ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት
በአዱኛ ጌታቸው
ክፍል ሁለት
የዘረኝነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?
አንዳንድ የዓለማችን ሀገራት እየተባባሰ የመጣውን የዘር ጥላቻ ለማስወገድ በሕግ አስደግፈው ቢሠሩም ዘርን ወይም ማንነትን መሠረት ያደረ ጥላቻንና መድሎን ማስቀረት አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ ሠለጠኑ በሚባሉት አገራት ሳይቀር የዘረኝነትን ጠባይ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልቻሉም፡፡ የዘረኝነት እሳቤ በአገራችን መቼ እንደገባ በትክክል ባይታወቅም በሰነድ የተደገፈ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ፲፱፻፷ዎቹ ጀምሮ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ሕዝቦች ባለቤት በመሆኗ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ማንነትን የፖለቲካ ማእከላቸው በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ማንነትን መሠረት ያደረገ አለመግባባት ወይም ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡
በሀገራችን በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ግጭት አሁን ባለበት ደረጃ ባይሆንም በታሪክ አጋጣሚ በተለያየ ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት መዋቅር የተደገፈና በማንነት ላይ የተመሠረተ መገፋፋት እየተባባሰ የመጣው ከዐለፉት ሠላሳና ዐርባ ዐመታት ወዲህ ነው፡፡
ስለ ዘረኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው” በማለት ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ከሊቀ ነቢያት ሙሴ መጻሕፍት መካከል “አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት” የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ዘሩ አንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው፡፡ (ሐዋ. ፲፯፥፳፮፣ ዘፍ. ፫፥፳፣ ፩፥፳፰)
በመሆኑም አዳምና ሔዋን ለመላው የሰው ዘር አባትና እናት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የኖኅ ዘመን ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት የጥፋት ውሃ መጥቶ በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ባጠፋ ጊዜ ኖኅና ቤተሰቡ ከመጣው የጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የኖኅ ልጆች እንደሆንን መረዳት እንችላለን፡፡ (ዘፍ.፱፥፲፰)
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ በማለት ክርስቲያኖች ገንዘብ ሊያደርጉት የሚገባውን ማንነት አስተምሯቸዋል፡፡፣ ማቴ. ፳፫፥፰)
ከምንም በላይ ክርስቲያኖች ለአንድነት ይተጉ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ ሆኖ አስተምሮናል (ዮሐ. ፲፯፥፳)፡፡ አንድነትንና አብሮነትን አጥብቆ የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክት “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ሆናችሁ ኑሩ” በማለት ክርስቲያኖች ከመከፋፈልና ከመለያየት ሐሳብ እንዲርቁ አስተምሯል፡፡(፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲)
ይኸው ሐዋርያ በመልእክቱ “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳሁም ብልቶች ናችሁ” በማለት ክርስቲያኖች በክርስቶስ አንድ እንደሆንን ይመሰክራል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፲፪፤፳፯)፡፡ በአጠቃላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት የምንማረው መለያየትን ሳይሆን አንድነትን፣ ጠላትነትን ሳይሆን ወንድማማችነትን፣ ጥልን ሳይሆን ሰላምን፣ ራስ ወዳድነትን ሳይሆን መተሳሰብን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን ነው፡፡
ዘረኝነትና የክርስትና ሕይወት አብረው መሄድ ይችላሉን?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ አብረው አይሄዱም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው ስንፍና አምላክን እስከመካድ ያደርሳል(መዝ. ፲፫፥፩)፡፡ ዘረኝነት ስንፍና ነው፡፡ ዘረኝነት ሃይማኖትን እስከ መካድ ያደርሳል፡፡ ዘረኝነት ከግብረ ገብነት ያፈነገጠ ጠባይ ነው፡፡ ከግብረገብነት የወጣ ሰው ደግሞ ለምኞቱ ድንበር የለውም፡፡ በዘረኝት የተለከፈ ሰውም ለጥፋቱ ዳርቻ የለውም፡፡ ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ሲሆን ዘረኝነት ደግሞ ሰይጣንን ወይም ዲያብሎስን መምሰል ነው፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩)
ክርስትና አንድነትንና ፍቅርን ይሰብካል፤ ዘረኝነት ደግሞ መለያየትንና ጥላቻን ይደሰኩራል፤ ክርስትና ባልእንጀራን እንደ ራስ መውደድን ያስተምራል፤ ዘረኝነት ደግሞ ባልንጀራን መግደልን ማሳደድን ይሰብካል፡፡ ክርስትና “የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ፤ ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፡፡ እርስ በእርሳችሁም በአንድ ሐሳብ ተስማሙ በማለት ያስተምራል፡፡(ሮሜ. ፲፪፡፲፮) ዘረኝነት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ በቀልን ጠላትነትን ይሰብካል፡፡ ስለሆነም ዘረኝነትን ልንርቀው የሚገባ ክፉ ጠባይ ነው፡፡
ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!