የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ስለ ተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት ስለሚነገርበት “ቅዱስ ሳምንት” ይባላል፡፡ በተጨማሪም “የመጨረሻ ሳምንት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመኾኑ ነው፡፡
በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ግብረ ሕማማት መጽሐፍ እንዲሁም ከሌሎች ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ባዘጋጀው መዝሙር ያመሰግናሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡
ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡
ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ መኾኑ ይነገራል፡፡“ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም”
ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ. ፶፫፥፬-፲፪)፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መኾኑን በማሰብ፤ ከማንኛውም የሥጋ ሥራ በመታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር ሰሙነ ሕማማትን እናከብራለን፡፡ ብድራትን የማያስቀረው አምላካችን እግዚአብሔር መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎናልና፡፡
በሕማማት ሳምንት ውስጥ ከሚገኙት ዕለታት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (ሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሰኞ
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አንደኛ፡- ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ፡- ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡
ፍሬ ያልተገኘባት ዕፀ በለስን ረግሟል፡–
በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ “በማግሥቱ ተራበ” የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም” ይላል(ኢሳ.፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበር፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፡-“የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው” ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?
ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ “ተራበ” ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በርግጥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባር ፍሬ የፈለገ መኾኑን ለማጠየቅ“ተራበ” ተባለ፡፡
“በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ” እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› ብሏል፡፡
እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ ርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ “አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሦኩሰ
ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው” ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ እርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል “ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ይለናልና እግዚአብሔር
ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡“የሰው ልጅ
ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?” ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡
የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከቤተ መቅደስ አስወጥቷል፡-
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ አይሁድ የጸሎት ቤት የሆነውን ቤተ መቅደሱ የገበያ አደባባይ አድርገውት አገኘ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አይሁድ ያደረጉትን የማይገባ ሥራ ያስወግድ ዘንድ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ አስወጣ፡፡ “በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ፣ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” እንዲል(ማቴ.፳፩፥፲፪-፲፫)፡፡
ማክሰኞ
በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ “የትምህርት ቀን” ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማር. ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ ሉቃ. ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰)፡፡
በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑም ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲሆኑ፣ ጥያቄውም፡- “በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ?
ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?” የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን መድድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀናቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡
ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን “በራሴ ሥልጣን” ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡ ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ “የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው
ወይስ ከምድር?” ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም “ከሰማይ ነው” ቢሉት” ለምን አላመናችሁበትም?” እንዳይላቸው፤”ከሰው ነው” ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ “ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም “እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡
ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች “ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?” በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት “ዓለም የሚወደው የገዛ
ወገኑን ነው” የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ረቡዕ
በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፡-
አንደኛ፡- የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤ ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡ ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡
ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር “ምን ትሰጡኛላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” በማለት ጌታችንን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል (ማቴ.፳፮፥፲፭)፡፡
የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ አሰምቶ ነበር፡፡
“ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” በማለት ያቀረበው አሳብ“አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች” እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮)፡፡
የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ሁሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡
ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን ርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ “ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው” ተብሎ እንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው “ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?” ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡
ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም ብቻ በመያዝ እምነታቸውን፣ በገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳውያን ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡– ስምዐ ተዋሕዶ ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!