በጊዜው ሁሉ ጸልዩ(ፊል.፬.፮)
ክፍል ሁለት
በእንዳለ ደምስስ
ጸሎት ጸለየ፣ ለመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን መለመን፣ ማመስገን፣ በንጽሕና በእግዚአብሔር ፊት መቆም፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ “ጸሎትስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚናገርባት ናት” (ፍትሐ. ነገ. አንቀጽ ፲፬) እንዲል፡፡
አዳም አባታችን ተግቶ በመጸለዩ ዲያብሎስ ሊፈትነው በቀረበ ጊዜ ድል ነስቶታል፣ ሔዋን ግን ሥራ ፈትታ፣ እግሯን ዘርግታ በመቀመጧ በቀላሉ በዲያብሎስ ተረትታለች፣ ዕፀ በለስንም በልታ አጋርዋን አዳምን እስከማብላት ደርሳለች፡፡ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፈዋልና ተረግመው፣ ስደተኛ ሆነው ከገነት ተባረሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተግተን መጸለይ እንደሚገባን ሲያስረዳ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “እግዚአብሔር ቅርብ ነው፣ ምንም ምን አታስቡ፣ ነገር ግን በጊዜው ሁሉ ጸልዩ፣ ማልዱ፣ በምታመሰግኑበትም ጊዜ ልመናችሁን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ” ይለናል፡፡ ዲያብሎስን ድል መንሣት የምንችለውም በጸሎት ኃይል እንደሆነ አስረድቶናል፡፡(ፊል.፬.፮)፡፡
ጸሎት ለመንፈሳዊ ሰው አስፈላጊና ትልቁ መሣሪያው ሊሆን ይገባል፡፡ በዓለም ውስጥ ያለን ሰው በመውጣት በመውረድ፣ ጥሮ ግሮ ይበላ ዘንድ በታዘዘው መሠረት በርካታ ነገሮች ማለትም በጎም ሆነ መጥፎ ነገር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ለገጠመው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ችግሩን እንዲያስወግድለት በትጋት መጸለይ፣ እንዲሁም ለተደረገለት መልካም ነገር ሁሉ በጸሎት እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በደስታችን ወቅት ሳይሆን በችግራችን ጊዜ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ጥረት ስናደርግ እንታያለን፡፡ ነገር ግን በጊዜውም ያለጊዜውም ቢሆን ወደ እግዚአብሔር መጸለያችንን መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ እርሱንም መለመንና ማመስገን ለሰው ልጅ የተሰጠ ስጦታ ነውና፡፡
ለመሆኑ በጸሎት ምን እናገኛለን? ጥቅሙስ ምንድነው? ቀጥለን እንመለከታለን፡-
የጸሎት ጥቅም
ስለተደረገልንና ለሚደረግልን ሁሉ ምስጋና ለማቅረብ፡- ከላይ እንደጠቀስነው በችግራችን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በደስታችንም ጊዜ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ተቀብለኸኛልና የጠላቶቼ መዘባበቻ አላደረግኸኝምና አመሰግንሃለሁ” በማለት ምስጋና ሲያቀርብ እንመለከታለን፡፡(መዝ.፳9.፩)፡፡ ምስጋና ማቅረብ በእግዚአብሔር እንድንታመን፣ የነገ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲቃና ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይታደገናልና፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ የምናቀርበው የምስጋና ጸሎት ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ ስላለው ዘወትር መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛው መልእክቱ “ስለማትመረመርና ባላሰቡአት ጊዜ ስለምትመጣው ጸጋው እግዚአብሔር ይመስገን” እንዲል(፪ቆሮ.9.፲፭)፡፡
ስለበደላችን ይቅርታን እናገኛለን፡- ይቅርታ ከዚህ በፊት ስለተፈጸመና ወደፊት ደግመው ሊያደርጉት በማይገባ በደል ምክንያት የሚጠየቅ ትሕትናን የተላበሰ፣ በተሰበረ መንፈስ ለተበዳይ የሚቀርብ ነው፡፡ ሰዎችን ብንበድል ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አፈንግጠናልና በማይገባ መንገድም ተጉዘናልና ተበዳዩን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ጭምር ነው ያሳዘንነው፡፡ ስለዚህ ለፈጸምነው በደል በግለሰቡ ፊት ወድቀን ይቅርታ ስንጠይቅ ግለሰቡም እግዚአብሔርም ይቅርታውን ይቀበላሉ፡፡ “ይህን አስቡና አልቅሱ፣ የተሳሳታችሁ ሆይ ንስሓ ግቡ፣ ልባችሁንም መልሱ” ይለናል(ኢሳ.፵፮.8)፡፡ ልብን መመለስ፣ በቀናውም መንገድ መጓዝ ቀድሞ ስለበደሉት በደል መጸጸትና ማልቀስ፣ በተሰበረ ልብም ሆኖ ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት “አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ታሸንፍ ዘንድ” እያለ ስለ በደሉ ይቅርታ ሲጠይቅ እናያለን፡፡ (መዝ.$..፬)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልም “ማቅ ለብሼ በዐመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ፡፡ ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ … አቤቱ ስማ፣ አቤቱ ይቅር በል፣ አቤቱ አድምጥና አድርግ አምላኬ ሆይ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና ስለ ራስህ አትዘግይ” እያለ እግዚአብሔርን ይማጸናል ይቅር ማለት የሚችል እግዚአብሔር ነውና፡፡ ይቅርታ የኅሊና ዕረፍትን ይሰጣል፣ ይቅርታ ለአድራጊውም፣ ለተደረገለትም ሰላማዊ ግንኙነታቸውን የሚቀጥሉበት የሰላም ድልድይ ነው፡፡ ከኅሊናችን ጋር ታርቀን፣ ንስሓ ገብተን የወደፊት ሕይወታችንን ልንመራ የምንችለው ይቅርታን ስናገኝና እኛም የበደሉንን ይቅር ስንል ነው፡፡ ጸሎታችንም ይህ ሊሆን ይገባል፡፡ “አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ” እንዲል(ማቴ.፳፩.፳፪)፡፡
ንጉሡ ሕዝቅያስ በታመመና ለሞትም በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ልኮ “ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው፡፡ ሕዝቅያስም ይህንን በሰማ ጊዜ ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡- “አቤቱ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደሄድሁ፣ መልካም ነገርንም እንዳደረግሁ አስብ” በማለት አልቅሷል፡፡ እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ተቀበለ፡፡ እንዲህም አለው፡- “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ ዕንባህንም አይቻለሁ፣ እነሆም እኔ እፈውስሃለሁ፣ … በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ” ሲል መልካሙን ዜና ለመስማት በቅቷል፡፡(፪ኛ ነገ.፳.፩)፡፡ ስለዚህ በጸሎት ኃይል ይቅርታን እናገኛለን፡፡
መንፈሳዊ ኃይልን እናገኛለን፡- መንፈሳዊ ኃይል በአንድ ጀምበር የሚገኝ አይደለም፡፡ ማመን፣ ለአመኑትም አምላክ መገዛት፣ ዘወትር በሚያምኑት አምላክ ፊት መቆምንና መጸለይን ይጠይቃል፡፡ መንፈሳዊ ኃይል መንፈሳዊ ልምምድ በማድረግ፣ በጸሎት በመበርታት የሚገኝ ጸጋ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “እርስ በእርሳችሁ ኃጢአታችሁን ተናዘዙ፣ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፣ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፣ ግዳጅም ትፈጽማለች” ይላል ከራስ አልፎም ስለ ሌሎች መጸለይ እንደሚገባ ሲያስረዳን፡፡(ያዕ.፲፭.፲፮) ይህም ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ጸጋ ነውና፡፡ ጸሎት በንጹሕ ኅሊና ሆነው ቢጸልዩ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ” እንዲል ቅዱስ ዳዊት የለመኑትን የማይነሣ አምላክ በጸጋ ላይ ጸጋንም ያላብሰናል፡፡(መዝ.፻፵፥፪)፡፡ ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!