የግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መርሐ ግብር ተካሄደ
በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ለመከለስ የግብአት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን አስመልክቶ ቅዳሜ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም በማኅበሩ ሥራ አመራር መሰብሰቢያ አዳራሽ ከባለ ድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ከፍተኛ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎችና ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን የተገኙ ሲሆን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አበበ በዳዳ የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት መከለስ ያስፈለገበትን መሠረታዊ ምክንያት በመተንተን ጉባኤውን አስጀምረዋል፡፡
አቶ አበበ የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ጉድለቶች በመተንተን የክለሳውን አስፈላጊነት ሲገልጹ፡- ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ዲጂታል ቴክኖሎጂን አለማካተቱ፣ ከተመደበው ጊዜና ቅደም ተከተል ጋር የተያያዙ ጉድለቶች መኖራቸው፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ተቋማዊ ለውጥ አስተሳሰቦች አንጻር፣ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርትና ሥልጠና የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉና ትግበራ መጀመሩ፣ የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ትግበራ መጀመር፣ ከሌሎችም ምክንያቶች አንጻር ተመዝኖ ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት መከለስ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት ያስችል ዘንድ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በክፍል ሁለት ዝግጅት ሥርዓተ ትምህርቱን በመከለስ ረገድ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የዘርፉ ምሁራን መካከል ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል “ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ላይ ተግባራዊ የሚደረገው የሥርዓተ ትምህርት ፍልስፍና” በሚል ዐቢይ ርእስ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ያቀረቡ ሲሆን፡፡ እነዚህም፡- የሥርዓተ ትምህርት ትኩረት፣ የመምህሩ ሚና፣ የትምህርት አሰጣጥ መንገዶችና የማስተማሪያ ዘዴዎች፣ እንዲሁም የምዘናና የግምገማ ሥርዓት እንዴት መሆን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
ዲ/ን አንዱአምላክ በክፍል ሦስት ገለጻቸውም በሥርዓተ ትምህርት ሊታሰቡ የሚገባቸው የግቢ ጉባኤያት ነባራዊ ሁኔታዎች /Theoritical Approach/ ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ማብራሪያቸው የሀገራችንን አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ታሳቢ ስለማድረግ፣ የተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ መለወጥ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተለየ አቀራረብ መኖሩ፣ የመደበኛ ትምህርት ነባራዊ ሁኔታዎች፣ የተማሪዎች አስተዳደርና ሃይማኖታዊ ግንዛቤ፣ የሀገሪቱ ውጥረትና ፖለቲካዊ የሥልጠና ፖሊሲዎች አለመረጋጋት፣ … እንዲሁም ሌሎች ነጥቦችን አንሥተው ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የክፍል አራት ገለጻው ደግሞን ከፍተኛ የትምህርት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሀብቴ “የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጭብጦች /Thematic Areas/” በሚል ርእስ ላይ ያቀረቡ ሲሆን ከሥርዓተ ትምህርቱ ይዘት፣ ከመምህራን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ የሥርዓተ ትምህርቱ አቀራረብ፣ ምዘናና ሠርቲፊኬሽን ሂደት፣ የተማሪዎች ዳራ፣ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም የነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ግምገማና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድረገው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም በክፍል አምስት ላይ “የሥርዓተ ትምህርቱ የመማር ብቃቶች” በሚል ርእስ ባቀረቡት ማብራሪያ፡- ዶግማዊ የመማር ብቃት፣ ፖለቲካዊ የመማር ብቃት፣ ኢኮኖሚያዊ የመማር ብቃት፣ ማኅበራዊ የመማር ብቃትን ሌሎችንም ጉዳዮች አንሥተዋል፡፡
ቀጥሎም በሁለቱ የትምህርት ባለሙያዎች የቀረቡትን ዝርዝር ነጥቦች መነሻ በማድረግ በአራት መሠረታዊ የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች ማለትም፡- ለተማሪዎች ምን ምን ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች እናስተምራቸው? የትምህርት አቀራረቡ በምን መልኩ ይሁን? የማኅበረ ቅዱሳን የመምህራን ትምህርት ሥልጠና በተሻለ ሁኔታ እንዴት ይቅረብ? የምዘናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም ከታዳሚው የቀረቡትን አስተያየቶች በመቀበል ጠቃሚ ግብአቶችን እንዳገኙና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ነጥቦችን በመለየት እንደሚሠሩ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎቹ በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ ለግቢ ጉባኤት ተማሪዎች የሚሆን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ተግባራዊ ያደረገው በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ሲሆን ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሥርዓተ ትምህርቱን የበለጠ ውጤታማና ዘመኑን የዋጀ አድርጎ ለማቅረብ አሁን እየተሠራበት ያለውን ሥርዓተ ትምህርት በ፳፻፪ ዓ.ም ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!