ወርኀ ጳጉሜን
የዘመናት ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ ጨለማንና ብርሃንን እያፈራረቀ፣ ቀናትን በቀናት እየተካ፣ ሳምንታት፣ ወራት፣ ዓመታት፣… በማፈራረቅ ከዘመን ዘመን እንሸጋገራለን፡፡ አንዱ ሲያልፍ ሌላው እየተተካ እንደ በደላችን ሳይሆን እንደ አምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት መሸጋገራችንን ቅዱስ ዳዊት “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፣ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ” በማለት ገልጾታል /መዝ.፷፬፥፲፩/፡፡
እንደ ቅድስት ኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ፲፫ ወራት ይፈራረቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጳጉሜን ወር (አምስቱን ቀናት ወይም ስድስት ቀናት በአራት ዓመት) ፲፫ኛው ወር አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡
የጳጉሜን ትርጒም አስመልክቶ ደስታ ተክለ ወልድ ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በሚለው መጽሐፋቸው “ጳጉሜን የወር ስም፣ ዐሥራ ሦስተኛ ወር፣ ተረፈ ዓመት፣ በነሐሴ መጨረሻ በሦስት ዓመት አምስት አምስት፤ በዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት የሚሆን ሲሆን፤ ትርጓሜውም ጭማሪ ማለት ነው፡፡” (ገጽ ፲፪፻፳፰) በማለት ይፈቱታል፡፡
በዚህ ወር ጳጉሜን ሦስት ቀን ቤተ ክርስቲያን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ሢመትን ታከብራለች፡፡
እንዲሁም በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በእርሱ ስም ከደሴት ላይ የተሠራችውን ቤተ ክርስቲያን ዓሣ አንበሪ ሊገለባብጣት፣ ሕዝቡንም ሊያጠፋቸው ሲል በቅዱስ ሩፋኤል ጸሎት፣ ምልጃና ተራዳኢነት በእግዚአብሔርም ቸርነት እንደተረፉ በድርሳነ ሩፋኤል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለሆነም ይህ ወር የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል የሚከበርበት መሆኑን ያስታውሰናል፡፡
በወርኀ ጳጉሜን ሰዎች የፈቃድ ጾም ይጾማሉ፣ ጠበል ይጠመቃሉ፡፡ ጾሙን የሚጾሙበት ምክንያት በዮዲት ጾም እስራኤላውያን ከጦርነት፣ ከመከራ የዳኑበትን ምክንያት በማድረግ ጾመውታልና ዛሬ ደግሞ የሚጾሙት አዲሱን ዓመት የሰላም እንዲያደርግላቸው ነው፡፡ ዮዲት ከ፮፻፭ እስከ ፭፻፷፪ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በባቢሎን በከለዳውያን የነገሠው ናቡከደነፆር የተባለው ኃያል ንጉሥ በነበረበት ዘመን የተገኘችና ሕዝበ እስራኤልን በቅኝ እንዳይገዛ ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱንም እንዳያጠፋ ትልቅ ተጋድሎ የፈጸመች እስራኤላዊት ሴት ነች፡፡
እግዚአብሔር በቸርነቱ መፍትሔ ይሰጣቸው ዘንድ በጾም፣ በጸሎት፣ በልቅሶም ልመናዋን አቀረበች፡፡ እግዚአብሔርም የመፍትሔውን አቅጣጫ አመለከታት፡፡ ለጦርነት የወጣውንም የናቡከደነፆር ቢትወደድ የሆነውን ሆሎፎርኒስን ሰይፈ አንስታ አንገቱን ቆረጠች፡፡ ሕዝቦችዋንና ቅድስቲቱንም ከተማ ከጥፋት ታደገች፡፡
ዛሬም ምእመናን የዮዲትን ጾምና ጸሎት ሰምቶ ኢየሩሳሌምንና ሕዝቦችዋን ከጥፋትና ከመከራ እንደዳናቸው ያለፈ በደላቸውን ደምስሶላቸው አዲሱን ዘመን የደስታና የተድላ፣ የድልና የስኬት፣ የቅድስናና የበረከት ያደርግላቸው ዘንድ የፈቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡
በዚህ የጳጉሜን ወር አምስቱንም /ስድስቱንም/ ዕለታት ምእመናን ጠበል ይጠመቃሉ፡፡ ጠበል መጠመቁ ሃይማኖታዊም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በድንግል ማርያም፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በመላእክት፣ በአጠቃላይ በቅዱሳን እና በእግዚአብሔር ስም በፈለቀ ጠበል ላይ ጥምቀትን ያከናውናሉ፡፡
በገጠሩ የሀገራችን ክፍልም በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሌሊት ምእመናን አቅራቢያቸው ወደሚገኘው ወንዝ ወርደው ይጠመቃሉ፡፡
ይህ የጳጉሜን ጠበል የመጠመቁ ሃይማኖታዊ ምክንያትን ስንመለከት፡-
የመጀመሪያው ከበሽታ ለመዳን ምእመናን ይጠመቃሉ፡፡ ሰዎች በሥጋዊ ሕመም ሲያዙ ጠበል ተጠምቀው ከሕመማቸው ይፈወሳሉ፡፡ ከብሉይ ኪዳን ታሪክ ብናስታውስ ንዕማን በዮርዳኖስ ጠበል ተጠምቆ ከበሽታቸው ተፈውሷል፡፡ (፩.ነገ.፭፥፩)፡፡ ኢዮብም እንዲሁ በዮርዳኖስ ተጠምቆ እንደተፈወሰ መምህራን በትርጓሜ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
ሁለተኛው ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፤ ተራራው ይስተካከል፤ ጎድጓዳው ይሙላ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ልባችሁን ከኃጢአት ከጣዖት አጽዱ፤ ሰውነታችሁን ለክርስቶስ ማደሪያነት አሰናዱ” እያለ ያስተምርና የንስሓ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር፡፡ ዛሬም ይህን ለማስታወስ ምእመናን በጳጉሜን ወር ይጠመቃሉ፡፡
ሦስተኛው በንጹሕ ሰውነት አዲስ ዓመትን ለመቀበል ሲሉ ይጠመቃሉ፡፡ የእግዚአብሔርን በዓል ሰውነትን ታጥቦ፣ ንጹሕ ልብስ ለብሶ ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉና ለበዓሉ ባለቤት ያለንን ክብር ያስረዳል፡፡ ሥርዓቱም በብሉይ ኪዳን ሲደረግ የነበረ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን እንመልከት፡፡ “ውረድ ዛሬና ነገ ራሳቸውን ያነጹ፤ ልብሳቸውንም ያጥቡ ዘንድ ሕዝቡን እዘዛቸው፡፡ በሦስተኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጅተው ይጠብቁ” (ዘፀ. ፲፱፥፲-፲፩) እንዲል፡፡
ምእመናን ዓመቱን ሙሉ የተለያየ ኃጢአትን ሲሠራ የቆየ ሰውነትን ለመገሰጽ፣ በደልን እያሰቡ በዕንባና በዋይታ፣ በንስሓ፣ እየጾሙ፣ እየጸለዩና እየሰገዱ አምላካቸውን ይማጸናሉ፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ ማንነትና ስሜት እንዲሁም ባለፈው ዓመት ያላሳኩትናን ያልሠሯቸውን ሥራዎች ለማሳካት ዕቅድ የሚያወጡበት ወር ነው፣ ጳጉሜን፡፡
ስለዚህ የበደልነውን ክሰን፣ ከንስሓ የራቀውን ማንነታችንን ገልጠን በአባቶቻችን ፊት ቀርበን፣ ንስሓ ገብተን አዲሱን ዓመት እንቀበል ዘንድ ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ ዘመን ያረጀው ዓመት በአዲስ ሲተካ እኛም ደግሞ በኃጢአት ያደፈውን ሰውነታችን አንጽተን መቅረብ ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን እንድናደርግ እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!