“ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ፤ የማትረግፍ አበባ” (ቅዱስ ያሬድ)
በዲ/ን ሕሊና በለጠ
በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ሃያ ስድስት እስከ ኅዳር አምስት ያለው ዓርባ ቀናትን የያዘው ጊዜ ዘመነ ጽጌ፣ ወርኃ ጽጌ በመባል የሚታወቅ ነው። ከዋክብትን ለሰማይ ውበት የፈጠራቸው አምላካችን እግዚአብሔር አበቦችን ደግሞ ምድርን ያስጌጧት ዘንድ ፈጥሯቸዋል። አበቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ መታየት የጀመሩት በዕለተ ሠሉስ፣ በሦስተኛው የፍጥረት ዕለት ነው። ይህንን የመዘገበልን ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንዲህ ይለናል፡ ‹‹ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ››። (ዘፍ.፩፡፲፪)።
ጊዜን በወቅቶች ከፍሎ፡ በየትኛው ጊዜ ምን ዓይነት ምስጋናን ማቅረብ እንደሚገባን ሥርዓትን በመጻሕፍቱ የሠራልን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፡ በዚህ የሙሴ ቃል ላይ ተነሥቶ በድጓ ዘጽጌ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ወሤሞ ለፀሐይ ውስተ ጠፈረ ሰማይ ወርእየ ከመ ሠናይ ወካዕበ ይቤ ለታውፅዕ ምድር ጽጌያተ ዘበድዱ ወፍሬያተ ዘበበዘመዱ – በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ሠራ፤ ፀሐይንም በጠፈር ላይ አሠለጠነው፤ የሠራው ሁሉ መልካም እንደ ሆነ እግዚአብሔር አየ። ዳግመኛ ምድር አበቦችን በየግንዱ ፍሬዎችን በየነገዱ ታውጣ እንዳለ››። (ድጓ ዘጽጌ)። እግዚአብሔር ሰውን በዕለተ ዓርብ የፈጠረው ሰማይን በከዋክብት፣ ምድርን በዕፅዋት አስጊጦ ከፈጸመ በኋላ ነው። ቅዱስ ያሬድ በዚሁ በጽጌ ድጓው እንዳለውም ‹‹ወወሀበ ገነተ ምስለ ጽጌያት – ገነትንም በአበቦች እንዳሸበረቀች ሰጠው›› እንዲል።
አንድ ደጋሽ ምግቡን አዘጋጅቶ፣ መጠጡን አሰናድቶ፣ ቤቱን አስውቦ የከበረ እንግዳውን በመጨረሻ እንደሚጠራው፡ እግዚአብሔር አምላክም ከፍጥረታት ይልቅ የከበረውን ሰው ሁሉን አሰናድቶ ከፈጸመ በኋላ ፈጠረውና በሁሉ ላይ ሾመው። አዳም ይኖርባት ዘንድ የተሰጠችው ገነትም ያማረችና የተዋበች ነበረች። ለዚህ ነው አምላካችን ‹‹ወይቤሎ ለአዳም ወሀብኩከ ርስተ ገነተ ትፍሥሕት በጽጌ ሥርጉተ ወበፍሬ ክልልተ- ለአዳም ‹አዳም ሆይ በፍሬ የተከበበች በአበባ የተሸለመች የደስታ ገነትን ለአንተና ለልጆችህ ርስት ትሆንህ ዘንድ ለርስትነት ሰጠሁህ›› በማለት ገነትን ‹‹የደስታ ገነት›› ብሎ የሰጠው። (ድጓ ዘጽጌ)። አዳም በበደለ ጊዜ ግን ባሕርይው ጎሰቆለ። ከገነት ወጣ፤ ስደተኛ ሆነ፤ ምድርም በአዳም ምክንያት ተረገመች። ዕፀ በለስን በመብላት መዋቲነትን መረጠ። ምንም እንኳን ለዘላለም ሕይወት ቢፈጠርም በበደሉ ምክንያት የሚሞት ሆነ። እንደ አበባ ሊያብብ ቢፈጠርም ባለመታመኑ ምክንያት ጠወለገ። አበባ እሳት ሲያቃጥለው፣ ፀሐይን ሲያጣ ወይም ሙቀቷ ሲበረታበት፣ ውኃን ሲጠማ፣ ውጫዊ ኃይል ሲያርፍበትና ከግንዱ ሲለይ ይጠወልጋል፣ ይረግፋል። አዳምም ከጕንደ ወይኑ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ጠወለገ፤ ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በሲኦል ረገፈ። መልሶ እንዲያብብ ‹‹የሕይወት ውኃ›› የተባለ ‹‹ፀሐየ ጽድቅ›› ክርስቶስ ያስፈልገው ነበር። ለዚህ ደግሞ ለድኅነቱ ምክንያት የሆነችው ንጽሕት እመቤት ድንግል ማርያም ታስፈልገው ነበር። ለዚህ ነው ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል የገለጻት፡- ‹‹እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ… መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኃኒተ ሕዝብ – የባርያይቱን መዋረድ አይቷልና ኃይልን በክንዱ አደረገ፤ የማትረግፈውን አበባ የዓለም መድኃኒት የቅዱሳን መዓዛ እንድትሆን አደላት›› (ድጓ ዘጽጌ)።
ቅዱስ ያሬድ ‹‹የማትረግፈው አበባ›› ያላት የማይረግፍ ዘላለማዊ ክብርና ቅድስና ያላትን እመቤታችንን ነው። ስለ እርሷ ‹የማይረግፍ አበባነት› ከማየታችን በፊት ግን፡ ሊቁ በአበባ ከመሰላቸው መካከል ከእመቤታችን ጋር ዐቢያን አምሳላት የሚባሉት መስቀሉ እና ቤተ ክርስቲያንም ይህ ”ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ፤ የማትረግፍ አበባ” ዐውደ ስብከት ዲ/ን ኅሊና በለጠ ቅዱስ ያሬድ ጥቅምት/ ፳፻፲፫ ዓ.ም 5 ቅጽል ይገባቸዋልና የእነርሱንም ‹የማይረግፍ አበባነት› በጥቂቱ ልናይ ይገባናል። ይልቁንስ ከጠቀስናቸው ከሦስቱም ይልቅ በአበባ ከሚመሰሉት ከዐራቱ ዐቢያን አንዱ የሆነው ጌታችን፡ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ነው፤ ሌሎቹም ይህን ጸጋ ያገኙት ከእርሱ ሥር ተጠልለው ነውና ከሁሉ አስቀድሞ የእርሱን አበባነት ማየቱ ተገቢ ነው። የጌታችን አበባነት ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል›› ሲል የጌታችንን ከእመቤታችን መወለድ ገልጾአል። (ኢሳ. ፲፩፡፩)። ‹‹በትር›› የተባለችው ያለ ዘር የጸነሰችውና ከእሴይ የዘር ሐረግ ሥር የተገኘችው ድንግል ማርያም ስትኾን ከበትሩ ላይ ያቆጠቆጠው አበባ ደግሞ ጌታችን ነው። ይህንን ሲያስረዳ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ትወፅዕ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ… ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘወፅአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ – ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ያቆጠቁጣል፤ ይህች በትር ቅድስት ማርያም ናት፤ ከእርሷ የወጣው አበባም የወልድ ምሳሌ ነው››። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማርያም አበባ ነው። ከእርሷ በትርነት የተገኘ አበባ ነው።
ጠቢቡ ሰሎሞን በመኃልየ መኃልይ ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ማለቱን ሊቃውንት ከጌታችን ጋር አያይዘው ተርጉመውታል። (መኃ.፪፡፩)። ሳሮን (Sharon) በይሁዳ የሚገኝ ሸለቆ ነው። ብዙ ውኃ ያለበትና መለምለም የሚችል ሥፍራ ነው። ነገር ግን በግብፅና በሶሪያ መካከል እንደ መንገድ የሚጠቀሙበት ጠባብ ሥፍራ በመኾኑ አበቦች የሉበትም። ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› በሚለው ጥቅስ ላይ ሳሮን የሕዝበ እስራኤል፣ ቆላ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። በእስራኤልም ሆነ በሕዝብ መካከል ፍሬ ድኅነት አልተገኘባቸውም ነበር፤ ድኅነትን የሚሰጠውን አበባ፣ ማለትም ክርስቶስን አላገኙም ነበርና። የማርያም አበባ የሆነው ጌታችን በተወለደ ጊዜ ግን በሳሮን ለተመሰሉት ለእስራኤላውያን ጽጌረዳ፣ በቆላ ለተመሰሉት አሕዛብም አበባ ሆነላቸው። ያውም በጊዜ ብዛት የማያልፍና የማይጠወልግ፣ የማይረግፍም አበባ። ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ያለው ጌታችን በጠቢቡ አንደበት ቀጥሎም ‹‹በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት›› ይላል። (መኃ.፪፡፪)።
ይህን ያብራሩ ሊቃውንት ‹‹እርሱ የቆላ አበባ እንደ ሆነው ሁሉ የሚወዳቸው ሁሉ የእርሱን ምሳሌነት ተከትለው አበባ እንዲኾኑ ይፈልጋል። ማለትም የእርሱን መንገድና ምሳሌነት የሚከተል ነፍስ ሁሉ አበባ ይኾናል›› ይላሉ። በእሾህ እንደ ተከበበች የሱፍ አበባ ወዳጄ ብሎ የገለጻት የሰው ነፍስን ነው። ይህን ክፍል በተረጎመበት ትምህርቱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ‹‹ነፍስ ወደ መሲሁ የምትናፍቅ አበባ ናት፤ የዚህን ዓለም ፈተና ሁሉ ድል አድርጋ ወደ እርሱ የምትጓጓ አበባ ናት›› ይላል። (A Patristic Commentary on The Song of Songs; Fr. Tadros Y. Malaty;) የቅዱስ መስቀሉ አበባነት አበው ‹‹በሴት ጠፋን በሴት ዳን›› እንደሚሉት ሁሉ ‹‹በዕፅ ጠፋን በዕፅ ዳን››ም ይላሉ። ያጠፋን ዕፅ ዕፀ በለስ ሲኾን ያዳነን ዕፅ ደግሞ ዕፀ መስቀሉ ነው። የመስቀሉ ጠላቶች የሚበሰብስ መስሏቸው ዕፀ መስቀሉን ከመሬት ሥር ለሦስት መቶ ዓመታት ቀብረውት ቢቆዩም ‹‹የማይረግፈው አበባ›› መስቀሉ ግን ምንም ሳይኾን በቅድሰት ዕሌኒ ምክንያት ተገኝቷል።
ዛሬም ማዕተብና መስቀሉ የሚወክለው ክርስትናን ጨርሶ ለመቅበር የሚጥሩ ሰዎች የማይሳካላቸው መስቀሉ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ስለ ሆነ ነው። ውኃ የማይጠጣ ተክል ይጠወልጋል፤ መስቀሉ ግን ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ›› ያለውን የክርስቶስን ደም ‹ጠጥቶ› ስለ ለመለመ የሚጠወልግ አይደለም – የማይረግፍ አበባ ነው እንጂ። (ዮሐ.፬፡፲፬)። ቅዱስ ያሬድም ‹‹በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ንትፈጋዕ ወኢይኅልፈነ ጽጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በሥነ ማርያም – ሰሎሞን ስለ ድንግል ማርያም ሲናገር እነሆ ክረምቱ አልፎ በረከት ተተካ እንዳለ የክርስቶስ መስቀል ከድንግል ማርያም ባሕርይ በተገኘው (በተወለደው በክርስቶስ) ዛሬ አብርቷልና የበረከት አበባ ሳያልፈን ኑ እንደሰት›› ይላል። (ድጓ ዘጽጌ)። ለዚህም ነው መዘምራን የመስቀል በዓል ሲደርስ ‹‹መስቀል አበባ ነህ ውብ አበባ አደይ አበባ ነህ ውብ አበባ›› እያሉ የሚዘምሩት። የቤተ ክርስቲያን አበባነት ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያንን አበባነት ሲመሰክር እንዲህ አለ፡- ‹‹ልዑለ ረሰዮ ለመሠረትኪ አረፋትኪ ዘመረግድ ደቂቅኪ ምሁራን በኀበ እግዚአብሔር…- የተለየሽ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሆይ መሠረትሽን ከፍ ከፍ አደረገው። ግድግዳዎችሽን በመረግድ በወርቀ ደማቸው። ልጆችሽ በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠኑ ናቸው። በምድረ በዳ እንዳለች የሱፍ አበባ ለጋ የሆነ የወይን አበባ ሽታን ትሸቻለሽ። የበረከትንም ፍሬ ታፈሪያለሽ››። ዳግመኛም በዚሁ በድጓ ዘጽጌው ‹‹ሐረገ ወይን እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕፁቂሃ እንተ በሥሉስ ትትገመድ ወታፈሪ ለነ አስካለ በረከት ሲሳዮሙ ለቅዱሳን – ሥሯ በምድር ጫፏ በሰማይ የሆነች በፈቃደ ሥላሴ ተገርዛ የምትለቀም የበረከት ፍሬን የምታፈራልን የወይን ሐረግ የተለየች ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ናት›› ይላል። ቤተ ክርስቲያን ‹‹ፍሬ›› የተባለ የክርስቶስን ሥጋ ወደሙን ዘወትር የምትሰጠን የማትረግፍ አበባ ናት። ብዙዎች ሊያረግፏትና ሊያጠወልጓት ለዘመናት ቢዘምቱባትም፣ ዲያቢሎስ ጦሩን ሁሉ ቢወረውርባትም፡ ልክ ለምለም አበባ በረጅም ሥሩ ውኃን ከመሬት እየሳበ የበለጠ እንደሚያብበው ‹‹የውኃ ግድግዳ የደም መሠረት›› እያልን የምንዘምርላት ቤተ ክርስቲያንም የበለጠ አበበች እንጂ አልጠወለገችም። አትጠወልግምም።
የእመቤታችን አበባነት ‹‹የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው›› ለተባለው ለእውነተኛው ፍሬ መገኛ የሆነችው እመቤታችን የማትረግፍና ዘወትር የምታብብ አበባ ናት። እመቤታችን በማይጠወልግና በለምለም ተክል መመሰሏ ነገረ ማርያምን ለተማረ ሰው አዲስ አይደለም። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው ያየው ምሥጢር ለእሳተ መለኮትና ለትሥብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው። ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ››። (ዘፀ. ፫፡፪)። እሳት ተዋሕዶት ያልጠወለገው ሐመልማል ለእመቤታችን ምሳሌ እንደ ሆነ ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሲያስረዳ ‹‹ጌታችን ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ከእርሷ ወደ ሰው ሕይወት የበራው የመለኮት ብርሃን ሐመልማሉን አላቃጠለውም። በተመሳሳይም በእርሷ ውስጥ ያለው የድንግልናዋ አበባም አምላክን በወለደችው ጊዜ አልረገፈም›› ይላል። ሌሎች እናቶች ሲያገቡና ሲወልዱ ጽጌ ድንግልናቸው ይወገዳል፤ የማትረግፈው አበባ ድንግል ማርያም ግን ወልዳም ጽጌድንግልናዋ አልተለወጠም። የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ እግዚአብሔር በእንቅልፍ ምክንያት የሠወረው አቤሜሌክ፡ ከቀጠፋት ከስልሳ ስድስት ዓመት በኋላ ሳትጠወልግና ሳትደርቅ ወተቷ ሲንጠባጠብ የተገኘችው የበለስ ቅጠል ምሳሌነቷ ለእመቤታችን እንደ ሆነ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አመሥጥረው ያስረዳሉ። (ተረ. ባሮ. ፫)። ይህች ቅጠል ተቀጥፋ ከስልሳ ስድስት ዓመታት በኋላም ከነ ልምላሜዋ መገኘቷ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና፣ ንጽሕናና ቅድስና የሚያሳይ ነው።
“የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው” ለተባለው ለእውነተኛው ፍሬ መገኛ የሆነችው እመቤታችን የማትረግፍና ዘወትር የምታብብ አበባ ናት። የካህኑ አሮን የደረቀ በትር መለምለሙም ለእመቤታችን ሌላው ምሳሌ ነው። ‹‹እንዲህም ሆነ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች››። (ዘኁ. ፲፯፡፰)። ይህም አስቀድመን እንዳየናቸው ምሳሌዎች ሁሉ መጠቀስ የሚችል ነው። ‹‹በሰላመ ገብርኤልን›› አዘውትሮ የሚጸልይና ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር የነበረው አንድ አስቴራስ የተባለ ዲያቆን ነበር። ይህም ዲያቆን ወደ ሩቅ አገር እየሔደ ሳለ ጨካኞች በመንገድ አገኙትና ገድለውት ሳይቀብሩት ከመንገድ ዳር ትተውት ሔዱ። ነገር ግን ሌሎች መንገደኞች ሲያልፉ አይተውት ከዚያው ከመንገዱ ዳር ቀብረውት ሔዱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በዚያ አቅራቢያ ባለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግል አንድ መልካም ዲያቆን እመቤታችን በራእይ ትገለጣለች። ጓደኞቹን አስተባብሮም የዲያቆን አስቴራስን አስከሬን ከመንገዱ ዳር በማውጣት በቤተ ክርስቲያን ግቢ እንዲቀብሩት ታዛቸዋለች። ዲያቆኑም እመቤታችን እንዳዘዘችው ሌሎች ዲያቆናትን ይዞ ወደ ቦታው በመጓዝ አስከሬኑን ቢያወጡት ርሔ እንደሚባል ሽቱ መዓዛው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ከአስከሬኑ የበቀለ የጽጌሬዳ አበባን አገኙ። በዚህም እየተደነቁ አስከሬኑን በክብር ገንዘውት በታዘዙት ሥፍራ ቀበሩት። ይህን የተአምረ ማርያም ታሪክ አባ ጽጌ ድንግል እንዲህ ተቀኝቶበታል፡- “ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ እምዐፅሙ፣ ለዘአምኀኪ ጽጌ ለገብርኤል ምስለ ሰላሙ፣ ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዓዛ ጣዕሙ፣ ለተዐምርኪ አሐሊ እሙ፣ ማሕሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ። ትርጉም፡- የክርስቶስ እናቱ የሆንሽ ድንግል ማርያም ሆይ መልአኩ ገብርኤል ደስ ይበልሽ እያለ ካቀረበልሽ ሰላምታ ጋር አበባን ይዞ እጅ ከነሣሽ ሰው ዐፅም የጽጌሬዳ አበባ በቅሎ ታየ ስለዚህም የተአምርሽ ዜና ባስደሰተኝ ጊዜ ስሙ ማኅሌተ ጽጌ የሚባል ምስጋናን አመሰግንሻለሁ። (ማኅሌተ ጽጌ) (ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል፣ የማሕሌተ ጽጌ ትርጉምና ታሪክ፣ ፳፻፬፣ ፳)፡፡
አንድ ሌላ የእመቤታችን ወዳጅ የሆነ ዲያቆንም እንዲሁ በግፍ ተገድሎ በተቀበረ በአራተኛ ቀኑ፡ በመቃብሩ ላይ ፈርከሊሳ የተባለ አበባ ይበቅላል። የአበባው ቅጠል ላይም ዲያቆኑ በሕይወት እያለ ዘወትር ይጸልየው የነበረው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› ጸሎት ተጽፎበት ተገኝቷል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በመልክአ ውዳሴው፡- ማርያም ጽጌ ዘትምዕዚ እምፈርከሊሳ፣ ይማዖ ጽድቀ ዚአኪ ለዘዚአየ አበሳ፣ ከመአራዊተ ይመውእ አንበሳ። ትርጉም፡- ፈርከሊሳ ከምትባል የሽቱ እንጨት መዓዛ ይልቅ አንበሳ አራዊትን እንደሚያሸንፍ ጽድቅሽ፣ መዓዛ ቅድስናሽ የኔን በደል ያጥፋው። (መልክአ ውዳሴ) በማሕሌተ ጽጌም ይህንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በማንሣት እመቤታችንንና ጌታችንን በአበባ እየመሰሉ ካህናቱና ምዕመናኑ ሲያመሰግኑ ያድራሉ። ማጠቃለያ፡- የዚህ ዓለም ሀብትና ጊዜ እንደ ጤዛ የሚረግፉ፣ እንደዚህ ዓለም አበባ የሚጠወልጉ ናቸው። የሰው ልጅ በዚህ ምድር ቢያዝን ኀዘኑ ዘላለማዊ አይደለም። ቢደሰትም የዚህ ምድር ደስታና ፈንጠዝያ የሚያልፍ ነው።
የሰው የጉብዝና ዘመንና የምድር ሕይወት እንኳን የሚረግፍ ነው። ነቢዩ የሰው ልጅን እንደ ሣር መጠውለግ ሲገልጽ ‹‹የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?›› ይላል። (ኢሳ.፶፩፡ ፲፪)። የሰው ልጅ ከሚጠወልግ ከዚህ ምድር ሕይወቱ ይልቅ ዘላለማዊውን የማይረግፍ ሕይወት ያገኝ ዘንድ ‹‹የማይረግፉ አበቦች›› ያልናቸውን ሊጠጋ ይገባዋል። የጌታችንን ሥጋውን ሊበላ ደሙን ሊጠጣ፣ ጌታችን ራስ ለሆነላት ለአካሉ ለቤተ ክርስቲያን ብልት ለመኾን ሊፋጠን፣ በእመቤታችን አማላጅነትና በመስቀሉ መማጸኛነት አምኖና ተመርኩዞ መንፈሳዊ ሕይወቱን ሊያበረታ ይገባዋል። ይህን በማድረግም ‹‹የክርስቶስ አበባ›› የተባለች ነፍሱን ከመጠውለግና ከመርገፍ ይታደጋታል። ‹‹ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ – የማትረግፍ አበባ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ የጠራት እመቤታችን ሁላችንንም ከመከራ ትጠብቀን። አሜን፡፡
ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!