ደም መለገስ ይቻላል?
የክርስትና ሕይወት መሠረቱ ፍቅር ነው፡፡ የክርስቲያኖች የእምነታቸውን መሠረት የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ በመስጠት ፍቅሩን ገልጦልናል፡፡ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት፤ ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም“ (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) በማለት የፍቅርን ተእዛዛት ሰጥቶናል፡፡
ፍቅር የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ “በወንድማማቾች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ የምትፈራሩም ሁኑ፣ እርስ በርሳችሁ ተከባባሩ“ እንዲል(ሮሜ. ፲፪፥፲)፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያት በሥራና በቃል ፍቅርን የሰበኩት፤ ስለ ፍቅር እስከ ሞት የደረሱት፡፡
በመሆኑም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሁሉ የፍቅርን ሕግ ልንፈጽም ፍቅራችንን ለሌሎች ልንሰጥ ይገባል፡፡ “…የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመርምር እላለሁ፡፡ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሃ ሆነ” (፪ቆሮ ፰–፱) ተብሏል፡፡
በዚህ መሠረት ክርስቲያኖች ሀብታም፣ ደሀ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ወገን፣ ጠላት ሳይሉ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍጹም የሆነ ፍቅራቸው ሊያሳዩ ይገባል፡፡ ይህም ፍቅር ተእዛዘ እግዚአብሔርን ሚዛኑ አድርጎ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ ልዩነት የሚፈጸም ነው፡፡ ሰዎች ደም የሚለግሱትም ይህን መሠረት በማድረግ ለወገኖቻቸው ያላቸውን ፍቅር በዚሁ ይገልጡታልና ፡፡
ክርስቲያኖች ከፍቅር የተነሣ እንኳን ደማችንን ሕይወታችንንም ልንሰጥ ይገባል፡፡ እንዲያውም ደም መስጠት በሕይወት እያለን ካለን እንደማካፈል ስለሆነም ታላቅ የክርስቲያንነት መገለጫ ነው፡፡ በእኛ መሥዋዕትነት የሌሎች ሕይወት የሚተርፍ ከሆነ ሕይወታችንንም እስከ መስጠት ልንደርስ ያስፈልጋልና፡፡
በእኛ መሥዋዕትነት የአንድ ሰው ሕይወት ከሞት ተርፎ ለንስሓ እንዲበቃ ማድረግ ለሰማያዊ ክብር የሚያበቃ ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ደም መለገስ የክርስትና ትምህርት ውጤትም ነው፡፡
ደማችንን የምንለግሰውም ለምናውቃቸው ሰዎች ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለእኛ እግዚአብሔር ጤናውን ከሰጠን እግዚአብሔር የሰጠንን ያለ ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ልናደርግ ይገባናልና፡፡ ይህ ሲባል ግን ደም የምንለግስበት ዓላማ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓላማው በፍቅር የሰውን ልጅ ሕይወት ማዳን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከዚያ ውጪ መሸጥ መለወጥ አይገባም፡፡ በተረፈ እኛም በታመምንና በተቸገርን ሰዓት ደም ተቀባዮች እስከ መሆን እንደምንደርስ መዘንጋት የለብንም፡፡ ይሁን እንጂ ከሰው ብድርን አገኛለሁ ብለን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋን ለማግኘት ደማችንን ብንሰጥ ለጋሶች ያሰኘናል፡፡ ከሥርዓተ ቤተ ክስቲያን አንጻርም ትርፍ ለማግኘት፣ ለዝና፣ … ወዘተ እስከ አላደረግነውና በፍቅርና በቸርነት ከፈጸምነው የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም፡፡
ምንጭ ፦ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ፳፻፬ ዓም፤ ቁጥር ፩.፪.እና ፫ ገጽ-፩፻፷፱
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!