለት ሦስት መመዘኛዎችን የሚያሟላ ነው፡፡ የመጀመሪያው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና የጋራ ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንደኛውን ጎሳ ከሌላው ጎሳ የሚለዩበት ማንነት በዋናነት አካላዊ ገጽታ (Phisical appearance) ሳይሆን የጋራ የሚሉት ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ ቋንቋቸው ነው፡፡ ሦስተኛው መመዘኛ ደግሞ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ሁኔታ በቁጥራቸው ጥቂት(Minority) ስሜት ያላቸው ናቸው፡፡ በእኛ አገር ፖለቲከኞች ጎሳ የሚለውን ትርጓሜ ብሔር ወይም ብሔረሰቦች የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ሲውል እንመለከታለን፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ትርጕም እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ስለ ማንነት፣ ስለ ዘር፣ እንዲሁም ስለ ጎሳ ይህን ካልን እገሌ ዘረኛ ነው፤ እገሊት ዘረኛ ናት፤ እነ እገሌ ዘረኞች ናቸው፣ በመካከላችን ዘረኝነት ተስፋፍቷል ወዘተ ስንል ምን ማለታችን ይሆን የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ እውነት በሀገራችን የምናስተውለው የእርስ በርስ መገፋፋት ጎሰኝነት የወለደው ነው ወይስ ዘረኝነት የወለደው የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች ዘረኝነትን ከአካላዊ ገጽታ ባሻገር ሰፋ አድርገው ይመለከቱታል፡፡

አንድን ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ወይም ተቋም የሌላ ዘር ወይም ጎሳ አባል በመሆኑ ብቻ በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን፣ ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን የምንመለከተው ጭፍን ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት የአካል ገጽታን ወይም የዘር ሐረግን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በዋናነት ባህልን፣ ቋንቋንና ሃማኖትን መሠረት ያደረገ ነው ብንል አሳማኝ ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ አንድ እውነታን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለማንነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ለሰው ልጅ እኩልነትም ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በማንነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ አስተዳደር በባሕርዩ አግላይ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ዕድል ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ በሕግ ደረጃ የተቀመጠ አግላይነት ባይኖርም በመንግሥት መዋቅር ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የእኔ ለሚሉት ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሊያደሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተዳደር በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ አሁን ላይ በአገራችን እየተስተዋለ ያለው የዜጎች መፈናቀል፣ ስደትና ሞት በዋናነት በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት የወለደው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

ይቆየን፡፡