የወላይታ ሀገረ ስብከት
የወላይታ ሀገረ ስብከት በወሊሶ በተከናወነው ሕገ ወጥ ሹመት ላይ የተሳተፉትንና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ለሀገረ ስብከቱ በሰጠው ኮታ መሠረት በዩኒቨርስቲው እየተማሩ ይገኙ የነበሩትን ‘አባ’ አብርሃም ገብረ መስቀል የተባሉት ግለሰብ ከአገልግሎት አግዷል
የሲዳማ_ክልል_ሀገረ_ስብከት_የአቋም_መግለጫ_አወጣ
የሲዳማ ሀገረ ስብከት በዛሬው ዕለት የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከቤተክርስቲያን እውቅና ውጭ በተደረገው ህገ ወጥ ሹመት ዙሪያ ውይይት አድርጎ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሕገ ወጡን ተሿሚ አገደ
@የምስራቅ ሐረርጌ ሐገረ ስብከት ጽ/ቤት Eastern Hararge Diocese secretary office
ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ በተፈጸመው “የጳጳስ ሹመት” ከታች የተዘረዘሩት አህጉረ ስብከት ላይ የስም ዝርዝራቸው የሚገኙትን የአህጉረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድና እውቅና ውጭ ወረራ እንዲፈጸምበት ስምሪት የተሰጠ በመሆኑ በየአካባቢው የምትገኙ ካህናትና ምእመናን መንበረ ጵጵስና አህጉረ ስብከቱን እንድትጠብቁ ጥሪ ቀርቧል፡፡
1.”አባ” ገ/ማርያም ነጋሳ – ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት
2.”አባ” ተ/ሃይማኖት ወልዱ – ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት
3.”አባ” ገብርኤል ወ/ዮሐንስ – ጉራጌ ሶዶ ሀገረ ስብከት
4.”አባ” ገ/እግዚአብሔር ታደለ – ምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት
5.”አባ” ሚካኤል ገ/ማርያም – ከምባታ ሀገረ ስብከት
6.”አባ” ኃይሉ እንዳለ – ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
7.”አባ” ተ/ማርያም ስሜ – ጉጂ ሊበን ሀገረ ስብከት
8.”አባ” ኃ/ኢየሱስ መንግሥቱ – ከፋ ሀገረ ስብከት
9.”አባ” ወ/ኢየሱስ ኢፋ – ቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት
10.”አባ” ጳውሎስ ከበደ – ሀዲያ ሀገረ ስብከት
11.”አባ” ኃ/ኢየሱስ ተስፋዬ – ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት
12.”አባ” ገ/ኢየሱስ ገለታ – ሆሮ ጉዱሩ ሀገረ ስብከት
13.”አባ” ጸጋዘአብ አዱኛ – ምሁር ኢየሱስ ገዳም “የበላይ ጠባቂ”
14.”አባ” ኃ/ማርያም ጌታቸው – ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
15.”አባ” ወ/ጊዮርጊስ ኃ/ሚካኤል – ከሚሴ ሀገረ ስብከት
16.”አባ” እስጢፋኖስ ገብሬ – ባሌ ሀገረ ስብከት ረዳት
17.”አባ” ገ/መድኅን ገ/ማርያም – ጎፋ ባስኬቶ ሀገረ ስብከት
18.”አባ” ኃ/ሚካኤል ንጉሤ – ጊኒር ሀገረ ስብከት
19.”አባ” አብርሃም መስቀሌ – ዳውሮ፣ኮንታ ሀገረ ስብከት
20.”አባ” ንዋየ ሥላሴ አክሊሉ – ምዕራብ ጉጂ ሀገረ ስብከት
21.አባ ኪ/ማርያም ቶሎሳ – ጅማና የም ሀገረ ስብከት
22.”አባ” ወ/ማርያም ጸጋ – ቦረና ሀገረ ስብከት
23.”አባ” አምደሚካኤል ኃይሌ – አርሲ (አሰላ) ሀገረ ስብከት
24.”አባ” መርሐጽድቅ ኃ/ማርያም – ጌዴኦ ፣ቡርጁ፣ አማሮ ሀገረ ስብከት
25.”አባ” ሞገስ ኃ/ማርያም – መናገሻ አምባ ቅድስት ማርያም ፣ ጋራ መድኃኔዓለምና ደ/ፀሐይ ቅ/ጊዮርጊስ “የበላይ ጠባቂ”
26.”አባ” ገ/ኢየሱስ ንጉሤ – ቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
@ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት
ከጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም የሣውላ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የነበሩት በቀን 14 /5 / 2015 ዓ.ም በአቡነ ሳዊሮስ ከተሰጠው “የጳጳሳት ሹመት” ውስጥ ቆሞስ አባ ገ/መድኅን ገብረማርያም የጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው የተሾሙትን ኮሚቴውና ሕዝቡ የማያውቀው ምንም አይነት ከጥያቄያችን ጋር ግንኙነት የሌለው ስለሆነ ኮሚቴውና ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚገባ እና ቤተ ክርስቲያናችንን በቅርበት ማየትና መከታተል ያስፈልጋል ሲል ኮሚቴው ገልጿል፡፡
ከጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
በአሁኑ ወቅት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን፤ በሚያገለግሉበትም ቦታ መደብን የሚሉ ሕገ ወጥ አካላት የሕግና የሥርዓት ምንጭ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚያቃልል፤ አንድነቷን የሚከፋፍል፤ ቀኖናዋንና ትውፊቷን የሚሸረሽር ተግባር ፈጽመዋል፡፡ የጉራጌ ሶዶ ሀ/ስብከት ጳጳስና የምሁር ኢየሱስ ገዳም የበላይ ጠባቂ ጳጳስ ተደርገው ሁለት ሰዎች ለጉራጌ ሀ/ስብከት መመደባቸውንም በአግራሞት ተመልክተናል፡፡
በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው ሕገ ወጥ ሿሚና ተሿሚዎች እኛን የሰበሰበችንን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመበተን የሚያደርጉትን የቀኖና ጥሰት ለማውገዝ የጉራጌ ሀ/ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገናል፡፡
በመሆኑም፡-
፩) የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆናችሁ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የምትወስኑትን የአንድነት ውሳኔ በአንቃዕድዎ ሆነን እየጠበቅን መሆናችንን በታላቅ አክብሮት እንገልጻለን፤
፪) የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት፣ የሀ/ስብከቱ ወረዳ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ ካህናትና ምእመናን በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከወትሮው በተለየ ንቃትና ታማኝነት በመጠበቅ፤ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግና መረጃዎችን በመለዋወጥ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አጥብቀን እናሳስባችኋለን፤
፫) በጉራጌ ዞን በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና በማስጠበቅ ሀገራዊ አደራችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት
ወልቂጤ-ኢትዮጵያ
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም.
“የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት፣ ቀኖናዊ ጥሰት እና አስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” አወገዘ፡፡” የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ
የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት በአካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት፣ ቀኖናዊ ጥሰት እና አስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” ማውገዙ ተገለጸ፡፡
ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ሁሉን አቀፍ ክህደት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን ክህደቱን የፈጸሙት አካላት ሥልጣን የሰጣቸውን መዋቅር (ተቋም) በመካድ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዛኝ ነው ብሏል።
የተፈጸመው ጉዳይም ሕገ ወጥና ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ወንጀል ነው ያለው አስተዳደር ጉባኤው በምንም መመዘኛ ይህን ከፈጸሙ አካላት ጋር መደራደር በተዘዋዋሪ የቤተ ክርቲያናችንን ሕግና ሥራዓትን ማፍረስ ነው ብሏል።
በማያያዝም ጎሰኝነት ኑፋቄ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው ይህን በመሰለ ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ክህደቶች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት መነቀፋቸውን በማንሳት በቋንቋ መማርና ማስተማር ችግር እንዳልሆነ በመረዳት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን በመሾም አገልግሎት እንዲሰጡ ስታደርግ መቆየቷን ሕገ ወጥ ድርጊቱን ከፈጸሙ አካላት በላይ ማስረጃ አይኖርም ብሏል።
ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ የውሳኔ ሐሳቦችን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሕግ አንጻር በመነሳት የጠቆመ ሲሆን የተፈጸመው ክህደት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሕግ አንጻር እንዴት እንደሚገለጽ የሚያመለክት ሰፊ የሚዲያ ሥራ እንዲሠራ በመወሰንና በቂ ማብራሪያ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመመደብ ከዛሬ ጀምሮ በሁሉም ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ወስኗል።
ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ተቋማቱን በንቃት መጠበቅና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፍ መመሪያን በትጋት መጠበቅ እንደሚገባና አስፈላጊው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲተላለፍ የወሰነው አስተዳደር
ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንዲታገድ፣ በተቋማችን ውስጥ የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአገግባቡ እንዲጠበቁ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን መንግሥትም እያደረገ ያለውን የቤተ ክርስቲያንን ጥበቃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጠይቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምእመናንና ምእመናት ከጸሎት በተጨማሪ መዋቅራዊ መመሪያዎችን በትዕግሥት እንዲጠብቁ አደራ በማለት የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት አጠናቋል።
@የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት