ጾመ ነቢያት
ጾመ ነቢያት ቅዱሳን ነቢያት ጌታ ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው ሱባዔ በመቁጠር የክርስቶስን ልደት በመጠበቅ የጾሙት ጾም ነው፡፡
በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በተሰጣቸው ጸጋ ትንቢት የራቀው ቀርቦ፣ የረቀቀው ገዝፎ ያዩት ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ፣ ጸለዩ፡፡ ነቢያት ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስደት፣ ሞቱና ትንሣኤው፣ እንዲሁም ጨለማ የሆነውን የሰው ልጆችን ልቡና በትምህርቱ ስለ ማብራቱ፣ ጨለማውን ዓለም በብርሃኑ ስለ መግለጡ፣ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ጸዋወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍጻሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን በየዘመናቸው “አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ” እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሣምንታት፣ በወራት፣ በዓመታት ቆጠሩ፡፡
ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም “እግዚአብሔር የማያደርገውን አይናገር፣ የተናገረውን አያስቀር” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ዘመኑ ሲደርስም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትንቢቱ ተፈጸመ፡፡ ስለዚህ ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል እያሉ የጾሙት በመሆኑ “ጾመ ነቢያት” ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ስለሆነም “ጾመ ስብከት” ይባላል፡፡ ጾመ ነቢያት ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እንዲጾም ደንግጋለች፡፡
ጾም ቃላዊ ትርጉሙ ጾመ፣ ተወ፣ ታረመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ነው፡፡ በታወቀ ጊዜ ከምግብ መከልከል፣ መጠበቅ ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ጾም ለሰውነት ከሚያስፈልገው ኃይል ከሚሰጡ ምግቦች፣ ከክፉ ሐሳብና ድርጊት በመከልከል ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ለክፉ ሥራ/ኃጢአት ከሚያነሣሱና ሰውነትን ከሚገነቡ ምግቦችና መጠጦች በመከልከል በጾም፣ በጸሎት በመወሰን ልቡናችንን ለእግዚአብሔር ሰጥተን፣ በፍጹም ትኅትና የምንጾመው ጾም ነው፡፡ በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምንበረታበት፣ ንስሓ የምንገባበትና ለቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የምቀርብበት በመሆኑ ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ አይገባንም፡፡ ከቅዱሳን ነቢያት በረከት እንሳተፍ ዘንድ የትሩፋት ሥራዎችን እየሠራን ልናሳልፈውም ይገባል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!