“በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” (ኤፌ ፪፥፳)

   

                                                        ኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ

                                                     ክፍል -፩

ጾም የሚለው ቃል “ጾመ“ ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ እና ጥቅል ትርጉምን የያዘ ቃል ነው፡፡ ይህም የጥሉላት መባልዕትን ለተወሰኑ ወራት መተው፣ መከልከልን እንዲሁም ከክፉ ነገር ሁሉ ራስን መጠበቅ፣ መቆጣጠርና መግዛት ማለት ነው፡፡

ጾም የመላው ሰውነታችን መታዘዝን የሚጠይቅ መንፈሳዊ ተግባር እንጂ በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ ገደብን የሚጥል አለመሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ይጹም ዐይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እመሰሚዐኅሡም፤ ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት፤ አንደበትም ክፉ ነገርን ከመናገር፤ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” በማለት ይመክረናል፡፡

ከቅዱስ ያሬድ ምክር በመነሣት ሰውነታችንን የምንከለከለው ከእህልና ውኃ ማለትም ከምግበ ሥጋ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን፣ ሰዎችንም ከሚጎዳ ከማንኛውም ዓይነት የኃጢአት ሥራ ከሐሜት፤ ከዝሙት፤ ከክፋት፣ ከምቀኝነትና ከመሳሰሉት የሥጋ ፍሬዎች ፈጽሞ መቆጠብና መከልከል እንደሚገባ ነው፡፡

የጾም መሠረታዊ ዓላማ
ጾም ከጸሎትና ከስግደት እንዲሁም ከምጽዋት ጋር የሚፈጸም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትጥቅ የአንብዕ፣ የንስሓ ምንጭና የመልካም ተጋድሎ መሠረት ነው፡፡

በሃይማኖት ስንኖር ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከለው በራሳቸው ኃጢአት ኖሮባቸው አይደለም፤ ይልቁንም ምግብ በልተን መጠጥም ጠጥተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብና የሥጋ ፍሬ ለሆነው ኃጢአት ከምንዳረግ ይልቅ መንፈሳዊ ትጥቃችንን በማጥበቅና ስሜታችንን በመጎሰም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ለማስገዛት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንንም ያጠፋቸዋል” (፩ኛ ቆሮ ፮÷፲፫) በማለት ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ በመነሣት የምንጾምበት መሠረታዊ ዓላማ ለመራብና ለመጠማት ወይም አካላዊ ሥጋችንን ለማጎሳቆል ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጽናትና ዘለዓለማዊውን መንግሥት ለመውረስ ነው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉ በሥርዓት እንዲሆን ታስተምራለችና ለጾምም ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ በዚህም መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማትን ዐውጃለች፡፡ ከእነዚህም መካከል ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም) አንዱ ነው፡፡

ይህ ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው ስለ ጾሙት አስቀድሞ “የጰንጤቆስጤ ጾም” ወይም “የደቀ መዛሙርት ጾም” ይባል ነበር፡፡ ከኒቅያ ጉባዔ በኋላ እስከ ዛሬ የምንጠቀምበትን “የሐዋርያት ጾም” የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ”(ማቴ. ፱÷፲፭-፲፮) በማለት እንዲጾሙ አዟቸዋል፡፡ እነርሱም ወደ አገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገው ጾመውታል፡፡

የሐዋርያት ጾም በሦስተኛው እና በአራታኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፉት መጽሐፈ ድዲስቅልያ፣ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ እንዲሁም ቅዱስ አትናቴዎስ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክት ላይ ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ሰፍረውና ቆጥረው ባስረከቡን ሐዋርያውያን አበው መሠረትነት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሁሉ የሐዋርያትን ጾም እንጾማለን፡፡

ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የጾሙት ስለ ሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ጾሟል፡፡ እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡

ከዚያም በ፪፻፰፶ ዓ.ም ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እስከ ሐዋርያት በዓል (The Feast of the Holy Apostles) ሐምሌ ፭ ድረስ እንዲሆን አባቶች ደነገጉ፡፡ ይህም የተደረገው የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም ዐደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ ነው በማለት ያጠናክሩታል፡፡ መጽሐፈ ድዲስቅልያ ደግሞ ሐዋርያት ፵ ቀን እንደ ጾሙ ከዚያም በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ እግራቸውን አጥቧቸው ለስብከተ ወንጌል እንደተሰማሩ ያስረዳል፡፡

              ይቆየን !

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *