የቅዱስ ቶማስ ዘመርአስ ሐዋርያዊ አገልግሎቱና ዕረፍቱ
ከመ/ር ጌራ ሞገስ
ቅዱስ ተማስ ዘመርዓስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ በመጻሕፈ ስንክሳር ነሐሴ ፳፬ ቀን ከምትዘክራቸው ሐዋርያውያን አባቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (የመርዓስ ኤጲስቆጶስ) ታሪክ እጅግ አስደናቂና ለቤተክርስቲያን መሪዎች አርአያነት ያለው ነው።
1. ትውልዱና ትምህርቱ
በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” (ኤር.፩፥፭) የሚለው የነቢዩ ቃል የተፈጸመለት ታላቅና ቅዱስ ሐዋርያዊ አባት ለአገልግሎት የተፈጠረ ዕንቍ የቤተ ክርስቲያን አባት ነው።
ትውልድና ጥሪ
ምንም እንኳን በመጽሐፈ ስንክሳር ላይ የወላጆቹ ስም ባይጠቀስም ቅዱስ ቶማስ የተወለደውና ያደገው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ውስጥ ሲሆን፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህች ዓለም ብርሃን እንዲሆን የመረጠው የከበረ ዕቃ ነው (ንዋይ ኅሩይ)፣ በመጽሐፈ ስንክሳር እንደሰፈረው እርሱ አስቀድሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቀንና ሌሊት ተጠምዶ የሚኖር፣ ሕጉንና ሥርዓቱን የሚጠብቅ ቅዱስ አባት ነበር። (መጽሐፈ ስንክሳር ነሐሴ ፳፬)
መንፈሳዊ ማዕረግ
በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ብቁ ሆኖ በመገኘቱ “መርዓስ” ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ (ሊቀ ጳጳሳት/እረኛ) ሆኖ ተሾመ፤ የማዕረጉም ስም ከዚህ በመነሳት “ቶማስ ዘመርዓስ” ተብሎ ይጠራል።
2. ሐዋርያዊ አገልግሎቱና ወንጌልን ስለመስበኩ
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ሐዋ. ፳፥፳፰)
ይህንን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ኀላፊነቱን በትጋት የተወጣ ታላቅ አባት ነው።
እረኛዊ ኃላፊነት
ኤጲስቆጶስ ሆኖ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ የመንጋውን (የሕዝቡን) ነፍስ ለመጠበቅ እንደ እውነተኛ እረኛነቱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ሕዝቡን በቅን ሃይማኖትና በትምህርተ ወንጌል አጸና። በዚህም ሐዋርያትን ምሳሌ በማድረግ ወንጌልን ከዳር እስከ ዳር በመስበክ፣ ሕዝቡን ከጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ለመመለስ ታላቅ ትጋት አሳይቷል።
3. ዕቅበተ እምነት (Apologetic) እና ተጋድሎ ከአላዊው ንጉሥ (ዲዮቅልጥያኖስ) ጋር
የመከራው ዘመን
በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተዘገበው(ነሐሴ ፳፬) በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ክርስቲያኖች እጅግ የጸኑበትና መከራን የተቀበሉበት በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ (ዓላዊውና ሰይጣናዊው ንጉሥ) ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስደት ታወጀ። ዲዮቅልጥያኖስና መኳንንቱ ክርስቶስን እንዲክዱና ለጣዖት እንዲሰግዱ አስገደዱ። ይህ ቅዱስ ግን እንዲህ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል በማሰብ ለመከራው አልተንበረከከም።
“ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ።” (1ኛ ጢሞ ፮፥፲፫-፲፬)
መከራውን እና ስቃዩንም በዚህ መልኩ ተሻግሮታል፦
ጽኑ ዕቅበተ እምነት
ቅዱስ ቶማስ ጭፍሮች ጎትተውና ደሙን አፍስሰው ወደ መኰንኑ ፊት (“ለአማልክት ስገድ” በሚል) ባቀረቡት ጊዜ በሃይማኖቱ ጸንቶ፦
“እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነው!” በማለት ፊት ለፊት በመግለጽ የሐዋርያዊ ዕቅበተ እምነት ምሳሌ ሆኗል። (መጽሐፈ ስንክሳር ዘነሐሴ ፳፬)
ከባድ ስቃይና የ፳፪ ዓመታት እስር
መኰንኑም ይህ ቅዱሱ በእግዚአብሔር ጸንቶ ሃይማኖቱን በመጠበቁ ተቆጥቶ ከባድ ሥቃይ አደረሰበት። ይሁን እንጂ ቅዱሱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጸንቶ ስሕተታቸውን ይዘልፍና ይከራከርባቸው ነበር። በዚህም የተነሣ በጨለማ ቤት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ተጥሎ ኖረ። ከሀድያንም በየዓመቱ እየገቡ ህዋሳቱን (አፍንጫውን፣ ከንፈሮቹን፣ ጆሮዎቹን፣ እጆቹንና እግሮቹን) እየቆረጡ አካሉን አጎሳቆሉት፤ እርሱ ግን በሆነው ሁሉ እግዚአብሔርን “ተመስገን” በማለት በጽናት ኖረ። (ዝኒ ከማሁ)
በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ። (ሉቃ. ፳፩፥፲፱)
4. ከቤተ ክርስቲያን ታሪክና ከኒቅያ ጉባኤ ጋር ያለው ቁርኝት
የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መነሣትና መፈታት
በእግዚአብሔር ፈቃድ ክርስቶስን የሚያከብረው ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በነገሠ ጊዜ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉ ክርስቲያን እስረኞች እንዲፈቱ አዘዘ። በአንዲት ክርስቲያናዊት ሴት አማካኝነት መረጃው ደርሶ ካህናቱ ወስደው ከአስከፊው እስር ቤት አወጡት።
የኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭ ዓ.ም.)
ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የብፁዓን አባቶችን የ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ጉባኤ በኒቅያ ሃገር ባሰባሰበ ጊዜ፣ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ከጉባኤ አባላት አንዱ ነበር። ንጉሡ ወደ እርሱ ቀርቦ የተቆረጡ ሕዋሳቱን እየተሳለመ፣ በዕድሜና በገድል ላበረከተው አስተዋጽኦ ክብር ሰጥቶለታል። በጉባኤውም አርዮስን ከነተከታዮቹ አውግዘው በመለየት “ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የተካከለ ነው” በማለት ጽንዕት ሃይማኖትን አጽንተዋል።
5. ዕረፍቱ
ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ (ወደ መርዓስ) ተመልሶ ሕዝቡን አጠናክሮ፣ ሃይማኖትን አስተምሮ፣ መልካሙን ገድል ፈጽሞ ነሐሴ ፳፬ ቀን በሰላም አርፏል። ቤተ ክርስቲያናችንም የዚህን ታላቅ ሐዋርያና ሰማዕት መታሰቢያ በየዓመቱ ነሐሴ ፳፬ ቀን በደማቅ ሁኔታ ታከብረዋለች።
“መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፯-፰) የሚለውን የሐዋርያው ቃል በተግባር ፈጽሟል።
እንዳጠቃላይ ቅዱስ ቶማስ ዘመርአስ የደረሰበት መከራ የተጋደለውን የወንጌል ተጋድሎ መቼም ዘርዝረን አንፈጽመውም፤ ትልቁ ነገር “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ቃል የነገሯችሁን ዋኖቻችሁ አስቡ” ብሎ ቅዱስ ጳወሎስ እንደመከረን (ዕብ. ፲፫፥፯) የደረሰበትን መከራ በቃል ብቻ ሳይሆን በሕይወት የነገረንን የወንጌል እውነታ ተመልክተን በክርስትናችን መጠንከር የገባናል፤ የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ጸሎትና በረከት ከእኛ ጋር ይሁን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድነግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!