“በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ”(መዝ.፩፻፳፭:፭)

በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ

ክፍል ሁለት

የተከበራችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች፡- በክፍል አንድ ዝግጅታችን ቅዱስ ዳዊት “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ” በማለት የተናገረበትን ምክንያት በተብራራበት ጽሑፋችን ስላለፈው ዘመን መናገሩን ገልጸን ቀሪውን በክፍል ሁለት እንደምናቀርብ በገባነው ቃል መሠረት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡-

ለ. ስለ ጊዜው ተናግሮታል፡-

ስለ ጊዜው ተናግሮታል ስንል ቅዱስ ዳዊት በነበረባቸው ዘመናት ስለተፈጠረው ክስተት የተናገረውን የሚያመላክት ነው፡፡ በአንደበቱም ሆነ በድርጊቱ ምንም የበደለው ነገር ባይኖርም ንጉሡ ሳዖል በቅንዓት ሰይጣናዊ ተነሣስቶ ቅዱስ ዳዊትን ብዙ ጊዜ አሳዶታል፡፡ እግዚአብሔር አዳነው እንጂ ሁለት ጊዜ ጦር ወርውሮበታል፣ ለዚያውም እርሱን እያገለገለ ባለበት ሰዓት፡፡ ዱር ለዱር፣ ገደል ለገደል በተሰደደበት ወቅት ውሎውና አዳሩ በልቅሶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር እጁ ላይ የጣለለት ቢሆንም ክፉን በክፉ ሊቃወም፣ የሚያሳድደውን ሳዖልን ሊገድለው አልፈለገም፡፡ ኃዳጌ በቀልነቱ ንጽሕናውና ፍቅሩ፣ ቅንነቱና ደግነቱ እንዲሁም እግዚአብሔርን መፍራቱ ከልቅሶው ውስጥ የተሸከመው ፍሬ/ዘር/ ነበርና፡፡

ቅዱስ ዳዊት የገዛ ልጁ አቤሴሎም በተነሣበት ወቅት ተመሣሣይ የመከራ ሕይወትን ከመንፈሳዊነቱ ጋር አስተናግዷል፡፡ በሁለቱም የመከራ ጣሮች ላይ ቅዱስ ዳዊትን ያቆየው በእግዚአብሔር ቸርነት የተዘጋጀ የበረከት ነዶ ነው፡፡ ያንን ተሸክሞ ወደ ኢየሩሳሌም በምስጋናና በደስታ ተመልሶ የነገሠው፡፡

በዚህ የነቢዩ ዳዊት ሕይወት ላለፈ፣ እያለፈ ላለና ለሚያልፍ ክርስቲያን ሁሉ ታሪኩ የሚናገረው ለማን ነው? የመጀመሪያው ለሰዎች መልካም እያደረገላቸው ቤተ ክርስቲያንም በቅንነት እያገለገለ የሚገኝ ሰው እንደ ሳዖል በሥልጣን ኮርቻ ላይ በተፈናጠጡ እኩያን ሰዎች መከራ ሊደርስበት እንደሚችል ስገነዝበን ሲሆን ክፉ ላደረጉብኝ ክፉ ላድርግባቸው ሳይልና መልካምነቱን ሳያዛባ ለሚያገለግል ሁሉ ምላሹ መንፈሳዊ ደስታን መጎናጸፍ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ እንደ አቤሴሎም በሥጋ፣ በመንፈሳዊ ልጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ እኅቶቹ፣ እናቶቹ፣ አባቶቹና ወገኖቹ ከሚኖሩበት ቤት፣ ከሚሠራበት ድርጅት፣ ከተቀመጠበት መንበር፣ ከሚገለገልባትና የሚያገለግልባት ቤተ ክርስቲያኑ ስደት የገጠመው የዘመኑ ዳዊት ቅዱስ ዳዊትን ተሸክሞ እያለቀሰ መከራን ከተቀበለና ከጸና እሴተ ቅዱስ ዳዊትን ተሸክሞ በደስታ እየተፍለቀለቀ ዛሬም በዚህ ነገም በወዲያኛው ዓለም በመንግሥተ ሰማያት እንዲያርፍ የሚያስገነዝበን ነጥብ ነው፡፡ በአንጻሩም ግብረ አቤሴሎምን፣ ግብረ ሳዖልን ለሚሠሩ ሥልጣናቸውንና አጋጣሚዎችን ተገን በማድረግ እውነተኛችን ለሚያሳድዱ ሰዎችም ለሕይወት የሚሆነን ተግሣጽ ነው፡፡ መልእክቱም ፍጻሜአቸውን ከእነ ሳዖል ፍጻሜ ተለይተውና ለንስሓ በሚሆን ዕንባ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኹ የሚያነቃ የጥሪ ደወል ነው፡፡ አለበለዚያ በቁማቸውም እንደ ሳዖል መንፈሰ እግዚአብሔር ተለይቷቸው መንፈሰ እርኩስ እያሰቃያቸው እንደሚኖሩ ሲያስረዳን /፩ሳሙ.፲፮፤፲፬/ አሟሟታቸውም እንደሚከፋና ፍጻሜያቸውም እንደማያምር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ማነጻጸሪያ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ራስን ማየትና ማስተካክል ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

ሐ. ስለ ፍጻሜው ዘመን ተናግሮታል፡-

በዚህ ንዑስ ክፍል የምናየው ከቅዱስ ዳዊት ዕረፍት በኋላ በተለይ ስለ አዲስ ኪዳን ዘመን የተናገረውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ከቅዱስ ዳዊት ዕረፍት በኋላ በነቢያት አባቶቻችንና ሕዝበ እግዚአብሔር ላይ የደረሰባቸው የመከራ ሕይወትና በአጸፋው ያገኙት ደስታ በይዘቱ በ”ሀ” እና “ለ” ካየናቸው ተመሳሳይ ታሪኮች ጋር የተሰናሰለ በመሆኑ የእነርሱን ትተን ስለ አዲስ ኪዳን የተነገረውን ብቻ በአጭሩ እንቃኛለን፡፡

ከአዳም ጀምሮ የነበረው የሰው ልጅ በሙሉ በአዳም በደል ምክንያት ምንም ጻድቅ እንኳን ቢሆን ገነት መግባት ሳይችል ቀርቷል፡፡ የእግዚአብሔርን ቸርነት እየጠበቀ ተስፋ ደኅንነትን ተሸክሞ በሕገ ልቡናና ሕገ ኦሪት እየተመላለሰ ወደ ሲዖል እያለቀሰ ይወርድ ነበር፡፡ በሲዖልም ዲያብሎስ መከራ እያጸናባቸው በልቅሶና በስቃይ ረጅም ዘመናትን ኖረዋል፡፡ በክህነታቸው፣ በዕጣናቸው፣ በመሥዋዕታቸው ፍጹም ድኅነትን ማምጣት ባይችሉም እያለቀሱ የተሠማሩበት የብሉይ ኪዳን የአገልግሎት ሕይወት ነዶ አዲስ ኪዳንን ተሸክመው በደስታ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡ አዳምና ሔዋን እያለቀሱ ትተዋት የወጡበትን ገነት ደስ ብሏቸው ተመለስው ገብተውበታል፡፡ “በልቀሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ” እንደተባለ በአዳም በደል ተይዘው በልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ እያለቀሱ የቅድስና ሕይወትን በተጋድሎ የዞሩ አበውና እመው ተስፋ ድኅነት ተሸክመው በደስታ ዐርፈዋል፡፡

የቀጠሮው ዘመን በደረሰ ጊዜ ሰው የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ በመከራ ውስጥ በማለፍ ያሳየን ሲሆን “ዛሬን የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና” /ማቴ.፭፤፬/ በሚልና በመሳሰሉት የሕይወት ቃሎች በዚህ ምድር ላይ በልቅሶ የሚዘሩ ማለትም እንደ ቃሉ የሚጋደሉና ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ምእመናን የደስታን ፍሬ እንደሚያጭዱ አስተምሯል፡፡

ሕይወቱን ሕይወታቸው አድርገውና መከራ መስቀሉን ተሸክመው በልቅሶ የዘሩ ጻድቃን ሰማዕታት በገነት በደስታ ተሰብስበዋል፣ ብዙዎችንም በአርአያነታቸውና በቃልኪዳናቸው ሰብስበዋል፡፡ በገድል የሚታሰሩበትን እንጨት ተሸክመው ጸብአ አጋንንቱን፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ድምፀ አራዊቱን ታግሰው ከእኩያት ፍትወታተ ኃጣውእ፣ ከዓላውያን ነገሥታት ከሰይጣን ጋር ታግለው ከፈጣሪያችን ለሁላችንም የሚተርፍ የቃልኪዳን ነዶዎችን ተቀብለው በደስታ ዐርፈዋል፡፡

ለሁላችንም መድኃኔዓለም ክርስቶስም ያሳየንና ያስተማረን በዚሁ የልቅሶ ሕይወት ውስጥ በማለፍ የደስታ ባለቤት መሆንን ነው፡፡ በኋላ በገሃነም ላለማልቀስ ዛሬ በንስሓ ማልቀስ እንደሚገባ በቅዱሳን አባቶቻችን ሕይወት ከተማርን ዘንድ በደስታ የሕይወት ፍሬ ለመስበክስ በተሰጠን ዘመን መከራ መስቀሉን ተሸክመን እናገልግል፡፡ መስቀሉን ሳይሸከሙ የሕይወት ባለቤት መሆን እንደማይቻል እግዚአብሔር በቅዱኑ ነግናል፡፡ ስለ ክርስርስቶስ መከራ ባየንባቸው፣ ባለቀስንባቸው ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን በታመምንባቸው ዘመናት ፈንታ አምላካችን በዚሁ ጊዜ ያበቃል የማይባል ተድላ ደስታ ይሰጠናል፡፡ /መዝ.፹፱፥፲፬‐፲፭/ ከላይ ባየናቸው በ፫ቱም ሂደቶች ውስጥ የምንማረው ተጨማሪው ቁም ነገር ያለውን የሀገርና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በማስታወስ ደካማውን በማሻሻል ከጠንካራው ጎን ደግሞ በመማር እምነትና ሥርዓትን፣ ታሪክንና ትውፊትን እንድንጠብቅና የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የቀደመ ሕይወት እንዳንረሳ ነው፡፡ /ዘዳ.፴፪፤፯/ ስለዚህ ቅዱስ ዳዊት ስላለፈው ማወቅና መናገር እንደሚገባ ሲያጠይቅ ስላለፈው ተናግሮታልና፡፡ ስለ ጊዜውም አጠቃላይ የዓለም፣ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ቀርቦ መረዳትና በልቅሶ ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲን የሚጠቅሙ መልካም ዘርን መዝራት እንደሚገባና መራራ በሆነው ጉዞ ውስጥ ከማለፍ ባሻገር ያለውን ጣፋጭ ደስታ ማጣጣም እንደሚቻል ሊያመለክተን ስለ ጊዜውም ተናገረው፡፡

ለጊዜው ትውልድ ስላለፈው የልቅሶና የተጋድሎ ኑሮ ሰለተገኘው አስደሳች ሕይወት በጊዜው እሱም አባቶቹንና እናቹን መስሎ እንዲኖር በቃልም በሕይወትም ምሳሌ ልንሆን እንደሚገባ ያስረዳናል፡፡

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ነገን በተስፋ ከመጠበቅ በዘለለ ለነገው የተሻለና ታሪክ ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ለነገዋ የበለጸገች ሀገር መገነትና ለነገዋ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ በልማት አድጋ መንጋዎቿን በሁሉም ዘርፍ የምትመግብ ቤተ ክርስቲያን መታየት ዛሬ ሁላችምን መከራውንና ፈተናውን ሳንሰቀቅና ሳናፈገፍግ ማገልገልና መታገል እንደሚገባ መርሳት የለብንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት ስለሚመጣው ዘመን በመናገር ብቻ የኖረ አባት ሳይሆን በጊዜው ከእርሱ በኋላ ለሚሆነው ነገር በጾምና በጸሎት በሚችለው ሁሉ ሠርቶ አሳይቶናል፡፡ ስለ ልጁ ስለ ሰሎሞን ለሚሠራውም ቤተ መቅደስ፣ ስለ ቤተ መንግሥቱ አስተዳደርና ስለመሳሰለው ሁሉ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ አርአያ ሆኖናል፡፡

እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስንቅ አድርገን በአዲሱ ዓመት የአሮጌውን ዘመን አሮጌ ሕይወት አርቀን መልካም የሆነውን ምርኩዝ አድርገን በአዲስ ርዕይና መንፈስ ለመሥራት እንነሣ፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ መሆንን ይሻልና፡፡ በዓመቱ መተርጎም በማይችሉ ያማሩ ዕቅዶች አዲስ ዓመትን እየተቀበልን ደግሞ በዕቅድነት እያሸጋገሩ መኖር ራስን ማሞኘት ነው፡፡ ዘመኑ ስለ ድሎቻችን የመጨረሻም ሊሆን እንደሚችል አንርሳ፡፡ እንደ ቤት ተከራይ ድንገት ውጡ/ልቀቁ/ ልንባልና ልንጠራ እንደምንችል እንዴት ልንዘነጋ እንችላለን፡፡ /ኢዮ.፰፥፱/ ስለዚህ ዘመን እንደ ሞላ ውኃ /ወንዝ/ ሳያቋርጥ እየፈሰሰ ዝም ብለን የምናይ ወይም ልቅሶንና መከራን ሸሽተን ለጊዜያዊ ደስታ ብለን ብቻ የምንሯሯጥ መሆን የለብንም፡፡ ቅዱስ ይስሐቅ “ንስሓ ያልገባሁበትን ዕለት እንደኖርኩባት አልቆጥራትም” እንዳለ በልቅሶና በመከራ ዘለዓለማዊው ደስታ ለማግኘት ያልተጋንበት ዘመን እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ መጽናናትና ደስታን ልቅሶና መከራ እንደሚቀድሙትም እናስታውስ /ኢሳ.፷፩፥፩‐፫/ ሰው የሚዘራውን ነው የሚያጭደውና፡፡ /ገላ.፮፤፯‐፲/ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ደግሞ በደስታ የሚያጭዱት በፈንጠዚያ /በመቀማጠል/ የዘሩት አይደለም፡፡ ክርስቶስ እንዳስተማረን ነውና አለዘር በተለያየ መንገድ በዘህች ምድር ላይ ዘሩ በኋላም በተለያየ መንገድ አዝመራቸውን ሰበሰቡ፡፡ /ሉቃ.፲፮፥፲፱‐ፍጻሜ/ ቅዱስ ጳውሎስም “…በውርደት ይዘራል፣ በክብር ይነሣል፣ በድካም ይዘራል፣ በኃሉም ይነሣል፣ …” /፩ቆሮ.፲፭፥፵፪‐፪፫/ በማለት ስለ ትንሣኤ ሙታን ያስተማረን ትምህርት ይህንኑ የሚያጸናልን ነው፡፡ በመከራዎቻችን ውስጥ ጸንተንና ቀቢጸ ተስፋን አስወግደን ዘር ሃይማኖታችንን ተሸክመን በመልካም ምግባራት ተሰማርተን ነዶ ቃለ ሕይወትን ለመስማት አምላካችን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *