ኦርቶዶክሳዊ የአለባበስ ሥርዓት

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋ የሰው ሕይወትን በመልካም ጎዳና በሥጋም ሆነ በነፍስ የሚመራ ነው፡፡ ትምህርትዋም ፍጹም መንፈሳዊ ነው፡፡ የምታስተምረውም የአምላክዋን ቃል በቀጥታ ሳትቀንስ እና ሳትጨምር ሳታስረዝምና ሳታሳጥር ለሚሰማት ሁሉ ታደርሳለች፡፡ የሥርዓትዋም መነሻ እና መድረሻ ከምድር ሳይሆን ከሰማይ ነው፡፡ “ሥርዓተ ሰማይ ተሠርዐ በምድር” እንዲል:: ይህም ሰማያዊውን ሥርዓት ተከትላ በምድር ያሉ አባላቶቹዋ የሰማዩን ሥርዓት በእምነት በመመልከት በምድር የሚኖሩ ሰማያውያን እንዲሆኑ የምታደርግበት ጥበብ ነው፡፡ የዚህች የሰማይ ደጅ የሆነች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅ ነኝ የሚል ሁሉ ሀገሩ በሰማይ እንደሆነ ላፍታም እንኳ ቢሆን ሊዘነጋው አይገባም፡፡ በዚህ ዓለም የሚኖረው እስከተፈቀደለት ዕድሜ ብቻ እንደሆነ ያስተውላልና ራሱን በምታልፍ ዓለም ውስጥ ደብቆና ደልሎ ለማይረባ አስተሳሰብ ተላልፎ አይሰጥም፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ልጆቿ ለዘለዓለም ቅዱሳን መላእክትን መስለው የሚኖሩበትን ሥርዓት በምድር ሠርታ እንዲኖሩት በማድረግ ዜግነታቸው ሰማያዊ እንደሆነ በተግባር እያሳየች ታስተምራቸዋለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሠራችውን ሥርዓት ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ስንመለከተው በቀጥታ ቃሉን በተግባር ወይም በትርጉም የምንተገብርበት ነው፡፡

በዚህ ርእስም የምንመለከተው ኦርቶዶክሳዊ የአለባበስ ሥርዓት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እና ከአዋልድ መጻሕፍት፣ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ምን መምሰል አለበት የሚለውን በተለይም ባለንበት ዘመን ያለው የብዙ ወንዶችና ሴቶች አለባበስ ወዴት እያመራ ነው የሚለውን መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ እንዲሉ አበው አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ አካልን በቅጠል፣ በቆዳ፣በጨርቅ መሸፈን ተጀመረ፡፡ ይህም ቅድስናቸው ንጽሕናቸው እንደልብስ ሆኖላቸው እንዲኖር የተሰጣቸው ሀብት ሆኖ ሳለ ሰውነታቸውን  ከአስተሳሰብ ጀምሮ በተግባር በፈጸሙት በደል ምክንያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስለራቃቸው ክብር ስለጎደላቸው ራቁታቸውን መሆናቸው ታወቃቸው፡፡ ስለዚህም አካላቸውን መሸፈን አስፈለጋቸው፡፡

ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ለመቆምም ሆነ በሰው ፊት ለመታየት እንደ መላእክት ንጹሕ በመሆን መንፈስ ቅዱስን ጸጋ እግዚአብሔርን መልበስ የግድ አስፈላጊ ስለነበር ነው፡፡ ከውድቀት በኋላ ግን የቀድሞው ንጽሐ ጠባይ ስላደፈብን ገነት ደግሞ ባደፈ በጎሰቆለ ማንነት የማይኖሩባት ሰማያዊት ሀገር ናትና ወደ እዚህ ዓለም ተሰደድን፡፡ በዚህ ዓለም እየኖርን ለሰማያዊት ርስት የምንበቃበትን ሥራ፣በመሥራት የገነት ምሳሌ በሆነች በቤተ ክርስቲያን ስንኖር የአለባበስ ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡ ሥርዓቱም በጾታ ተለይቶ እንደየ ተፈጥሮአችን የወንድ ልብስ፣የሴት ልብስ፣የሕፃናት ልብስ፣ የመነኮሳት ልብስ፣የካህናት እና  የዲያቆናት ልብስ፣የኤጲስ ቆጶሳት  የሊቃነ  ጳጳሳት  ልብስ  ተብሎ  እንደየ  መልኩና አስፈላጊነቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በጠበቀ መልኩ፣ሰማያዊውን ሥርዓት መሠረት ባደረገ መልኩ ቅድስት ቤተ ክርስቲን ሥርዓት ሠርታለች፡፡

አሁን አሁን የምንመለከተውና የምንታዘበው ግን ብዙዎቻችን ከዚህ ሥርዓት ወጣ ብለናል፡፡ ወንዱ የሴቷን፣ሴቷም የወንዱን፣ምእመኑ የካህኑን፣ካህኑም የመነኮሳትን በመልበስ ሥርዓት አልበኝነት በብዙዎቻችን ላይ ይታያል፡፡

በተለይም ደግሞ በከተሞቻችን እጅግ ገዝፎ የሚታየው የሴቷ  እና የወንዱ አለባበስ ቅጥ ያጣ ፍትወተ ሥጋን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሴት በወንድ ልብስ ስታጌጥ ከማየት የበለጠ የስነ ምግባር ዝቅጠት የለም፡፡ አስቀድሞ እግዚአብሔር ለሙሴ የወንድም ሆነ የሴት የአለባበስ ሥርዓት መጠበቅ እንዳለበት በሕጉ መጽሐፍ አስፍሮታል፡፡

“ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና”(ዘዳ.፳፪፥፭)፡፡ ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ማለት በራሷ በሴቷ ስም የተሰፋ ሱሪ ትልበስ ማለት አይደለም፡፡ ያማ ከሆነ የመጥበብና የመስፋት አልያም የማነስና የማጠር እንጂ ቅርጹ ያው ሆነ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮ እንደሚያስተምረን ሱሪ መልበስ ለሴት የተፈቀደ አለመሆኑን ነው፡፡ ሴት ሱሪ አለመልበስ ብቻ ሳይሆን አካሏ ተገላልጦ መታየት ስለ ሌለባት ከልብስ በመራቆትዋ ምክንያት ወንዱ በእርስዋ እንዳይሰነካከል በምኞት ኃጢአት እንዳይወድቅ አካሏን የሚሸፍን ልብስ መልበስ ስለሚገባት ነው፡፡

ተፈጥሮ አያስተምራችሁምን በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረን ሴቷ ይህንን የአለባበስ ሥርዓት ባለመጠበቅዋ ምክንያት ለሚሰናከልባት ወንድ ሁሉ ተጠያቂ ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ኃጢአትን ያደረጋት ብቻ ሳይሆን ለኃጢአት ምክንያት የሆነው ሁሉ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡

“በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል  የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል”(ማቴ.፲፰፥፮)፡፡

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ “ከታናናሾቹ አንዱን” ያለው በምግባር ደከም ያሉትን ይባሱኑ በሚያዩት ወይም በሚሰሙት ነገር ተስበው ኃጢአትን እንዲያደርጉ ምክንያት የሚሆን ይፈረድበታል ሲል ነው፡፡

አንዳንድ እኅቶች ሌላውን የሚያሰናክል ልብስ ለምን ትለብሳላችሁ? ሲባሉ እኔን ከተመቸኝ ስለ ሌላው ምን አገባኝ የሚል መልስ መመለሳቸው ያሳዝናል፡፡ እውነት ግን ለነሱስ ቢሆን የአካልን ቅርጽ የሚያሳይ ጥብቅ ያለ ታይት መሰል ለብሶ በአደባባይ መታየቱ፣ባታቸውን እያሳዩ አጭር ጉርድ ለብሰው ብዙዎችን ለኃጢአት መሳባቸው፣ለወንድ የተፈቀደ ሱሪ ለብሰው የሴትነት ወጉን እርግፍ አድረገው መጣላቸው ምን አይነት ስሜት ይሆን የሚሰማቸው? ምቾቱስ ምን ላይ ነው? አጭር ጉርዳቸውን ጨብጠው ዝቅ ለማድረግ የሚገጥሙት ትግልና መሸማቀቅ በሚዲያዎቻችን ሳይቀር የምንታዘበው አይደል፡፡ ቁራጭ ከመሆኑም አልፎ ከስስነቱ የተነሣ የአካል ቅርጽን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ልብስ ከሰውነታቸው ጣል አድርገው  ነፋስ ሲመጣ ጭራሹኑ ከላያቸው በኖ እንዳይጠፋ ጨብጦ መያዝ፣የአየሩ ሁኔታ በተቀየረ ቁጥር በብርድ መጠበሱ የቱ ላይ ነው ምቾቱ? ወይንስ ደግሞ ሌላውን በማሰናከል የሚያገኙት ደስታ፣ጥቅም አለ ማለት ነው? ከሆነ ይህ ሰይጣናዊ ሥራ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ከአለባበሳችን ጀምሮ ንግግራችን፣አረማመዳችን፣አኗኗራችን፣አመጋገባችን ሁሉ በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል፡፡ “አለባበስህ በጥንቃቄ ይሁን”እንዲል (ሃይ.አበው ዘሠለስቱ ምዕት ፳፩፥፲፪) ጥንቃቄያችንም ለእኔስ እንዲህ አይነት ይፈቀድልኛል? ወይስ አይፈቀድም? ለሌላውስ መሰናክል አልሆንበትም? ብሎ አስቦ በጥንቃቄ መልበስ እንዳለብን ነው አበው ቅዱሳን ያስተማሩን፡፡

አንዳንድ እኅቶችማ በዓለም ጫጫታ ውስጥ የሚለብሱት ቅጥ ያጣ አለባበስ ሳያንሳቸው በሱሪ ተወጣጥረው፣አጫጭር ጉርዶችን ለብሰው ቤተ እግዚአብሔር ሳይቀር ለጸሎት የቆመውን ወጣት ቀልብ በመስረቅ መሰናክልነታቸው ጎልቶ የሚታይ  መሆኑ ሐቅ ነው፡፡ በውኑ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ገበያ የሚሸመትባት፣በምንዝር ጌጥ ራሳችንን አታለን ርካሽ የሆነውን ጠባያችን የምናንጸባርቅባት ናትን? አንድ ክርስቲያን የትም ቦታ ይሁን ምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ይሁን ክርስቲያናዊ ሕይወቱን የሚያስነቅፍ የስንፍና ሥራ ሊሠራ አይገባውም፡፡ ድንገት ተሳስቶ ቢወድቅ እንኳ በንስሓ መነሣት አለበት፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንኳንስ በሕግ የተከለከለውን ሴት የወንድን ወንድም የሴትን ልብስ መልበስ ይቅርና በሕግ የተፈቀደውን መብል መብላት ወንድምንየሚያሰናክል ከሆነ አለመብላትን እንደሚመርጥ አስተምሮናል፡፡ “ነገር ግን በመብል ምክንያት ወንድሜ የሚሰናከል ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክል ለዘላለም ሥጋ አልበላም(፩ኛቆሮ.፰፥፲፫)

ይህው ሐዋርያ “እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ ሴት ወደ እግዚአብሔር በምትጸልይበት ጊዜ ልትከናነብ አይገባምን? ተፈጥሮዋስ አያስረዳችሁምን? ወንድ ግን ጠጉሩን ቢያሳድግ ነውር ነው  ለሴት ግን ጠጉርዋን ብታሳድግ ክብርዋ ነው ለሴት ጠጉርዋ እንደ ቀጸላ ሆኖ ተሰጥቶአታልና”(፩ኛቆሮ.፲፩፥፲፫)፡፡

እነዚህንና በዚህ ያልጠቀስናቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት በማድረግ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአለባበስ ሥርዓታችን በማያስነቅፍና ለውድቀት ምክንያት በማይሆን ይልቁንም እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና በክርስቶስ ደም የከበረ አካላችንን በማያራቁት ሌላውንም  በማያሰናክል  መልኩ  መልበስ  ክርስቲያናዊ  ግዴታችን  መሆኑን  መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከቀደሙት እናቶቻችንና አባቶቻችን መልካም የሆነውን የአለባበስ ሥርዓት እንውረስ እነርሱ ኢትዮጵያዊነትን ከኦርቶዶክሳዊነት አንጻር አዋሕደው ሀገራዊ እሴታቸውን ጠብቀው ሃይማኖታዊም ግዴታቸውን ተወጥተው ማለፋቸው ሊያስቀናን ይገባልና፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *