“እየባረካቸው ራቃቸው” (ሉቃ. ፳፬፥፶፩)
ዘመነ ዕርገት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ከ፵ኛው ቀን ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያለው ነው፡፡ ዕርገት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ፱ኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ የጌታችን ዕርገት ታሪክ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬፥፶ ጀምሮ የተጻፈ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በዓይናቸው እያዩት፣ እየባረካቸው ከዓይናቸው መሠወሩ ተገልጧል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱን ለሐዋርያት ማሳየቱ ለቅዱሳን፣ ጻድቃን ዕርገት እንዳላቸው ለማሳየት ነው፡፡ እርሱ ሰው ሲሆን ያየው የለም፤ሲያርግ ግን ሁሉ እያየው ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ፴፫ ዓመት ከሦስት ወር እየተመላለሰ ክርስትናን ሰብኳል፣ ድውያንን ፈውሷል፤ ከተነሣ በኋላም ለ፵ ቀናትም ለሐዋርያት እየተገለጠ ጸሎተ ኪዳንን አስተምሮ ዐርጓል፡፡
ይህም ማለት ፶፻ወ፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን ሲፈጸም በዘመነ ማቴዎስ ማክሰኞ መንፈቀ ሌሊት ተወልዶ በዘመነ ማርቆስ በዕለተ ሐሙስ በ፫ ሰዓት ግንቦት ፰ ቀን ዐረገ፡፡
ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ ዐርባ ቀን ሐዋርያትን እያስተማረ ስለሚመጣው አጽናኝ እያስረዳ ሰነበተ (ዮሐ. ፳፩፥፫) ቅዱስ ዳዊትም “እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ፣ እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ” ይላል (መዝ.፵፮፥፭—፯)
ሠለስቱ ምዕትም “ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ፤ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ” ብለዋል፡፡ (ጸሎተ ሃይማኖት) “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፡፡ ሕይወታችሁም የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር ትገለጣላችሁ” እንዲል፡፡ (ቆላ. መ፫፥፩-፬)
የዕርገት በረከቶች
፩. ቡራኬ፡- “እጆቹን በላያቸው ላይ ጭኖ ባረካቸው፣እየባረካቸውም ራቃቸው ወደ ሰማይም ዐረገ” ይላል፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፶፩) ይህ ቡራኬ ለቅዱሳን ሐዋርያት በመዋዕለ ሥጋዌው ከሆነው የመጨረሻ ቡራኬ ነው፡፡ ይህን ቡራኬ ለመቀበል መጽናትና መታገስ ይጠይቃል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት የጸኑት የተባረኩበት ነው፡፡ቡራኬው ዛሬም የማይቋረጥ መሆኑን ሲያረጋግጥልን ደግሞ “እየባረካቸው ራቃቸው፣ ወደ ሰማይም ወጣ” በማለት ይነግረናል፡፡
ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴ ፍጻሜ ላይ ካህኑ እጆቹን አመሳቅሎ “እግዚአብሔር ከሁላችሁ ጋር ይሁን” በማለት የዕርገት በረከት (ቡራኬ) ለምእመናን ስታድለው(ስታካፍለው) ትኖራለች፡፡ ይህ ደግሞ “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. ፳፰፥፳) በማለት የገባልን ኪዳን ማረጋገጫ ቡራኬ ነው፡፡
፪. ሹመት፡- “ወእምዝ አውፅኦሙ አፍአ እስከ ቢታንያ ወአንሥአ እዴሁ ላዕሌሆሙ ወባረኮሙ፤ ወደ አፍአ እስከ ቢታንያ ድረስ አውጥቶ በአንብሮተ እድ እስከ ፖትርያርክነት ያለውን ማዕርግ ሾማቸው፤ ሾሟቸውም የርቀት ያይደለ የርኅቀት ተሰውሯቸው ወደ ሰማይ ዐረገ” (የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ምዕራፍ ፳፬፥፶-፶፩)፡፡ በቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ዕርገት ድረስ የተሰጣቸው ሹመት ሁሉ በቡራኬ የተረጋገጠው በዕርገት ዕለት ነው፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ሰጣቸው የሚለውን ሲያብራሩ አስቀድሞ የሰጣቸውን ለማጽናት ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡
፫. ተስፋ፡- መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት እንደሚወርድላቸው ተጽፏል፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፳፮፣ ሉቃ. ፳፬፥፵፱) ዳግመኛም ሐዋርያትን “እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ. ፲፬፥፫) በማለት የሰጠን የመጨረሻ ተስፋ የተረጋገጠበት ነው፡፡
“…. ወደሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል” (የሐዋ. ፩፥፲፩) በማለት አስረግጠው ቅዱሳን መላእክት ተናግረዋል፡፡ አቡቀለምሲስ ዮሐንስም “እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፣ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል” (የዮሐንስ ራዕይ ፩፥፯) በማለት በዕርገቱ ያየነውን ደመና በዳግም ምጽአቱ እንደምናየው አስተምሮናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!