ሱባኤ
ቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የጽሞና ጊዜያት ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ ሱባኤ ነው፡፡ ሱባኤ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ይኸውም የሚፈጸመውን የጾም ወቅት በቀናት፣ በሳምንታት እና በወራት በመወሰን የአንድ ሱባኤ ልክ ሰባት ቀን ሆኖ የሚፈጸምበት ሥርዓት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ትውፊት መሠረት ሰባት ቁጥር የፍጹምነት መገለጫ ነው፡፡ በተለይም የኦሪትን ሕግ በሙሴ አማካኝነት በተቀበሉት በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡
በሥነ ፍጥረት ታሪክ ሰባቱ ሰማያት እንዳሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ፍጥረትን በየወገኑ በስድስት ቀን ፈጥሮ በመፈጸም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፤ ሰባተኛውንም ቀን ቀደሰው፡፡ ለዚህም ነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሲጽፍ፡- “ሰማይና ምድር ዓለማቸውም ሁሉ ተፈጸሙ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና” እንዲል (ዘፍ.፪፥፩)፡፡
እግዚአብሔር ሊፈጥረው ያሰበውን ሁሉ በስድስተኛው ቀን ፈጽሞ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ ማለቱ እግዚአብሔር ሲሠራ የሚደክመው ወይም ያሰበውን ለመሥራት ሲነሣ አቅም የሚያንሰው ሆኖ አይደለም፡፡ በሥራው ሁሉ ጉድለት እና እንከን የሌለበት ፍጹም ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ዓውደ ምንባብ እንደተመለከትነውም “እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም”‘ ማለቱ እነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ለክብሩ የተፈጠሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጥረትን ሲፈጥር ለምስጋና፣ ለተዘክሮ፣ ለምግብ ሥጋ፣ እና ስሙን ቀድሰው መንግሥቱን ይወርሱ ዘንድ፣ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ በመልኩ ፈጥሮታልና ነው፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” በማለት ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ሰባት ጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን እንዳለባቸው ይመክራል (መዝ.፻፲፰፥፻፷፬)፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” ሲል ፍጹም ምስጋና አቀርብልሃለሁ፣ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፣ በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለው ማለቱ ነው፡፡ የቅዱስ ዳዊትን ቅኔ (ምስጋና) አብነት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበረቱት በቀን ሰባት ጊዜ ለጸሎት እንዲቆሙ ታስተምራለች፡፡ በተግባርም በገዳም ባሉ አባቶች እና በከተማ የሚኖሩ ጠንካራ ክርስቲያኖችም በየቀኑ ሕይወታቸው ወይም ሱባኤ ይዘው ይኖሩበታል፡፡
ሱባኤን በመንፈሳዊ ትርጒሙ ስንመለከተው አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምሕላ ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያስበው መንፈሳዊ የልቡና መሻት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ሳያቋርጥ ቢጾም፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ አንድ ሱባዔ ፈጸመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ ሁለት ሱባኤ ፈጸመ እየተባለ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሱባኤ ምእመናን ስለ በደላቸው እያሰቡ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚለምኑበት ሥርዓት ሲሆን የምንሹትንም ነገር ለማግኘት እግዚአብሔርን መማጠኛ (መለመኛ) የልቅሶ፣የዋይታ እና የጥሞና ጊዜ አድርገው የሚሰነብቱበት የቀናት ወይም የሰዓታት ድምር ነው፡፡
የሱባኤን አጀማመር ስንመለከት ምክንያቱ ውድቀት ነው፡፡ይህም የተጀመረው በመጀመሪያው ሰው በአዳም እና በሔዋን ሲሆን ከውድቀት በኋላ ነው፡፡ አዳም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ አፍርሶ የፈጣሪውን ቃል ጥሶ ከገነት ተባሯል(ተሰድዶአል)፡፡አዳምን ይኖርባት ዘንድ ከተሰጠቸው ከዔደን ገነት ማን አባረረው ወይም ማን አሳደደው ብለን ስንመለከት ማንም ሳይነካው የሠራው ኃጢአት (ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፉ) በክብር አላኖር ብሎት ራሱን ስደተኛ አደረገ፡፡ለዚህም ነው ሙሴ አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ከበላ በኋላ ስለ ገጠመው ነገር ሲጽፍ፡- ”እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ አዳም ወዴት አለህ? አለው አዳምም አለ በገነት ስትመላለስ ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም‘(ዘፍ.፫፥፱) በማለት ራቁትነቱ የኃጢአቱ ውጤት እንደሆነ የእግዚአብሔርንም ድምጽ ሰምቶ በፊቱ ለመቆም የሚያስችል ድፍረት እንዳጣ ከነበረው ክብር እንዳነሰ እንደተጎሳቆለ ራሱ አዳም ተናገረ፡፡ በኃጢአት የወደቀው አዳም ከውድቀት እስኪነሣ ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደደ፡፡ ከዚህ በኋላ አዳም በሱባኤ ፈጣሪውን ለመነ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ስፍራ አጥቶ መኖር እንደማይችል በንስሓ እንባ ፈጣሪውን ጠየቀ፡፡
በመጨረሻም ”በሐሙስ ዕለት ወመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅከ ውሰተ መርህብከ‘ አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁው ብሎ ተስፋውን ሰጥቶታል፡፡ ይህም አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ቃል ኪዳን እንደ ገባለት የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ያትታል፡፡ በመሆኑም ሱባዔ መግባት የሚያስፈልግበትን ዋና ዋና ምክንያቶች በዝርዝር ስንመለከት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት
ጸጋ የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ስጦታ ማለት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ሲገልጽ፡- ”ነገር ግን ስለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ ደግሞም የምትሻለውን መንገድ አስተምራችኋለሁ‘(፩ኛቆሮ.፲፪፥፴፩) ይላል፡፡ ከሁሉ የምትበልጠው ጸጋ ከእግዚአብሔር የምትገኝ ስትሆን ብዙዎቻችን በኃጢአታችን ምክንያት እናጣታለን፡፡ ለዚህ ነው ቅዱሳን የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድልባቸው ሁሉን ጥለው፣ ሁሉን እያጡ ራሳቸውን በዓለም ድሃ አደረጉ፡፡ የጸጋ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ብለው በፍቅሩ ተቃጥለው ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉ መራራውን ሞት በመታገሣቸው ከሁሉ የሚበልጠውን ሰማያዊውን ጸጋ ወረሱ፡፡ በዓለም እንደምናምንቴ ተቆጠሩ፣ አገር ላገር ስሙን ተሸክመው ተንከራተቱ፣ዳዋ ጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ጤዛ ልሰው፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሠው ገድላቸውን በመፈጸማቸው ከሁሉ ይልቅ የሚበልጠውን ዘላለማዊውን ክብር ተጎናጸፉ ፡፡
ስለዚህ ቅዱሳንን አብነት አድርገን ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት መትጋትና አብዝተን መሻት ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው ሥጋው ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ እግዚአብሔር አዋቂ አድርጎ የሰጠው በጎ ኅሊናው የፈጸመው በደል ትክክል እንዳልሆነ ይወቅሰዋል፤ በዚህም የተነሣ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ይደነግጣል፡፡ አምላኩን በማሳዘኑ እና ሕግ በመተላለፉ ከሚመጣበት ቅጣት ለመዳን ንስሓ ገብቶ ሰውነቱን በጾምና በጸሎት በመጥመድ ራሱን በጽድቅ ሥራ ያሳትፋል፤ ይህም የቀድሞ ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለት ከሁሉ የምትበልጠውን ጸጋ እንዲያገኝ በፍጹም መመለስ እግዚአብሔርን በሱባኤ መጠየቅ ያስፈልገዋል፡፡ ድካመ ሥጋ የሚፈታተነው የሰው ልጅ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት ሱባዔ መግባት በኃጢአት ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ሰላሙን ለመመለስ መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡
ስለምንሻው በጎ ነገር እግዚአብሔርን ለመማጸን
በየትኛውም መንገድ ቢሆን ሱባዔ ከምንይዝባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ይሆንልን ዘንድ ወይም ይፈጸምልን ዘንድ ስለምንሻው መልካም ነገር እግዚአብሔርን ለመማፀን ሲሆን ሱባዔ ለመያዛችን መሠረታዊ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት ሱባኤ የምገባው ለምንድን ነው? የማገኘውስ ጥቅም ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች አስቀድሞ ከመምህራንና ከመጻሕፍት መረዳት አለበት፡፡በመቀጠልም ከራሱና ከንስሓ አባቱ ጋር በግልጽ በመምከር መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ምንም የሚጠይቀው ነገር ሳይኖር ሱባዔ ቢገባ የሚያገኘው መልስ ላይኖር ይችላል፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባኤ የሚገቡ ሰዎች ከሱባኤ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር አይኖርም ሲባል ቢያንስ ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት አስቦ መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ሰው ሱባኤ ከመግባቱ አስቀድሞ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት “እግዚአብሔርን መማፀን የምፈልገው ምንድን ነው?” በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ፣ስለ ቤተሰቡ፣ስለ አካባቢው፣ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤናና ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ ለገባው ሱባኤ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ ወይም መልሱ ሊዘገይ ይችላል ፣ይህ ካልሆነ ደግሞ የማያስፈልግ ጥያቄ ከሆነ ጭራሹኑ መልስ ሳያገኝ ሊቀር ይችላል፣ ከዚህ ባለፈ ግን እምነቱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን በጸሎት፣በጾም፣በስግደት(በሱባኤ) ስንለምን እምነት ሊኖረን ይገባልና ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ከተሐራሚው ስለ ሁሉም ነገር በማስተዋል፣በትዕግሥት (በመታገሥ) የእግዚአብሔርን ሥራ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በሱባኤ እግዚአብሔርን ጠይቄው እኔ ባሰብኩት መንገድና ጊዜ ለምን አልሆነም? ለምንስ ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝም?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለውና፡፡
ከቅዱሳን በረከት ለማግኘት
እግዚአብሔር የአባትነቱን በረከት ሲያድለን ቅዱሳን ደግሞ በጸጋ እግዚአብሔር ከብረዋል እና ከእግዚአብሔር በተገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያድሉናል፡፡ ይህም ቅዱሳን የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር በስማቸው በታነጹ ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ ከቅዱሳኑ በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን የተጋደሉበት ቦታ ቅዱስ ነውና፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ቅዱሳን ስለተገባላቸው ቃል ኪዳን ሲናገር፡- ”እግዚአብሔር ለጃንደረቦች እንዲህ ይላል ሰንበቴን ቢጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ቢመርጡ በቃል ኪዳኔም ጸንተው ቢኖሩ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ‘ በማለት እግዚአብሔር ለቅዱሳን ቃል ኪዳን እንደ ገባላቸው እና በስማቸው የሚጠራ ቦታ እንደሚሰጣቸው ይናገራል (ኢሳ.፶፮፥፬)፡፡
ለዚህም ነው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በገዳማት እና በአድባራት ለተወሰነ ጊዜ ሱባኤ በመግባት ከእግዚአብሔርን ምሕረት ከቅዱሳን በረከታቸውን መሳተፍ እንደሚገባ የምታስተምረው፡፡ ይህም በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል ከቅዱሳን በረከት ለመቀበልና የቅዱሳን አጽም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ለማግኘት ደጅ የሚጠኑ መናንያንና ምእመናን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡
የቅዱሳንን ሕይወት አብነት በማድረግ በትሕርምት የሚኖሩ መናንያን ያገለገሉበትን በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህን ትውፊት ለማጥፋትና ምእመናን ለመናንያን አባቶች ክብር እንዳይሰጡ ያልተገባ ተግባር የሚፈጽሙ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቀን ቀን በልብስ ተመሳስለው መናኝ መስለው የሚታዩ መሸት ሲል እንኳንስ ከአንድ አባት ይቅርና ክርስቲያን ተብሎ ከሚጠራ አማኝ የማይጠበቅ ሥራ ሲሠሩ ሊታዩ ይችላሉና፡፡ በተለይ በከተሞች እንዲህ አይነት ማጭበርበሮች በስፋት ይስተዋላሉና በጥንቃቄ መለየቱ አስፈላጊ ነው፡፡
የተሠወረው ተገልጦ፣ የረቀቀው ጎልቶ እንዲታየን (ምሥጢር እንዲገለጥልን)
ቅዱሳን አባቶቻችን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢርና ትርምጒም እንዲገለጥላቸው ሱባኤ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባኤ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ከነበሩት አበው ነቢዩ ዕዝራን ብንመለከት የመጻሕፍትን ምሥጢር እግዚአብሔር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል (፩ኛ ዕዝ..፲፫፥፵፫)፡፡
በዘመነ ሐዲስም እንዲሁ ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም ዕረፍትዋ ሲደንቃቸው ሥጋዋን መላእክት ወስደው በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ማኖራቸውን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲነግራቸው እነሱም ይህ ምሥጢር እንዲገለጽላቸው ከነሐሴ ፩-፲፬ የገቡት ሱባኤ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ሱባኤ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሠውሮባቸው የነበረውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የሥጋዋን መገለጥ ብቻ ሳይሆን እያዩ ዳሥሠው የቀበሩትን የሥጋዋን ዕርገት እና ትንሣኤዋንም ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡
በመሆኑም ሱባኤ ከአምላካችን ከልዑል እግዚአብሔር ጸጋውን በረከቱን እንድናገኝ፣ ምሕረት ቸርነት እንዲሆንልን በፍጹም ልባችን የምንቀርብበት እና ከቅዱሳን ረድዔት በረከት የምናገኝበት ነው፡፡ እንዲሁም በሕይወታችን በጎ መሻታችን እንዲፈጸም ለተማጽኖ ወደ እግዚአብሔር በጾም፣በጸሎት፣በስግደት ተወስነን ለተወሰነ ጊዜ ጽሙና ላይ በመሆን በተሰበረ ልብ በተዋረደ መንፈስ ሆነን የምንቀርብበት መንገድ ነው፡፡
በዚህ ክፍል የሱባኤን ምንነት እና ለምን ሱባኤ እንደምንገባ ለየሚያስረዳውን ክፍል የተመለከትን ሲሆን በቀጣዩ ክፍል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የሥጋዋ ፍልሰት(ዕርገትዋን) በማስመልከት አዘጋጅተን ይምናቀርብ ይሆናል፡፡
እጅግ መልካም ትምህርት ነው እግዚአብሔር ይስጥልን። ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር