ለግቢ ጉባኤያት ተተኪ መምህራን እና አመራሮች ሥልጠና ተሰጠ
በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ከማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ጋር በመተባበር ከሐምሌ ፩ – ፴ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ድረስ ለተተኪ መምህራን የደረጃ ሁለት እና ለአመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መሰጠቱን በማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል አስታወቀ፡፡
ሥልጠናው በሀገር ውስጥ በሚገኙ ስድስት ማስተባበሪያዎች በ፲ ሥልጠና ማእከላት የተሰጠ ሲሆን ፫፻፸፩ የደረጃ ሁለት ተተኪ መምህራንና ፫፻፴፬ አመራሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን በደረጃ ሁለት የመምህራን ሥልጠና ከወሰዱት መካከል ፷፩ መምህራን በአፋን ኦሮሞ የሠለጠኑ መሆናቸውን ዋና ክፍሉ ገልጿል፡፡
ተተኪ መምህራኑ ዐሥራ አንድ የትምህርት ዓይነቶችን ማለትም ትምህርተ ሃይማኖት፣ ነገረ ማርያም፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ሥነ ምግባር፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ እና የስብከት ዘዴ፣ ትምህርተ አበው፣ ኦርቶዶክሳዊ የጾታ ትምህርት እና የማማከር አገልግሎት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ነባራዊ ሁኔታዎች እና የሰባክያነ ወንጌል ድርሻ በሚሉ ትምህርቶች ለአንድ ወር ሲሠለጥኑ ቆይተው ተመርቀዋል፡፡
የግቢ ጉባኤያት አመራሮች ሥልጠናም ለአንድ ሳምንት የተሰጠ ሲሆን የመሪነት ክህሎት፣ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትና ክህሎቱ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአመራርነት ሚና ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ፣ ግቢ ጉባኤያትና መገለጫ ጠባዮቻቸው፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና አገልግሎቱ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ሥልጠናው እንደተሰጣቸው በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ማደራጃና የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፡፡
ለተተኪ መምህራኑና ለአመራሮቹ ከተሰጡት ሥልጠናዎች በተጨማሪ ሠልጣኞቹ ለሚያነሷቸው ጥያቆዎች ምላሽ፣ የምክክር እና የውይይት መርሐ ግብሮች ተካሂደዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ በሚገኙ ፬፻፴፩ እና በውጭ ሀገራት በ፳፫ ግቢ ጉባኤያት፣ በአጠቃላይ በ፬፻፶፬ ግቢ ጉባኤያት መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!