ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ሕይወቷ እና ተጋድሏ
በዲ/ን ኃይለማርያም ታደሰ
1. አስተዳደግና ስሟ፡ “በክርስቶስ የተመረጠች”
ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የተወለደችው ቡልጋ (በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር) ልዩ ስሙ ጌየ በሚባል ሥፍራ ነው። ወላጆቿ እጅግ ባለጸጋና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጎች ነበሩ። ከአባቷ ከቅዱስ ደርሳኒ እና ከእናቷ ከቅድስት ዕሌኒ በግንቦት ዐሥራ ሁለት ቀን ተወለደች።
ወላጆቿ እርሷን ከወለዱ በኋላ በደም ግባቷና በጸባይዋ እየተደሰቱ የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አያስተማሩ ስላሳደጓት ከልጅነቷ ጀምራ በሥነ ምግባር፣ በሃይማኖት የታነጸች ሆነች። በደም ግባቷም እጅግ ውብና ያማረች ነበረች። ወላጆች ልጆችን በመልካም አስተዳደግ ማሳደግ እንደሚገባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው። “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” (ምሳሌ ፳፪፥፮) የሚለውን ቃል ፍጹም ማሳያ ነው።
“ክርስቶስ ሠምራ” ማለት “ክርስቶስ መረጣት” ማለት ነው። ስሟ ደግሞ ከእናታቸው ማሕፀን ጀምሮ ስለተመረጡ ቅዱሳን ይናገራል። “ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።” (ኤፌ. ፩፥፬)።
2. የትዳር ሕይወት እና ሕይወትዋን የቀየረው ክስተት
ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ በወቅቱ የንጉሥ ባለሟል ለነበረው ሠምረ ጊዮርጊስ ለተባለ ክቡርና ደግ ሰው በግድ አጋቧት። በትዳር ሕይወቷ ውስጥ ፲፪ ልጆችን (ወንዶችና ሴቶችን) አፍርታለች።
እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት የነበረች ኢትዮጲያዊት ጻድቅ ስለነበረች ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ገብረ መስቀል በትዳሯ፣ በሥነ ምግባሯና በሃይማኖቷ በሁለመናዋ የተመሰገነች መሆንዋን ሲሰማ “በጸሎትሽ አስቢኝ” በማለት ከአገልጋዮቹ ውስጥ እሷን እንዲያገለግላት አንዲሁም ለነገሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማም ላከላት።
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “እነሆ ይህንን ኅብስት ተመገቢ እግዚአብሔር በቸርነቱ ብዛት ሰጥቶሻል” አላት ። እርስዋም ፈጣሪዋን አመስግና ኅብስቱን ከመልአኩ እጅ ተቀብላ ተመገበች፤ መዓዛ ጣዕሙም ሰውነቷን አለመለመው። ከዚህም የተነሣ ሦስት ቀን እህል ሳትበላ ውኃ ሳትጠጣ ቆየች፤ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ አድሮባታልና።
ያልተጠበቀው ክስተት፡ በአንድ ወቅት በቤቷ ውስጥ ከነበሩት ከአገልጋዮቿ አንዷ ምግባሯ የከፋ ነበርና በጣም ስላበሳጨቻት በቁጣ በፈጸመችው ድርጊት አገልጋይቱ ሕይወቷ ያልፋል። ክርስቶስ ሠምራ በታላቅ ድንጋጤና ንስሓ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፤ ጸሎቷም ተሰምቶ አገልጋይቱ ከሞት ተነሣች። ይህ ታሪክ ሙሴ ግብፃዊውን ከገደለ በኋላ ንስሓ ገብቶ ወደ ምድረ በዳ የኮበለለበት ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዘጸአት ፪፥፲፩) በጸሎቷ ከሞት ማስነሣቷ በብሉይ ኪዳን ኤልያን የሱነማዊቷን ልጅ በጸሎት ያስነሣበት (፪ኛ ነገ. ፬፥፴፪-፴፮) እንዲሁም በሐዲስ ኪዳን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታን ከሞት ማስነሣቱን (ሐዋ. ፱፥፵) ያስታውሰናል። የታላቁ ሊቅ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት እንደሚለው፡ “ኃጢአት መሥራት የሰው ነው፤ መጸጸትና ንስሓ መግባት ግን የመለኮት መንገድ ነው።”
3. የምነና ሕይወት፡ ሁሉን ትቶ መውጣት
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር ጸሎቷን ሰምቶ አገልጋይዋን ከሞት አስነሣላት፤ እናታችን “ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከእኔ ከባርያው ያላራቀ አምላክ ይክበር ይመስገን” ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔርን ካመሰገነች በኋል አስቀድማ አገልጋይዋን ከሞት ቢያስነሣላት ያላትን ገንዘብና ሀብት ትታ ባላት ዘመኗ ሁሉ አገልጋዩ እንደምትሆን ብጽዓት (ስእለት) አድርጋ እንደምትሰጥ ቃል ገብታ ነበርና የገባችውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኩስናዋን አዘጋጀች።
“ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን።” (መዝ. ፷፮፥፳) ይህ ተአምር የዓለምን ከንቱነት እንድትረዳ ስላደረጋት፣ ሀብቷንና ልጆቿን በሙሉ ትታ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሄድ አስቀድማ ያዘጋጀችውን የምንኩስናን ልብስ ለብሳ ከሴቶች ገዳም ገባች። በኋላም በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ወደ ጣና ሐይቅ (ጉንጉት ደሴት) አቀናች።
“ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ. ፲፥፴፯-፴፰) ክርስቶስ ሠምራ ይህንን ፈታኝ የወንጌል ቃል በተግባር የኖረች እናት ናት።
4. አስገራሚው ተጋድሎ፡ በባሕር እና በጉድጓድ
የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ተጋድሎ ሰብአዊ አቅምን የሚፈታተንና የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ ፍጹም ያስገዛ ነበር። ይኸውም፡-
፲፪ ዓመት በባሕር ውስጥ መጸለይ፡– በጣና ሐይቅ ውስጥ እስከ አንገቷ በሚደርስ ውኃ ውስጥ ገብታ ሌሊትና ቀን ትጸልይ ነበር። ሰውነቷ ተበሳስቶ የባሕር ዓሳ መመላለሻ እስከሚሆን ድረስ እንደ ተተከለ ዓምድ ሆና ሳትወጣ ዐሥራ ሁለት ዓመት ቆማ ስትጸልይ ኖረች። ከዐስራ ሁለት ዓመት በኋላ ጌታችን ተገልጦላት ቃል ኪዳን ሰጥቷታል። ከዚህ በኋላ ሕይወቷን በሙሉ በታላቅ ተጋድሎ ስታሳልፍ ጌታችንም ከቅድስት እናቱ ጋር ሆኖ በየጊዜው ይጎበኛት ነበር። “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ” (ሮሜ. ፲፪፥፩) የሚለውን ወንጌል በተግባራዊ ሕይወት አሳይታለች።
ማዕቀበ እግዚእን ማማለድ፦ መልአከ ጽልመት “ፈጣሪህን ክደህ ይህንን ዕፅ በሰውነትህ ብትቀብር ሞትና እርጅና አያገኝህም” አለው። እርሱም ፈቃደኝነቱን ቢገልጥለት መልአከ ጽልመት በሰውነቱ ዕፅ ቀብሮለት ሄደ። ከእለታት አንድ ቀን ማዕቀበ እግዚእ ወደ ክርስቶስ ሠምራ ሂዶ “አማልጅኝ አላት” እርሷም ጌታችንን ማርልኝ አለችው። ይህም ሙሴ ለሕዝበ እስራኤል እንዳማለደ ያለ ነው። “አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ።” (ዘጸ. ፴፪፥፴፪) በዚያ መሠረት ምሕረትን አሰጠችው።
፲፪ ዓመት በጉድጓድ ውስጥ፡ ከባሕር ከወጣች በኋላም፣ መሬት አስቆፍራ ሹል ብረቶችና ችንካሮች ላይ በመቆም ሥጋዋን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አደረገች። ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፳፯) እንዳለው ሥጋዋን ለነፍሷ አስገዝታለች።
የጠላቶች ፍቅር፡ ጸሎቷ ስለ መላው ዓለም ድኅነት ነበር። “ዲያብሎስን እንኳ ማርልኝ” ብላ እስከ መጸለይ የደረሰ በክርስቶስ መስቀል ላይ የታየውን ፍጹም የፍቅር ጥግ ያሳየች እናት ናት።
5. የዕረፍት ቀንና ታላቁ ቃል ኪዳን
ይህን ታላቅ ተጋድሎ ከፈጸመች በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ታላቅ ቃል ኪዳን ሰጣት። “ስምሽን የጠራውን፣ ዝክርሽን ያዘከረውን፣ በቃል ኪዳንሽ የታመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ” አላት። “እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፦ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” (ኢሳ. ፶፮፥፭-፮) ነፍሷ በክብር ያረፈችው ነሐሴ ፳፬ ቀን ነው። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ለቅዱሳን የተሰጠ መለኮታዊ ስጦታ ነው። “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” (መዝ. ፻፲፮፥፲፭)
“ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል” (ማቴ.፲፥፵፩)
6. ተማሪዎችና ወጣቶች ከእርሷ ምን እንማራለን?
የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የሕይወት ታሪክ ለመንፈሳዊ ሰው ብቻ ሳይሆን በትምህርት ዓለም ውስጥ ላለ ማንኛውም ተማሪ ትልቅ የሥነ ልቦና እና የሞራል ሥንቅ ይሰጣል።
ሀ. ቆራጥነት (Determination)
እርሷ የኋላውን የዓለም ክብር ትታ ወደ ፊት እንደገሰገሰች ሁሉ፣ ተማሪዎችም በትምህርታቸው ስኬታማ ለመሆን ቆራጥ መሆን አለባቸው። “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ… ወደ ምልክቱ እገሰግሳለሁ” (ፊልጵስዩስ ፫፥፲፫-፲፬) ያለፉ ውድቀቶችን፣ ስንፍናና ጊዜ የሚያጠፉ ምድራዊ ነገሮችን (ሶሻል ሚዲያ፣ ሱስና አጓጕል ዘመናዊነትን) ትቶ ለዕውቀት መቁረጥን ያስተምረናል።
ለ. ጽናት (Perseverance)
በባሕር ውስጥና በችንካር ላይ በነበረችበት ጊዜ የገጠማትን አስፈሪ የሥጋ ስቃይና የዲያብሎስን ፈተና በጽናት አልፋዋለች። “በፈተና የሚጸና ሰው ብፁዕ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና” (ያዕቆብ ፩፥፲፪) “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” (ማቴ. ፳፬፥፲፫) በትምህርት ጉዞ ላይ ድካም፣ አስቸጋሪ ፈተናዎችና ተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች ሊመጡ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በዓላማ ጸንቶ መቆም ወደ ስኬት ማማ ያደርሳል።
እንዳጠቃላይ የክርስትን ሕይወት ጽናት፣ ትዕግስት፣ ተስፋ አለመቁረጥ የሚጠይቅ ፈተናዎቹም ከአንድ በኵል ሳይሆን ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣ ነው። የተለያየ ፈተና አምጥቶ ዓለም እንደሚፈትነን አምላካችን “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” ብሎ ሲያስጠነቅቀን “ነገር ግን አይዟችሁ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ. ፲፮፥፴፫) በማለት ዓለምን ማሸነፍ እንደምንችል አረጋግጦልናል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!