ጾም ምንድን ነው?
…በመ/ር ቅዱስ ያሬድ…
ጥያቄ፡- የጾምን ምንነትና ዓይነቶቹን ጠቅለል አድርገው ቢገልጹልን?
መምህር ቅዱስ ያሬድ፡- በመጀመሪያ ጾም ‹‹ጾመ›› ጾመ /ጦመ/ ታቀበ፣ ታረመ፣ ተወ፣ ተከለከለ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሃይማኖት ምክንያት ምግብና መጠጥ መተው፤ ወይም ከምግብና ከመጠጥ መከልከል፤ ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከክፋትና ሥጋን ደስ ከሚያሰኝ ነገር ሁሉ መታቀብና መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾም በታወቀው ዕለትና ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው /አስ. 4፥16፤ ዳን.10፥2፤ ፍት. መን. አን 15/፡፡
በተጨማሪም ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት የምትጠቅም የስሜት ልጓም፤ እንዲሁም ኃይለ ፍትወትን የምናደክምባት መሣሪያ ናት፡፡ ‹‹ጾም ትፌውስ ቍስለ ነፍስ፤ ወታፀምም ኩሎ ፍትወታተ ዘሥጋ፡፡ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ ጾም የነፍስ ቁስልን ታደርቃለች፤ ተድላ ሥጋን ታጠፋለች፣ ለወጣቶች ርጋታን /ጭምትነትን/ ታስተምራለች» እንዳለ /ቅዱስ ያሬድ/፡፡ በሌላ በኩል ጾም ደካማው ሥጋ በነፍስ ላይ እንዳይሠለጥን የተሠራ ድንበር ነው፡፡ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን ለንጉሠ ሰማይ ወምድር የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት፡፡ ‹‹ጾምሰ ጸባሕተ ሥጋ ውእቱ፤ በከመ ምጽዋት ጸባሕተ ንዋይ ይእቲ፤ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት» እንዲል /ፍት. መን. አንቀጽ 15/፡፡
ጥያቄ፡- የጾም ዓላማ ምንድን ነው?
መ/ር ቅዱስ፡- የጾም ዋናው ዓላማ ሰው ራስን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ሰው ሲጾም ጊዜውን ሊያስተውል ይገባዋል /ዕዝ. 8፥23/:: የሚጾም ሰው ውስጡ በረኀብ ጦር ውጊያ ስለሚቆስል በረኀብ ጦር ለተወጉ ሁሉ የማዘንና በችግራቸው ጊዜ ከጎናቸው የመቆም ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ‹‹ወኵሉ ርኁብ የኀዘን ለርኁብ ወጽጉብሰ ለእመ ርእየ ርኁባነ ይሜንን፤ የተራበ ሁሉ ለተራበ ያዝናል፤ ያስባል፡፡ የጠገበ ግን ለተራበ አይራራም አያዝንም» እንዳለ /ርቱዐ ሃይማኖት/፡፡ የሰው ልጅ ባሕርይ እንስሳዊና ባሕርይ መልአካዊ አሉት፡፡ በእንስሳዊ ባሕርዩ በጾም በሰጊድ፤ በመልአካዊ ባሕርዩ ደግሞ በጸሎት፣ በምስጋና፣ በስግደትና በጾም እግዚአብሔርን ማገልገል ይገባዋል፡፡ ይህም ክርስቲያኖችን ሁለንተናቸውን ከዓለማዊ አሳብ፣ ፍላጎትና ምኞት ተመልሰው ሀልዎተ እግዚአብሔርን እያሰቡ መንፈሳዊ በሆነው ነገር ላይ ብቻ አርፈውና ተግተው እንዲጸልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በጾም ጊዜ ከሚበላ፣ ከሚጠጣ መከልከል ብቻ ሳይሆን የስሜት ሕዋሳቶቻችንም ከክፉውና ሥጋዊ ደስታን ከሚፈጥር ነገር ሁሉ መከልከል /መቆጠብ/ ይገባል፡፡ ‹‹ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሡም በተፋቅሮ ዓይን ክፉ ከማየት፤ አንደበት ክፉ ከመናገር፤ ጆሮም ክፉ ከመስማት መቆጠብ ይገባቸዋል» እንዲል /ቅዱስ ያሬድ/፡፡ ርቱዐ ሃይማኖትም «ኦ ጸዋሚ ይጹምኬ ኵሉ መለያልይከ፤ አፉከ እምነቢብ ሕሡመ፤ ወልሳንከ እምሐሜት ወእምፅርፈት፤ ወዓይንከ እምርእየተ አንስት፤ ወዕዝንከ እምሰሚዐ ማሕሌት ወተውኔት፤ ጸዋሚ ሆይ መላው አካልህ ይጹም፤ አፍህ ክፉ ከመናገር፤ አንደበትህ ከሐሜትና ከስድብ፤ ዓይንህ ሴቶችን ከማየት ጆሮህም ዘፈንና ጨዋታ ከመስማት ይጹም» በማለት መላው አካላችን መጾም እንደሚገባው ይናገራል /ድርሳን ዘጾም፣ ገጽ 118/፡፡
ጾም በሐዲስ ኪዳንም በብሉይ ኪዳንም ከሃይማኖት ጋር የተቆራኘ ሥርዓት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከፈጣሪያቸው ጋር በሚገናኙበት ወቅት እህል ውሃ በአፋቸው አይገባም ነበር /ዘፀ. 34፥28/፡፡ በኀጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰውም በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር /ዮና. 2፥7/፡፡ ‹‹ቀድሱ ጾመ፤ ወስብኩ ምሕላ፤ አስተጋብኡ ሊቃውንተ፤ ወኵሎ ዘይነብር ውስተ ምድር ኀበ ቤተ አምላክነ፤ ወጽርሑ ኀበ እግዚአብሔር ኅቡረ፤ ጾምን አጽኑ፤ ያዙ፤ ምሕላንም አውጁ፤ ሽማግሌዎችን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ ጌታ ጩሁ፤ ለምኑ›› እንዳለ ነቢዩ ኢዩኤል /ኢዩ.1፥14/፡፡
በሐዲስ ኪዳን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራው መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕገ ጾምን ነው /ማቴ. 4፥2/፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን መብል የኀጢአት መግቢያ፣ መሠረት እንደ ሆነ ሁሉ ጾምም ለምግባር ለትሩፋት መሠረት ነው፡፡ ‹‹እስመ ጾም እማ ለጸሎት፤ ወእኅታ ለአርምሞ፤ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኵሉ ገድል ሠናይት፤ ጾም የጸሎት እናቷ፣ የአርምሞ እኅቷ፣ የዕንባ መገኛዋ መፍለቂያዋ፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ መጀመሪያ መሠረት ናት እንዳለ /ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4፣ ምዕ. 6/፡፡
ጥያቄ፡- ጾም ግዴታ ነው ወይስ ውዴታ?
መ/ር ቅዱስ፡- ወደ ጾም ዓይነቶች ስንመጣ ጾም የአዋጅና የግል ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የአዋጅ ጾም በአዋጅ ተነግሮ በአንድነት፣ በጋራ የሚጾም የጾም ዓይነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከነቢያትና ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ ትምህርትና ሥርዓቱንም ሕግና ትውፊት ሳትጨምርና ሳታጎድል ጠብቃ ትኖራለች፡፡ በዚህም መሠረት በሐዋርያት ሲጾሙ የቆዩ፤ ሥርዓት ተሠርቶላቸው፤ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው ሁሉም ሰው እንዲጾማቸው የተደነገጉ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉን፡፡ እነዚህም ጾመ ኢየሱስ፣ ጾመ ድኅነት /ዓርብ ረቡዕ/፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ገሀድ፣ ጾመ ነነዌ ናቸው፡፡ እነዚህን አንድ ክርስቲያን የሆነ ሰው ሊጾም ይገባዋል፡፡
የግል ጾም ምእመናን በስውር /በግል/ የሚጾሙት ሲሆን ከዐዋጅ ጾም ጋር አንድ አይደለም፡፡ የግል ጾም ደግሞ በራሱ የንስሓ ጾምና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የንስሓ ጾም ምእመናን ንስሓ ገብተው ቀኖና ሲቀበሉ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ አንድ ምእመን በራሱ ፈቃድ ሊጾም ይችላል፡፡ ይህም ጾመ ፈቃድ (የፈቃድ ጾም) ይባላል /ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምእት/፡፡ ጾመ ፈቃድ በራሱ ተነሣሽነት የሚጾመው እንጂ ባይጾም ሐጢአት አይሆንበትም፡፡ ቢጾም ግን በረከትን፣ ጽድቅን፣ ሰማያዊ ፍሬን ያፈራበጻል፡፡