ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል
በጳጉሜን ወር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ነው፡፡ “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ (ጦቢ. ፲፪፥፲፭) ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ ጳጉሜን ፫ ቀን በየዓመቱ በዓሉን ታከብራለች፡፡
በዓሉን የምናከብርበት ምክንያት በድርሳነ ሩፋኤል ላይ እንደሚከተለው ተጽፏል:-
ይህም ዕለት በሊቀ ጳጳሱ በአባ ቴዎፍሎስ ዘመን እስክንድርያ በምትባል ሀገር ዳርቻ ባለች ደሴት በውስጧ ብዙ ተአምራት የተፈጸሙባት በቅዱስ ሩፋኤል ስም ያታነጸች ቤተ ክርስቲያን የተባረከችበትና የተቀደሰችበት ዕለት ነው፡፡ ይህም የሆነው አንዲት በጣም ሀብታም የሆነች ሮማዊት ሴት ንዑድ ክቡር የሚሆን የቅዱስ ሩፋኤልን ሥዕልና ልጆቿን እንዲሁም ከባሏ በውርስ ያገኘችውን ብዙ ገንዘብ ይዛ ወደ ሊቀ ጳጳሱ ወደ አባ ቴዎፍሎስ ዘንድ በመጣችበት ጊዜ ነበር፡፡ ከመጣችም በኋላ በሊቀ ጳጳሱ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችና ከመሬት ውስጥ ወርቅ የተከማቸበት ሳጥን ተገኘ፡፡
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ አባ ቴዎፍሎስ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አሣነጸ፤ ከእነዚህም ውስጥ እስክንድርያ በምትባል ሀገር ዳርቻ ባለች ደሴት ላይ ክቡር በሚሆን በቅዱስ ሩፋኤል ስም የተሠራች ይህች ቤተ ክርስቲያን ትግኝበት ነበር፡፡ ሥራዋንም ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ በዚችው ዕለት በታላቅ ክብር አከበራት፣ ባረካት፣ ቀደሳት፡፡ ብዙ ሕዝብና ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሲጸልዩ ሣለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተንቀጠቀጠች፤ ብዙም ታወከች ማዕበልም እንደሚያንገላታው መርከብ ተንገላታች፡፡ ከመንቀጥቀጡም የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በባሕር አሸዋ ላይ እና ለመንቀሳቀስ በባሕር ውስጥ ጸንቶ የሚኖር ከሌሎች ዓሣ ነባሪዎች እጅግ የሚበልጥ አሣ ነባሪ ጀርባ ላይ የታነጸች መሆኗን ዐይተው ተረዱ፡፡
ያም ዓሣ ነባሪ ከሰዎች ብዛት የተነሣ ክብደት ስለተሰማው ያቺን ቤተ ክርስቲያን ይገለብጣት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፤ በውስጡ ያሉ ሰዎች እና ሊቀ ጳጳሱ ያድናቸው ዘንድ ወደ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ቃል ጮኹ፡፡ ክቡር የሚሆን ወደ ቅዱስ ሩፋኤልም ማለዱ፡፡
በዚያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ንዑድ ክቡር የሚሆን ቅዱስ ሩፋኤልን ላከላቸው፡፡ ከጭንቀታቸውም አዳናቸው፤ ከሐዘናቸውም አረጋጋቸው፣ ዓሣ ነባሪውንም “ባለህበት ቦታ ሳትንቀሳቀስ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጸንተህ ኑር” በማለት በያዘው ጦር ወግቶ እንዳይንቀሳቀስ ጸጥ አስደረገው፡፡ ያለ ምንም መንቀሳቀስ ባለበት ቦታ ጸጥ ብሎ ቆመ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ብዙ ድንቅ ተአምራት ሲደረግባት፣ ሕሙማን ከደዌአቸው ሲፈወሱባት ቆዩ፡፡
ነገር ግን የእስላሞች መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ በዚያ ሁኔታ እንዳለች ከዕለታት በአንድ ቀን ዓሣ ነባሪው ተንቀሳቀሰና የረጋ ባሕር ማዕበል ሞገድ ተነሥቶ ስለመታው ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈራረሰች፡፡ በዚያች ቦታ ላይም የሚኖሩትን ብዙ ሰዎች ባሕሩ አሰጠማቸው፡፡
የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ስለ ቅዱስ ሩፋኤል ታላላቅ ተአምራት ለጻድቁ አኖሬዎስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ንጉስ ሆይ እንግዲህ በማስተዋል ስማ ወደ አንተ እንመጣ ዘንድ በመርከብ ተሣፍረን ነበርና እንዲሁ በጉዞ ላይ ሳለን በአንድ ደሴት ውስጥ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አየን ቀኑም ቀዳሚት ሰንበት ነበር፡፡ ወደ ወደቡም በደረስን ጊዜ ቅድስትና ክብርት በምትሆን በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል ወደ እርሷ ስናመራ በዚያች ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንዲት አነስተኛ ደብር አገኘን፡፡ በውስጧም የሚኖሩ ብዙ ወንድሞች መነኮሳት ነበሩ፡፡ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁንና በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ እነርሱ በደረስን ጊዜ ምናልባት ከቀድሞ አባቶች የተፃፈ መጽሐፈ ብሉይ በእናንተ ዘንድ ቢኖር እመራመርበት ዘንድ ብትሰጡኝ ፈቃዳችሁን እጠይቃለሁ” አልኳቸው፡፡ እነርሱም “በቤተ ክርስቲያኒቱ ግምጃ ቤት ውስጥ ብዙ መጻሕፍት ይገኛሉ፤ ነገር ግን እኛ ትርጉማቸው ምን እንደሚል አናውቅም” አሉኝ፡፡
እኔም እስኪ አምጥታችሁልኝ ልመልከታቸው አልኳቸውና ካመጡልኝ በኋላ በእግዚአብሔር በደቀ መዛሙርት ፊት ያደረጋቸውን ልዩ ልዩ ተአምራትና ስለ ሰማይና ምድር ጥንት ተፈጥሮ እንዲሁም ከፍጥረተ ዓለም እስከ ኅልቀተ ዓለም ድረስ ያሉትን ሁኔታዎች ስመራመር አገኘሁ፡፡ እንዲሁም ሌሎችን መጻሕፍት ስመራመር ደቀ መዛሙርቱ ምሥጢረ መለኮቱን ይገልጥላቸው ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጠይቀውት በደብረ ዘይት ሰብስቧቸው ሳለ ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና ማዕረግ የሚያስረዳ አባቶቻችን ሐዋርያት የጻፉትን አንድ መጽሐፍ አገኘሁ፡፡
በውስጡ የተፃፈውም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ሐዋርያት ፈጣሪያቸውን ጌታችን አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ ስለ ቅዱስ ሩፋኤል ክብር ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን፡፡ በምን ቀን፣ በየትኛው ወር እንደሾምኸው፣ ክብሩና ማዕረጉ፣ ከሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ክብር ጋር ትክክል እንደሆነ ስለ እርሱ በዓለሙ ሁሉ እንድናስተምር ትገልጽልን ዘንድ እንማልዳለን አሉት፡፡
እርሱም ከወሩ አነስተኛ በሆነችው በጳጉሜን ሦስት ቀን የመታሰቢውን በዓል አድርጉ ብሎ ስለ አዘዛቸው በዚሁ ዕለት በዓሉ ይከበር ዘንድ ሕግ ሠርተው ወሰኑ፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻሉ፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም
ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል ላረገዙ ሴቶችም ረዳታቸው ነው፡፡ ሴት በፀነሰቸወበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ጽንሱ በማኅፀን እያለ ተሥዕሎተ መልክዕ (መልኩ በሥላሴ አርአያ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የሰውን ልጆች በምንዝር ጌጥና በመሳሰሉት እንዲያጌጡ እንዲሁም ክፉ ሥራን እንዲሠሩ፣ ከእግዚአብሔርም እንዲለዩ ለማድረግ የሚጥረውን ጋኔን የመገሠጽ እና ያደረባቸውን ክፉ መንፈስ እንዲያስወግድ ሥልጣን የተሰጠው መልአክ ነው፡፡ “አዛዝዓልም ለሰዎች ሰይፍን ሾተል፣ ጋሻና ጥሩር መሥራትን አስተማራቸው፡፡ ከእነርሱም በታች ላሉት አምባሮችን፣ ጌጥን፣ ዐይን መኳልንና ቅንድብ መሸለልን፣ ከተመረጠና ከከበረ ከዕንቍም ሁሉ በከበረውና በተመረጠው ዕንቍ ማጌጥን፣ እንሶስላ መሞቅን ሁሉና የዓለሙን ለውጥ አሳያቸው፡፡” እንዲል (ሄኖክ ፪፥፲፰)፡፡ ይህን አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አሥሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በረከት ረድኤት ይደርብን፡፡