“ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ”(ዮና.፩፥6)
በእንዳለ ደምስስ
እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ከሌሎች ፍጥረታት አልቆ የፈጠረው የሰው ልጅ የተሠራለትን ሕግና ትእዛዝ በማፍረስ፣ ለእርሱ የተሻለውን፣ የተሰጠውን ትቶ የተከለከለውን በማድረጉ ወደቀ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የእጁ ሥራ የሆነው የሰው ልጅ(አዳም) ቢበድልም ዝም ብሎ አልተወውም፡፡ አዳም ንስሓ በገባ ጊዜ እግዚአብሔር የአዳምን ከልብ የመነጨ ጸጸትና ልቅሶ ተመልክቶ ራራለት፡፡ “አምስት ቀን ተኲል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ”(ቀሌ.፫፥፲፰-፲9) በማለት ስለ ፍጹም ፍቅሩ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡
የሰው ልጅ በደሉ እጅግ አስከፊ ቢሆንም ንስሓ ይገባ ዘንድ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃል፡፡ ከዚህም አልፎ ይታዘዙለት ዘንድ የመረጣቸውን የእግዚአብሔር ሰዎችን እያስነሣ በእነርሱ ላይ አድሮ በመገሰጽ ወደ ቀናው መንገድ ይመለሱ ዘንድ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጅ ያልበደለበት ጊዜ የለም፡፡ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በበዛ ቁጥር ደግሞ የሰው ልጆች በደልም እጅግ እየከፋ በመሄዱ እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ እሰከመጸጸት እንዳደረሰው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “እግዚአብሔርም የሰዎችን ክፉ ሥራ በምድር ላይ እንደበዛ የልባቸው ሐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ”(ዘፍ.6፥፭-6) እንዲል፡፡
በየዘመናቱ የሰዎች ኃጢአት እየከፋ፣ ከኃጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔር ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሊቃውንቱንና መምህራኑን ቢያስነሣም፣ እግዚአብሔርን በመፈታተናቸው ትዕግሥቱንም በማሳጣት ተቀስፈዋል፤ ምድር ተከፍታም ውጣቸዋለች፣ ለጠላቶቻቸውም አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡ “የኃጢአት ትርፍዋ ሞት ነውና” እንዲል(ሮሜ.6፥፳፫)፡፡ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙና እንደ ቃሉም የሚጓዙ ቅዱሳን እንዳሉ ሁሉ፣ ለጥፋት የሚፋጠኑ፣ ምድሪቱንም የሚያስጨንቁ ተነሥተው ያውቃሉ (የነነዌ ሰዎች)፡፡
እግዚአብሔር በየዘመናቱ ሰዎችን እያስነሣ በቅዱሳን አድሮ እየገሰጸ መንገዳቸውን እንዲያቀኑ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በነበረበት ዘመን እግዚአብሔር የሰዎችን ክፋት ተመልከቶ ነቢዩ አሳይያስን ይልከው ዘንድ ተገልጦለታል፡፡ መልአኩንም ልኮ አፉን በፍም ዳሰሰው፣ ኃጢአቱም ተወገደለት፡፡ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ፤ እኔም እነሆኝ ጌታዬ እኔን ላከኝ” አልሁ፡፡ በማለት ለእግዚአብሔር በቅንነት እንደታዘዘ እንመለከታለን፡፡ (ኢሳ.6፥6-9)፡፡
ነቢዩ ዮናስ ግን የነነዌ ሕዝብን በደል የተመለከተው እግዚአብሔር ሕዝቡን ይገስጽ ዘንድ በላከው ጊዜ ግን የነነዌ ሰዎችን ከበደላቸው ይመለሱና ንስሓ ይገቡ ዘንድ እንዲሰብክ(እንዲናገር) ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ትእዛዝ በመጣስ ሽሽቷል፡፡ ምክንያቱም የነነዌ ሰዎች ክፋት መብዛት፣ ልባቸው እንደደነደነና ለጩኸቱ ሁሉ በጎ ምላሽ እንደማይሰጡት በሰው ሰውኛ አስተሳሰብ በራሱ መዝኖ አይሳካልኝም በሚል ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰዎቹን ፈርቶ ሽሽትን ምርጫው አደረገ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ዘነጋ፡፡ “ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረ(ዮሐ.፲፥፭)፡፡ በራሱ ሐሳብና ፍላጎት ተመርቶ ከእግዚአብሔር ሸሽቶ ያመለጠ የለም፡፡ ዮናስ ይህንን እውነታ ባለመገንዘብ የነነዌ ሕዝብ ልቡ የደነደነ ነው፣ እኔ ብናገርም የሚሰማኝ የለም፣ አያምኑኝም በማለት ከእግዚአብሔር ያመለጠ መስሎት ወደ ተርሴስ ኮብልሏል፡፡
ብዙዎቻችን እግዚአብሔር የሚለንን ትተን በራሳችን ስሜትና ፍላጎት ተመርተን ኃጢአትን እንሠራለን፡፡ ለኃጢአታችን ሥርየትን ከመፈለግና ወደ እግዚአብሔር ከመጮህ ይልቅ ሰበብ እየፈለግን ያደረግነውን ክፉ ነገር ለመሰወር እንሯሯጣለን፡፡ የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታይ የተሸሸገ የለምና” አንዲል (ሉቃ.፲፪፥፪)፡፡ ከእግዚአብሔር ሸሽተን የት እንደርሳለን? ትእዛዙን ተላልፈንስ መጨረሻችን ምን ሊሆን ነው? ዮናስ የእግዚአብሔርን ድምጽ ከመስማትና ከመፈጸም ይልቅ ለራሱ ክብር ተጨነቀ፡፡ መኮብለል ምርጫው ሆነ፡፡
በእርግጥ የዮናስ ጭንቀት ሕዝቡም ከመበደል፣ እግዚአብሔርም ምሕረት ከማድረግ አይመለሱም፣ ተናግሬ ውሸታም ከምባል መኮብልል ይሻለኛል በሚል ከንቱ ሐሳብ ተመርቶ ተጓዘ፣ ግራና ቀኛቸውን ለይተው ስለማያውቁ ሕፃናትና እንስሳት ማሰብ ተሳነው፡፡ ወደ ተርሴስም ለመሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡
ዮናስ ከእግዚአብሔር ያመለጠ መስሎት ቢሄድም ያጋጠመው ነገር ግን ከባድ መከራ ነው፡፡ ተሳፈሪዎችንና ዮናስን ለመታደግ እግዚአብሔር ብዙ ዕድሎችን ለዮናስ ሰጥቶት ነበር ነገር ግን በመርከቡ ታችኛው ክፍል ገብቶ፣ ሐሳቡን ጥሎ እንቅልፍ ተኛ፡፡ ዐውሎ ነፋስም ተቀሰቀሰ፡፡ የመርከቡ አለቃና ተጓዦችም ተጨንቀው ዮናስን ከተኛበት በማስነሣት “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አሉት፡፡ ዕጣም ተጣጣሉ፣ ዕጣው በዮናስ ላይም ወደቀ፡፡
ከእግዚአብሔር ትእዛዝና ጥሪ አፈንግጦ ኮብልሏልና ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደደረሰባቸው የተረዳው ዮናስ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ” አላቸው፡፡ ዮናስ ዘግይቶም ቢሆን እግዚአብሔርን እንደበደለ፣ ከእርሱም ማምለጥ እንደማይቻል ሲረዳ በራሱ ላይ ፈረደ፡፡ ወደ ባሕሩም ጣሉት፡፡ እግዚአብሔርም ይሞት ዘንድ ፈቃዱ አይደለምና ዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አሳድሮታል፡፡ በመጨረሻም ነነዌ ላይ ዓሣ አንበሪው እንዲተፋው አደረገ፡፡ (ዮና.፩)፡፡
ነቢዩ ዮናስ የታዘዘውን ለመፈጸም ወደ ነነዌ ገብቶም ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ፣ ከእንስሳቱና ከሚያጠቡ ሕፃናት ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዋይታና በልቅሶ፣ በጾምና ጸሎት እንዲቆዩ ሰበከ፡፡ ከሰማይ ወርዶ ከሚበላቸው እሳት ዳኑ፡፡ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደታደገ እኛም በደላችንን እያሰብን፣ በጸጸትና በንስሓ ሆነን እግዚአብሔርን ብንለምን የለመንነው ሁሉ ይከናወንልናል፡፡ ዘመናችን እጅግ አስከፊ ነገሮች የምንሰማበት ጊዜ ቢሆንም ከኃጢአተኞች ጋር ከመተባበር ይልቅ ወደ እግዚአብሔር በተሰበረ ልብ መመልስ ይሻለናል፡፡ የነነዌ ሰዎችን ከኃጢአት እስራት ፈትቶ እንዳዳናቸው እኛንም ያድነናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!