“ጠፍተው የተገኙ”
በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
ስለ መጥፋት ስናነሣ በቅድሚያ አእምሮአችን ውስጥ የሚመጣው እና የመጥፋትን አስከፊነት የተማርንበት የሰው ልጅ ጥንተ ታሪክ ነው፡፡ በመላእክት ሥነ ተፈጥሮ ደግሞ ጠፍቶ መገኘትን፣ወድቆ መነሣትን፣ተሰብሮ መጠገንን ሳይሆን ጠፍቶና ተዋርዶ መቅረትን ያየንበት ዲያብሎስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን ጠፍቶ በመገኘት የመውጣት እና ተመልሶ የመግባት ዕድል ማግኘትን ያየንበት ታሪክ ነው፡፡ ይህም በሰው ልጅ ሕይወት የአባታችን አዳም እና እናታችን ሔዋን መጥፋት የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ መጥፋት ውስጥ የሚከሠተው የመጀመሪያው ወድቆ መሰበር ነው፡፡ እሱም ከብሮ መዋረድ፣አግኝቶ ማጣት፣ገብቶ መውጣት፣ነግሦ መሻር፣ሥቆ ማልቀስ፣ተደስቶ ማዘን፣ሕያው ሆኖ ተፈጥሮ መሞት ነው፡፡
አዳም እና ሔዋን ጠፍተው የተገኙ ናቸው፡፡ከጠፉበት ለመገኘት ደግሞ የፈላጊ መኖር የግድ ነው፡፡ ይህን ስንል ግን የጠፉት ለመገኘት ጠፊዎቹ ምንም ሚና የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጠፉት ለመገኘት መጥፋታቸውን ማመን፣መጸጸት፣ምሕረትን መሻት መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን የፈላጊያቸውን ድምጽ መለየት እና ወደሚፈልጋቸው ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የጠፋውን መፈለግ፣የወደቀውን ማንሣት፣ያዘነውን ማጽናናት፣የተሰበረውን መጠገን አምላካዊ ባሕርዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ”እግዚአብሔር ይጠብቀኛል የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ ነፍሴን መለሳት ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም‘ በማለት እግዚአብሔር ፍጥረቱን የማይንቅ እና የሚጠብቅ መሆኑን የመሰከረው (መዝ.፳፪፥፩) ፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአተኛው እንኳ ቢሆን ተመልሶ ንስሓ እንዲገባ እና እንዲምረው (ምሕረት ማድረግን) የሚወድ አምላክ ነው እንጂ ጠፍተን እንድንቀር የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በነቢየ እግዚአብሔር በሕዝቅኤል እንደተገለጸው ” አንተም የሰው ልጅ ሆይ የእስራኤልን ቤት እናንተ በደላችንና ኀጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው፡። እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ ? በላቸው‘ ይላል፡፡ (ሕዝ.፴፫፥፲)
እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ መሞት የማይሻ ደግ አባት ነው፡፡ስለዚህ ስንጠፋ ይፈልገናል፤ስናዝን ያጽናናናል፤ ስንወድቅ ያነሣናል፤ ስንርቀውም በፍቅር እየተከተለ ይጠራናል፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ዕፀ በለስን በልተው ከክብር በተዋረዱ ሰዓት የሠሩት ኃጢአት ስላስፈራቸው በበለሶች መካከል ተደበቁ፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር በፍቅር እየተከተለ አዳም አዳም እያለ መጣራት ጀመረ፡፡ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ይፈልገናል፡፡ ይህም ፍፁም ፍቅሩን የሚያሳይ ነው፡፡
ለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ”የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና‘ በማለት ራሱን የሰው ልጅ ሲል የገለጸው(ሉቃ.፲፱፥፲)፡፡
በዚህ ገጸ ንባብ ላይ ሰው የሆነበትንም ዓላማ ሲጠቅስ የጠፋውን ሰው መፈለግ እና ማዳን መሆኑን አስረድቶናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዲሁ ስለወደደው ከጠፋበት ይፈልገው እና ያድነው ዘንድ የባሕርይ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ላከው፡፡ ይህም በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ፣በእግዚአብሔር ወልድ ፈቃድ፣በእግዚአብሔር መንፍስ ቅዱስም ፈቃድ ምሥጢረ ሥጋዌ ተፈጽሞአል፡፡
በበደል ምክንያት ርስቱን ያጣውን እና ከፈጣሪው የተጣላውን የጠፋውን የሰውን ልጅ ፈልጎ ያገኘው እና ወደ ራሱ አቅርቦ ከራሱ ጋር በማስታረቅ ልጅነቱን አግኝቶ ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመለስ ዘንድ ቤዛነቱን የፈጸመለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ጠፍተው የተገኙትን ነገሮች በምሳሌ ያስረዳበት ትምህርቱ በግልጽ እንድንረዳው ያደርገናል፡፡ ጠፍቶ የነበረ ግን የተገኘ፣ወድቆ የነበረ ግን ታድሶ የተነሣ፣ በባርነት ተይዞ ተጎሳቁሎ የነበረ ግን ዳግም ልጅነትን አግኝቶ የከበረ መሆኑን ጠፍተው በተገኙ በተለያዩ ምሳሌዎች አስተምሮናል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠፍተው ስለ ተገኙት በምሳሌ እየተናገረ ያስተማረባቸው ምሳሌዎችም ከቤት ኮብልለው በውጪ ስለጠፉት፡- የጠፋው ልጅ ታሪክ( ሉቃ.፲፭፥፳፬) ፣ በቤት ውስጥ እያሉ ስለጠፉትም፡- በቤት ውስጥ ጠፍታ ስለተገኘችው ድሪም (ሉቃ.፲፭፥፰) ፣ ከበጎች መካከል ተለይታ ስለ ጠፋቸው እና ስለተገኘችው በግ (ሉቃ.፲፭፥፩) ሲሆኑ እነዚህ ሁሉ ጠፍተው የነበሩ ቢሆንም ተፈልገው መገኘታቸውን እና ፈላጊያቸው(ባለቤታቸው) በመገኘታቸው መደሰቱን በምሳሌ አስተምሯል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ በሚገባው መንገድ ወንጌልን በምሥጢር፣በቀጥታ እና በምሳሌ አስተምሯል፡፡ የሰውን በሕይወት መኖሩን እንጂ ሞቱን የማይሻ በመሆኑ ላሉት ጠባቂ፣ለጠፉት ደግሞ ፈላጊ እውነተኛ እረኛ ነው፡፡ለዚህም ነው ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳይለየን ስንለምን ከወደቅንበት ኃጢአት ደግሞ በምሕረቱ እንዲያነሣን ይቅርም እንዲለን የምንጠይቀው፡፡
በየትኛውም ስፋራ እና ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ጠባቂያችን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም ነው በወንጌል ”ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል‘ በማለት ያስተማረን(ዮሐ.፲፥፲፩)፡፡ ዓለም የእግዚአብሔርን ልጆች የምታስጨንቅበት የክፋት መረብ ስላላት በተለያየ መንገድ የጠፉ አሉ፡፡ የጠፉትን ሁሉ ደግሞ የሚፈልግ እርሱ ቸሩ ጠባቂያችን እግዚአብሔር ነውና የፍለጋ ድምጹን ሰምተው በኃጢአታቸው የተጸጸቱ እና ምህረቱን የሚሹ ሁሉ ያገኙታል፡፡
ጠፍተው የተገኙ የተባሉትም በተለያየ በደልና ኃጢአት ምክንያት ከቅድስና ሕይወት ወጥተው በእምነታቸው ተጠራጥረው በምግባራቸው ደክመው የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ልባቸው ተመልሰው በንስሓ ታድሰው ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ናቸው፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!