በዓለ ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐረገ እና ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከላከላቸው በኋላ ሐዋርያት የአገልግሎታቸው መጀመሪያ ያደረጉት ጾምና ጸሎት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በጾም በጸሎት በሱባኤ ቆይተው አንድ ጊዜ ለወንጌል አገልግሎት በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠሩበትን ተልእኮ ለመፈጸም እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወደ አገልግሎት ተሰማርተዋል፡፡ በአሕዛብ እና በአረማውያን የሚደርስባቸውን መከራ በመቋቋም ከአንዱ ቦታ ሲያሳድዷቸው ወደ ሌላው እየተሰደዱ ወንጌልን ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ በዚህ አገልግሎት ውስጥ ሳሉም በርካታ መከራና ሥቃይ ተቀብለዋል፡፡ ሕይወታቸውንም ለሞት እስከ መስጠት ታምነው ተገኝተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት ያረፉትን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ መታሰቢያ በዓልን በድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛም ዕለቱን በማስመልከት ስለ ሁለቱ ሰማዕታት ታሪክ በጥቂቱ እናቀርብላችኋለን፡፡   

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን እና ወንድሙ ሐዋርያው እንድርያስን ያገኛቸው በገሊላ ባሕር ዳር ዓሣ በማጥመድ ላይ ሳሉ ነው፡፡ ጌታችንም “ኑ ተከተሉኝ ሰውን የምታጠምዱ እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ (ማቴ. ፬፥፲፱) ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ለአገልግሎት ሲጠራ የ፶፭ ዓመት ሰው ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ሰብስቦ “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” ብሎ በጠየቀ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ መመስከር የቻለ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ ጌታችንም መልሶ እንዲህ ብሎታል “እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦል በሮችም አይበረቱባትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ …” (ማቴ.፲፮፥-፲፱) ይህም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠውን ምስክርነት ተከትሎ የሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እምነት የጎደለው ሆኖም እናገኘዋለን፡፡ ሐዋርያት በታንኳ ሆነው በባሕሩ ላይ ይሻገሩ ዘንድ ጉዞ እንደጀመሩ ባሕሩን ማዕበል አናወጠው፡፡ በማዕበሉም ምክንያት ሐዋርያት እጅግ ታወኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ ይህን የተመለከተው ቅዱስ ጴጥሮስ “… ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው፡፡ እንዲመጣ ባዘዘውም ጊዜ ፍርሃት እንዳደረበት እንመለከታለን፡፡ ጥቂት እንደተጓዘም ነፋሱን ባየ ጊዜ ፈራ፡፡ መስጠምም ጀመረ፡፡ ያን ጊዜም “አቤቱ አድነኝ ብሎ ጮኸ“ ወዲያውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጁን ይዞ አወጣው፤ እንዲህም አለው “አንተ እምነት የጎደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” ብሎ ጌታችን ገሥጾታል፡፡ ማቴ ፲፬፥፳፬-፴፫)

ቅዱስ ጴጥሮስ ለክህደት ቅርብም እንደነበር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያት “እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ አዲስ ትእዛዝ ከሰጣቸው በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ወደምትሄድበት እከተልሃለሁ ብሎ ጠይቋል፡፡ “ወደ ምሄድበት ልትከተለኝ አትችልም፡፡ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ብሎታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ዝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡ “ጌታ ሆይ ስለምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ነፍሴን እንኳ ቢሆን ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል መልሶለታል፡፡ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና የጴጥሮስንም ክሕደት ስለሚያውቅ “ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ዶሮ አይጮህም” ብሎ እንደሚክደው ነግሮታል፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፴፬-፴፰) ይህም ጌታችን በመስቀል ላይ ሲሰቀል ሸሽቶ ወደ መንደር ገብቶ አብሯቸው እሳት ሲሞቅ “ይህ ሰው ከእርሱ ጋር ነበር” ብለው በተናገሩ ጊዜ የእርሱ ደቀ መዝሙር እንዳልሆነ፣ ከእርሱም ጋር እንዳልነበር ክዶ መስክሯል፡፡ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ምንም እንኳን በክሕደት ቢታማም በጸጸት የሚመለስና የንስሓ አንብዕ የሚያነባ እንደሆነ መጽሐፍ ይገልጻልና ምርር ያለ የጸጸት ልቅሶን አልቅሷል፡፡ ይህም ጸጸቱ ንስሓ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ (ማር.፲፬፥፷፰-፸፪)

በሌላ በኩል ደግሞ በጽናት ወንጌልን ለመስበክ ሳይሰቀቅ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ታግሶ አስተምሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ካረገ በኋላም በአይሁድ ሸንጐ ድውይ ፈወስክ ተብሎ በተከሰሰ ጊዜ በድፍረት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ መሥክሯል፡፡ በፍልስጥኤም፣ በሶርያና በተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን የሰበከ ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ከገለጠ በኀምሳኛው ቀን በዕለተ ጰንጠቆስጤ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸው ሦስት ሺህ ሰዎችን በአንድ ቀን ስብከት ማሳመንና ወደ ክርስትና መመለስ የቻለ ሐዋርያ ነው፡፡

 ወደ ፍልስጥኤም፣ ሶርያ፣ ጳንጦን፣ ገላትያ፣ ቀጰዶቅያ፣ ቢታንያ እና ሮሜም ሀገርም በመጓዝ ለአሕዛብ ወንጌልን አስተምሮ በማሳመን ወደ ክርስትና ብዙዎቸድን መልሷል፤ አስተማረ፤ ድውያንንም ፈውሷል፡፡ (ሐዋ ፭፥፲፭)

ዝናው በሮማ ባለሥልጣናት ዘንድ ተሰማ፤ ብዙዎችም ወደ ክርስትና ለመመለስ ቻለ፡፡ በዚህም ምክንያት ኔሮን ክርስቲያኖችን ማሳደድና መግደል ተያያዘው፡፡ በመጨረሻም የሮም ከተማን በእሳት አቃጠላት፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከሮማ ወደ ኦፒየም ጎዳና ተጓዘ፤ በዚያም ጌታችን በሽማግሌ አምሳል ተገለጠለት፤ ሆኖም ግን ጴጥሮስ ጌታ እንደሆነ ዐውቆ በፊቱ ተደፋና “ጌታዬ ወዴት እየተጓዝክ ነው?” አለና ጠየቀው። “ዳግም በሮም ልሰቀል” አለው። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲሰማ እጅግ አዝኖ ወደ ሮማ ተመለሰ። ሲፈልጉት ወደ ነበሩት የኔሮን ወታደሮች ሄዶ “እነሆኝ ስቀሉኝ” አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስንም ይዘው ካሠሩት በኋላ ሊሰቅሉት የመስቀያውን እንጨት ሲያቀርቡ “እኔ እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም” በማለት ቁልቁል እንዲሰቅሉት ለመናቸው። እነርሱም ቁልቁል ሰቀሉት ይህም የሆነው ሐምሌ ፭ ቀን ፷፯ ዓ.ም. ነበር፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን የሕግና ፍልስፍና ትምህርት ቤቶች በብዛት ይገኝባት በነበረችው በጠርሴስ ከተማ የተወለደ ነው፡፡ የዘር ሐረጉም ከነገደ ብንያም ነው፤  እርሱም ሮማዊ እንደሆነ ራሱ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን አስተዳደጉ በአይሁድ ሥርዓት ነበር፡፡ የኦሪት መምህር የሆነው የገማልያል ተማሪም ስለነበር የሕግ ትምህርት ተምሯል፤ ድንኳን መስፋትም ተምሮ እንደነበር ታሪኩ ምስክር ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ ሳውል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ክርስቲያኖችን እያሳደደ የሚያሳድድ፤ ለኦሪት ሥርዓትና አስተምህሮ ቀናዒ ሰው ነበር፡፡ “ሳውል ግን አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን ይቃወም ነበር፤ የሰውንም ቤት ሁሉ ይበረብር ነበር፤ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ ቤት ያስገባቸው ነበር፡፡” እንዲል (የሐዋ.፰፥፫) ደማስቆ ከተማ ሲደርስም በድንገት መብረቅ ከሰማይ ብልጭ ሲልበት መሬት ላይ ወደቀ፤ ወዲያውም “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጽ ሰማ፤ ሳውልም “አቤቱ፥ አንተ ማነህ” አለው፤ እርሱም አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾላ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስብሃል” አለው፤ እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ “አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” አለው፤ ጌታም፥ “ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርግ የሚገባህን ይነግሩሃል” አለው፡፡

ሳውልም ከምድር ተነሥቶ በሚቆምበት ጊዜ ማየት ተሳነው፤ ዓይኖቹ ቢገለጡም የሚያየው ነገር ግን አልነበረም፡፡ ለሦስት ቀናት ያህል ሳይበላና ሳይጠጣ ከቆየ በኋላም ጌታ በራእይ ለሐናንያ ተገልጦ ባዘዘው መሠረት እጁን ጭኖ ዓይኖቹን ፈወሰለት፤ ስለመመረጡ ነገርም አስረዳው፡፡ “በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና፡፡” እንዲል፤ (የሐዋ.፱፥፬-፲፭)

ሳውልም ተጠመቀ፤ ከበላና ከጠጣ በኋላ ስለበረታ በደማስቆ ከደቀ መዝሙርቱ ጋር ሰንብቶ ወደ ምኵራቦቹ በመግባት ሰብኳል፡፡ ደማስቆም ከተመለሰ በኋላ አሕዛብን በማሳመን አጥምቋቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ በዚያ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ሊገድሉት በማሰባቸው ክርስቲያኖቹ እርሱን ለመደበቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱት፡፡

እርሱም ማስተማሩን ሳያቋርጥ በአንጾኪያ፣ ኤፌሶን፣ ቆሮንቶስ፣ ሮም ከተሞች እየተዘዋወረ የእግዚአብሔርን ቃል ሰብኳል፡፡ በተአምራት ሙት አስነሥቷል፤ ድውይ ፈውሷል፡፡ ትምህርቱንም የሚያደርገው የነበረው ሰው በተሰበሰበበት በምኵራብ፣ በዐደባባይ፣ በገበያ ቦታዎች፣… ነበር፡፡ (ሐዋ.፱፥፩-፳፭)

ቅዱስ ጳውሎስ በቃል ካስተማራቸው ትምህርቶችም ይልቅ በመልክእት መልክ በጽሑፍ ያስቀመጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈዋል፡፡ በዚህም መሠረት ፲፬ መልእክታትን ጽፏል፡፡

በ፷፭ ዓ.ም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኒቆጵልዮን ከተማ ያስተምር በነበረበት ወቅት ንጉሥ ኔሮን ይዞ ወደ ወኅኒ አስገብቶ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው፤ በ፸፬ ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ሐምሌ ፭ ቀን ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም በዚህ ቀን በየዓመቱ ሁለቱን ማለትም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ጳውሎስን መታሰቢያቸውን በድምቀት ታከብራለች፡፡

በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤ አሜን!

 ምንጭ፡፹፩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ ፭፣

እግዚአብሔርን ማመስገን

ክፍል ሦስት

በዳዊት አብርሃም

ስለ ምን እናመስግን?

ከአፈር አንስቶ ሰው ስላደረገን፡-

እግዚአብሔር ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ብሎ ሰውን የሠራው ከምድር አፈር ሲሆን ዳግመኛም የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎ ሰጥቶታል፤ በልጅነት ጸጋም አክብሮታል፡፡ ልጅ ሆነን ከወላጆች ስንገኝም ሰውነታችንንም ያገኘነው በእርሱ በአምላካችን ፈቃድ ነው እንጂ በራሳችን ወይም በወላጆቻችን ፈቃድ አይደለም፡፡ “እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው፡፡” (መዝ.፻፳፯፥፫) እንዲል፡፡

የሚያስፈልገንን ሁሉ አሟልቶ ስለፈጠረን፡-

እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በዕለተ ዐርብ በፍጥረት መጨረሻ ቀን ነው፡፡ መጨረሻ መፍጠሩ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቅድሚያ ለሰው የሚያስፈልገውን ምቹ የሆነውን ሁሉ አሟልቶና አዘጋጅቶ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ” በማለት በሊቀ ነቢያት ሙሴ ላይ አድሮ እንደተናገረው፡፡ (ዘፍ. ፪፥፳፭)

ስለ በጎ ስጦታዎቹ፡-

ከተአምራትና ከድንቆች በፊት ጥበብና ዕውቀት ተሰጥቶናል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፰-፲) ልዩ ልዩ ስጠታዎችንም ሰጥቶናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፤ እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፡፡ ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር፤ የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ …” በማለት እንተናገረው፡፡

ክርስቲያን እንድንሆን ስላደረገን፡-

ብዙዎች የክርስትናን እውነት ለማግኘት አልታደሉም፤ እኛ ግን በስሙ ለመሰየም በቅተናል፡፡ ይህን ያገኘነው በራሳችን ብቃት እንዳልሆነ እናውቃለንና ስለማይነገር ስጦታው አምላክን ማመስገን ይገባናል፡፡

ሕይወት ስለሰጠን፡-

ሕይወትን የሰጠን አምላክ በሕይወተ ሥጋ ጠብቆ ለዚህች ሰዓት ስላደረሰን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ደግሞም ለዚህኛው ሕይወት ብቻ አይደለም፤ ከዚህኛው ሕይወት በኋላ እንድንወርሳት ስላዘጋጀልን የዘለዓለም ሕይወት ከምስጋና በቀር ምንን እንመልሳለን?

በቀጥተኛይቱ ሃይማኖት እንድንጸና ስላስቻለን፡-

ጥንታዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ ከመጀመሪያው ጌታ ከመረጣቸው ሐዋርያት ጀምሮ ተያይዞ የመጣውን የክርስትናን መንገድ ሳንለቅና ሳንስት ጸንተን መኖራችን የአምላክ ቸርነት ረድቶን ነው፡፡ “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፡፡” (ዕብ. ፬፥፲፬) እንደተባለው የዚህ ጸጋ ባለቤቶች እንሆን ዘንድ ቸርነቱ እንደረዳን በማሰብ ማመስገን አለብን፡፡

እንደ ኃጢአታችን ስላልቀጣን፡-

“እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፤ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ ነው፤ ሁል ጊዜም አይቀስፍም፤ ለዘለዓለምም አይቆጣም፡፡ እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ፡፡ ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ፡፡ አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፡፡” (መዝ.፻፫፥፰-፲፬) በቅዳሴአችንም “አቤቱ እንደ ቸርነትህ እንጂ እንደ በደላችን አይሁን” የምንለው ለዚህ ነው፡፡ የእርሱ ቸርነት የእኛን ኃጢአት ይበልጣል፡፡ መሐሪነቱ ከሐሳባችን በላይ ነው፡፡ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልቡናችሁንና ሐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡” እንዲል(ፊል.፬፥፯)

ስለ ርኅራሔውና አዛኝነቱ እንዲሁም ስላደረገልን እንክብካቤ፡-

ስንት ጊዜ ከመከራ ውስጥ አወጣን? በሌሎች ፊት ስንት ጊዜ መከበርን አደለን? ስንት ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር አለን? ስለ ጠበቀን፣ ስለ ረዳን፣ ስላቆየን፣ ስለ ተቀበለን፣ ስለራራልን፣ ስለ ደገፈን እስከዚህችም ሰዓት ስላደረሰን ብለን በቅዳሴ ጸሎታችን እንደምናመሰግነው ዘወትር የማይቆጠር መግቦቱን አስታውሰን ልናመሰግን ይገባናል፡፡

ስለ ጤንነታችን፡-

ይህንን በረከት አስበነው አናውቅም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የታመመ ዘመድ ባይኖራቸው እንኳ ወደ ሐኪም ቤት በመሄድ ሕሙማንን ይጎበኛሉ፡፡ እንዲህ ማድረጋቸው ከሚያስገኝላቸው ሰማያዊ ዋጋ በተጨማሪ ስለ ራሳቸው ጤንነት ለማመስገንም እንዲችሉ አጋጣሚው አእምሯቸውን ይከፍትላቸዋል፡፡

ስለ ሕመማችን፡-

ሕመም መጥፎ ወይም ክፉ ገጽታ ብቻ ያለው አይደለም፡፡ አልአዛር በቁስል ተመትቶ ነበር፤ ውሾች ቁስሉን እስኪልሱለት ድረስ ደርሶም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታው ግን ከእግዚአብሔር የሚለየው አልሆነም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ጋር ይበልጥ የሚያቀራርበው ሆነለት፡፡ በእቅፉ ያደረገው አብርሃም እንደመሰከረለት “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ክፉን ተቀበለ….” (ሉቃ. ፲፮፥፳፭) ታላቁ ባስልዮስ እንዲህ ተናግሯል፡፡ “ለአንተ መልካም የሆነው የቱ እንደሆነ አታውቅም፡፡ ጤና ወይም ሕመም” ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ፡፡” (፪ኛ ቆሮ. ፲፪፥፰) ሲል አስቸጋሪ የሆነበትን ሕመም እግዚአብሔር ለሥጋው መውጊያ ይሆነው ዘንድ እንደሆነ ሲያውቅ መቀበሉን ገልጧል፡፡ በተፈጥሮ ጤነኛ መሆንን እንፈልጋለን፡፡ በእርግጥም ለምድራዊ ሕይወታችን አስፈላጊው ጤንነት መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ግን አንድ ጥቅም አለው፡፡ ሕመም በአኮቴት ለሚቀበለው የኃጠአት መደምሰሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምናየውና ለማናየው መልካም ነገር ሁሉ፡-

በሥጋዊ ዓይናችን ለምናየውም ሆነ በእምነት ዓይን ለምናየው የአምላክ በረከት ሁል ጊዜ ማመስገን ይገባናል፡፡ (ማቴ. ፮፥፬-፮)

በእኛ ውስጥ ስለሚሠራው የእግዘዚአብሔር ጸጋ፡-

በምስጋና ጊዜ በአንደኛ ደረጃ የምናስበው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም፤ ከሁላችን ይልቅ ግን ደከምሁ፣ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡” (፩ቆሮ. ፲፭፥፲) ሲል እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የምናውለው ልፋታችንና የሰመረው ጥረታችን ሁሉ በተሰጠን ጸጋ የተከናወነ ነው፡፡

ጌታችን ለሰጠን መዳን፡-

ከሞት ፍርድ የዳንነው በእርሱ ሞት ነው፤ ዘለዓለማዊ ሕይውትንም ያገኘነው በእርሱ የማዳን ሥራ ነው፡፡

እርሱን የማወቅ ችሎታን ስለሰጠን፡-

የምሥራቹ ወንጌል ስለተሰበከልን፣ የተሰበከውንም ስለተረዳነው፤ ይህም የሆነው በእርሱ ዕርዳታ ስለሆነ ዘወትር ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ስለ ሰጠን ቃል ኪዳን፡-

“ታላቅም ድምጽ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፡፡” (ራእ.፳፩፥፫) “ሄጄም ስፍራ ባዘጋጀሁላችሁ፤ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ፡፡” (ዮሐ.፲፬፥፫) “ነገር ግን ዓይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ እንዲህ እንናገራለን፡፡” (፩ኛ ቆሮ.፪፥፱)

ልጆችና ወዳጆች ብሎ ስለ ጠራን፡-

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፤ እንዲሁም ነን፡፡ ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፩) “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፡፡ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” (ማቴ.፮፥፱)

የእግዚአብሔር ወዳጆቹ እንደሆንም ሲነግረን “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደረገውን አያውቀውምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቃችኋለሁና፡፡” (ዮሐ. ፲፭፥፲፭) ፤ “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ ዐውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው፡፡” (ዮሐ.፲፫፥፩) ስለ እነዚህና ቆጥረን ስለማንጨርሳቸው በረከቶች ለአምላካችን ምንን እንመልሳለን? ከምስጋና በቀር ምንም ልንመልስ አንችልምና ዘወትር እናመስግነው፡፡ አምላካችንን ከማማረር ተለይተን የእርሱን መልካምነት እያሰብን እናመስግነው ዘንድ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እግዚአብሐርን ማመስገን

በዳዊት አብርሃም

ክፍል ሁለት

ላለማመስገን የሚቀርቡ ምክንያቶች

ለራሳችን መልካም የሆነውን ስለማናውቅ፡-

ጥሩ ነው ይበጀናል ብለን የምናስበው ነገር ይኖርና በእርግጥም ያንን ነገር ማግኘት የሚጠቅመን ሊመስለን ይችላል፡፡ እውነታው ደግሞ የሐሳባችን ተቃራኒ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለእኛ የሚያስፈልገን በትክክል የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሰለሆነም በእኛ ላይ ሊሆን ያለውን በሙሉ ለእርሱ ልንተው፣ እርሱ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ልናምን ይገባናል፡፡ እመቤታችንና ጻድቁ ዮሴፍ ወደ ግብጽ እንዲሸሹ ሲታዘዙ ተቀብለው ፈጸሙት እንጂ አላቅማሙም፤ ወይም አላማረሩም፡፡ ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር የሆነው አማራጭ እንዲበልጥ ማመን ካልቻልን እርሱ በፈቃዱ እንዲሆን በሚያደርገው ነገር ተደስተን ምስጋና ልናቀርብ አንችልም፡፡

የወደፊቱን ማሰብ አለመቻል፡-

ሳናመሰግን ስንቀር ያላመሰገንነው ባለፉት ጊዜያት ወይም በዚህ አሁን ባለንበት ጊዜ የገጠመንን ችግር በማስብ ብቻ ተወስነናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሚመጡት ዘመናት ሊቀየር ወይም ሊሻሻል አይችልም ብለን አስበናል፡፡ ውጤቱን ደርሶ ካላየነው በስተቀር ለማመስገን አንፈቅድም፡፡ ለምሳሌ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ሁኔታ እንይ፡- ደቀ መዛሙርቱ ይህ ሰው በኃጢአቱ ነው እንዱህ የሆነው ብለው ደምድመው ጨርሰዋል፡፡ ጥያቄአቸው ውስጥ ድምዳሜአቸው ይሰማል፡፡ “ደቀ መዛሙርቱም መምህር ሆይ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ. ፱፥፪) ጥያቄአቸው የሚነግረን የአሕዛብ ተጽእኖ በከፍተኛ ደረጃ እንዳረፈባቸው ነው፡፡ ጌታ ግን ምስጋና የሚገባውን መለኮታዊ እቅዱን ገልጦ ነገሩ እነርሱ በክፉ እንዳሰቡት እንዳልሆነ አሳያቸው፡፡ “ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፡፡” (ዮሐ. ፱፥፫) ይህ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ዕውር ባይሆን ኖሮ በእግዚአብሔር ለማመንም ሆነ ስለ ክርሰቶስ ለመመስከር አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ያለፈውና ነባሩ ሁኔታው ለወደፊቱ መጥፎ ሆኖ አልቀጠለም፡፡ መጥፎ የነበረው ሁኔታው በጊዜው የሚያስከፋው ቢሆንም ለኋላው ግን ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሸጋግር  ሆነለት፡፡ በታሪክ ውስጥ የሚወሳ፤   የእግዚአብሔርም ሥራ የሚገለጥበት ለመሆን በቃ፤ ለብዙዎች ማመንም ምክንያት ሆነ፡፡

ሌላው ለምሳሌ የአልአዛር ሞት ነው፡፡ የአልአዛር እኅት ማርያም እንዲህ ብላ ነበር፡፡ “ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየቸው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ ጌታ ሆይ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው፡፡” (ዮሐ. ፲፩፥፴፪) ሆኖም የአልአዛር ሞት የላቀ ዓላማ ነበረው፡፡ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር የሚከብርበት ነው፡፡ ኢየሱስም ሰምቶ ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ፡፡” (፲፩፥፬)

እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ሳናስብ ስንቀር፡-

የማያመሰግን ሰው ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ውለታ ይረሳል፤ በረከቶቹ ላይ አያተኩርም፤ ሁል ጊዜ ሌላውን ብቻ ያስባል፡፡ ያጠውን፣ የጎደለበትን ወይም መጥፎ የሚለውን ገጠመኝ ብቻ ያስባል፡፡ በዚህም የተነሣ ያለፈው ዘመን ክፉ ብቻ ያመጣበት ይመስላል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ግን ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልካምነት እያሰበ እንዲህ ይላል፡፡ “ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ፣ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፡፡” (መዝ. ፻፫፥፪)

ትዕቢተኝነት፡-

በሥራችን ሁሉ ዋጋ የምንሰጠው ለራሳችንና ለገዛ ጥረታችን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዳከናወነልን አንገነዘብም፡፡ በራስ መመካት ደግሞ ወደ ትዕቢት ይወስዳልና እግዚአብሔርን እንረሳለን፡፡ “እርስ በእርሳችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ የትዕቢትን ነገር አታስቡነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል፡፡ (ሮሜ. ፲፪፥፲፮)

ከመልካም ገጠመኞች ይልቅ ክፉ ገጠመኞቻችን ላይ ይበልጡን በማተኮር ባሉበት መቆም፡-

የማያመሰግን ሰው ሁል ጊዜ ትኩረቱ አሉታዊ በሆኑ ያለፉ ነገሮች ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ባለፉት መጥፎ ገጠመኞች ላይ ተመሥርቶ የነገሮችን ከባድነት የበለጠ ያስባል፡፡ ስላለፉትም ሆነ አሁን ስላሉብን አሉታዊ ሐሳቦች ማሰብ እንደማይገባን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር “ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝኩት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፡፡” (ሉቃ. ፫፥፲፫) እንዲል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  “ኢየሱስ ግን ማንም እርፍ በእጁ ይዞ ወደኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው፡፡” (ሉቃ. ፱፥፷፪)

አለመርካት፡-

የማይረካ ሰው እግዚአብሔር የቱንም ያህል መልካሙን ሁሉ ቢሰጠው መርካት ይሳነዋል፡፡ አለመርካት ከራስ ወዳድነትና ከስስታምነት ይመነጫል፡፡ ሐዋርያው ከዚህ የተለየውን ሐሳብ ይዞ መገኘት እንደሚገባ ራሱን አርአያ አድርጎ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡፡ “ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና፡፡” (ፊል. ፬፥፲፩)

አማራሪነት፡-

የሚያማርር ሰው  አመስጋኝ መሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የማማረር ዝንባሌዎች ሥር እየሰደዱ የሥነ ልቡና ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ችግር የተጠናወተው ሰው ሲያማርር፣ ሲወቅስ፣ ሲቃወም ብቻ ይሰማል፡፡ ምንም ነገር ቢሆን አይጥመውም፤ አያስደስተውም፡፡ ይህ ችግር ሥነ ልቡናዊ ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ ማኅበራዊ በሽታ ወደ መሆን ይዛመታል፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ ደዌም ነው፡፡

ራስ ወዳድነት፡-

ራስ ወዳድነት የሚያጠቃው ሰው ዘወትር ሐሳቡ እንዴት በቁሳዊ ነገሮች ራሱን ማርካት እንደሚችል ብቻ ነው፡፡ አንዱን ሲያገኝ ሌላው ስለሚያስፈልገው ለምስጋና የሚሆን ፋታ የለውም፡፡

ስለ ዓለማዊ ሀብት ብቻ ማሰብ፡-

ፍላጎታቸውና ግባቸው በሙሉ ገንዘብ፣ ዓለማዊ ደስታ፣ ዝና፣ ቁሳዊ ሀብት የሆኑ ሰዎች ሊረኩ፣ የምስጋና ሕይወት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በሆነ አጋጣሚ ከእነዚህ ሀብቶቻቸው መካከል አንዱን ቢያጡ ሕይወታቸው መራራይሆንባቸዋል፡፡ እጦታቸው ጊዜያዊ ብቻ እንኳ ቢሆን ትዕግሥት አይኖራቸውም፡፡

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መተውና በራስ ፈቃድ ብቻ መመራት፡-

በራሱ ፈቃድ እየተመራ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚዘነጋ ሰው የምስጋና ሕይወት አይኖረውም፡፡ ራሱ የሚሻውን እንጂ የእግዚአብሔርን ፈቃድ  አይጠይቅም፡፡ ያሰበውን ሁሉ ጥሩም ይሁን መጥፎ ሳይመዝን፣ ይጥቀመው ወይም ይጉዳው ሳይረዳ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ምክንያት ይሰናከላል፡፡

ኃጢአትን መርሳት፡-

የማያመሰግን ሰው ኃጠአቱን ለማሰብ ያልቻለ ሰው ነው፡፡ የኃጢአታችንን ብዛትና የእግዚአብሔርን ቸርነት የምናስታውስ ከሆነ በምስጋና መኖር ለእኛ በጣም ቀላል መሆኑ አይቀርም፡፡

በመከራ ውስጥ ያለንን በረከት ለመመልከት አለመቻል፡-

ስንፈተንና በመከራ ውስጥ ለማለፍ ስንገደድ ምላሻችን ማማረርና ሳይመሰግኑ መቅረት ይሆናል፡፡ በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና እርሱ የሚሰጠንን በረከት እንዳለ አምነን ማመስገን ተስኖናል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” ሲል ያስተምረናል፡፡ (ፊል.፩፥፳፱)፤ እንዲሁም “ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ አብረንም ደግሞ እንድንከብር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾችን ነን፡፡” (ሮሜ. ፰፥፲፯) እንዲል፡፡

መቅረት የሌለበትና ሊቀርም እንደማይችል አድርጎ ማሰብ፡-

ምግብ፣ ውኃ፣ ልብስ፣ መጠለያና የመሳሰሉት ነገሮች ስለተሰጡን ልናመሰግን ቀርቶ እስከ ጭራሹም መኖራቸው ትዝ አይለንም፡፡ እነዚህ ነገሮች ተራና ሊኖሩንም ግድ የሆኑ የመስለናል፡፡ ስለዚህም ምስጋና ማቅረብ አስፈላጊ መስሎ አይታየንም፡፡ የእነዚህ አምላካዊ በረከቶች ምንነት የምንገነዘበው ስናጣቸው ነውና ብዙ ጊዜ ለምስጋና ምክንያት ሳናደርጋቸው እንዘነጋቸዋለን፡፡

  ይቆየን 

እግዚአብሐርን ማመስገን

በዳዊት አብርሃም

ክፍል አንድ

“እነሆም ሲሔዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግምባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡” (ሉቃ. ፲፯፥፲፭-፲፰) በዚህ የወንጌል ክፍል የምናገኘው ታሪክ ስለ ምስጋና የሚያስተምር አንድ እውነት አለ፡፡ በጌታችን ገቢረ ተአምራት ከለምጽ ሕመም የዳኑት ዐሥር ሰዎች ናቸው፡፡ ታሞ የተነሣ ፈጣሪውን ረሳ እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል በተደረገላቸው ታላቅ ነገር እግዚአብሔርን ማመስገን እንዳለባቸው ግን ዘጠኙ ትዝ አላላቸውም፡፡ ለምስጋ የመጣው አንዱ ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔርን ለማመስገን ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ፍጡር ነንና ፈጣሪን ማመስገን ግዴታ ነው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ግን የሰው ልጅ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ስለተደረገለት ታላቅ ውለታ እንኳ ማመስገን ሊዘነጋ ይችላል፡፡ ከላይ በመግቢያችን የጠቀስነው የወንጌል ቃል ይህን የሚገልጥ ነው፡፡ በክርስትና ውስጥ ግን ማመስገን ለተሰጠን ብቻ ሳይሆን ላልተሰጠንም ጭምር ነው፡፡ ለመልካሞቹ ነገሮች ብቻም ሳይሆን ለክፉዎቹም ነገሮች ለመከራዎቻችንም እንኳ ሳይቀር ለልናመሰግን እንዲገባን ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ሁል ጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርሰቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ፡፡” (ኤፌ. ፭፥፳) ይለናል፡፡ በተጨማሪም “ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና፡፡” (፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፮-፲፰)፡፡

ምስጋና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሌም ቢሆን የጸሎቶች ሁሉ መግቢያ ነው፡፡ በቅዳሴም ይሁን በማንኛውም የማኅበር ጸሎታችን ውስጥ ምስጋና ዋና ነገር ነው፡፡ በማዕድ ጸሎት እንዲሁም በጸሎተ ፍትሀት ውስጥ እንኳን ምስጋና ቀዳሜ ነው፡፡ በታላቁ ጸሎታችንም ውስጥ ከሁሉ አስቀድመን “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ” በሚል ምስጋና እንድንጀምር ጌታችን አስተምሮናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ” (መዝ. ፻፲፱፥፷፪) እንዳለው በቤተ ክርስቲያን በመዓልት ብቻ ሳይወሰን ምስጋናው በሌሊትም ይቀጥላል፡፡

እግዚአብሔርን ስለ ሁሉ ነገር ማመስገናችን እርሱ የሚያደርገው ማንኛውም ነገር ሁሉ መልካም ስለሆነ ነው፡፡ ጸሎታችን እርሱን ስናነሣ ቸር፣ ለጋስ፣ መሐሪ የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ “እግዚአብሔርምን ለሚወዱት እንደ ሐሳቡም ለተጠሩት ሁሉ ነገር ከበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡” (ሮሜ. ፰፥፳፰) ሲል ሐዋርያው እንደገለጸው ክፉ ገጠመኝ ሲደርስብን እንኳ የአምላካችንን መልካምነት ተስፋ በማድረግ እንደ ኢዮብ ልናመሰግን እምነታችን ግድ ይለናል፡፡

እግዚአብሔር የሚሠራው ሁሉ ሙሉ በሙሉ መልካም መሆኑን ከዮሴፍ ሕይወት መማር እንችላለን፡፡ ወንድሞቹ በክፋትና በምቀኝነት ተነሳስተው ለባርነት አሳልፈው ሸጡት፡፡ እግዚአብሔር ግን ወደ መልካምነት ቀየረለት፡፡ ግብፅ ከወረደ በኋላ መልካም ነገር ገጠመው፡፡ ቀጥሎም ሌላ ክፉ ሰው ገጥሞት ወደ ወሕኒ ቢገባም አሁንም እግዚአብሔር ፈተናውን ለበጎ አድርጎለት በግብፅ ከንጉሡ ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን ለመቀበል ቻለ፡፡ እርሱ ራሱ ዮሴፍ ለወንድሞቹ እንዲህ ነበር ያላቸው፡፡ “እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው፡፡”” (ዘፍ. ፶፥፳)፡፡

የምስጋና ደረጃዎች፡-

የምስጋና ትንሽ ደረጃ እግዚአብሔርን ስለ ተዓምራቶቹ፣ ስለ ስጦታዎቹ፣ ደስ ስላሰኘን፣ ስለ ምድራዊ በረከቶቻችን፣ ስላገኘነው ስኬት፣ ስለ ብልጽግናችን፣ ሕይወታችን ስለ መባረኩና ኑሮ ቀለል እንዲለን ስላስቻለን ብለን የምናቀርበው ምስጋና ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በዚህ ደረጃ እንኳ ማመስገን ሲሳነን ይታያል፡፡

የምስጋና ታላቁ ደረጃ ደግሞ አለ፡፡ ይኸውም በሕይወት ውስጥ ቀላል ከሚመስሉ በረከቶች ከራሱ ከሕይወት አንሥቶ፤ ታሞ መዳንን የመሰሉ አስደናቂ ስጦታዎችና በዓይን የማይታዩትን መንፈሳዊ በረከቶች ስለመቀበላችን የምናርበው የምስጋና ዓይነት ነው፡፡ መልካሙ ስለተደረገልን ብቻ ሳይሆን ክፉውም ስላልሆነብን የምናቀርበው ምስጋና ደረጃው ከዚሁ ጋር ነው፡፡ የምስጋና ከፍተኛው ደረጃ ደግሞ ስለገጠሙን መከራዎች የምናቀርበው ነው፤ በመከራ ውስጥ ሆነን እንኳ ልናመሰግነው ይገባናልና፡፡ ቅዱሳን ሐዋርት ይህ ዓይነት የምስጋና ሕይወት ነበራቸው፡፡ “እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ደስ እያላቸው ከሸንጎው ፊት ወጡ፡፡” (የሐዋ. ፭፥፵፩) መከራውን ተቋመቁን በአሸናፊነት እንድንወጣው ስላደረገን ልናመሰግን ይገባናል፡፡ ሌሎቹም የጌታ ደቀ መዛሙርት ሁላቸው መከራ በተቀበሉ ቁጥር የማይገባቸውን በረከት እንደተቀበሉ ቆጥረው ደስ እያላቸው ያመሰግኑ ነበር፡፡ “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፡፡” (ፊል. ፩፥፳፱) እንዲል፡፡ እንዲሁም “በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፤ እስረኞቹም ያደምጧቸው ነበር፡፡” (ሐዋ. ፲፮፥፳፭) በማለት ምስጋና እንዲገባ ይነግረናል፡፡

ይቆየን

በዓለ ጰራቅሊጦስ

በዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ

በዓለ ጰራቅሊጦስ ከዘጠኙ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው። ጰራቅሊጦስ ማለት ከአብ እና ከወልድ ጋር ለምንሰግድለት የዘለዓለም አምላክ ለሆነው ለሚያነጻ፣ ሊሚያጽናና እና ለሚቀድስ ለመንፈስ ቅዱስ የመጠሪያ ስም ነው፡፡ በዚህም በዓለ መንፈስ ቅዱስ ለማለት በዓለ ጰራቅሊጦስ ብለን እንጠራዋለን፡፡

ይህ ታላቅ በዓል የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ቀን ነው፡፡ ይህም ስለ ምነው ቢሉ ቤተ ክርስቲያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዘመኑ በተነሡ ገዢዎችና እናውቃለን፣ እንመራመራለን በሚሉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በሚያደርሱት አድርገው ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ስትፈተን ብትኖርም ሳትጠፋ ፈተናውን ሁሉ እያለፈች ከዛሬ የደረሰችው መሳሪያዋ ጠላት የማያከሽፈው፣ ዲያብሎስ የማይችለው፣ ዘመን የማይሽረው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህች ዕለት ሲናገር “ዛሬ ከበረከት ሁሉ ጫፍ ላይ ደርሰናል፤ ጌታችን የገባልንን የተስፋ ቃል ፍሬውን አግኝተናልና” ብሏል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ሊሰጥ የሚችለውን የመጨረሻውን ስጦታ በምልዓት ሰጥቶናል፤ ይህም ስጦታ ምንድን ነው ቢሉ መንፈስ ቅዱስ ነው ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህችን ቀን “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብሏታል፡፡ (ሃይማኖተ አበው)

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ቅዱስ ሉቃስ በዚህ በዓል ዕለት የተደረገውን በተመለከተ ሲገልጽ “በዓለ ኀምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፤ ተቀምጠውም የነበሩበትን ቤት ሁሉ ሞላው፤ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩዋቸው በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፤ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር፡፡” በማለት ጽፏል(ሐዋ. ፪ ፥ ፩ – ፬)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በጌታችን ጥምቀት ጊዜ በርግብ አምሳል እንደታየ አሁን ደግሞ ዓለሙን ሁሉ ሊለውጥ ቤተ ክርስቲያንም ልትተከል ባለበት ዕለት በአምሳለ እሳት ታየ፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው በቁሙ ነፋስ ሳይሆን እንደ ዐውሎ ነፋስ በማለት ረቂቅ አመጣጡን የገለጸው፡፡

ድንገትም እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ ያለውም መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡ ይህም ስለ ምን ነው ቢሉ ነፋስ ረቅቅ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና ፤ ነፋስ ኃያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኃያል ነውና፤ ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና፤ ነፋስ በምልዓት ሳለ አይታወቅም መንፈስ ቅዱስም በምልዓት ሳለ አይታወቅም፤ ነፋስ ባሕር ሲገስጽ ዛፍ ሲያናውጥ ነው እንጂ አይታወቅም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ /ልሳን/ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም ነው እንጂ አይታወቅም፤ ነፋስ መዓዛ ያመጣል መንፈስ ቅዱስም መዓዛ ቅድስና ያመጣልና፡፡

በእሳት አምሳል መውረዱም እንዲሁ እሳት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም   “ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ወበእሳት፤ እርሱ ግን በመንፈስ እና በእሳት ያጠምቃችኋል” በሚለው ቃለ ወንጌል ይታወቃል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፩)

በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው ማለቱ በእነርሱ አድሮ ሳይለያቸው ቤቱ ማደሪያው አደረጋቸው ማለት ነው፡፡ ተቀመጠባቸው የሚለው ማደር፣ ከዚያው ሳይለዩ መቀጠልን እና አለ መለየትን ያሳያልና፡፡

፩. ሐዋርያት ይህንን ታላቅ ጸጋ ያገኙ ዘንድ ብቁ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

ሀ. በእምነት እና በትዕግሥት መጠበቃቸው(ሉቃ.፳፬፥፵፱)

ለ. ትዕዛዙን መፈጸማቸው(ሐዋ. ፭፥፳፱)

ሐ. በአንድ ልብ ሆነው ስለተጉ ነው

፪. ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን በመቀበላቸው ምን አገኙ?

ሀ. ኃይልን፣ብርታትን፣ቆራጥነትን እና ጽናትን አገኙ፡- መንፈስ ቅዱስ ኃይል ባይሰጣቸው ኖሮ መከራውን ሁሉ ተሸክመው ይጸኑ ዘንድ አይችሉም ነበር፡፡ ለዚህም ነው በጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን በፍጹም ፈቃዱ በአይሁድ እጅ በተያዘ ጊዜ ከዮሐንስ እና ከጴጥሮስ በቀር ሁሉም ፈርተው የተበታተኑት፡፡ አልክድህም ከአንተ ጋር እሞታለሁ ሲል የነበረው ጴጥሮስም በአንድ ምሽት ውስጥ ሦስት ጊዜ ነው የካደው፡፡ ተስፋ አድርጎ የተናገረውን ከመፈጸም ወደ ኋላ የማይል እግዚአብሔር በተስፋው መሠረት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ጽናትን እና የማይዝል ብርታትን አግኝተዋል፡፡

ለ. ዕውቀትንና ማስተዋልን አገኙ፡- በዚህ ዕለት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት አእምሮአቸው ብዙ ምሥጢር ለመስማት እና ለመሸከም የማይችል እንደ ሕፃን አእምሮ ነበር፡፡ ጌታችን እንዲህ ሲል እንደ ተናገራቸው “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፤ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡”(ዮሐ. ፲፮፥፲፪-፲፫) በተስፋ ቃሉ መሠረት መንፈስ ቅዱስን ሲልክላቸው ከእነርሱ ጋር በአካል ሳለ ያስተማራቸው እና የነገራቸው ሁሉ ግልጽ ሆነላቸው አዕምሮአቸውም የእግዚአብሔርን ድንቅ እና ረቂቅ ምሥጢር የሚረዳ እና የሚያስታውል ሆነ፡፡

ሐ. በአስተሳሰባቸው ከምድራዊነት ወደ ሰማያዊነት ተሸጋገሩ፡- ዓላማቸው ሁሉ የክርስቶስን ክብር መንገር ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ሆነ፡፡ በዚህ ዓለም የሚያስጨንቃቸው እንዴት ሀብት ንብረት እንደሚያገኙ እና እንደሚሾሙ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ነገር ብቻ ሆነ፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፩-፳፰)

እንግዲህ የሐዋርያት መባረክ እና ጸጋን ማግኘት ይህን ከመሰለ እኛም በጥምቀት የምንቀበለው ጸጋ እነርሱ የተቀበሉትን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህ የተቀበልነውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ የእርሱ ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በኃጢአት እንዳናቆሽሽ እና እንዳናሳዝነው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ “ለቤዛ ቀን የታተማችኁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” (ኤፌ. ፬፥፴) እንደተባልን ሰው ከመሆን የተነሣ ውድቀቶች ቢገጥሙንም በንስሓ እናስወግዳቸው፡፡ ሐዋርያትን ያጸና አምላክ እኛንም እንዲያጸናን ክብሩን ለመውረስ እንዲያበቃን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡

በእንተ ዕርገት

መምህር በትረማርያም አበባው

ዕርገት ዐርገ ዐረገ፣ ወጣ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው፡፡ “ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ” (መሳ.፲፫፥፳) ከዚህ እንደምናየው ዐረገ ማለት ወደ ላይ ወጣ ማለት ነው፡፡ ይህ ቃላዊ ትርጓሜው ሲሆን ምሥጢራዊው ትርጓሜ ግን ዕርገት ማለት የሰው አምላክ መሆን ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በዚህ አንጻር ርደት ማለት ደግሞ የአምላክ ሰው መሆን ተብሎ ይተረጎማል፡፡ “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” ይላል (ማር.፲፮፥፲፱)፡፡ በዚህ አነጋገር ደግሞ የቤዛነት ሥራውን ማጠናቀቁን ያሳየናል፡፡

የዕርገት ዓይነቶች

ስለ እግዚአብሔር በምንነጋገርበት ጊዜ ግን ዐረገ ማለት ወደ ላይ መውጣትን አያመለክትም፡፡ በተመሳሳይ ወረደ ማለትም ወደ ታች መውረዱን አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ብለን ስለ እግዚአብሔር ስንናገር ሰው ሆነ ወይም ተዋሐደ ብለን እንተረጉመዋለን፡፡ “አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ዐረገ” (መዝ.፵፯፥፭) እንዲል፡፡

ዕርገተ ክርስቶስ በሁለት ይከፈላል፡፡ እነዚህም የርኅቀት ዕርገት እና የርቀት ዕርገት ናቸው፡፡

የርኅቀት ዕርገት

በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜ ላይ “ወእምዝ አውፅኦሙ አፍኣ እስከ ቢታንያ ወአንሥአ እደዊሁ ወአንበረ ላዕሌሆሙ ወባረኮሙ ወእንዘ ይባርኮሙ ተረኀቆሙ ወዐርገ ሰማየ፤ እስከ ቢታንያ አወጣቸው ከአጻዌ ኆኅት እስከ ፓትርያርክነት ያለውን ማዕረግ በአንብሮተ ዕድ ሾማቸው ባርኳቸው እየራቃቸው ወደ ሰማይ ዐረገ የርቀት ያይደለ የርኅቀት” ይላል (ሉቃ.፳፬፥፶)፡፡ ርኅቀት ማለት መራቅ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡  “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፤ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ…” (ሐዋ. ፩፥፱-፲) እያለ ከእነርሱ እየራቀ እየራቀ ሄዶ ተሰወራቸው፤ ለዚያም ነው ይህንን ዕርገት ኢትየጵያውያን ሊቃውንት የርኅቀት ዕርገት ብለው የሚጠሩት፡፡

የርቀት ዕርገት

ይህንን ዕርገት በተመለከተ በሃይማኖተ አበው ትርጓሜ (ሃይ. አበ.፲፯፥፱) ላይ “ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት፤ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በከመ ጽሑፍ በከበሩ መጻሕፍት እንደተጻፈ እንደ ተነገረ ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ በቅዳሴ መላእክት በክብር በብርሃን በሥልጣን ዐረገ” ካለ በኋላ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን የቃል ዕርገት በአርባ ቀን ይላል፡፡ የቃል ዕርገት በ፵ ቀን ያለው ከላይ ያየነው የርኅቀት ዕርገትን ሲሆን ከትንሣኤ በኋላ በአርባ ቀን ማረጉን የሚያሳውቅ ነው፡፡ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን ያለው ቃል ሥጋ ሲሆን የቃል ገንዘብ ማለትም ረቂቅነት፣ ምሉእነት፣ ሁሉን ቻይነት እና የመሳሰሉት የሥጋ ገንዘብ መሆናቸውን እና የሥጋ ገንዘብ የሆኑት ደግሞ የቃል ገንዘብ መሆናቸውን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ርደት የሥጋ ዕርገት ምክንያት ናት የምንለውም ይህንን በማኅፀን የተደረገውን ረቂቅ ዕርገት ለማመልከት ነው፡፡ ሥጋ ቃልን በመዋሐዱ ግዘፉን ሳይለቅ የቃልን ረቂቅነት ገንዘቡ አድርጓልና ይህንን ምሥጢር ሊቃውንቱ የርቀት ዕርገት ይሉታል፡፡ ይኸውም ሥጋ በማሕፀን እያለ ከቃል ጋር በመዋሐዱ በኪሩቤል ጀርባ ተቀመጠ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን “ወሶበ ርእዩ እግዚኦሙ ዘአስተጋብአ ኵሎ ፍጥረታተ እንዘ ይነብር ውስተ ሕፅንኪ ወዘይሴሲ ለኵሉ ፍጥረት ይጠቡ ሐሊበኪ ከመ ሕፃን ኀሠሥዎ ውስተ አርያም ወበህየ ረከብዎ ምስለ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ትካት” የሚለው ይህንን ነው፡፡ ቃልም በኪሩቤል ጀርባ ሳለ ምልአቱን ሳይለቅ በድንግል ማሕፀን ተወሰነ፡፡ መጋቢት ፳፱ ቀን ጌታ ሲፀነስ የቃል  ገንዘብ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብ የቃል የሆነበትን ቀን ቀድሞ ፍጡር የነበረ ሥጋ ፈጣሪ ሆኗልና ዐረገ ይባላል፡፡ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን የተባለውም ሥጋ አምላክ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ የቃል ዕርገት በ፵ ቀን መባሉም ቃል ሥጋን ገንዘብ በማድረጉ ከሐዋርያት ሳይለይ በሥጋ ወደ ሰማይ በማረጉ ነው፡፡

ለምን በ፵ ቀን ዐረገ?

በ፵ ቀን ማረጉ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ሰው እንደሆነ ለማጠየቅ ነው፡፡ አራተኛው ክፍል ዘመን የተባለውም ዘመነ ካህናት ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ዘመነ አበው፣ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ዘመነ መሳፍንት፣ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ዘመነ ነገሥት ሲሆን አራተኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመነ ካህናት ነው፡፡ ሌላው አዳም በተፈጠረ በ፵ ቀን ገነት ገብቷልና የዚያ ምሳሌ፡፡ ማረጉም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ትንቢቱም “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን” የሚለው ነው፡፡ (መዝ.፵፯፣፭) ምሳሌውም በመቅድመ ወንጌል እንደተገለጠው “ወዐርገ ውስተ ሰማያት ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሓን እምድኅረ ትንሣኤ ኀበ መንግሥት ዘድልው ሎሙ፤ ከትንሣኤ በኋላ በጣዕም በሥን በመዓዛ በብርሃን በክብር ተዘጋጅቶላቸው ወደ አለ ወደ መንግሥተ ሰማያት ጻድቃን መግባታቸውን ያስረዳ ዘንድ ወደ ሰማይ ዐረገ” ይላል፡፡ ጻድቃን ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ጸጋ እየተጨመረላቸው ለዘለዓለም የሚኖሩ መሆኑን ያስረዳል፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት ወይትዌሰክ ሥን በዲበ ሥን እንዲል በክብር ላይ ክብር እየተጨመራቸው በማያቋርጥ ጸጋ እንደሚኖሩ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ እንዳረገ ሁሉ ጻድቃንም በዳግም ምጽአት ጊዜ ከሞት ተነሥተው ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብተው ለዘለዓለም እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

ዳግም ትንሣኤ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በኋላ የሚውለውን እሑድ ዳግም ትንሣኤ ብላ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ይህም በአከባበር፥ በሥርዓት የመጀመሪያውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡ ከትንሣኤ ዋዜማ ጀምሮ የሚጸለየው ጸሎት፣ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤ በሙሉ በዚህ ቀንም ይደገማል፡፡

ዕለቱንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ለሁለተኛ ጊዜ መታየቱን(መገለጡን) በማሰብ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ፣ በሦስተኛውም ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣና በትንሣኤው ትንሣኤአችንን ካወጀልን በኋላ ሐዋርያት በአንድነት ተሰብስበው ሳለ ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ በመተባበር ገልጸውታል፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው”(ዮሐ.፳፥፲፱-፳፤ማቴ.፳፰፥፲፮-፳፤ሉቃ.፳፬፥፴፮-፵፱) በማለት ገልጾታል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ አብሯቸው አልነበረምና የሆነውን ቢነግሩት አላምንም አለ፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ ሲገልጹት “… ጌታችንን አየነው” አሉት፡፡ እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ፤ ጣቱንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ፤ እጄንም ወደ ጎኑ ካላስገባሁ አላምንም” አላቸው፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፬-፳፭)፡፡

ከስምንት ቀን በኋላም ሐዋርያት፣ ካላየሁ አላምን ያለው ቶማስን ጨምሮ በአንድነት ተሰብስበው ባሉበት በሩ እንደተዘጋ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በመካከላቸውም ቆመ፡፡ እንዲህም አላቸው፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን”፡፡ ከዚህም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው፡፡ ቶማስም ”ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ስለአየኸኝ አመንህን? ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው” አለው፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱)፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ዕለት ዳግም ትንሣኤ ብላ ሰይማ ሥርዓቱንም እንደ ትንሣኤው ትፈጽማለች፣ በድምቀት ታከብራለች፡፡

በዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፡-

  • በገባሬ ሰናይ ዲያቆን፡- (፩ቆሮ.፲፭፥፩-፳)
  • በንፍቅ ዲያቆን፡- (፩ዮሐ.፩፥፩- ፍጻሜው)
  • በንፍቅ ቄስ፡- (ሐዋ.፳፫፥፩-፲)
  • ወንጌል፡- (ዮሐ.፳፲፱-ፍጻሜው)
  • ቅዳሴ፡- የዲዮስቆሮስ

የክርስቶስ ትንሣኤ በሊቃውንት

የጌታችን መድኀኒታችን ኤሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከተ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ብዙ አስተምረዋል፣ ጽፈዋል፡፡ ለዛሬ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት መካከል በሃይማኖተ አበው ያገኘውን በጥቂቱ እናቀርባለን፡፡

“ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ‘በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ’ ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞት ነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፡፡ አምላክ የኾነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፡፡ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደ ኾነ ሥራውን አስረዳ፡፡ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት (እትራት) አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በአራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ‘ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው’ ብለው አስረዱ” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

“ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የድሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፣ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ ‘እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም’ ተብሎ እንደ ተጻፈ” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፯፥፫-፮)፡፡

“ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‘አባት ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ’ ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ” (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

“የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይልን እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፡፡ ከሞትም በኋላ ፈርሶ፣ በስብሶ መቅረትን አጠፋ” (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

“እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት፣ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዅሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፤ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

“እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ” (ሠለስቱ ምዕት፣ ሃይ. አበ. ፲፱፥፳፬)፡፡

“ሞትን ያጠፋው፣ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፣ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል” (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

ይቆየን፡፡

ቀዳም ሥዑር

በሰሙነ ሕማማት በስቀለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ ጌታችን መድኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ አገዛዝና እስራት ነጻ ለማውጣት የተቀበለውን መከራ፣ እንዲሁም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ማደሩን በማሰብ በጾም ታስቦ ስለሚውል ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረው ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የማይጾመው ቅዳሜ ስለሚጾም ስዑር /የተሻረ/ ተብሏል፡፡

ቀዳም ሰዑር ሌሎችም ስያሜዎች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለምለም ቅዳሜ፡-

ካህናቱ ሌሊት ለምእመናን ለምለም ቄጤማ ስለሚያድሉ ዕለቲቱ በዚህ ስያሜ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡

የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቄጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ

ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡

ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸቶች

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ በይሁዳ አማካይነት ተላልፎ ከተሰጠበት ሐሙስ ምሽት ጀምሮ ስቃይ ሲያጸኑበት ቆይተዋል፡፡ በዕለተ ዐርብም ይሰቅሉት ዘንድ አስከ ቀራንዮ መስቀል አሸክመው የተለያዩ ጸዋትወ መከራ እያጸኑበት ወስደውታል፡፡ በመሰቀል ላይ በሁለቱ ወንበዴዎች መካከል ከተሰቀለበት ሰዓት ጀምሮም የተናገራቸው ቃላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸቶች ወይም “ሰባቱ አጽርሐ መስቀል” በማለት ሰይማ ታስባቸዋለች፡፡ እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ሲሆን ቀጥለንም በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡-

፩ኛ. “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማሰበቅታኒ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ”፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ በዘጠኝ ሰዓት የተናገረው ቃል እንደሆነ በወንጌል ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ “በዘጠኝ ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ ኤሎሄ ኤሌሄ ላማሰበቅታኒ ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ፡፡ይኸውም አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት በሰሙ ጊዜ ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ” (ማቴ.፳፯፥፵፭) እንዲል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ ብሎ የተናገረበት መሠረታዊ ሐሳብ፡- ያችን የድኅነት ቀን ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ያለችውን ዕለተ ዓርብ በተስፋ ይጠባበቅ የነበረውን አዳምን ወክሎ እንደሆነ አበው ያስረዳሉ፡፡ (ማቴ.፳፯፥፵፭ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡ በመሆኑም አምላኬ አምላኬ ያለው በአዳም ተገብቶ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም አምላኬ አምላኬ ያለው ሰውነቱን ሲገልጥ ነው፡፡ ይህም ፍጹም አምላክነቱንና ፍጹም ሰውነቱን ማለት ነው፡፡

፪ኛ. “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ”፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖርበት እንደ በደለኛ ተቆጥሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ነበር የተሰቀለው፡፡ “ከእርሱ ጋርም ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ፡፡ መጽሐፍ ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ ያለው ተፈጸመ” (ማር.፲፭፥፳፯) ይላልና፡፡

በቀኝ በኩል የተሰቀለው ወንበዴ ጌታችንን “አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›” አለው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እንዲህ አለው “እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ፡፡” (ሉቃ.፳፫፥፵፫)፡፡

፫ኛ. “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ”፡-

“ያን ጊዜም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድምጹን ከፍ አድርጎ አባት ሆይ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ሉቃ.፳፫፥፵፮)፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት የተናገረው ቃል የተሰቀለው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነና የአብ የባሕርይ ልጁ እንደሆነ ያሳያል፡፡

፬ኛ. “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው”፡-

ምንም በደል ሳይኖርበት አይሁድ በክፋት ተነሳስተው መከራ አጸኑበት፤ ያን ሁሉ የግፍ ግፍ በጭካኔ የተሞላ መከራ ሲያደርሱበት ልባቸውን ዲያብሎስ ስላደነዘዘው የሚራራ ልብ አጡ፡፡በዚያንም ጊዜ መምህረ ይቅርታ ቸሩ አምላካችን ለሠቃዮቹ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ” (ሉቃ.፳፫፥፴፬)፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደለኞች ይቅርታን ያገኙ ዘንድ ይቅር በላቸው አለ፡፡ ልመናውንም ያቀረበው ወደ ባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ጋር ደግሞ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡ እንዲሁም የሰውን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ፍጹም ሰው እንደሆነ ሲያስረዳ ነው፡፡ይህም በደለኞችን ከራሱ ጋር ያስታረቀበት የፍቅር ድምጽ ነው፡፡

አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅርበላቸው ማለቱ አባት ሆይ ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን ከመግለጹ በተጨማሪ ይቅር በላቸው ማለቱ ጠላትን ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ የመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችሁን ውደዱ ብሎ ያስተማረ እርሱ ብቻ ነውና፡፡

፭ኛ. “እነሆ ልጅሽ፤ እናትህ እነኋት”፡-

“ጌታችን መድኀኒታችንን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን ‘አንቺ ሆይ እነሆ ልጅሽ’ አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‘እናትህ እነኋት’ አለው፡፡ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት” (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ ደቀ መዝሙሩ ተብሎ የተጠቀሰው ጌታችን ይወደው የነበረ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው ነው፡፡ ይህንንም የጻፈው እርሱ ነው (ዮሐ.፳፩፥፳፬)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቢሆንም ሐሙስ ማታ እረኛው ሲያዝ ከተበተኑት በጎች ጋር አብሮ አልሸሸም፡፡ በዚያች በአስጨናቂዋ ሰዓት ከጌታችን ጋር እስከ እግረ መስቀሉ ተጓዘ፡፡የክርስቶስ ፍቅር ፍርሃቱን ሁሉ አርቆለት የአይሁድን ቁጣና ዛቻ ሳይፈራ ጸንቶ በመቆሙ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ ሁሉ እርሱ በኩል ተሰጠችን፡፡ እናታችን ድንግል ቅድስት ማርያም ሁል ጊዜም ቢሆን ከእግረ መስቀሉ ሥር ለሚገኙ፣ ልባቸው ቀራንዮን ለሚያስብ ሁሉ እናት እንድትሆን እነርሱም ልጆቿ እንዲሆኑ በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ተሰጥታናለች፡፡

በመሆኑም “እነሆ ልጅሽ፤ እናትህ እነኋት” የሚለው የመስቀሉ ቃል በመስቀል ላይ የተከፈለልንን ዋጋ አስበን በእርሱ አምነን በምግባር ታንጸን እንደ ፈቃዱ በምንኖር ክርስቲያኖችና ለድኅነታችን ምክንያት በሆነች በእመ አምላክ በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል የእርሷ እናትነት፣ የእኛ ልጅነት የተመሠረተበት የፍቅር ቃል ነው፡፡

፮ኛ. “ተጠማሁ”፡-

“ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‘ተጠማሁ’ አለ” (ዮሐ.፲፱፥፳፰)፡፡

ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፣ የባሕር አሸዋን የቆጠረ፣ ውኆችንም ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈሳቸው፣ የባሕር ጥልቀትንና ዳርቻን የወሰነ፣ የኤርትራን ባሕር እንደ ግድግዳ ያቆመ አምላክ “ተጠማሁ” ብሎጮኸ፡፡ (ኢሳ.፵፥፲፪፣አሞ.፱፥፮)፡፡

“የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደ ተናገረ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል” (ዮሐ.፯፥፴፯) በማለት እርሱ የሕይወት ውኃ እንደሆነ ተናገረ፡፡ አምላክ ሲሆን “ተጠማሁ” ብሎ መጮኹ ስለ ምንድንነው ብለን ቅዱሳት መጻሕፍትን ስንመረምር፡- አንደኛ የመከራውን ጽናት፣ ከሚነገረው በላይ መከራውን እንዳጸኑበት የሚያሳይ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እርሱ የተጠማው የሰውን መዳን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በዚያን ወቅት እንኳ ከክፉ ሥራው ተመልሶ የሚጸጸት፣ የሚራራ፣ ንስሓ የሚገባ ሰው በማጣቱ መድኃኒት እርሱ ቀርቦ ሳለ የሰው ልጅ ባለማስተዋሉ ወደ እርሱም በፍቅር ባለመቅረቡና ባለመመለሱ ተጠማሁ አለ፡፡

፯ኛ. “ሁሉ ተፈጸመ”፡-

”ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ ሁሉ ተፈጸመ አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ዮሐ.፲፱፥፴)፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕተ ዐርብ በመስቀል ላይ ሳለ ‘ተፈጸመ’ ብሎ መናገሩ ብዙ ትርጉም ያለው ቃል ነው፡፡ እነርሱም፡-

 በነቢያት ስለ እኔ የተነገረው ትንቢት፣ የተመሰለው ምሳሌ፣ በቅዱሳን አበው የተቆጠረው ሱባኤ፣ ጊዜው ደርሶ የአዳም ተስፋ ተፈጸመ፡፡

 የሰው ልጅ በዲያብሎስ አገዛዝ በሞትና በጨለማው ሥልጣን፣ በአጋንንት ወጥመድ ታስሮ የሚኖርበት የፍዳ ዘመን አለቀ ተፈጸመ፡፡

 በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ የነበረው የጥል ግድግዳ ፈረሰ፣ የተጻፈው የዕዳ ጽሕፈት ተደመሰሰ፣ የሰው ልጅ ዕዳ በደል ተከፈለ በአምላክ የቤዛነት ሥራ ሁሉ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡

እነዚህ ከአንድ እስከ ሰባት የጠቀስናቸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መራራውን መከራ እየተቀበለ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላቶቹ ናቸው፡፡ ወደዚህ ዓለም ሰው ሆኖ የመጣበትን ዓላማ አከናውኖ ሲጨርስ በመጨረሻ “ተፈጸመ ኵሉ” በማለት ነፍሱን ከሥጋው ለየ፡፡ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶም በሲኦል ባርነት ለነበሩት አዳምና ልጆቹ ነጻነትን ሰበከላቸው፡፡ በአካለ ሥጋ ደግሞ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን አጠፋልን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡