“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)
መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረው የመገለጡን ምክንያትም አያይዞ በመጥቀስ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን ምስክርነት የሰጠውም ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ከዓለም አስቀድሞ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ በባሕርይ አባቱ በአብ፣በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ፣በራሱም ፈቃድ ለድኅነተ ዓለም ከድንግል ማርያም በሥጋ እንደተወለደ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ በዚህም ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት በመወለዱ ድኅረ ዓለም ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደተወለደ እንረዳለን፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡እሱም ከላይ የተመለከትነው ሲሆን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መስክሯል፡፡ “ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡፡ ስሙም ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል”(ኢሳ.፱፥፮)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ሕፃን ተወልዶልናል ያለው ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም መወለዱን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል በባሕርዩ ሲመሰገን ሲወደስ የነበረው በአምላካዊ ባሕርዩ በመፍጠር፣ በመግዛት፣ በመመለክ፣ በመፍረድ፣ በጌትነት ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት የነበረው፣ ያለው፣ የሚኖረው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ ዓለምን ያድን ዘንድ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” ያለው የኢየሱስ ክርስቶስን ከድንግል ማርያም መወለድ መሆኑን በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡
ይህው ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም… ያም ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ ለአባቱ አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው”(ዮሐ.፩፥፩-፲፬)፡፡
“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” ማለትም አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ፤ አካላዊ ቃል ሥጋን በመዋሐዱ (ሰው በመሆኑ) የማይታየው ታየ፣ የማይወሰነው ተወሰነ፣ ረቂቁ ገዝፎ (ጎልቶ) ታየ፣ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ ማለት ነው፡፡ ይህ የሆነውም በደኀራዊ ልደቱ ነው፡፡ በደኀራዊ ልደቱ ዓለምን ለማዳን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በሥጋ በመገለጡ ቀዳማዊ ልደቱ ታውቋል፡፡
የሰው ልጅ ድኅነትን ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅ ዳግም በመወለዱ ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ተለያይተው የነበሩትን ሰውና መላእክት አንድ ያደረገ፤ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ወገን ያደረገ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጡም የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ፣ በሞት ጥላ ሥር ወድቆ፣ ሳለ አማናዊው ብርሃን መታየቱ ሰውን የመውደዱ ምሥጢር ነው፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ.፯፥፲፬) ያለው መፈጸሙን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ደግሞ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው” (ማቴ.፩፥፳፫) ሲል ተርጉሞታል፡፡
ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጥ (ሰው መሆን) እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በምሕረት መመልከቱ፣ ከጽድቅ ተራቁቶ ለነበረው የጸጋ ልብስ ስለመሆኑ ብርሃን ሆኖ ድቅድቁን ጨለማ ያራቀ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያው መልእክቱ “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” (፩ኛዮሐ.፩፥፪) በማለት ምስክርነቱን ገልጾልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትንና በሥጋ የተገለጠበትን ምክንያት ሲጠቅስም በርእሳችን መነሻ ያደረግነውን የእግዚአብሔር ልጅ የመገለጡን ዓላማ ሲያብራራም፡-
“ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል ኀጢአት በደል ናትና እርሱም ኀጢአትን ያስወግድ ዘንድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ በእርሱም ኀጢአት የለም በእርሱም የሚኖር ሁሉ አይበድልም የሚበድልም ሰው አያየውም አያውቀውምና ልጆቼ ሆይ ማንም አያስታችሁ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው ኀጢአትን የሚሠራትም ከሰይጣን ወገን ነው ጥንቱን ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ”(፩ኛዮሐ.፫፥፬-፱)እንዲል፡፡
በአምላክ ሰው መሆን(መወለድ) ከኀጢአት ማሰሪያ፣ከዲያብሎስ ቁራኝነት፣ከሲኦል ባርነት ነጻ ወጥተናል፡፡እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅሩ ወደ ራሱ አቀረበን፣አባ አባት ብለን እንጠራው ዘንድ በልጅነት ጸጋ አከበረን፣የሞትን ቀንበር ከላያችን አንከባሎ ጣለልን፣በማዳኑ ሥራ ከጨለማው ገዢ ታደገን፣ወደ ቀድሞ ክብራችንም እንመለስ ዘንድ ከራሱ ጋር አስታረቀን፣እርሱ ከእኛ ጋር ሲሆን ሞት ከፊታችን ተወገደ በዚህ ሁሉ ክብርና ጸጋ የጎበኘን ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ ነውና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን፡፡ በሚቀጥለው ክፍል የመገለጡን ምሥጢር በስፋት የምንመለከት ይሆናል እስከዚያው ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!