“ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል” (ዮሐ. ፫፥፯)
ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ በጥምቀት ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ እንደማይችል ባስረዳበት ትምህርቱ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የአይሁድ መምህር ቢሆንም ምሥጢሩን እያመሠጠረ የኦሪትን ትምህርት ቢያስተምርም ስለ ዳግም መወለድ ምሥጢር ተሠውሮበት ጌታችንን ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ እንመለከታለን፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሲመላለስ ኢአማንያንን በትምህርቱ ፣ የታመሙትን በተአምራት እየፈወሰ፣ አምስት እንጀራና ሁለት አሣን አበርክቶ የተራቡትን አጥግቦ፣ የተጠሙትን አጠጥቶ እንደመሻታቸው ፈጽሞላቸዋል፡፡ ነገር ግን አምላክ ሲሆን የአዳምን ሥጋ ለብሷልና ራሱን “የእግዚአብሔር ልጅ” እያለ ይጠራል በማለት አይሁድ በምቀኝነት ተነሥተው በየጊዜው ይፈትኑት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲሕ ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ዘመናት በሮማውያን በባርነት ቀንበር ስለ ተሰቃዩ ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ መሲሕ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ፣ ሠራዊት አስከትሎ እንደሆነ ነበር የሚያምኑት፡፡ ለዚህም ነው የክርስቶስን መሲሕነት ያልተቀበሉት፡፡
ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነው የኦሪት መምህሩ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሰው ለማሰብ የዐቢይን ጾም ሰባተኛ ሳምንት እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡
ኒቆዲሞስ ማነው?
ከአይሁድ መካከል ፈሪሳውያን ሕግን የሚያጠብቁ ቀሚሳቸውንም የሚያስረዝሙ፣ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑና ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ የሚያደርጉ፣ የአብርሃምን ሥራ ሳይሠሩ “አባታችን አብርሃም ነው” እያሉ የሚመጻደቁ ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢሆንም አለቃ እንዲሆን በሮማውያን የተሾመ ባለ ሥልጣን ነው፡፡
ኒቆዲሞስ ለአይሁድ መምህራቸው ሲሆን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቱን ሰምቶ፣ ተአምራቱን አይቶ በፍጹም ልቡ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ የተሠወረውን ይገልጥለት ዘንድ ለመማር ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ በፍጹም ልቡ ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ በቀን በብርሃን ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ለመማር የአይሁድን ክፋትና ተንኮልን ያውቃልና ይህንን ፍራቻ በጨለማ አምላኩን ፍለጋ መጥቷል፡፡ “መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለትም መስክሯል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፪)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኒቆዲሞስን ምስክርነት ሲሰማም “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” በማለት መልሶለታል፡፡ ኒቆዲሞስ ምሥጢሩ ቢረቅበትና መረዳት ቢሣነው “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” ሲል ጠይቋል፡፡ ጌታችንም የኒቆዲሞስን ጥያቄ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስላልሁህ አታድንቅ” በማለት ለእግዚአብሔር ምንም የሚሣነው ነገር እንደሌለና የኒቆዲሞስ አመጣጥ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ልደትን) ገለጸለት፡፡ (ዮሐ.፫፥፭-፯)
ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ጭ ብሎ ተምሯልና በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ “እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም” ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር ሲበታተኑ፣ ቀራንዮ ላይ የተገኘው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ጌታችን “ሁሉ ተፈጸመ” ብሎ ነፍሱን ከሥጋው ሲለይ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆነው የክርስቶስን ሥጋ ከአለቆች ለምነው በመገነዝ በአዲስ መቃብር ለመቅበር በቃ፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት “ኒቆዲሞስ” በማለት ታከብራለች፡፡(ማቴ.፳፮፥፴፩-፴፭፤ ዮሐ. ፲፱፥፴)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!