ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ (ሰቈቃወ ድንግል)

ክፍል ፩

በቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን

የቃሉ ተናጋሪ አባ ጽጌ ድንግል ነው። ቃሉን የተናገረውም የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደቷን፣ በስደቷ ጊዜም የደረሰባትን መከራና ኃዘን አምልቶና አስፍቶ በገለጸበትና በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና አምላክን የወለደች ድንግል ማርያምንም ባመሰገነበት ክፍሉ ነው። ሙሉ ቃሉን እንደሚከተለው እንመልከተው።

“ሰሚዖ ሕፃን ለእሙ ገአራ፤ ባረከ ኰኵሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ፤ ወእምኔሁ ለጽምዓ ትስተይ አመራ፤ ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሀገር ለይእቲ ማይ አምረራ፤ ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ፤ ሕፃኑ የእናቱን ጩኸት (ለቅሶ) ሰምቶ፤ ዐለቱን ባርኮ ከቆመችበት ቦታ ውኃ አፈለቀ፤ ከውኃውም ትጠጣ ዘንድ አመለከታት፤ የዚያች ሀገር ሰዎች እንዳይጠጧት ያችን ምንጭ አመረራት፤ ከሩቅ ለመጡት ግን መድኃኒት የጣፈጠችም አደረጋት።” (ሰቈቃወ ድንግል)፡፡

ይህ ኀይለ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራና ሁሉን የሚችለው አምላክ ወልደ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት መካከል አንዱን የሚያስታውሰን ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው “የተወለደው የአይሁድን ንጉሥ የት አለ” እያሉ ሲመጡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ በቅንዐት ተነሳሳና ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ነገረውና በሌሊት እናቱንና ሕፃኑን ይዞ ወደ ግብፅ ሸሸ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህን ታሪክ “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ገብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር አለው። እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።” (ማቴ.፪፥፲፫-፲፬) በማለት እንደጻፈው ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ጠላት ተነሣበትና ስደተኛ ሆነ።

ሰው ከሀገሩ ወጥቶ ስደተኛ ሲሆን ስንቁ ያልቃል፤ ይራባል፤ ይጠማል፤ የሚሰጠው ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም በሄሮድስ ላይ አድሮ በጠላትነት እንዲነሣሣ ያደረገ ሰይጣን በሰዎች ላይ እያደረ የሚያዝንላቸው አጥተው ስለነበረ ተራበ፤ ተጠማ፣ ዐለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ የሚያጠጣው አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ተጠማና አለቀሰ። የልጇን ልቅሶ ስትሰማ እናቱም ምርር ብላ አለቀሰች። ሁሉን የሚችል አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ቢወሰንም አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ሲያስረዳ፣ ዐለቱን ባርኮ ውኃ አፈለቀ። ማፍለቁ ብቻ ሳይሆን ያፈለቀው ውኃ ለስደተኞች የሚጥምና የሚጣፍጥ በአካባቢው ላሉትና በክፋት ለተሞሉት ሰዎች ደግሞ የሚመር ሁለት ዓይነተ ጣዕም ያለው ውኃ ሆነ።

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ምሥጢር የገለጸለት ደግ አባት አባ ጽጌ ድንግልም ከእግዚአብአብሔር ሁሉን ቻይነት አንጻር የማያስደንቅ ቢሆንም ከፍጡራን ባሕርይና ችሎታ አንጻር ግን እንዲህ እጅግ የሚያስደንቀውን ምሥጢር ገለጸልን። ሰዎች እርሱ የሰጣቸውን ውኃ ሲከለክሉት እርሱ ግን ከአንድ ምንጭ ተገኝቶ ለአንዱ ጣፋጭ ለሌላው መራራ የሆነ ተአምረኛ ውኃ አፈለቀ። ይህ እጀግ የሚያስደንቅና ልዩ የሆነ ምሥጢር ያን ጊዜ እንደ አዲስ የተጀመረ ሳይሆን ጥንትም ሀልወቱን፣ መግቦቱን፣ አምላካዊ ጥበቃውን ሲገልጽበት የኖረ፣ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖርም ነው። ለማሳያ የሚሆነን ታሪክ እንመለከታለን።

እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት በከፋ አገዛዝ ሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ኖረዋል። የገዢዎቻቸው ጭካኔ ልኩን ሲያልፍና እነርሱም አብዝተው ሲጮኹ ጩኸታቸውን ሰምቶ በሙሴ አማካኝነት ከግብፅ ምድር አውጥቷቸዋል። በጉዟቸውም ጊዜ መና ከሰማይ እያወረደ ሲመግባቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ እያፈለቀ ሲያጠጣቸው የነበረ መሆኑ የእስራኤልን ታሪክ የጻፈልን ሊቀ ነቢያት ሙሴ መዝግቦት እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስም “ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡሙ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” (ዘፀ.፲፭፥፳፪-፳፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናነበው በዚህ ጥቅስም እንደተመለከትነው በወቅቱ መራራ የነበረው ውኃ በሙሴ ጸሎትና ልመና አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ጣፍጦላቸው ጠጥተዋል። በጊዜው መጠጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሕይወታቸው መመሪያ የሚሆናቸውን አምላካዊ ቃል በሙሴ አማካኝነት አስተላልፏል። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” እንዲል። እስራኤላውያን ሕጉን ጠብቀው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ እንደ ሥርዓቱ ቢጓዙ በግብፅ ላይ የወረደው መቅሰፍት እንደማይደርስባቸው እንደተነገራቸው ሁሉ ዛሬም በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን የተፈቀደልንን እያደረግን ያልተፈቀደልንን እየተውን ብንኖር አምላካዊ ጥበቃው ሳይለየን እንደምንኖር ያስረዳናል።

በወቅቱ መራራ የነበረውን ውኃ አጣፍጦ እንዳጠጣቸው ሁሉ በሙሴ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል ከዐለት ላይ ውኃ ፈልቆላቸው ጠጥተዋል። (ዘፀ.፲፯፥፩-፯) እግዚአብሔር ያለውን ማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን ከሌለበት ማምጣትና መስጠትም እንደሚችል እንረዳለን። የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተከተለን በቀር ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ አይቻለንም። እርሱ ግን የማንም ረዳት ሳያስፈልገው ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ ይቻለዋል። የኤርትራን ባሕር ከፍሎ እስራኤላውያንን ማሻገር፣ ግብፃውያንን ደግሞ በባሕር ተሰጥመው እንዲቀሩ ማድረግ ችሏል። አሁንም ሁሉን ማድረግ ይችላል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ዕብን ዘመነንዋ ነደቅት ወይእቲ ኮነት ውስተ ርእሰ ማዕዘንት፤ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ እርሷ የማዕዘን ራስ ሆነች።” (መዝ.፻፲፯፥፳፪) በማለት የተናገረውን መተርጉማኑ የተናቀች ደንጊያ የተባለችው ዕብነ ሙሴ እንደሆነች አስረድተዋል። ይቺ ዕብነ ሙሴ ዐሥራ ሁለት ምንጭ ያላት ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል እያፈለቀች የምታጠጣ፣ በፊት በኋላ በቀኝ በግራ ሁና ከለላ የምትሆን፣ ጠላት ሲመጣ ረግረግ እየሆነች የምታሰጥም፣ ቀን እንደደመና እየሆነች ከቀን ሐሩር የምትከላከልላቸው፣ ሌሊት የብርሃን ዐምድ እየሆነች የምትመራቸው እንደነበረች በትርጓሜ አስረድተዋል። (መዝ.፻፲፯፥፳፪ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ለእስራኤል የተደረገውን ድንቅ ተአምር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።” (፩ቆሮ.፲፥፫-፬) በማለት ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ አስረድቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይከተላቸው የነበረ መንፈሳዊ ዐለት በማለት የገለጸውን ይህም ዐለት ክርስቶስ ነበረ በማለት ተርጕሞታል። ሁሉን የሚችለው አምላክ ዐለቱን የውኃ መፍለቂያ ምንጭ አድርጎ የተጠማውን ያጠጣበታል፤ የተራበውን ኅብስተ መና አድርጎ ይመግብበታል፤ ለጠላት መከላከያ መሣሪያም ያደርገዋል። ይሁን እንጂ መለስ ብለን በታሪክ እንደምናስታውሰው ይህ ሁሉ የቸርነት ሥራ ለክፉዎች አይመችም ነበር። አንዱ ሲድንበት ሌላው ሲጠፋበት ኖሯል። በስደቱ ወቅት ያደረገው ተአምርም የሚያስረዳን እንዲህ ያለውን ጉዳይ ነው።

ዛሬም ለአንዱ መራራ ለሌው ጣፋጭ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። በእርግጥ መራራም ሆነ ጣፋጭ የሚሆነው ተቀባዩ ለዚያ ነገር ከመብቃትና ካለመብቃት፣ ወዶ ፈቅዶ ከመቀበልና ካለመቀበል፣ ለሚሰጠው ነገር አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግና ካለማድረግ ወዘተ የሚመጣ ነው እንጂ ስጦታው በተፈጥሮው መራራ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ነገር አይሰጥም። ሰዎች ግን በአጠቃቀም ስሕተት በመድኃኒቱም ይሞቱበታል። ይህን በተመለከተ የተወሰኑትን እንጥቀስ፡-

. የእግዚአብሔር ቃል

ከላይ እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚመር ሆኖ አይደለም። ከአቀባበል መለያየት የተነሣ ግን የመረራቸው፣ አሁንም የሚመራቸው አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። የጣፈጣቸውም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ። የሚጣፍጣቸውንም ሆነ የሚመራቸውን እንመልከት።

. የሚጣፍጣቸው

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ጥዑም ለጕርዔየ ነቢብከ እምዓር ወሦከር ጥዕመኒ ለአፉየ፤ ቃልህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ.፻፲፯፥፻፫) በማለት እንደገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚጣፍጥ ለሕይወትም መሠረት ነው። ለዚህም ነው “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው” ካለ በኋላ በምድር ላይ ጣፋጭ ከሚባለው “ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ” በማለት እኛ ልንረዳውና ልንገነዘበው በምንችለው አገላለጽ ነገረን። የቃሉን ጣፋጭነትና መድኃኒትነት የተረዳው የመቶ አለቃው “በቃልህ እዘዝ፤ ልጄም ይድናል” (ማቴ.፰፥፰) በማለት ፍጹም የሆነ ሃይማኖቱን ገለጠ።

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜም ቃሉ የሚጣፍጣቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። በቅዱስ ወንጌል “በየምኵራቦቻቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።” (ሉቃ.፬፥፲፭) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን። እንዲሁም በቅዱስ ወንጌል “ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆምም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ በር።” (ሉቃ.፬፥፴፩) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ቃሉን በደስታ የተቀበሉት እንዳሉ ነው።

በመሆኑም “ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ” እንደተባለው ቃሉን ለሚሹት፣ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ፈልገው ሲለምኑት ለኖሩት ለአበው ቀደምት፣ ለነቢያት፣ ለቅዱሳን ጣፋጭ አደረጋት። እንዲሁም ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት፣ ከሩቅ ለመጡት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልተባሉት ጣፋጭ አደረጋት።

በሌላ አገላለጽ ትንቢት ለተነገረላቸው ሱባኤ ለተቈጠረላቸው ወገኖቹ ለተባሉት እስራኤላውያን መራራ አደረጋት። ማለት እንዳይቀበሉት ዐይነ ልቡናቸው ታወረ። “ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፩-፲፫) እንዲል የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ ያልተቀበሉትም እንደነበሩ ልንገነዘብ ይገባል።

. የሚመራቸው

በዚህ አገላለጽ አምነው ባለመቀበላቸው አለመጠቀማቸውንና መጎዳታቸውን ለማስረዳት ነው። በመሆኑም ከአብርሃም ዘር በመወለዳቸው የሚመኩትን አይሁድን “እውነት እውነት እላችኋለሁ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር)” (ዮሐ.፰፥፴፱) በማለት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የወቀሳቸው እውነተኛውን ቃሉን ሲነግራቸው ማመን ባለመቻላቸው ነበር። ቃሉን አምነው ከመቀበል ይልቅ ሊገድሉት ይሹ ነበር። በእውነት መንገድ ለማይጓዝ፣ እውነትን ገንዘብ የማያደርግ አካል ምንጊዜም ቢሆን እውነት ይመረዋል። እውነቱን ስለነገራቸው ስለኃጢአታቸውም ስለዘለፋቸው ጋኔን አድሮበታል ይሉትም ነበር። “አይሁድም ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም፡፡ አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ መናገራችን የሚገባ አይደለምን? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ.፰፥፵፰) እንዲል።

ቃሉ ሕይወት መድኃኒት ሲሆን በሚገባ ባለመቀበላቸውና የሕይወታቸው መመሪያም ባለማድረጋቸው የተነሣ ተፈርዶባቸዋል። በዕለተ ምጽአትም መፈራረጃ ይሆንባቸዋል። ይህን አስመልክቶ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አመ ይመጽእ ንጉሥ በግርማ መንግሥት ኵነኔ ድልው ቅድሜሁ ነፍስ ትርእድ ወመጻሕፍት ይትከሠታ ለስምዕ፤ ንጉሡ በግርማ መንግሥት በክበበ ትስብእት በመጣ ጊዜ ፍርዱ በፊቱ ነው፤ ነፍስ ትንቀጠቀጣለች መጻሕፍትም ለምስክርነት ይረቀርባሉ” (ጾመ ድጓ ዘደብረ ዘይት) በማለት ያስረዳናል። ቃሉን ሰምተው አለመጠቀማቸው ለፍርድ ይሆንባቸዋል።

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *