ዕቅድ ከክንውን የተስማሙለት ግቢ ጉባኤ
በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
ጊዜው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ሲሆን በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎቹ ሰፊ የሆነ መርሐ ግብር እና የመሰበሰቢያ አዳራሽ ስለሌላቸው መርሐ ግብራቸውን ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው፣ ዛሬ አዳራሹ ተሠርቶ ከሚገኝበት ቦታ በነበሩ ዛፎች ጥላ ሥር ያካሒዱ ነበር፡፡ ይህን የተቀደሰ ተግባር በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ያበረታታ፤ ይደግፍ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሲፈቅድ፤ የተማሪዎቹና የማእከሉ ጥረት ተሳክቶ ተቋሙ ከተመሠረተ ከስድስት ወር በኋላ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተብሎ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት መዋቅር ውስጥ ታቅፎ የካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም አገልግሎቱን በተጠናከረ መንገድ ጀመረ፡፡ በምሥረታው ዕለት በተቋሙ ከሚገኙ ፯፻፷ ተማሪዎች መካከል ፭፻፴፮ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ፳፻፣ በ፳፻፩ እና በ፳፻፪ ዓ.ም ተማሪዎችን የመቀበል ዐቅሙ እያሳዳደገ በመሔዱ፣ ግቢ ጉባኤውም አገልግሎቱን አሰፋ፤ በተለይ የቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ተቋሙ ሲቀበል የግቢ ጉባኤው አገልግሎት ይበልጥ እየጎለበት መጣ፡፡
ከባህር ዳር እና ከጎንደር ዪኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤያት የመርሐ ግብራትን ተሞክሮዎች በመውሰድ የአገልግሎት አድማሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ የሔደው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ዛሬ ላይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ተማሪዎችን በዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ዐቅፎ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ግቢ ጉባኤው ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም ለአዲስ ተማሪዎችና ለነባር ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መርሐ ግብር ባዘጋጀበት ወቅት በመርሐ ግብሩ ላይ የጉባኤ ቃና ዘገቢዎች በመገኘት፣ ስለግቢ ጉባኤው አጠቃላይ አገልግሎት የሚከተለውን በመዘገብ ለመጽሔቷ ዕድምተኞች ተዘክሮ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
በግቢው የሚካሔዱት መርሐ ግብራት ከዓመት ዓመት እየተሻሻሉና ተማሪዎች በደንብ እየተሳተፉባቸው የሚገኙ ሲሆኑ፣ የመርሐ ግብራቱን ዕቅድ በማዘጋጀትም የግቢው ተማሪዎች ጥሩ ልምድ አላቸው፡፡ ለሌሎች ግቢ ጉባኤያትም ተሞክሯቸው ይጠቅማል በማለት እንደሚከተለው ስናቀርብ ለዝግጅቱ መሳካት የረዱንን የግቢ ጉባኤውን ሥራ አስፈጻሚዎች አስቀድመን በማመስገን ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ እንደሌሎቹ ግቢ ጉባኤያት ሁሉ በአጥቢያው አብያተ ክርስቲያናት የተማሪዎችን መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ከመጠበቅ አንጻር ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራትን ያከናውናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ግቢ ጉባኤው የተማሪዎች መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታቸው ተጠብቆ ብቁ ዜጋ መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ከሚያካሒዳቸው መርሐ ግብራት መካከል የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
፩. የኮርስ መርሐ ግብር
ግቢ ጉባኤው ለኮርስ መርሐ ግብር ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ከአንደኛ ዓመት እስከ አምስተኛ ዓመት የሚገኙ ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤው ሥር አቅፎ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርት ያስተምራል፡፡ ግቢ ጉባኤው ተማሪዎቹ በሚመቻቸው ሁኔታ የኮርስ መርሐ ግብራትን ይከታተሉ ዘንድ “Modular and non Modular” በሚሉ የማስተማሪያ ዘዴዎች ትምህርቱን ይደግፋል፡፡
በግቢው ከአንደኛ ዓመት እስከ ሦስተኛ ዓመት የሚገኙ ተማሪዎች ብዛታቸው ከሁለት አዳራሽ በላይ በመሆኑ ከአዳራሽ ውጭ በፀሐይና በዝናብ እየተመቱ የሚማሩ ሲሆን የዐራተኛና የአምስተኛ ዓመት ተማሪዎች ደግሞ በአንድ ላይ መርሐ ግብራቸውን ያከናውናሉ፡፡
፪. የአብነት ትምህርት
ከግቢው ምሥረታ ጋር ተያይዞ ከሚነሡ አገልግሎቶች አንዱ የአብነት ትምህርት ሲሆን፤ አገልግሎቱን ቀደም ብለው የጀመሩት የእንድማጣ ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መምህር ናቸው፡፡ ግቢ ጉባኤውም የተማሪዎችን ፍላጎት በመመልከት ከእንደማጣ ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተጨማሪ በግቢው የሚገኙ መሪጌቶችንና ዲያቆናትን በማስተባበር ተማሪዎች በሚኖራቸው ትርፍ ጊዜ የአብነት ትምህርት ይማሩ ዘንድ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡
ከ፬፻ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በግቢ ጉባኤው ታቅፈው ከዘወትር ጸሎት እስከ መጻሕፍት ይማራሉ፡፡ ከተማሪው ብዛትና ለእያንዳንዱ ተማሪ መምህር መመደብ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሣ አንዱ ተማሪ ሌላውን ተማሪ በማስቀጸል ይማማራሉ፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባለው ጊዜ ጠዋት ከ፲፪ ሰዓት እስከ ፩ ሰዓት ነው፡፡ ተማሪው ለአብነት ትምህርት ካለው ከፍተኛ የመማር ፍላጎት የተነሣ በግቢው ከነበሩ የቅዳሴና የዜማ መምህራን ተጨማሪ የቅኔና የሐዲስ ኪዳን መምህራንን ግቢ ጉባኤው በ፳፻፭ ዓ.ም በመደበኛነት መድቦ አገልግሎቱን ይበልጥ ይደግፋል፡፡
እኛም ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም በግቢ ጉባኤው አዳራሽ ከጠዋቱ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ተገኝተን በነበረበት ወቅት በቁጥር ከ፬፻ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በቡድን ሆነው ንባብ፣ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ዜማና ቅኔ ሲማሩ ተመልክተን ከተወሰኑ ተማሪዎች ጋር ቃለ መጠይቅ አደረግን፡፡
“ቅኔ ማወቅ የምንጸልየውን ጸሎት በይበልጥ እንድንረዳ ያስችለናል” በማለት የነገረችን ጠጄ ጣዕሙ ስትሆን ጠጄ የአምስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ ናት፡፡ ጠጄ የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃንና ሌሎች የአብነት ትምህርትን በሚገባ ተምራ አጠናቃለች፡፡
ጠጄ አባቴና ወንድሞቼ በግእዝ ቋንቋ ሲነጋገሩ፤ እኔንም በግእዝ ቋንቋ ሲያናግሩኝ ቋንቋውን በደንብ ካለመረዳቴ የተነሣ ከፍተኛ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኝ ነበር፡፡ ምኞቴንም በግቢ ጉባኤው በሚሰጠው የቅኔ ትምህርት በመግባት ለማሳካት እየሞከርኩ ነው፡፡ በቅኔ ቤት ሴት ወንድ የሚባል ነገር የለም፡፡ በመሆኑም እኅቶቼ እንደ እኔ ቅኔ ቢማሩ ይጠቀማሉ በማለት ነግራናለች፡፡
የቅኔ ምሽት
በሀገራች ተዘውተረው ከሚነሡ የቅኔ መፍለቂያ ቦታዎች መካካል ጎጃም አንዱና ተቀዳሚው ሥፍራ ነው፡፡ በጎጃም ስመጥር የቅኔ ሊቃውንት የፈለቁባቸውና የሚፈልቁባቸው የቅኔ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤም በዚሁ ክልል እንደመገኘቱ መጠን ለቅኔ ትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በግቢ ጉባኤው የቅኔ ትምህርት ከመሰጠቱ በተጨማሪ የቅኔ ምሽት ይካሔዳል፡፡ መርሐ ግብሩ በትምህርት ክፍል አማካይነት የሚከናወን ሲሆን ክፍሉም መርሐ ግብሩን ለማከናወን ቅድመ ጥናት ይደረጋል፡፡
ትምህርት ክፍሉ ይህን ጥናት የሚያካሒደው በግቢው ምን ያህል የቅኔ መምህራን ይገኛሉ? ምን ያህል ቅኔ አዋቂ መሪጌቶች አሉ? ቅኔ በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ምን ያህል ይሆናሉ? የሚሉትን ያጠናል፤ “በዕለቱ አጃቢ መርሐ ግብራት ምን ምን ቢቀርቡ መልካም ነው” በሚለው ጉዳይ ላይ ይወያያል፡፡
የቅኔ ምሽት መርሐ ግብሩ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ የሚካሔድ ሲሆን፣ በተለይ ግንቦት ፲፩ ቀን የሚከናወነው የቅኔ መርሐ ግብር ልዩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዕለቱ በቅኔ መምህራንና በግቢ ጉባኤው ተማሪዎች ቅኔ ይቀርባል፤ ትምህርት ይሰጣል፣ ሥነ ጽሑፍ፣ መዝሙር … ይቀርባሉ፡፡
ክረምትን በአብነት ትምህርት
የደብረ ማርቆስ ግቢ ጉባኤን ለየት ከሚያደርጉት መርሐ ግብራት አንዱ የክረምት አብነት ትምህርት ነው፡፡ ግቢው በክረምት ወቅት የአብነት ትምህርት መማር ለሚፈልጉ ተማሪዎች አስፈላጊውን ነገሮች ያመቻቻል፤ ሙሉ ወጭያቸውንም (ለምግብ፣ ለመኝታና ለጤናና ለልዩ ልዩ ቁሳቁሶች) ይሸፍናል፡፡ ዳቦ በማኮሸር ከግቢው ውጭ ለሚገኙ የአብነት ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚያደርገው ሁሉ በክረምት ለሚማሩ የግቢ ጉባኤው ተማሪዎችም ለምግብነት እንዲጠቀሙበት ያደርጋል፡፡ ለአብነት ያህል በ፳፻፭ ዓ.ም ፵፪ ተማሪዎችን፤ በ፳፻፮ ዓ.ም ደግሞ ፶፫ ተማሪዎችን እንዲማሩ አድርጓል፡፡
በአብነት ትምህርት ቤቶች ሁል ጊዜ የሚደርሰው የውዳሴ ማርያም የጸሎት ሥርዓት በግቢ ጉባኤው በዜማ ከዓመት እስከ ዓመት ሳይቋረጥ ይደረሳል፡፡ ይህም ለጉባኤው መስፋፋት እንደረዳ ሥራ አስፈጻሚዎቹ ይናገራሉ፡፡
ግቢ ጉባኤው በአብነት ትምህርት ዙሪያ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት የዐራቱ ጉባኤ ቤት መመሥረት ዕቅዱ ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ውጭ ባላቸው ጊዜ የአብነት ትምህርት ተምረው ማስመስከር የሚችሉበትን መንገድ እያመቻቸ ነው፡፡
፫. ጸሎት
ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” (፩ኛ ተሰ ፭፥፲፯) በማለት እንዳስተማረው ግቢ ጉባኤው የአባላቱን መንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚደግፈው በዋነኛነት በጸሎት ነው፡፡ ለዚህም በግቢው ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዓመቱ ፍጻሜ ድረስ የተለመዱ የጸሎት ቀናትና ሰዓታት አሉ፡፡
በጸሎት ሕይወት አብነት ለመሆን የግቢው የጸሎት ሥርዓት ሁል ጊዜ የሚጀመረው በሥራ አስፈጻሚዎች ሲሆን ሥራ አስፈጻሚዎች ከተማሪው ቀደም በማለት የጸሎት መርሐ ግብር በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለአንድ ሱባኤ ያደርጋሉ፡፡ በሱባኤው ወቅት ሁሉም ሥራ አስፈጻሚዎች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የሥራ አስፈጻሚዎች የአንድነት ጸሎት በአገልግሎታቸው ሁልጊዜ እግዚአብሔር ይቀድም ዘንድ በሳምንት አንድ ቀን(ረቡዕ) ዓመቱን በሙሉ ያካሔዳሉ፡፡
ሁሉም ተማሪዎች ወደሚሳተፉበት የጸሎት መርሐ ግብራት ስንመለስ በማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ከሚደረጉት የጸሎት መርሐ ግብራት አንዱ የአርብ ሠርክ ጸሎት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን የጸሎት ሥርዓት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችም በየግቢያቸው እየተገበሩት ሲሆን፤ በደብረ ማርቆስ ግቢ ጉባኤም በዕለተ አርብ ከማለዳው ፲፩ እስከ ፲፪ ሰዓት ይካሔዳል፡፡ በጸሎት መርሐ ግብሩ ላይ የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ መዝሙረ ዳዊት፣ የነቢያት ጸሎት እንዲሁም በዜማ መሐረነ አብና እግዚኦ መሐርነ ክርስቶስ ይደርሳሉ፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህ ጊዜያት የግቢው ተማሪዎች ከምን ጊዜውም በላይ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለመበርታት ቆርጠው የሚነሡባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡ የጸሎቱ ሥርዓት በግቢው እንደሚደርሰው የአርብ ጸሎት ዓይነት ሲሆን፣ ከሰዓት አንጻር ግን መሐረነ አብ በዜማ አይደርስም፡፡ በዓቢይ ጾም ወቅት ግን ከሌሎች የአጽዋማት ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ከበዓላት ውጭ “እግዚኦ መሐርነ ክርስቶስ” ሲባል በስግደት ነው፡፡ ወቅቱን ብዙዎች በናፍቆት የሚጠብቁት ከመሆኑ አንጻር በተማሪው ገጽታ ላይ መንፈሳዊ ደስታ የሚነበብበት ነው፡፡ በዕለተ እሁድ እንኳ ምህላው እንዳይቋረጥ ከመጠንቀቅ አንጻር ተማሪዎቹ ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ጸሎቱን አድርሰው ወደ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ይሔዳሉ፡፡
ግቢ ጉባኤው ከላይ ከተመለከትናቸው የጸሎት መርሐ ግብራት በተጨማሪ በምድራዊ ፈተናዎች ወቅት ከአንድ እስከ ሁለት ሱባኤዎችን ይይዛሉ፡፡ በግቢው ተማሪዎቹ ከሚያከናውኗቸው የጸሎት መርሐ ግብራት በተጨማሪ ግቢ ጉባኤው ለገዳማት መባ በመላክ ግቢውን በጸሎት ያሳስባል፡፡
፬. በዓላት
የእመቤታችን የልደት ቀን
በግቢ ጉባኤው በደመቀ ሁኔታ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የእመቤታችን ልደት ግንቦት አንድ ቀን ነው፡፡ ግቢ ጉባኤው ግንቦት አንድ ቀንን የእመቤታችን ልደትና የማኅበረ ቅዱሳን የምሥረታን በዓል አያይዞ፤ ንፍሮ በማንፈር በዓሉን በእንድማጣ ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ በቃለ እግዚአብሔር ያከብራል፡፡ በዕለቱ ተማሪው ከዕለቱ በዓል በተጨማሪ ስለማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረትና አገልግሎት ይበልጥ እንዲረዳ ከማድረግ አንጻር፣ ግቢው ስለማኅበረ ቅዱሳን ማንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ያካሒዳል፡፡
በዕለቱ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት የሚቀርቡ ሲሆን ተመራቂ ተማሪዎች ተሞክሯቸውንና የሕይወት ልምዳቸውን ያካፍላሉ፡፡ በተለይ ተመራቂ ተማሪዎች ዕለቱን ከመናፈቃቸው የተነሣ “እግዚአብሔር ቢያደርሰን ለግቢው ይህን አደርጋለሁ” በማለት በሰፊው ይሳላሉ፡፡ የስለት መርሐ ግብሩ “ቢያደርሰን” በማለት የሚጠራ ሲሆን “እግዚአብሔር በሚቀጥለው ዓመት ቢያደርሰን ይህን እንሠራለን” በማለት ተማሪዎች ስለት የሚገቡበት መርሐ ግብር ነው፡፡ ከግቢው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተን በዕለቱ በማደሪያ ክፍሉ የሚቀር ተማሪ ያለ አይመስልም፡፡
“የቢያደርሰን” መርሐ ግብር በአባላት ጉዳይ አማካይነት የሚዘጋጅ ሲሆን፣ አባላት ጉዳይ የስለት ቅጽ አዘጋጅቶ ለተማሪው ያደርሳል፡፡ ተማሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከ፩፻፻ በላይ ተማሪዎች ይሳላሉ፡፡
ትንሣኤና ልደት
በግቢው ከሚከበሩ በዓላት መካከል የትንሣኤና የልደት በዓላት በቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ በዓላት ዕለት ብዙ ተማሪዎች ከአርብና ቅዳሜ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ግቢውም ይህን በዓል በተሳካ ሁኔታ ለማክበር ያስችለው ዘንድ አክፋይ የሆኑ ተማሪዎች ለነዳያን እንዲያዋጡ ያደርጋል፡፡ በዚህም ዳቦም ሆነ እንጀራ ለነዳያን የሚታደልበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ ግቢ ጉባኤው ከተማሪው የሚያገኘውን በሁለት መልኩ ለነዳያን ያደርሳል፡፡
የመጀመሪያው ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም፣ ቅዱስ ሚካኤል ፣ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እና ከእንድማጣ ገነተ ኢየሱስ ሰንበት ትምህር ቤት ተማሪዎች ጋር በመቀናጀት ለነዳያን በመስጠት የሚፈጸም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ግቢ ጉባኤው ከነዳያን ጋር በዓሉን በጋራ በማክበር ነው፡፡
ግቢ ጉባኤው ነዳያንን ለማስፈሰክ ቀደም ብሎ ለነዳያን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላልፋል፡፡ በእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ወቅትም ግቢ ጉባኤው በበዓሉ ዕለት በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ከነዳያን ጋር በዓሉን እንደሚያከብር ያስታውቃል፡፡ ተማሪዎችም በተግባር ቤት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆነ የምግብ ዝግጅት ከሌሊት ጀምረው ያዘጋጃሉ፡፡ በበዓሉ ዕለትም ከሁለት ሰዓት ጀምሮ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከነዳያን ጋር በመዝሙርና በቃለ እግዚአብሔር ያከብራሉ፡፡
የግቢው ተማሪዎች ደግሞ በዓሉን ሌሊት ከቅዳሴ መልስ በግቢው አዳራሽ በመገኘት የሚያከብሩ ሲሆን ቅዳሴው እንዳበቃ ተማሪዎቹ በሙሉ በግቢ ጉባኤው አዳራሽ በመገኘት በተልባና በመክፈልት ጾማቸውን ይፈስካሉ፤ እስከ ማለዳው ፲፩ ሰዓት በመዝሙርና በቃለ እግዚአብሔር በአዳራሹ ይቆያሉ፡፡ ፲፩ ሰዓት ላይ የተቋሙ ካፌ ሲከፈት ተቋሙ ያዘጋጀውን ምግብ ተመግበው በማደሪያ ክፍላቸው እስከ ከሰዓቱ መርሐ ግብር አርፈው ይውላሉ፡፡ የከሰዓቱ መርሐ ግብር ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ዐሥራ አንድ ሰዓት የሚከናወን ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ስብከት፣ መዝሙርና ቅኔ ይቀርባል፡፡ በዓሉን ለማድመቅም ፈንዲሻና ዳቦ ይቀርባል፡፡
ሌላው በግቢው ከሚከበሩ በዓላት መካከል የደብረ ዘይት በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡ ዕለቱ ስለ ነገረ ምጽአት በሰፊው የሚነገርበት የአንድነት ጉባኤ ነው፡፡ በመርሐ ግብሩ የግቢው የንስሐ አባቶች ሁሉም ይገኛሉ፡፡ ለአባቶች የምሳ ግብዣ በማድረግ እና ስለወደፊቱ አገልግሎት ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ መርሐ ግበሩ ይጠናቀቃል፡፡
፭. የጉዞ መርሐ ግብራት
ግቢ ጉባኤው የተማሪውን መንፋሳዊ ሕይወት ከመገንባት አንጻር በተለያዩ ጊዜያት መንፈሳዊ ጉዞዎችን ወደ አድባራት፣ ገዳማትና ገጠር አብያተ ክርስቲያናት ያካሒዳል፡፡ ግቢው ለጉዞ መሳካት ይረዳ ዘንድ ጉዞው ከማካሔዱ በፊት ቅድመ ጥናት ያደርጋል፤ በጉዞው ዕለትም ትምህርት የሚሰጥበትን መንገድ ያመቻቻል፤ በወቅታዊ ጉዳዮችና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራትን በማቅረብ ተማሪው እንዲሳተፍ ያደርጋል፡፡
ረዥም ጉዞዎች፡- ከደብረ ማርቆስ ከተማ ራቅ ብለው በሚገኙ አድባራትና ገዳማት የሚደረጉ ናቸው፡፡ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ ደብረ ኤልያስ፣ ዲማ ጊዮርጊስና መርጡለ ማርያም ቀደም ባሉት ጊዜያት ተማሪዎቹ ጉዞ ያደረጉባቸው ቅዱሳት መካናት ሲሆኑ ጉዞው ረዥም ከመሆኑ አንጻር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ይከናወናል፡፡
፮. የጽዋ መርሐ ግብራት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ፈለግ ተከትላ የጽዋ መርሐ ግብራትን ልጆችዋ በፍቅር ተሰባስበው ይጠጡ ዘንድ ታስተምራለች፡፡ ልጆችዋም በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በመላእክትና በቅዱሳን ስም በመሰባሰብ ጽዋ ይጠጣሉ፡፡ የደብረ ማርቆስ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ፈለግ ተከትለው በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤልና በአቡነ ተክለሃይማኖት ስም ጽዋ የሚጠጡ ሲሆን መርሐ ግብራቸውንም በእንድማጣ ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ያካሒዳሉ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ መርሐ ግብራት ዙሪያ ያዘጋጀነውን ዝግጅት በዚሁ አጠቃልልን፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-ጉባኤ ቃና