ሰሙነ ሕማማት

ክፍል ሦስት

. ዕለተ ረቡዕ

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፡-

 • የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
 • ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ ማርያም እንተ ዕፍረት ስለ ኃጢአቷ ተጸጽታ ዕንባዋን እያፈሰሰች ውድ ሽቱ ቀብታዋለች፤
 • ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተማክሯል (ተስማምቷል)፡፡

 . ምክረ አይሁድ፡ 

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምንት በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ለመያዝና ለመግደል በቀያፋ የሚመራው ሸንጐ በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት ነበሩት፡፡ በዕለቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡

ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር “ምን ትሰጡኛላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” በማለት ጌታችንን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል (ማቴ. ፳፮፥፲፭)፡፡

በዚህም  መሠረት ይህቺ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታ ኢየሱስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የመከሩበት ምክራቸውንም ያጸኑበትና ሰቅለው ይገድሉት ዘንድ የወሰኑባት ቀን በመሆኗ የአይሁድ የምክር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ምክራቸው ወቅት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን እንዴት አድርገው እንደሚይዙት በጣም ይጨነቁ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ወቅት በመሆኑ በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ብዙ ሕዝብ ትምህርቱን ያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር ከመፍራታቸው የተነሣ ነው፡፡ በዚህ ጭንቀትም ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው ተገኝቶ ጌታ ኢየሱስን እርሱ በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው፤ ለዚህ ተግባሩም ሠላሳ ብር ወረታውን እንዲከፍሉት ከእነርሱ ጋር በመስማማቱና የምክራቸው ተባባሪ በመሆኑ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማር. ፳፮፥፩-፭ ፤ ፳፮፥፲፬-፲፮ ፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩ ፤ ሉቃ. ፳፪፥፩)

. የመልካም መዓዛ ቀን፡

ዕለተ ረቡዕ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ተቀምጦ ሳለ በመላ ዘመንዋ ራስዋን ለኃጢአት በማስገዛት በዝሙት ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ ዕፍረት ኃጢአትን ይቅር የሚል መልካም መዓዛ ያለው አምላክ መጣ ስትል ውድ የሆነ ዋጋ ያለው ወይም የሦስት መቶ ዲናር ሽቱን ገዝታ ወደ እርሱ በመምጣትና በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው የመልካም መዓዛ ቀንም ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከኃጢአትዋ የተነሣ መልካም መዓዛ ያልነበራት ማርያም እንተ ዕፍረት በዚህ በጎ ተግባርዋ መልካም መዓዛ ያላት ሆና ወደ ቤትዋ ተመልሳለች፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፮ ፤ ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

. የዕንባ ቀን፡

ማርያም እንተ ዕፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን እያጠበች፣ በፀጉሯም እግሩን እያበሰች ስለ ኃጢአቷ ሥርየት ተማጽናዋለችና የዕንባ ቀን ትባላለች፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፮-፲፫ ፤ ማር. ፲፬፥፫-፱ ፤ ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ አሰምቶ ነበር፡፡

“ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” አለ፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮)፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም ብቻ በመያዝ እምነታቸውን፣ በገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳውያን ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሰሙነ ሕማማት

ክፍል ሁለት

. ዕለተ ሠሉስ

. የጥያቄ ቀን፡ ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት ውስጥ ዕለተ ሠሉስ የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት አንጽሖተ ቤተ መቅደስን ከፈጸመ በኋላ በዚህች ዕለት ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “በማን ሥልጣን ይህ ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እኔም አንዲት ቃል እጠይቃችኋለሁ፣ የነገራችሁኝ እንደሆነ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ” አላቸው፡፡ ጌታችንም ጥያቄውን ይመልሱለት ዘንድ “የዮሐንስ ጥምቀቱ ከየት ነው? ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰው?ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እርስ በርሳቸው ተነጋግረው እንዲህ አሉ “ከሰማይ ነው ብንለው እንኪያ ለምን አላመናችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንለውም ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራቸዋለን ተባባሉ፡፡ በመጨረሻም መልስ መስጠት ስላልቻሉ “ከወዴት እንደሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም “እንኪያስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯ ፤ ማር. ፲፩፥፳፯-፴፫፣ ሉቃ. ፳፥፩-፰) በዚህም ምክንያት የሰሙነ ሕማማት ማክሰኞ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

. የትምህርት ቀን፡ ይህቺ ዕለት ዕለተ ትምህርት ወይም የትምህርት ቀን በመባልም ትጠራለች፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት በማስተማር የተሰጠው ስያሜ ሲሆን ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብና መክሮ መመለስ እንደሚገባን ሲገልጽልን ነው፡፡

በዚህም ትምህርቱ ሁለት ወንድማማቾችን አባታቸው ወደ ወይን ቦታ ሄደው ይሠሩ ዘንድ እንደጠየቃቸው፤ የመጀመሪያው እምቢ ቢልም ተጸጽቶ ሊሠራ መሄዱን፤ ሁለተኛውም እሺ ብሎ ነገር ግን ቃሉን አጥፎ ሳይሄድ መቅረቱን ነገራቸው፡፡ እርሱም ትምህርቱን ከነገራቸው በኋላ አስተምሮ ብቻ አልተዋቸውም፤ ጥያቄውን አስከትሏል፡፡ “እንግዲህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ማንኛው ነው?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ፊተኛው ነዋ” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ሲል ገሠጻቸው፡- “እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥጥ በመግባት ይቀድሟችኋል፡፡ ዮሐንስ ወደ እናንተ በጽድቅ ጎዳና መጣ፤ አላመናችሁበትም፣ ቀራጮችና አመንዝሮች ግን አመኑበት፤ እናንተም በኋላ በእርሱ ለማምነን አይታችሁ እንኳ ንስሓ አልገባችሁም” አላቸው፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፰ ፤ ፳፭፥፵፮ ፤ ማር. ፲፪፥፪ ፤ ፲፫፥፴፯ ፤ ሉቃ. ፳፥፱ ፤ ፳፩፥፴፰)

 ሌላው በዚሁ ቀን በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ስለ ወይን እና ወይኑን የተከለው ባለቤት ድካም የተመለከተ ነበር፡፡ “ሌላ ምሳሌ ስሙ፤ ባለቤት ሰው ወይንን ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጭመቂያም አስቆፈረለት፤ ግንብንም ሠራለት፤ ለገባሮችም ሰጥቷቸው ሄደ፡፡ የሚያፈራበት ወራት በደረስ ጊዜም ከወይኑ ፍሬ ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮቹን ወደ ገባሮቹ ላከ፡፡ ገባሮቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን በበትር ደበደቡት፣ አንዱንም ገደሉት፣ ሌላውንም በድንጋይ መቱት፡፡” በማለት አስረዳቸው፡፡ በዚህም በብቻ አላበቃም ሌሎችን ከዚህ በፊት ከላካቸው አገልጋዮች ቁጥር በላይ ወደ ገባሮቹ ሰደዳቸው፡፡ ነገር ግን ገባሮቹ የተላኩትን አገልጋዮች ደብድበው አባረሯቸው፡፡

 ባለ ወይኑ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ልጄን ያከብሩትና ይፈሩት ይሆናል ብሎ አንድ ልጁን ከወይኑ ያመጣለት ዘንድ ወደ ገባሮቹ ላከው፡፡ ገባሮቹም ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው “እነሆ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ፡፡ ይዘውም ከወይኑ ቦታ ውጭ አውጥተው ገደሉት፡፡ እንግዲህ የወይኑ ቦታ ባለቤት በመጣ ጊዜ እነዚህ ገባሮች ምን ያደርጋቸዋል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡

 የካህናት አለቆችንና የሕዝቡ ሽማግሌዎችም “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ ወይኑንም በየጊዜው ፍሬውን ለሚሰጡት ለሌሎች ገባሮች ይሰጣል” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላቸው”… ግንበኞች የናቁአት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነች፡፡ … ስለዚህ እላችኋለሁ፡- የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርጉ ለአሕዘብ ትሰጣለች፡፡ በዚያችም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፡፡፣ በላዩ የሚወድቅበትንም ትፈጨዋለች” የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ፈሪሳውያንም ይህ ስለ እነርሱ የተነገረ መሆኑን ዐወቁ፡፡

ለሦስተኛ ጊዜም ለልጁ ሠርግ ስለ አደረገው ንጉሥ በምሳሌ አስተማራቸው፡፡ እነርሱ ግን ያስተማራቸውን ትምህርት ተረድተው ወደ ንስሓ ከመመለስ ይልቅ ጌታችን መድኃነኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስን በአነጋገሩ ያጠምዱትና ይይዙት ዘንድ ተማከሩ፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፵፭ ፤ ፳፪፥፩-፳፪)፡፡

ይቆየን

“መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?” (ማቴ. ፳፬፥፵፭)

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ሰያሜውንም የሰጠው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በሆነው ጾመ ድጓ በተባለው መጽሐፍ የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም መሠረት በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄር ወይም ታማኝ አገልጋይ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

ይህንንም ወንጌላው ቅዱስ ማቴዎስ እንዲህ እያለ ይገልጸዋል፡፡ “መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፣ ለአንድ አምስት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ወርቅ ቀበረ፡፡” (ማቴ. ፳፭፥፲፬-፲፰)

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ይቆጣጠራቸው ዘንድ ተመልሶ መጣ፡፡ “ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነት ያገኝ ይሆን?” እንዲል በእነዚህ አገልጋዮች አንጻር ምእመናን ለእግዚአብሔር ያላቸውን እምነትና ታማኝነት፣ ታምኖም መኖር ምን ያህል እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ (ሉቃ .፲፰፥፰)

አገልጋዮቹም ከጌታቸው የተቀበሉትን መክሊትና ያተረፉትን ይዘው በተራ ቀረቡ፡፡  በቅድሚያም አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና፡- “አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ፤ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- አቤቱ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፍሁ አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡” ሁለቱም የተሰጣቸውን መክሊት ተጠቅመው ወጥተው ወርደው ሠርተውና አትርፈው ተገኝተዋልና ያገኙትንም ይዘው በመቅረብ ከጌታቸው ዘንድ ሞገስና ክብርን አግኝተዋል፡፡

ጌታው ሠርቶ፣ አገልግሎ ያተርፍበት ዘንድ አንድ መክሊት የተሰጠው አገልጋ ግን ከሁለቱ በተለየ መንገድ ወደ ጌታው ቀረበ፡፡  “አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፡፡ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ መክሊትህ” አለው፡፡  ጌታውም መልሶ አለው፡- “አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ ካልበተንሁበት የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ ታውቃለህ? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፡- ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና ይጨምሩለታልም፡ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደአለ ጨለማ አውጡት፡፡” (ማቴ. ፳፭፥፲፬-፴) አለ፡፡

ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው፤ መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ የሚያሳይ ነው፡፡

ያገለገሉትና ታምነው የተገኙት ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ማለቱ ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ፤ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት፣ ስቃይ፣ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መውረዳቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ነቢያት፣ ጻድቃን ሠማዕታት፣ ቅዱሳን በታማኝ አገልግሎታቸው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ዮሴፍ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስን ማንሣት የምንችል ሲሆን፤ ለጌታቸው ያልታመኑት ደግሞ ይሁዳ፣ ሐናንያ፣ ሰጲራ፣ የመሳሰሉት የደረሰባቸውን ጉዳት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው አልቋልና፤ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና” በማለት የገለጸው፡፡ (መዝ. ፲፩፥፩) ስለዚህ ሁሉም በየአለበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ “አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ” የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል መስማት ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን መንግሥቱን እንድንወርስ፣ “ገብርኄር” እንድንባል አምላካችን ይርዳን፡፡

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

“መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሰይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ፡፡ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም– “ጌታው መልካም ሲሠራ አግኝቶ በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር በታናሹ የታመንህ ደግና ታማኝ አገልጋይ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡

 መልእክታት

የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት፡- (፪ኛጢሞ. ፲፮)

“እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል። …”

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት፡- (፩ኛጴጥ. ፲፪)

“እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። …”

 ግብረ ሐዋርያት፡- (ሐዋ. ፱)

“እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።”

ምስባክ፡- (መዝ. ፴፱፰-፱)

ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፤ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፤ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡
ትርጉም፦ “አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፡፡”

 ወንጌል (ማቴ. ፳፭፲፬፴፩)

“መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፣ ለአንድ አምስት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ወርቅ ቀበረ፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና፡- አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ፤ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ ፡- አቤቱ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፍሁ አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፡፡ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ መክሊትህ፡፡ ጌታውም መልሶ አለው፡- አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ ካልበተንሁበት የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ ታውቃለህ? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጠቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፡- ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና ይጨምሩለታልም፡ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደአለ ጨለማ አውጡት፡፡”

ቅዳሴ: ዘባስልዮስ

ቅድስት

ትዕግሥት ባሳዝነው

ሰውነቴን ሳስብ በትዕቢት መዛሉን፣                                                   ሰው ከንቱ፣ ሰው መና፤ ከአምላኩ ተጣልቶ፣

ከንቱነቴን አየሁ በስስት መድከሙን፣                                               ለዲያቢሎስ ግብር፣ ለክፋት ያደረ ያልተሰጠን ሽቶ፣

እኔነቴን አየሁ ማምለኩ ገንዘብን፡፡                                                      ሲሰግድ የሚያድር ለቂም ሐውልት ሠርቶ፣

ይህን ሁሉ ሠርቼ አምላክ ላንዴ ባየው፣                                             ሲዘምር የሚያድር በጥላቻ ሰክሮ፣

እኔን ለማዳን መች ተሣነው፡፡                                                              ሲቀድስ የሚውል በመለያየት ጸንቶ፣

አምላክነቱን ረስቶ ሰው የሆነ መስሎት፣                                            ሰው ከንቱ፣ ሰው መና በትዕቢት ተውጦ፣

ዲያብሎስ ሊያስተው ቢፈትነው በትዕቢት፣                                    ሽማግሌን አሳዝኖ፣ ታላቁን አቅልሎ፣

አርባ ቀን አርባ ሌት፣                                                                         ለስስት ተገዝቶ ባለእንጀራን ክዶ፣

ጾምን አስተባብሮ በመቆም ለፀሎት፣                                                ገንዘብን የሚያመልክ ከሰውነት ወጥቶ፡፡

ዲያቢሎስ አፈረ ወጥመዱ ከሽፎበት፡፡                                               ጾሙንም በትዕቢት፣ ጸሎትን በስስት፣

አምላክ በእኒህ ኃጢያት ቢፈተንም ቅሉ፣                                         ምፅዋትን በፍቅረ ንዋይ፣

ዳሩ ለእኛ ነበር ለክርስቲያን ሁሉ፣                                                    እንዲህ ቢያታልል ወደ አምላኩ ሳያይ፣

ክርስቲያን ከተባልን ከክርስቶስ ወስደን፣                                         እርሱ ግን ይታያል ሥራውም በአዶናይ፣

ጾምንም ከጾምናት ከአምላክ ተምረን፣                                              እናም እንዲህ አልኩኝ አምላኬን ስማጸን፣

ታዲያ ለምን ይሆን ትዕቢት ያሳበጠን፣                                            ጾምህን ስንጾም ትዕቢታችን ይራቅ፣

ስስት ያጎበጠን፣ ገንዘብ ያስመለከን?                                                ጸሎትህን ስንጸልይ ትኅትናችን ይድመቅ፡፡

ጾማችንን ሳንሽር ጸሎታችን ሳንተው፣                                             አባት ሆይ ስንልህ ስስታችን ይጥፋ፣

በኃጢያት ደልበን በበደል የኖርነው፣                                               አምላካችን ስንል ፍቅርችንን አስፋ፣

ንስሓን ረግጠን ልጅነት ያጣነው፡፡                                                     ፍቅረ ነዋይም ይጥፋ፣

ሰው ከንቱ፣ ሰው መና፤ በዓለም የታለለ፣                                          በጾምህ ቀድሰን፣ በጸሎትህ አጽናን፣

በሰም ብቻ ከብሮ በግብሩ የተጣለ፣                                                   ዛሬም እንደ ጥንቱ ስንጠፋ ፈልገን፣

ሰውነቱ ከብዶት ሰው መሆን የረሳ፣                                                   አባታችን ስንል ልጆቼ ኑ በለን፣

ለዲያቢሎስ ግብር ለእርሱው እጅ የነሳ፣                                           ዛሬም ስንበድል በንስሓ ማረን፣

ጓደኛውን ክዶ አምላኩን ያስቆጣ፣                                                    በፍቅርህ አክመን፣ በቁስልህ ፈውሰን፣

የሌለውን ሽቶ ያለውንም ያጣ፡፡                                                          በሞትህ አድነን በመስቀልህ ጋርደን፣

በበደሉ ደልቦ በክፋት የኖረ፣                                                              ቅድስቷን እንቀድስ ከበደል አረቀህ ፣

ቂም በቀልን ቋጥሮ ሕጉንም የሻረ፣                                                    ጾምህን አስጀምረን,

በባልጀራው መኖር እርሱ እንቅልፍ ያጣ፣                                        ትዕቢት፣ስስት፣ ፍቅረ ንዋይ አጠፋ ከልባችን።

ከሰውነት ክብር ከሥርዓት የወጣ፡፡

ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ ድርሰቱ በዐቢይ ጾም ለሚገኙት ሳምንታት ማለትም በየሳምንቱ ለሚውሉት እሑዶች መዝሙር አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል። ባለፈው ሳምንት “ዘወረደ”ን እንዳቀረብን ሁሉ በዚህ ዝግጅታችን ደግሞ ሁለተኛውን ሳምንት ቅድስትን እንመለከታለን፡፡ ፡፡

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ተብሎ ተሰይሟል። ቅድስት የሚለው ቃል ግሱ “ቀደሰ” ሲሆን “ለየ፣ አከበረ፣ መረጠ የሚል ትርጉም ሲኖረው፤- ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው። ቅዱስ የሚለው ቃል እንደ የአገባቡ ለፈጣሪም ለፍጡርም ያገለግላል። ለፈጣሪ ሲነገር እንደ ፈጣሪነቱ ትርጉሙ ይሰፋል፣ ይጠልቃል፡፡ ለፍጡር ሲነገር ደግሞ ቅድስናውን ያገኙት ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ “ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፡፡” እንዲል፡፡ (ሮሜ. ፰፥፴)

ዕለተ ሰንበት ቅድስት መባሏ በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል ለቅድስና ሕይወት ምልክት ማስታወሻ እንድትሆን ነው። በባሕሪይው ቅዱስ የሆነ አምላክ ዓለምን የማዳን ሥራውን የጀመረበትን፣ ፅንሰቱን፣ እንዲሁም የማዳን ሥራውንም አጠናቆ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያበሰረበትን ትንሣኤውን የምናስብበት በመሆኑ የዕለቱ ቅድስና፣ የፈጣሪን ቅዱስ ተግባር የምናደንቅበት፣ የዋለልንን ውለታ ከፍ ከፍ እያድረግን እርሱን የምናመሰግንበት ዕለት ነው። ይህም እኛን ወደ በለጠ የቅድስና ሕይወት የሚያሸጋግረን በመሆኑ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር በየጊዜው እንድናስብና በፍቅሩም እንድንኖር ያግዘናል፡፡

ዕለተ ሰንበት ነገረ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚዘከርባት ናትና “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘፀ. ፳፥፰) ተብሏል፡፡ የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ፣ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፣ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና“እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፪፥፫)

“እንግዲህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” የተባለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የባረከውን የቀደሰውን እኛ ድጋሚ የምንቀድስ የምንባርክ ሆነን ሳይሆን በዕለተ ሰንበት ራሳችንን በተለየ ሁኔታ ለቅዱስ ተግባር እንድንለይ፣ ለሥጋችን ከምንፈጽማቸው ተግባራት ይልቅ ለተግባረ ነፍስ እንድናደላ ያስረዳናል። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።እንዳለው (መዝ. ፻፲፯፥፳፬)

በዕለተ ሰንበት የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይባረካል፣ ይቀደሳል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “አንቀጸ ብፁዓን” በመባል የተጠቀሱትን መፈጸም ለክርስቲያን ሁሉ ይገባል፡፡ (ማቴ. ፭፥፩-፲፪) በዚህ ታሳቢነት ዕለቱም ዕለተ ቅድስና መሆኑን ለማጠየቅ ቅድስት ተብሏል። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ (ዘሌ. ፲፱፥፪) ተብለናልና ቅድስት በተባለች ዕለተ ሰንበት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመገስገስ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔር በመስማት፣ የታመመን፣ የታሠረን በመጠየቅ፣ በአጠቃላይ የቅድስና ሥራዎችን እንድንሠራ ለእኛ ለክርስቲያኖች ታዘናልና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የቅድስና ሕይወት መሠረቱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ መጠበቅና ማድረግ ሆኖ ሳለ ለመቀደስ የእኛ መሻት፣ መፈለግ ወሳኝ ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጾመ ሰብአ ነነዌ

ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ለሦስት ቀን የጾሙት ጾም ነው፡፡ የነነዌ ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትሆን መሥራቿም ናምሩድ ነው (ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪)፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶ ነበር (ዮናስ ፬፥፲፩)፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢዩ ዮናስን የስሙ ትርጓሜ ርግብ የሆነ ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሓ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ከተማ (ሕዝብ) ላከው (ሉቃ. ፲፩፥፴)፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፤ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ በዚያን ጊዜ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢት ተናገረ (፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩)፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል (፩ኛነገ.፲፯፥፲፱)፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ ብሎ የተባለውን ባለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ሳለ ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ዮናስ ግን በመርከቧ በታችኛው ክፍል እንቅልፉን ተኝቶ ያንኳርፍ ነበር፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ጀመሩ፡፡ የመርከቡም አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አለው፡፡ (ዮናስ ፩፥፮) ተሳፋሪዎቹም ተጨንቀው ይህ ነገር ያገኘን በማን ምክንያት ነው?  ብለው ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በነቢዩ ዮናስ ላይ ወደቀ፡፡

ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ” በማለት ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይሆንም አሉ፡፡ ነገር ግን ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜ ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ዋጠው፤ እግዚአብሔርበበዓሣ አንበሪውም ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አድርሶ በየብስ ላይ ተፋው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል (ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪)፡፡

የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዮናስ መጣ፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የነገርኩህንም የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ነቢዩ ዮናስም “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” እያለ ሰበከ፡፡ (ዮናስ ፫፥፩)፡፡ የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ።ጾምም ዐዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፤ ሰዎችና እንስሳትም አንዳች እንዳይቀምሱ ውኃም እንዳይጠጡ ዐዋጅም አስነገረ፡፡ (ዮናስ ፫)

ዮናስ ግን ፈጽሞ አዘነ፣ ተከዘም፡፡ ምነው ቢሉ፡- ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔር መሐሪነት፣ ቸርነቱም የበዛ እንደሆነ አውቋልና ቁጣውን በምሕረት እንደሚለውጥ ስለተረዳ “ሐሰተኛ ነቢይ እባላላሁ” በማለት ተበሳጨ፤ ከከተማይቱም ወጣ፡፡ ከፀሐዩ ግለት ይሸሸግ ዘንድ ጥጉን ያዘ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅሉን አዘዘለትና ከዮናስ ራስ ላይ ጥላ ትሆነው ዘንድ ከፍ ከፍ አደረጋት፡፡ ዮናስም ስለቅሊቱ ደስ አለው፡፡ ነገር ግን በነጋ ጊዜ እግዚአብሔር ትልቁን ትል አስነሥቶ ቅሊቱን መታ ቅሊቱም ወዲያው ደረቀች፡፡ ዮናስንም ፀሐዩ መታው፡፡ ተስፋ ቆርጦም “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ፡፡

ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ እግዚአብሔር አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል” በማለት ነቢዩ ዮናስን ተናገረው፡፡ ውሸታም ላለመባል መኮብለሉም ስሕተት መሆኑን አስረድቶታል፡፡

ነቢዩ ዮናስ ሐሰተኛ እንዳይባልም ከሰማይ የወረደው እሳት እንደ ደመና ሆኖ ከላይ የታላላቅ ዛፎች ቅጠል እስኪጠወልጉ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሓቸው በከንቱ እንዳልቀረም አስረድቷቸዋል (ትንቢተ ዮናስ)፡፡ በሦስት ቀን ሱባኤም በንስሓ ተመልሰዋልና እግዚአብሔር ሊያመጣ ካለው መቅሰፍት አድኗቸዋል፡፡

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኃጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ሆነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡

ስለሆነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኃጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” (ኤፌ ፪፥፳)

                                                                                  በኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ

                                                                                        ክፍል  -ሁለት 

      የሐዋርያት ጾም ስያሜና ቀኖናዊ መሠረቱ

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን መለኮታዊ ዓላማ አጠናቆ ወደ ባሕርይ አባቱ ከማረጉ በፊት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሰብስቦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ ያዘዝኋቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ፳፰÷፲፱ -፳) በማለት ታላቁን ተልእኮ አዟቸው ነበር፡፡

በፍርሃት ውስጥ ሆነው ይህንን መለኮታዊ አደራ የተቀበሉት ሐዋርያት ለአገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት ከፍርሃታቸው የሚያላቅቃቸው፤ የሚያጽናናቸው እና የሚያበረታታቸው እንዲሁም ከሐሰተኛው ዓለም ለይቶ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው ሰማያዊ ኃይል ያስፈልጋቸው ነበርና “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እም አርያም፤ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ፡፡”(ሉቃ ፳፬÷፵፱) የሚል ትእዛዝ ተነግሯቸው ተስፋም ተስጥቷቸው  ነበር፡፡
በተስፋውም መሠረት ኢየሩሳሌም በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም ተሰብስበው በጸሎት እየተጉና በአንድ ልብ ሆነው ይህንን ሕያው ተስፋ በመጠባበቅ ሳሉ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በተነሣ በኀምሳኛው ቀን  ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ እሳት ወረደላቸው፤ የፍርሃት መንፈስ ተወግዶ በምትኩ ደፋሮችና በብዙ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሆኑ፤ በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከትም በአንድ ቀን ሶስት ሺህ  ነፍሳት አምነው ተጠመቁ፡፡

ዕለቱም የቤተ ክርስቲያን መመሥረት እውን የሆነበትና አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ስለነበር የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ተባለ፡፡ (የሐዋ. ፪÷፩-፵፯) የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ ፍርሃትና ስጋታቸው የተወገደላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ለወንጌል አገልግሎት ከመሠማራታቸው በፊትና ሕገ ወንጌልን ከማስተማራቸው አስቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲቃና፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለያቸውና የመንፈስ ቅዱስን ምሪትና ኃይል ለመቀበል ሱባኤ ያዙ፡፡ ይህም ጾም “ጾመ ሐዋርያት” ወይም “የሰኔ ጾም” ተባለ፡፡ የሰኔ ጾም ለምን ተባለ ቢሉ ከክረምቱ መግባት ቀደም ብሎ ከወርኃ ሰኔ ጀምሮ የሚጾም በመሆኑ የሰኔ ጾም በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡

ሐዋርያት የአገልግሎት መጀመሪያ የሆነውን ጾም ሲፈጽሙም ዓለምን በወንጌል ጨውነት ያጣፍጡ ዘንድ የሚያገለግሉበትን ክፍለ ዓለም ዕጣ በመጣጣል ዕጣው ወደ ደረሳቸው የአገልግሎት ቦታ መሰማራታቸውን የቤተ ክርስቲያን የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት አባቶቻችን ያስረዳሉ፡፡

ጾመ ሐዋርያት “የቀሳውስት ጾም” ወይስ የክርስቲያኖች ሁሉ ጾም?

የሐዋርያትን ጾም አንዳንዶች “የቀሳውስት ጾም ነው” ሲሉት ይሰማል፡፡ ይህም ከአሰያየሙ ጋር የተያያዘ ብዥታን በመጠቀም ላለመጾም የሚፈልጉ ወገኖች ያመጡት አስተሳሰብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች “የሐዋርያት” የሚለውን ቃል ብቻ በመውሰድ ጥንት ይህንን ጾም ሐዋርያት ብቻ እንጂ ሕዝቡ አልጾመውም፤ ዛሬ ደግሞ በሐዋርያት እግር የተተኩ ካህናት (ቄሶች) ናቸውና ጾሙም የእነርሱ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ቤተክርስቲያን ግን ይህን የአዋጅ ጾም ጳጳስ፣ ቄስ/መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ሰንበት ተማሪ ምእመን ሳትል በ፵ እና በ፹ ቀን የተጠመቀና ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነው ሁሉ እንዲጾም ዐውጃለች፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል (ፍት.ነገ. ፲፭÷ ፭፰፮)፡፡

የሐዋርያት ጾም የሁላችንም ጾም ነው!!

            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” እንዳለ (ኤፌ ፪÷፳) በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ለታነጽን ለእኛ ለክርስቲያኖች የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው፡፡ ጾሙንም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምእመናን እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ በማሰብ በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ መታዘዝ እንፈጽም ዘንድ ይገባል፡፡ (ፊልጵ. ፪÷፲፪) ከልብ ንስሓ በመግባት፣ ከምጽዋትና ከጸሎት ጋር፣ እግዚአብሔር ደስ በሚሰኝበት መንገድ ከግብዝነት ሕይወት በጸዳ መልኩ እንጹም፡፡ ከጸሎትና ከምጽዋት ጋር በሚገባ ጾመን ከራሳችንን እና ከእግዚአብሔር አምላካችን ጋር የምንታረቅበት ሱባኤ ያደርግልን ዘንድ፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በረከትና ጸሎት አይለየን፡፡

 

 

 

      “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” (ኤፌ ፪፥፳)

   

                                                        ኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ

                                                     ክፍል -፩

ጾም የሚለው ቃል “ጾመ“ ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ እና ጥቅል ትርጉምን የያዘ ቃል ነው፡፡ ይህም የጥሉላት መባልዕትን ለተወሰኑ ወራት መተው፣ መከልከልን እንዲሁም ከክፉ ነገር ሁሉ ራስን መጠበቅ፣ መቆጣጠርና መግዛት ማለት ነው፡፡

ጾም የመላው ሰውነታችን መታዘዝን የሚጠይቅ መንፈሳዊ ተግባር እንጂ በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ ገደብን የሚጥል አለመሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ይጹም ዐይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እመሰሚዐኅሡም፤ ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት፤ አንደበትም ክፉ ነገርን ከመናገር፤ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” በማለት ይመክረናል፡፡

ከቅዱስ ያሬድ ምክር በመነሣት ሰውነታችንን የምንከለከለው ከእህልና ውኃ ማለትም ከምግበ ሥጋ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን፣ ሰዎችንም ከሚጎዳ ከማንኛውም ዓይነት የኃጢአት ሥራ ከሐሜት፤ ከዝሙት፤ ከክፋት፣ ከምቀኝነትና ከመሳሰሉት የሥጋ ፍሬዎች ፈጽሞ መቆጠብና መከልከል እንደሚገባ ነው፡፡

የጾም መሠረታዊ ዓላማ
ጾም ከጸሎትና ከስግደት እንዲሁም ከምጽዋት ጋር የሚፈጸም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትጥቅ የአንብዕ፣ የንስሓ ምንጭና የመልካም ተጋድሎ መሠረት ነው፡፡

በሃይማኖት ስንኖር ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከለው በራሳቸው ኃጢአት ኖሮባቸው አይደለም፤ ይልቁንም ምግብ በልተን መጠጥም ጠጥተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብና የሥጋ ፍሬ ለሆነው ኃጢአት ከምንዳረግ ይልቅ መንፈሳዊ ትጥቃችንን በማጥበቅና ስሜታችንን በመጎሰም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ለማስገዛት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንንም ያጠፋቸዋል” (፩ኛ ቆሮ ፮÷፲፫) በማለት ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ በመነሣት የምንጾምበት መሠረታዊ ዓላማ ለመራብና ለመጠማት ወይም አካላዊ ሥጋችንን ለማጎሳቆል ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጽናትና ዘለዓለማዊውን መንግሥት ለመውረስ ነው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉ በሥርዓት እንዲሆን ታስተምራለችና ለጾምም ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ በዚህም መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማትን ዐውጃለች፡፡ ከእነዚህም መካከል ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም) አንዱ ነው፡፡

ይህ ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው ስለ ጾሙት አስቀድሞ “የጰንጤቆስጤ ጾም” ወይም “የደቀ መዛሙርት ጾም” ይባል ነበር፡፡ ከኒቅያ ጉባዔ በኋላ እስከ ዛሬ የምንጠቀምበትን “የሐዋርያት ጾም” የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ”(ማቴ. ፱÷፲፭-፲፮) በማለት እንዲጾሙ አዟቸዋል፡፡ እነርሱም ወደ አገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገው ጾመውታል፡፡

የሐዋርያት ጾም በሦስተኛው እና በአራታኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፉት መጽሐፈ ድዲስቅልያ፣ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ እንዲሁም ቅዱስ አትናቴዎስ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክት ላይ ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ሰፍረውና ቆጥረው ባስረከቡን ሐዋርያውያን አበው መሠረትነት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሁሉ የሐዋርያትን ጾም እንጾማለን፡፡

ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የጾሙት ስለ ሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ጾሟል፡፡ እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡

ከዚያም በ፪፻፰፶ ዓ.ም ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እስከ ሐዋርያት በዓል (The Feast of the Holy Apostles) ሐምሌ ፭ ድረስ እንዲሆን አባቶች ደነገጉ፡፡ ይህም የተደረገው የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም ዐደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ ነው በማለት ያጠናክሩታል፡፡ መጽሐፈ ድዲስቅልያ ደግሞ ሐዋርያት ፵ ቀን እንደ ጾሙ ከዚያም በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ እግራቸውን አጥቧቸው ለስብከተ ወንጌል እንደተሰማሩ ያስረዳል፡፡

              ይቆየን !

ፈተና 

 

                                ክፍል  ሁለት

                     መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ (አውስትራልያ)

ፈተና ለምን?

ፈተና ከዬትም አቅጣጫና አካባቢ ወይም ምክንያት ይምጣ በውስጡ ግን ዓላማ ይኖረዋል። ትልቁ ነገር የፈተናው መምጣት ሳይሆን ለፈተናው ዓላማ ዝግጁና ብቁ ኾኖ መገኘቱ ላይ ነው።

 1. ፈተና የኃጢአታችን ውጤት ሊኾን ይችላል:: ምክንያቱም ሰው የዘራውን ያጭዳልና።
 2. ፈተና ሊቀሰቅሰንና ሊያተጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚተላለፍልን ደወል ሊኾን ይችላል።
 3. እምነታችንና ፍቅራችን ሊመዘንበት ሊሰጠን ይችላል።
 4. በፈተና ለተያዙ በኃጢአት ለወደቁ መራራትን እንድንማር ሊሰጠን ይችላል።
 5. ዋጋችንን ሊያበዛልን ልንፈተን እንችላለን።
 6. በእኛ መፈተን ውስጥ ሌሎችን ሊያስተምርበት ሊሰጠን ይችላል።

ከላይ ለመግለጥ እንደተሞከረው የፈተና ምክንያቱ በርካታ ነው። ዋናው ነገር እግዚአብሔር ልጆቹን እንደማይፈትንና ከአቅማችን በላይ ለኾነ ፈተና አሳልፎ እንደማይሰጠን ይልቁንም ከፈተናው ጋር መውጫውን አብሮ እንደሚሰጠን መረዳትና ማመናችን ነው።

ይኽም በቅዱሳት መጻሕፍት “ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።”(ያዕ. ፩፥፲፫) እንዲሁም ““ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” ተብሏል።( ፩ኛ.ቆሮ.፲፥፲፫)

ሊቁ ቅዱስ ባስልዮስ እንደተናገረው እግዚአብሔር የሰውን ድካም ያውቃል። ስለሚያውቅም ከአቅማችን በላይ በኾነ ፈተና እንድንወድቅበት አይሻም። ስለዚህ በእኛ ስሕተት ሳይሆን ከአእምሯችን ውጪ የኾነ ፈተና ሲገጥመን ተስፋ ልንቆርጥና ታዳጊ እንደሌላቸው ወገኖች ልንኾን አይገባንም። እርሱ ቅዱስ ጳውሎስ “በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።

እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል” በማለት እንዳስተማረን የሞት ጥላ ቢከብበን እንኳን ከፈተናው ያድነናል (፪ኛ ቆሮ.፩:፰-፲፩)

ፈተና ሲገጥመን ምን እናድርግ ?

ፈተናን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ አይቻልም። በመኾኑም እንደ ኦርቶዶክሳዊነታችን ፈተና ሲገጥመን ፈተናውን በምን ዓይነት መንፈሳዊ ጥበብ መፍታት እንዳለብን ተረጋግተን ማሰብ ይጠበቅብናል።

 1. መጸለይ

ጸሎት ከፈተና ያወጣናል። ወደ ፈተናም እንዳንገባ ይጠብቀናል። ስለዚህ በወንጌል “አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን: ከክፉ ኹሉ አድነን እንጂ” ብላችሁ ጸልዩ እንደተባለው ተግቶ መጸለይ ይገባል።  በሌላ አንቀጽም ጌታችን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” ብሎ እንዳስተማረን ከፈተና በፊትም ኾነ ፈተና ውስጥ ሳለን አጥብቀን መጸለይ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው።

 1. እግዚአብሔርን ማመስገን

መጽሐፍ በኹሉ አመስግኑ እንዳለን በፈተናችንም እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል። “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና” እንዲል።( ፩ኛ ተሰ.፭፥፲፯-፲፰) ጻድቁ ኢዮብ ሰውነቱን ሀብቱንና አስር ልጆቹን በአንዲት ቀን ባጣበት ወቅት “እግዚአብሔር ሰጠ: እግዚአብሔር ነሣ:: እግዚአብሔር ይመስገን” አለ እንጂ በአፉ የስንፍናን ነገር አልተናገረም። እስቲ እኛስ እንዳናመሰግን የሚያግዱንን ፈተናዎቻችንን ከኢዮብ ፈተና አንፃር እንመዝናቸው።

 1. መጽናት

ፈተና የሚጸናው እንዲጸና ሥጋዊ ፈቃዱን የሚከተለውም ምርጫውን እንዲከተል የሚመጣበት ጊዜ አለ። በፈተና ትእግስታችን ይለካል። በፈተና እምነታችን ይመዘናል። በፈተና ፍሬውና እንክርዳዱ ይለያል። በፈተና ልዩ የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት ይገኛል። መፍትሐው በእምነት ልብን አበርትቶ መጽናት ብቻ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና” ያለውን በፈተና መጽናት የሚያስገኘውን በረከት ያስረዳል (ያዕ.፩፥፲፪)

ቅዱስ ጳውሎስም በፈተና የመታገስን ጥቅም “ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ ፭፥፫)   ቅዱስ ያዕቆብም በበኩሉ “ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት” በማለት በፈተናችን ውስጥ እየጸናንና እየተጽናናን መታገስ እንዳለብን መክሮናል (ያዕ.፩፥፪-፫)

 1. ንስሐ መግባት

እግዚአብሔር  ስንረሳው ነፍሳችን በኃጢአት ስትጎሰቁልና ስትሞት ጽድቅ ጠፍቶ ሁሉም በበደል ተገርኝቶ ሲያዝ የራቀውን ሊያቀርብ: የወደቀውን ሊያነሣ: የተፍገመገመውን ሊያጸና  ይገሥጸናል።ለዚኽ መፍትሄው ምክንያት ሳያበዙ ንስሐ መግባት ብቻ ነው።እኛ በንስሐ ወደ ፈጣሪያችን ስንመለስ እርሱ ደግሞ በምሕረቱ ወደ እኛ ይመለሳል።

 1. ካለፈው ልምድ መቅሰም

አንዳንድ ጊዜ እንደግለሰብም እንደቤተ ክርስቲያንም አለያም እንደ ሀገርም መሥራት የሚገባንን ባለመሥራታችን: ኃላፊነታችንን በጊዜው ባለመወጣታችን: ስንፍናን በማብዛታችን: አሠራራችንን ለፈተና ተጋላጭ በማድረጋችን ከግለሰብ እስከ ቤተ ክርስቲያንና እስከ ሀገር ልንፈተን እንችላለን የሚለው ነው።አሁን ያገኘንን ፈተና በንስሐና በእንባ ብንመልሰውም መዘጋጀትና መሥራት በሚገባን ልክ ኾነን ካልተገኘን ድጋሚ በፈተና መያዛችን አይቀሬ ነው። ያ ደግሞ እጅግ አደገኛ ነገር ነው።

ስለዚህ ከእያንዳንዱ ፈተናችን ትምህርት ልንወስድና በርትተን ልንሠራ ይጠበቅብናል።በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውና የበርካታ ምእመናንን ሕይወት የቀጠፈው ፈተና ለቤተ ክርስቲያናችን አዲሷ ባይሆንም ካለፉት ፈተናዎቻችን ተምረን መሥራት ማደራጀት ማሠልጠን ማንቃት መጠበቅ በሚገባን ልክ ሆነን ስላልተገኘን ነው። በመኾኑም ወጣቶች እንደሚያገሳ አንበሳ ሊውጠን በሚያደባብን ፈተና ሳይረበሹ እያንዳንዷን ፈተና ለመልካም አጋጣሚና ዕድል በመቀየር ራሳችንና ቤተ ክርስቲያናችንን ለሚመጣው ትውልድ ማሸጋገር ይጠበቅብናል።ለዚኽ ደግሞ የአምላካችን ቸርነት የድንግል ማርያም ተራዳኢነት  አይለየን።

ፈተና

 መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ (አውስትራልያ)

                    ክፍል  አንድ

ፈተና በሕይወት ዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን እምነት ሥርዓት ቀኖናና ትውፊት መሠረት በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ጥፋታችን ከተለያዩ አካላት የሚገጥመን መሰናክል እንቅፋት መከራ ስደት ወይም በሂደት ሊጎዳንና ሊያሰናክለን የሚችል አሁን ግን መልካም መስሎ የሚታየን ነገር ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት ፈተና ከሦስት ታላላቅ ምንጮች ሊመጣብን ይችላል።

 1. ከራሳችን

በተለያዩ የስሜት ሕዋሳቶቻችን በኩል ወደ ልባችን የሚገቡና እንደ እግዚአብሔር  ፈቃድ ያልኾኑ ወይም በቅዱሳት መጻሕፍት ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ የተለዩ አሳቦች በሂደት ወደ ምኞት ያድጋሉ። በምኞት የሚጀምረው ፈተና በተግባር ሲፈጸም ደግሞ ኃጢአት ይሆናል። ይኽንን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ”ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ብሏል  (ያዕ. ፩:፲፫-፲፭)

ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌው ” የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፥ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል” ብሎ በስንፍና የምንያዝበት የአሳብና የምኞት መንገዳችን በሂደት የሚያስከትለውን መዘዝ አስረድቷል። (ምሳ. ፲፱፥፫) ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ የስሜት ሕዋሳቶቻችን ፈተና የሚያመጡብን መኾናቸውን ““ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” ብሏል (ማቴ.፲፥፴፮ )

በዚህ መሠረት በአንደበታቸው የማይገባ ነገር ተናግረው: በዐይናቸው መጥፎ ነገር አይተው: በጆሯቸው ክፉ ምክርና ወሬ ሰምተው: በሐፀ ዝሙት ተነድፈው በእጃቸው ወንጀል ሠርተው በእግራቸውም የኃጢአት ወጥመድ ወደ ተጠመደበት ተራምደው ሄደው በነፍስ በሥጋ ታላቅ ጉዳት ላደረሰባቸው ፈተና የተዳረጉ ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው።

 1. በዙርያችን ካለው ማኅበረሰብ

ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ቅድስት ኦሪት “ለሰው ብቻውን መኖር አይገባም” እንዳለችው በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የምንኖረው ከሌሎች ጋር ነው። በምንኖርበት በምንሠራበት በምንጓዝበት በመሳሰሉት ኹሉ በእምነት በባህል በአመለካከት በዕድሜ በጾታና በመሳሰሉት ሁሉ ከተለያዩ ሕዝብ ጋር እንገናኛለን። በዚህ አብሮነት ደግሞ የእውቀት የልምድ የአመለካከት ልውውጥ ይከሰታል። ደካማው በብርቱዎቹ ተጽዕኖ ይደረግበታል። በደካማነቱ እምነታቸውን ባህላቸውን ክህደታቸውን ሥጋዊ ፈቃዳቸውን ይጭኑበታል። በዚህም ጌታችን በእሾህ መካከል የወደቀ ዘር ብሎ እንዳስተማረው መልካም ክርስትናውን ከግራ ከቀኝ ያስጨንቁበትና ያለ ፍሬ እንዲቀር ያደርጉታል።

የሔዋን ምክንያተ ስሕተት መኾን: ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይኾናል። ቅዱስ ጳውሎስም “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ያለው ፈተና በዙርያችን ካሉና ከፈቃደ እግዚአብሔር ካፈነገጡ ሰዎች ስለሚመጣ ነው። (፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፴፫) ስለኾነም ነው ክቡር ዳዊት  “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” በማለት  ያስረዳው።(መዝ.፩፥፩ )

በክፉዎች ምክር የሚሄድ በኃጢአተኞች መንገድ (አሳብ ምክር) የሚሄድ በዋዘኞች ወንበር የሚቀመጥ (ድርጊት የሚተባበር) ለፈተና የተዳረገ ይኾናል። ይኸው ክቡር ዳዊት በሌላኛው መዝሙሩ ይኽንን አሳቡን ሰፋ አድርጎ “ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ” በማለት በዙርያችን ካሉት ሰዎች የተነሣ የሚገኘውን በረከትና የሚመጣብንን ፈተና አስረድቷል። (መዝ.፲፯:፳፭)

 1. ከሰይጣን

ሰይጣን ሥራው መፈታተን: ማዘግየት: ማሰናከልና መክሰስ ነው። ይኽ የማያቋርጥና ተስፋ የማይቆርጥ ባላጋራ ምእመናን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲክዱ አንድነታቸውን እንዲያፈርሱ ምግባር ትሩፋታቸውን እንዲተዉ ንጽህናቸውን እንዲያረክሱ በክፉ ድርጊት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቆጡ ተስፋ እንዲቆርጡ ይፈታተናቸዋል። ምክንያቱም እርሱ ፈታኝና መፈታተንም ሥራው ስለኾነ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ የዚኽን ጨካኝ ባላጋራ መፈታተንን “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” እያለ አስተምሮናል።

ፈታኝ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን በክፉ ምክሩ ከገነት አስወጥቷል። ቃየል ወንድሙ አቤልን እንዲገድለው መግደልን አስተምሯል። በበለዓም አድሮ እስራኤል የሚጠፉበትን ለባላቅ አስመክሯል። በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ኢዮብን ከስሷል። በምናሴ አድሮ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስን በመጋዝ አሰንጥቋል።በሄሮድስ አድሮ 144,000 ሕፃናትን አስፈጅቷል። ሕፃኑ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር እንዲሰደዱ አድርጓል። ጌታችንን በገዳመ ቆሮንቶስ ፈትኗል። ትንሣኤውን በአይሁድ አድሮ አስክዷል። ሐዋርያትን አሳድዷል። አስገድሏል። ሰማዕታትን በአላውያን ነገሥታት አድሮ አስጨፍጭፏል። ቤተ ክርስቲያንን አሳድዷል። አሁን እያሳደዳት ይገኛል። ብዙዎችን በፈተናውና በመከራው ጽናትና ብዛት ተስፋ አስቆርጧል።

ሰይጣን ፈተናውን የሚያመጣው አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሰይጣንነቱን ገልጦ ጨለማ ፊቱን አሳይቶ ሳይሆን እጅግ በተለያዩና በረቀቁ ስልቶች ነው። በክፋት ብቻ ሳይሆን በፍቅር እየተመሰለ: ሃይማኖተኛና ለእምነት ተቆርቋሪ እያስመሰለ: በድካማችን ረዳት በረሃባችን ምግብ በብቸኝነታችን ወዳጅ በጭንቀታችን አረጋጊ በድህነታችን ብልጥግና ሆኖና መስሎ ነው የሚቀርበን። ይኽንንም ወደ ጌታችን ቀርቦ መራቡንም አይቶ “ይኽን ድንጋይ ዳቦ አድርገህ ብላ” ካለው መረዳት ይቻላል። (ማቴ.፬፥፬)

በክርስትና ስንኖር ወደድንም ጠላንም ፈተና ከሦስቱ መንገዶች ቢያንስ በአንዱ ወደ እኛ መምጣቱ አይቀርም። እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ክርስቲያን ኾኖ ያለ ፈተና መኖር ጨርሶ አይቻልም። ከሰው ርቀው በበረሓ ቢኖሩ: ከኃጢአት ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ቢያደርጉ: በዚኽ ዓለም ሀብትና ክብር ቢከበቡ: የመጨረሻውን የሥልጣን ቁንጮ ቢጨብጡ ያለ ፈተና መኖር አይቻልም።አለመቻሉንም ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው አስረድተዋል። ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ “ወዮ ለዓለም፤ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና” ብሏል። ማቴዎስ 18፥7። በሌላኛው ወንጌሉም ““በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ አስረድቶናል።( ዮሐ.፲፮፥፴፫)

በክርስቶስ ለሐዋርያነት የተጠራና ከእርሱም የተማረው ቅዱስ ጴጥሮስ መከራና ፈተና የማይቀሩ በመኾናቸው “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።

ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር” በማለት በስፋት የመከረን (፩ኛ ጴጥ.፬:፲፪-፲፮) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ፈተናና መከራ አንዱ የተጠራንለት መኾኑን “በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና” በማለት አስተምሮናል (ፊል.፩:፳፥-፴ )

ይኽንን እውነታ ያልተረዱ አንዳንድ ምእመናን ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ በራሳቸው: በቤተሰባቸው: በቤተ ክርስቲያን: በማኅበረ ምእመናን ላይ ፈተና መከራና ስደት ሲመጣ ይረበሻሉ። እግዚአብሔርን ለምን ብለው ይሞግታሉ። እምነታቸው ስሕተት ያለበት መስሎ ይታያቸዋል። በስም ክርስቲያን የተባሉና በዙርያቸው የሚኖሩ በዓለሙ ደልቷቸው የሚኖሩ “ክርስቲያን” የሚባሉ ሰዎች ያላቸውን ሰላም: የሚያገኙት በረከትና ስኬት እያዩ ክርስትናቸውን በምድራዊ በረከት መመዘን ይጀምራሉ።  በተለይ ደግሞ በዘመናችን እያየነው እንዳለነው የፈተናው ምንጭ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች መኾናቸውን ሲያዩ እጅጉን በእምነታቸው የሚናወጹ አሉ። ይኽ ግን ክርስትናው ከዘመናችን ለመድረስ ያለፈበትን እጅግ ውጣ ውረድ የበዛበትን ጉዞ ካለመረዳት የሚመጣ ነው።የመጀመርያው የክርስትና ፈተና የመነጨው ከጌታችን እግር ተቀምጦ ይማር የአንደበቱን ቃል ይሰማ የእጁንም ተአምራት ያይ ከነበረው ከይሁዳ ነው።

ይቀጥላል !