“ጐልማሶች ሆይ፥ ክፉውን ድል ነሥታችሁታልና እጽፍላችኋለሁ” /፩ኛ ዮሐ. ፪፥. ፲፫/፡፡
በጥበበ ሲሎንዲስ
ቅዱስ ዮሐንስ “ጐልማሶች ሆይ፥ ክፉውን ድል ነሥታችሁታልና እጽፍላችኋለሁ” በማለት ክፉውን ዓለም ድል የነሡትን ጐልማሶች ያሞግሳቸዋል፡፡ ይህም በክፉ ዓለም እየኖሩ ክፉውን ማሸነፍ መንፈሳዊ ጥንካሬንና ድል መንሣትን ያመለክታል፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ‘በወጣትነት ዘመን ላይ እየኖሩ ቅዱስ መሆን እንዴት ይታሰባል? በዓለም እየኖሩ ጻድቅ መሆን እንዴት ይሞከራል?’ ይላሉ፡፡ ነገር ግን በክፉው ዓለም ኖረው ዓለምን ድል መንሣት እንደሚቻል ከጐልማሳው (ወጣቱ) ዮሴፍ ታሪክ እንማራለን፡፡
ዮሴፍ በገዛ ወንድሞቹ ተሸጦ፣ ከሀገሩ ከነዓን ርቆ በግብፅ ባርነት ሲኖር የመጣበትን ፈተና በመቋቋም ክፉን ድል ነሥቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፣ ‘አብረኸኝ ተኛ’ አለችው”(ዘፍ. ፴፱፥፯)፡፡ ልትይዘውም በሞከረች ጊዜ ዮሴፍ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” በማለት ልብሱን ጥሎላት እንደሸሸ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዘፍ. ፴፱፥፰-፱/፡፡
ዮሴፍ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል። የጲጥፋራ ሚስት ልትበቀለው ፈለገች። በመሆኑም ወዲያውኑ እየጮኸች አገልጋዮቹን መጣራት ጀመረች። ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረና እርሷ ስትጮኽ ሸሽቶ እንዳመለጠ ነገረቻቸው። ዮሴፍን ለመወንጀል ባሏ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን ይዛ ቆየች። ጲጥፋራ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ ያንኑ ውሸት ደግማ ተናገረች፤ ጲጥፋራ ይህን ባዕድ ሰው ወደ ቤት በማምጣቱ ለደረሰባት ነገር ተጠያቂው እርሱ እንደሆነ በተዘዋዋሪ ገለጸች። ጲጥፋራም ተቆጣ፡፡ ዮሴፍም ወደ ወኅኒ ተጣለ፡፡ የጲጥፋራ ሚስት አሳዛኝ ታሪክ እንዲህ ያለውን ክፋት አስከትሎአል፡፡
ዮሴፍ ግን ለራሱም፣ ለአለቃውም፣ ለፈጣሪውም የታመነ መሆኑን በተግባር አስመሠከረ፡፡ የዛሬ ወጣቶች ለምንሠራበት ተቋም፣ ለአለቃችን፣ ለጓደኛችን ታማኞች ነን? የአደራ ጥብቅነት ከሰማይ ርቀት ጋር ተነጻጽሮ በሚነገርበት ማኅበረሰብ መካከል አድገን ታማኞች መሆን አለመቻላችን ምክንያቱ ምን ይሆን? ዮሴፍ ዓለም በኃጢአት ስትፈትነው በወጥመዷ ላለመያዝ እግዚአብሔርን አስቧልና በሐሰት ወንጅለውና ወደ ወህኒ እንዲጣል አድርገው ለመከራ በዳረጉት ጊዜ እግዚአብሔር እርሱን አሰበው፡፡ ስደተኛው ዮሴፍ የግብፅ ሹመኛ ሆነ፡፡ እኛም “መንገዴንና አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፤ ኀጢአትም ሁሉ ድል አይንሳኝ፡፡” ብለን እንጸልይ /መዝ.፻፲፰፥፻፴፫/፡፡
የወጣትነት ዘመን የብርታት ዘመን ነው፡፡ አባቶቻችን ‘በወጣትነት የለቀሙትን እንጨት በስተርጅና ይሞቁታል’ ይላሉ፡፡ የወጣትነት ዕድሜ ሰው ሠርቶ ማግኘት፣ ወድቆ መነሣት የሚችልበት ወቅት ነው፡፡ “አንተ ጐበዝ፥ በጒብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጒብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ፥ ዐይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ ዕወቅ፡፡ ሕፃንነትና ጒብዝና፥ አለማወቅም ከንቱ ናቸውና ከልብህ ቊጣን አርቅ፥ ከሰውነትህም ክፉ ነገርን አስወግድ፡፡” እንዲል (መክ. ፲፩፥፱-፲)፡፡
ወጣትነት ብዙ ተስፋ ያለው የሕይወት ክፍል ነው፡፡ በአንድ ዕድል አለመሳካት እንደገና ከመሞከር አይቆጠብም፡፡ ወጣትነት ደስ ይላል፤ ሲያዩት ያምራል፡፡ ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ መዋቢያዎችን ባይጠቀሙም ወጣትነት ውበት ነው፡፡ ደግነትና ክፋት ግን ምርጫ ነው፡፡ ኃጢአትን የሚያስጥለን ዕድሜ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ራስን፣ ታሪክን፣ ሀገርን፣ ሕዝብን ለመለወጥ የሚያስፈልገው ትልቅ ዕድሜ ሳይሆን ትልቅ ልብ ነው፡፡ ዋናው ብዙ ዘመን መቆየታችን ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖራችን ነው፡፡ ባለን ጥቂት ዘመን ለዘመን የሚተርፍ፣ ለትውልድ የሚነገር ነገር መሥራት ይቻላል፡፡
ወጣትነት እንደ እሳት ብርቱ ነው፡፡ ይህ እሳት በአዎንታዊ መንገድ ሲገለጥ ተነሣሽነትን፣ ትኩስነትን፣ ባለ ራእይነትን ያመለክታል፡፡ ይህ እሳት በአሉታዊ መንገድ ሲገለጥ ደግሞ ቍጣን፣ ችኩልነትን፣ አለመታገሥን፣ ስሜታዊነትን፣ ንዴትን ማለትን ያመለክታል፡፡
እሳት በረከት እንደሆነ ጥፋትም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮች በአግባቡ ካልተያዙ የሚያጠፉት የጥቅማቸውን ያህል ነው፡፡ እሳት ሆነው ለመጡብን ውኃ ሆነን ማብረድ ይገባል፡፡ በሥጋ መሻት፣ በፍትወት ልብ ሲመጡብን በቅድስና፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር ማብረድና ወደ ንስሓ መጋበዝ ይገባናል፡፡ እሳትነታችን የሚያበስል እንጂ የሚያሳርር እንዳይሆን ውኃነታችንም የሚያመጣጥን እንጂ የሚያጠፋ እንዳይሆን መገምገም አለብን፡፡ “እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ” እንዲል (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፯)፡፡
በመጠን መኖር የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ጠባይ ነው፡፡ ይኸውም “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣህን ዐስብ” የሚለውን መመሪያ ለመጠበቅ ይጠቅማል (መክ.፲፪፥፩)፡፡ ፈጣሪው እግዚአብሔርን የሚያስብ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ሰው የሚከፋበትን አይናገርም፣ በሰዎች መካከል መለያየትን አይፈጥርም፣ ወላጆቹን አያሳዝንም፣ ጎረቤቶቹን አያውክም፣ ምስኪኖችን አያሳቅቅም፣ የሰዎችንም ክብር አይነካም፡፡
ልበ አምላክ ዳዊት “ጐልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል? ቃልህን በመጠበቅ ነው፡፡” በማለት እንደተናገረ (መዝ. ፻፲፰፥፱) ጐልማሶችን በቃለ እግዚአብሔር እንዲበረቱ ማስተማርና መንገድ መምራት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ንግግር ስለተማሩ፣ ገንዘብ አያያዝ ስላወቁ፣ የምስክር ወረቀት ስለያዙ ብቻ የሕይወት ብስለት አላቸው ማለት አይደለም፡፡ በታላላቅ ተቋማት ስለሠሩም ታላቅ ሆኑ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ታዋቂዎች ብቻ እንዲሆኑ ጥረት ከማድረግ ይልቅ አዋቂዎች እንዲሆኑ ማገዝ ይገባል፡፡ ለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ቃልም በእናንተ ዘንድ ጸንቶ ይኖራልና” በማለት እንደተናገረው ከሥጋዊ አስተሳሰብና ድርጊት ርቀው የእግዚአብሔርን ቃል የሕይወት መመሪያቸው አድርገው እንዲጓዙ መርዳት ያስፈልጋል፡፡
በልጅነታችን ጭቃ አቡክተን እንጫወት ነበር፡፡ በዚያም ደስ ይለን ነበር፡፡ ካደግን በኋላ ግን ጭቃን እንኳን በእጃችን ልንነካው በእግራችን ልንረግጠው እንጸየፈዋለን፡፡ ምክንያቱም ማደግ ያስገኘልን ዕውቀት ከጭቃ ከመቆሸሽ በቀር ምንም አይገኝም የሚል ነው፡፡ እንዲሁም በአእምሮ ሕፃን በነበርንበት ዘመን በኃጢአት ለመደሰት ሞክረናል፡፡ ተደልለንም አልፈናል፡፡ ለመንፈሳዊ አካለ መጠን ስንደርስ ግን ከኃጢአት ከመርከስ በቀር ምንም እንደማይገኝ ይገባናል፡፡ ደግሞም ኃጢአትን ልንተው የሚገባን ቅጣቱን ማለትም በሥጋ እስር ቤትን፣ በነፍስ ገሀነመ እሳትን ፈርተን ብቻ ሳይሆን የንጹሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ክቡር ፍጥረት ነኝ፣ የክርስቶስ ተከታይ ክርስቲያን ነኝ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ነኝ ብለን መሆን አለበት፡፡
በተረፈ ወጣቶች ሆይ! እናንተ ያወቃችሁት በዓለም ላይ ያለው ብቸኛ ዕውቀት አይደለምና፣ ደግሞም ዕውቀት በየዘመኑ ያድጋልና ሌሎችን ለመስማት ፈቃደኛ ሁኑ፡፡ እስከ ዘለዓለም የምንማር ነንና በሃያና በሠላሳ ዓመት ዕውቀትን ጠነቀቅናት ብላችሁ አታስቡ፡፡ በኃይል ሁሉን እቀይራለሁ ከሚል አስተሳሰብ ውጡ፡፡ ይህች ዓለም የወጣቶች ብቻ ሳትሆን የሕፃናትም፣ የጎልማሶችም፣ የአረጋውያንም ዓለም ናትና ለሌላው ዕድል ስጡ፡፡ ሕይወት ረጅም መንገድ እንጂ በአንድ ትንፋሽ የምትጠናቀቅ አይደለችምና በእርጋታና በማስተዋል መጓዝን አትርሱ፡፡ ያን ጊዜ “ጐልማሶች ሆይ፥ ክፉውን ድል ነሥታችሁታልና እጽፍላችኋለሁ” የሚለው መልእክተ ጽድቅ ይደርሳችኋል፤ የድል አክሊል ይዘጋጅላችኋል፤ የመንግሥተ ሰማያት በር ክፍት ይሆንላችኋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!