አዳም አርብ ቀን ተፈጠረ (ዘፍ.፩፥፳፯)
መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
አዳም ማለት፡- ያማረ መልከ መልካም ውብ ፍጡር ማለት ነው፡፡ አዳም የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ነው፡፡ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የሚባሉት ውኃ፣ እሳት፣ ነፋስ፣ መሬት ሲሆኑ ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የሚባሉት ደግሞ ለባዊት(የምታስብ)፣ ነባቢት(የምትናገር)፣ ሕያዊት(የምትኖር) ወይም በሌላ አገላለጽ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እሑድ ፍጥረትን መፍጠር የጀመረባት ቀን ናት፡፡ ለዚህም ነው በሥነ ፍጥረት ታሪክ እሑድ የመጀመሪያ ቀን ተብላ የምትጠቀሰው፡፡ የዕለቱ ስያሜም አሐደ፣ አንድ አደረገ ከሚለው የግእዝ ግስ እሑድ የሚለው ቃል የወጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እሑድ ቀን ፍጥረትን መፍጠር አሰበ ሊፈጥር ያሰበውንም እሑድ መፍጠር ጀመረ፡፡ አዳምንም በመጨረሻዋ የሥራ ዕለት በዕለተ ዐርብ በነግህ ከኅቱም ምድር ሚያዝያ አራት ቀን የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርጎ እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ አዳም የተፈጠረውም በምድር መካከል በምትገኘው ኤልዳ እየተባለች በምትጠራ ስፍራ ነው (ኩፋ.፭.፮)፡፡
“እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችን እንስሳትን እና ምድርን ሁሉ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ …እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ ስድስተኛም ቀን ሆነ፡፡”(ዘፍ.፩፥፳፮-ፍ)
እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ ነው አዳምን በዕለተ ዐርብ የፈጠረው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላካችን “ቸር አምላክ” ስለ ሆነ ነው፡፡ በጎ አባት ለልጁ የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚኖርበትን፣ የሚገዛውን፣ የሚመራውን፣ የሚያርስበትን ጥማድ፣ የሚያርሰውን መሬት፣ ወ.ዘ.ተ እንደሚያዘጋጅ ሁሉ ቸር የሆነው አምላካችንም ሁሉን ከፈጠረና ካዘጋጀለት በኋላ ሁሉን ወራሽ ሊያደርገው በዕለተ ዐርብ አዳምን አክብሮና አልቆ በአርአያውና በአምሳ ፈጠረው፡፡ በአዘጋጀለት በከበረ ስፍራም የፈጠረለትን ሁሉ እንዲገዛ በሁሉ ላይ አሠለጠነው፡፡
እንዲሁም አንድ ሰው ድግሥ ደግሦ ታላቅ የሚለውን ሰው ሲጠራ በክብር የተጠራው ታላቅ እንግዳ ከመምጣቱ አስቀድሞ ቤቱን ጎዝጉዞ፣ ሰንጋውን ጥሎ፣ እንጀራውን፣ ወጡን አሰናድቶ እንዲጠብቅ እና ያ በክብር የተጠራ ታላቅ እንግዳ በተዘጋጀበት መጥቶ ደስታውን እንዲካፈል አዳምም በእግዚአብሔር የተወደደ፣ የከበረ ታላቅ እንግዳ ፍጡር ሆኖ ፍጥረት ሁሉ ተፈጥረው በተጠናቀቁበት ሊገዛቸው፣ ሊነዳቸውና ሊኖርባቸው፣ ሊሠለጥንባቸውም በመጨረሻ ተፈጠረ፡፡
አባታችን አዳም በዕለተ ዐርብ ሲፈጠር እንደ መላእክት ንጹሕ ነበር፡፡ በዚህ ንጽሕናውም ረዳት ሆና ከጎኑ ከተፈጠረችለት ሔዋን ጋር በገነት ለሰባት ዓመት ያህል ኖረ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በዲያብሎስ አሳችነት ምክንያት ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደደ፡፡ ከገነት ተሰዶም ለመመለስ የፈጀበት ጊዜ ከነ ልጅ ልጆቹ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል እስኪፈጸም ማለት ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ እንዳለው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ቀድሞ በፈጠረበት ዕለት በዕለተ ዐርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በደሙ ፈሳሽነት ሰውን ከበደል ሁሉ አነጻው፡፡ ወደ ቀደመ ክብሩም መለሰው፡፡ አዳምና የልጅ ልጆቹ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ገነትን ሊወርሱ ችለዋል፡፡
አዳም በዕለተ ዐርብ ተፈጥሮ በበደል ምክንያት ያጣትን ገነት በዕለተ ዐርብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መሞት ዳግም ሊወርሳት ችሏል፡፡ ስለዚህ ዕለተ ዐርብ የተፈጠርንባትም፣ የዳንባትም ዕለት ናትና ዕለቲቱን በጾም በጸሎት አስበናት እንውላለን፡፡ ከዚሁ በተያያዘም ዕለተ ረቡዕም እንዲሁ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በአይሁድ ዘንድ ተመክሮ የዋለበት ነው፡፡
ረቡዕ ምክረ አይሁድ፣ ዐርብ ስቅለተ ክርስቶስ የተፈጸመበት ቀን ስለ ሆነ ዐርብ እና ረቡዕ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በጾም ታስበው ይውላሉ፡፡ ወሩ የፍስክ ጊዜ ቢሆን እንኳ ከበዓለ ኀምሣ ውጪ ዐርብ እና ረቡዕ በጾም ሁል ጊዜ ይታሰባሉ፡፡ ልደትና ጥምቀት ዐርብ ወይም ረቡዕ ላይ በዋሉ ጊዜ ተለዋጭ ቀን ጾመ ገሃድ ተብሎ በዋዜማቸው ይጾማል፡፡ ይህም ከበዓሉ ታላቅነት የተነሣ በደስታ በዓላቱ እንዲከበሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት መሠረት ነው፡፡
ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐርብና ረቡዕ በክርስቲያኖች ዘንድ ከሌሎች ቀናት ተለይተው ቅዳሴውም ከሰዓት እንዲቀደስ እና በእነዚህ ዕለታት አራስ ከሆነች እናት፣ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በታች ካሉ ከሕፃናት እና ሕመም ከጸናበት ሰው በቀር ሁላችንም መጾም እንዳለብን የምታስተምረን፡፡ ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ለሰው ያሳየውን ታላቅ ፍቅር የምናይበትና የምናስተውልበት ስለሆነ ምስጋና ይድረሰው አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!