አርባዕቱ እንስሳ
ኅዳር ስምንት ቀን “ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ነው፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ሠረገላዎቹ ናቸው” በማለት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፍ ስንክሳር ይገልጻል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ በራእይ ያየውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ፤ በዙፋኑም መካከል፣ በዙፋኑ ዙሪያም አራት እንስሶች አሉ፣ እነርሱም በፊትም በኋላም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፣ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፣ ሦስተኛውም እንስሳ ሰውን ይመስላል፣ አራተኛውም እንስሳ የሚበር ንስርን ይመስላል፡፡ ለእነዚህም አራቱ እንስሶች ለእያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሏቸው፤ በሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም፡፡ እነዚህ እንስሶችም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴን ምስጋናንም ይሰጣሉ”(ራእ.፬.፮-9፣ ስንክሳር ዘኅዳር ገጽ 2፻፸፯) በማለት ገልጿቸዋል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፣ ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር፡፡ ሱራፈልም በዙሪያው ቆመው ነበር፣ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፣ በሁለቱ ክንፎቻቸው ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፣ በሁለቱም ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን ይሸፍኑ ነበር፣ በሁለቱም ክንፎቻቸውም ይበርሩ ነበር፡፡ አንዱም ለአንዱም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች፣ እያለ ይጮኸ ነበር፡፡”(ኢሳ.፮.፩-፫፤ ስንክሳር ገጽ 2፻፰) እያለ የእግዚአብሔርን ዙፋን ስለሚሸከሙት አርባዕቱ እንስሳ ተናግሯል፡፡ አገልግሎታቸውም በዙፋኑ ፊት እግዚአብሔርን ሃያ አራት ሰዓት “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ ማመስገን ነው፡፡
ከአራቱ ዐበይት ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ነቢዩ ሕዝቅኤል በምርኮ ሳለ ያየውን ራእይ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡- “የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፣ እኔም አየሁ፣ እነሆም በሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና፣ የሚበርቅም እሳት መጣ፣ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፣ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ የሚብለጨለጭ ነገር ነበረ፣ ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ፡፡”(ሕዝ.፩.፫-፭) እንዲል፡፡
ስለ አርባዕቱ እንስሳ ልዕልናቸውና ክብራቸው ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል፤ መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው፡፡ ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፣ ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል፣ ገጸ ላሕም ስለ እንስሳት ይለምናል፣ ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል፡፡ ከሠማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና፡፡
ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነጹ በዚህችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ፣ እነርሱ ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና፡፡ (ስንክሳር ገጽ 2፻፸9)፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ኪሩቤል አማላጅነት ይማረን፣ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!