“ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?” (መዝ.፰፥፬)
ሊቀ ነቢያት ሙሴ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው መፍጠሩን ጽፎልናል (ዘፍ.፩፥፳፮)፡፡ ከሃያ ሁለቱ ሥነ ፍጥረታትም በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ክቡር ሆኖ የተፈጠረ ሰው በብዙ መንገድ እግዚአብሔርን ሲበድል ይታያል፡፡ ከመጀመሪያው ሰው አዳም ጀምሮ የሰው ድካሙንና በደሉን ስናይ እንደ ቅዱስ ዳዊት ሰው ምንድን ነው? እንላለን፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ እጅግ የሚያስደንቀው እንዲህ ለሚበድለው ሰው እግዚአብሔር የሚያደርገው ምሕረትና የሚሳየው ፍቅር ነው፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ስለ ሰው ክቡር ተፈጥሮ በመሰከረበት የዝማሬ ክፍል ‹‹ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ መሰላቸውም››(መዝ፵፰፥፲፪) በማለት እግዚአብሔር ሰውን አክብሮ የፈጠረው መሆኑንና ሰው ግን ይህንን የከበረ ተፈጥሮውን ልብ እንደሌላቸው እንስሳት በመሆን እንዳጎሳቆለ ይገልጻል፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ፍቅር ነውና በፍቅር ተስቦ በበደል ምክንያት ለተጎሳቆለው ሰው የገባለትን የምሕረት ቃል ኪዳን ለመፈጸም ሰው ሆነ፡፡ ለዘመናት በዲያብሎስ ቁራኝነት፣ በሲዖል ባርነት ተገዝቶ ይኖር ለነበርው ሰው ነጻነትን ሰበከለት፡፡ በኃጢአት ምክንያት ርስቱን አጥቶ ስደተኛ ወደ ሆነው ወደ ጎስቋላው ሰው መጣ፡፡ ታስረን ለነበርን መፈታትን፣ ባሮች ለነበርን ልጅነትን፣ ተቅበዝባዥ ለነበርን ዕረፍትን፣ ሙታን ለነበርን ሕይወትን አደለን፡፡ እርሱ መድኃኒት ነውና ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርቱ ፈወሰ፡፡ በሥጋው ደዌ ሥጋ፣ በነፍሱ በባርነት ቀንበር ተይዞ ይሰቃይ ለነበረ መጻጒዕ ለተባለ በሽተኛ ሰው ያደረገውን የማዳኑን ሥራ ስንመለከትና በኋላ ግን መጻጒዕ የመለሰለትን ምላሽ ስናስተውል አይ ሰው! ብለን ትዝብታችን እንደ ቅዱስ ዳዊት “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?” እንላለን፡፡
መጻጕዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ እርሱም በደዌ ዳኛ ተይዞ የአልጋ ቁራኛ ኾኖ ለብዙ ዓመታት(፴፰ ዓመት) ይኖር የነበረ በሰው የተናቀና የተረሳ ሰው ነው፡፡ መጻጒዕ ምንም እንኳ ለብዙ ዓመታት በመታመሙ ምክንያት ሰውነቱ ከአልጋ ተጣብቆ ከሰውነት ጎዳና የወጣ፣ ሰዎችም የናቁትና የተጸየፉት ቢሆንም፤ ፍጥረቱን የማይንቅ፣ ሰውን የሚወድ፣ ሳይንቅ
የጠየቀው፣ አይቶ በቸልታ ያላለፈው፣ የሰውን ድካሙን የሚረዳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደተረከው በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ቤተ ሳይዳ” የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡ ቤተ ሳይዳ ማለት ቤተ ሣህል (የይቅርታ ቤት) ማለት ነው፡፡ አምስት መመላለሻ የሚለውን ትርጓሜ ወንጌል እርከን ወይም መደብ ይለዋል፡፡ በእርከኑ ወይም በመደቡ ብዙ ድውያን ይተኛሉ፡፡ ከእነሱም ውስጥ የታወሩ፣ አንካሶች፣ የሰለሉ፣ ልምሾ የኾኑ፣ የተድበለበሉ፣ በየእርከን እርከኖቹ ላይ ይተኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ለመቀደስ በየዓመቱ በሚወርድ ጊዜ ድምፁ እስኪያስተጋባ ድረስ ውኃው ይናወጣል፡፡ ድውያኑም በዚያ ሥፍራ ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቃሉ፡፡ ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ውኃው ሲናወጥ ቀድሞ ወደ ውኃው የገባ አንድ ሰው ከደዌው ይፈወስ ነበርና፡፡
ፈውሱ በየጊዜው ከዓመት አንድ ጊዜ ይደረግ የነበረው የእግዚአብሔር ተአምራት በአባቶቻችን ጊዜ ነበር እንጂ አሁንማ የለም ብለው ድውያኑ ከማመን እንዳይዘገዩ ሲኾን፣ የድውያኑ መፈወስ አለመደጋገሙም (በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መፈጸሙም) በኦሪት ፍጹም ድኅነት እንዳልተደረገ ለማጠየቅ ነው፡፡ በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ከአልጋው ላይ ተጣብቆ ይኖር ነበር፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚያ ሰው ቀርቦ አየው፡፡ ጌታችን ክብር ይግባውና ተጨንቀን እያየ ዝም የማይለን፣ ስንቸገርም የሚረዳን ቸር አምላክ ነውና መጻጕዕ በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ለብዙ ዓመታት እንደ ተሰቃየ፣ ደዌው እንደ ጸናበት መከራውም እንደ በረታበት አውቆ በርኅራኄ ቃል “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ፈቃዱን መጠየቁ ነው፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ፍትሐዊ ነውና ለማዳን የእያንዳንዳችን ፈቃደኝነት ይጠይቃል እንጂ ሥልጣን ስላለው፣ ክንደ ብርቱና ሁሉን ማድረግ የሚቻለው ስለሆነ ብቻ ያለፈቃዳችን የሚገዛን አምላክ አይደለም፡፡ በእኛ ላይ የሚያደርገውን የማዳኑን ሥራ “ልትነጻ ትወዳለህን፣ ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ?” በማለት ከጠየቀ በኋላ “እንደ እምነትህ ይኹንልህ፤ እንደ እምነትሽ ይሁንልሽ” እያለ በነጻነት እንድንመላለስ ነጻነታችን ያወጀልን የፍቅር አምላክ ነው፡፡ መጻጕዕንም “ልትድን ትወዳለህን?” ባለው ጊዜ እሱ ግን የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ “ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” ብሎ መለሰለት፡፡ መጻጕዕ ሰዎች እንደሸሹት፣ በታመመ ጊዜ እንደተጸየፉት፣ “እንዴት ዋልህ? እንዴት አደርህ?” የሚለው ሰው እንዳጣ፣ ወገን አልባ እንደ ሆነ እና ተስፋ እንደ ቆረጠ ለጌታችን ተናገረ፡፡
ጌታችን የልብን የሚያውቅ አምላክ ሲሆን “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ የጠየቀበት ምክንያት አላዋቂ ሥጋን እንደ ተዋሐደ ለማጠየቅ ነው፡፡ አልዓዛር በሞተ ጊዜ “መቃብሩን አሳዩኝ፣ ወዴት ነው የቀበራችሁት?” እንዳለው ሁሉ መጻጕዕም በምላሹ “ሰው የለኝም” ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያየው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ነውና የውኃውን መናወጥ ተጠባብቆ ያወርደኛል ብሎ በማሰቡ ነው፡፡ እንዲሁም አምስት ገበያ ሰው ይከተለው ነበርና አንዱን ሰው ያዝልኛል ብሎ ነው፡፡
ብዙዎቻችን የሕይወታችን ዋልታ በሰው እጅና በሰው ርዳታ ያለ ይመስለናል፡፡ ሰዎች ካልረዱን፣ ካልደጎሙን፣ አይዟችሁ ካላሉን፣ ከጎናችን ካልሆኑና በሰዎች ካልታጀብን ነገር ሁሉ የማይሳካልን ይመስለናል፡፡ ለዚህም ነው በሰዎች ትከሻ ላይ እንወድቅና እነሱ ሲወድቁ አብረን የምንወድቀው፡፡ ሲጠፉም አብረን ለመጥፋት የምንዳረገው፡፡ እስኪ ከሚደክመው ከሰው ትከሻ፣ ከሚዝለው ከሰው ክንድ እንውረድና በማይዝለውና በማይደክመው በአምላክ ክንድ ላይ እንደገፍ፡፡ እርሱ መታመኛ ነው፤ ያሳርፋል፣ የማይደክምም ብርቱ መደገፊያ ነውና፡፡
መጻጕዕ ሁሉ ነገሩ በሰዎች እጅ ላይ ነው ብሎ ስላሰበና የሰዎች ርዳታ ስለ ቀረበት ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡ የተማመነባቸው ሰዎችም ሲርቁት ሕይወቱ ጨልሞበት ነበርና “ሰው የለኝም” አለ (ዮሐ.፭፥፯)፡፡ የተቸገረውን ለመርዳት፣ ድኃውን ባዕለ ጸጋ ለማድረግ፣ የተጨነቀችቱን ነፍስ ለማጽናናት አማካሪ የማይሻው አምላክ ግን ወዲያውኑ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” አለው፡፡ መጻጕዕም ወዲያውኑ ዳነ፡፡ አልጋውንም ተሸክሞ ሔደ፡፡ ቀነ ቀጠሮ ሳይሰጥ፣ መሻቱን ተመልክቶ በአምላካዊ ቃሉ ፈወሰው፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ እንደ ተገለጸው የእግዚአብሔር መልአክ የቀሳውስት፣ ውኃው የጥምቀት፣ አምስቱ እርከን የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር፣ አምስቱ ድውያን የአምስቱ ፆታ ምእመናን ማለትም የአዕሩግ፣ ወራዙት፣ አንስት፣ ካህናት፣ መነኮሳት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህንም ሰይጣን የሚዋጋበት ለእያንዳንዱ እንደየ ድካሙ ሊያጠቃው ይሞክራልና ያንን ድል
የሚነሱበትን ምሥጢር እንደሚያድላቸው ያጠይቃል፡፡ አዕሩግን በፍቅረ ንዋይ፣ ወራዙትን በዝሙት ጦር፣ አንስትን በትውዝፍት (የምንዝር ጌጥ)፣ ካህናትን በትዕቢት፣ መነኮሳትን በስስት ጦር ሰይጣን ይዋጋቸዋል፡፡ እነርሱም በጥምቀት ባገኙት ኃይል (የልጅነት ሥልጣን) ድል ያደርጉታልና የዚያ ምሳሌ ነው፡፡ ለመጻጕዕ መፈወስ የዘመድ ብዛት፣ የሰዎች ርዳታ አላስፈለገውም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተፈውሷል፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፤ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” (መዝ.፸፪፥፲፪) ሲል የተቀኘው፡፡ ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት(ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው” (ኢዮ.፳፮፥፪) በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡
የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቱ የደረሰለት ሰው እንዲህ ይባረካል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ ሐሴትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ”(መዝ.፵፥፲፮) እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች እንሁን፡፡
መጻጒዕ የተፈወሰው በሰንበት ቀን ነበርና አይሁድ በዚህ ቀን አልጋህን ልትሸከም አይገባህም ሲሉ ተቃወሙት፡፡ እርሱ ግን በተደረገለት ነገር ደስ ቢለውም ከእነርሱ ይልቅ ለሱ መልካም ነገር ያደረገለትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተደረገለት ነገር ሁሉ ሙሉ ተጠያቂው እርሱ ነው እንጂ እኔ ታዝዤ ነው ለማለት “ያዳነኝ እርሱ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም መልሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማነው ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱ ግን የፈወሰው ማን እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ብሎ እንደ ጠቀሰው የረዳውን፣ ያዳነውን፣ ሰው ቢረሳውም እንኳ ያልረሳውን፣ ሰው ቢንቀው እንኳ ያልናቀውን፣ ጎስቋላ ሕይወቱን የጎበኘውን ጌታ አለማወቁ፣ ለማወቅም አለመጠየቁ ሰው ምን ያህል ደካማ ፍጡር እንደሆነ የምንማርበት ነው፡፡
ሰው እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ከ፳፪ቱ ሥነ ፍጥረት እጅግ ውብና በእግዚአብሔር መልክ እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ ድንቅ ፍጡር ሆኖ ሳለ የፈጠረውን፣ ቢወድቅ ያነሣውን፣ ቢጠፋ የፈለገውን፣ ቢራቆት የጸጋ ልብስ ያለበሰውን፣ ቢጎሳቆል ያከበረውን፣ ቢሰደድ ወደ ርስቱ የመለሰውን እግዚአብሔርን አውቆ ሊገዛለት እንደ ፈቃዱም ሊኖር ይገባል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲኖች በጻፈላቸው መልእክቱ እንደጠቀሰው
‹‹እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው››(ሮሜ.፩፥፳፰) ይላልና ለማይረባ (ሰነፍ) አእመሮ ተላልፎ ላለመሰጠት እግዚአብሔርን ማወቅ፣መፈለግና መከተል ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “እነሆ ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል፣ ተጠንቀቅ አለው” ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡
መጻጉዕ ምንም እንኳን በዚያች አልጋህን ተሸክመህ ሂድ በተባለበትና ከደዌው በተፈወሰበት ሰዓት ለዘመናት ሲጠባበቅ የነበረውን ድኅነት በአንዲት ቃል ያዳነውን አምላክ ቢያንስ ከተደረገለት ከእግዚአብሔር ቸርነት ተነሥቶ ለማወቅ አለመፈለጉ በደል ሆኖ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ አግኝቶት እርሱ እንዳዳነው ከነገረው በኋላ እንኳን ስለ ተደረገለት አመስግኖ አዳኝነቱን መመስከር ሲገባው ሁለተኛ በደል ጭራሽ ለመክሰስ ተሰለፈ፡፡
አይሁድም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሰንበት ድውይ ፈውሷል፣ጎባጣ አቅንቷል፣እውር አብርቷል ለምጽ አንጽቷል፣ሙት አስነሥቷል፣ጉንድሽ ተርትሯል፣አጋንንትን ከሰው ልቡና አውጥቷል ስለዚህ ሰንበትን ሽሯል በሚል ክፉ ሴራቸው ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተራቡትን ትቂት እንጀራ አበርክቶ እያበላ፣የተጠሙትን እያጠጣ፣ የተጨነቁትን እያጽናና፣ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ድውያነ ነፍስን በትምህርቱ እየፈወሰ ድሃውን ስለ ድህነቱ ሳይንቅ፣ባዕለ ጸጋውን ስለ ሃብቱ ሳያፍር የሁሉን ልብ በአባታዊ ፍቅሩ አንኳኳ፡፡ ብዙዎች ግን ልባቸው በክፋት ስለ ሞላ ዲያብሎስ ልባቸውን ስላደነደነው መጽሐፍ እንዳለ ‹‹የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› በእርሱ አምነው ከመቀበል ይልቅ ላለመቀበልና ወንጀለኛ ነው ለማለት የውሸት ምክንያት ይፈልጉ ነበር፡፡
አይሁድ ጌታችንን ከጲላጦስ ፊት አቅርበው ካቀረቡበት ክስ መካከል ዋና ዋናዎቹ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል፣ ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ብሏል፣ ሰንበትን ሽሯል የሚሉ ነበሩ፡፡ በሰንበት ድውያንን በመፈወስ ሰንበትን ሽሯል ብለው ላቀረቡት ክስ መስካሪ ሆኖ መጻጒዕ ቀረበ፡፡ በሰንበት የፈወሰኝ እሱ ነው በማለት ያዳነውን አምላክ እጁን አንሥቶ በጥፊ መታው፡፡
በምህረቱ የተፈወሰች እጅ የሕይወትን ራስ ጌታዋን ለመምታት ተዘረጋች፡፡ ‹‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› እንደሚባለው ያ ለዘመናት ሰውነቱ ከአልጋ ተጣብቆ፣ ከሰውነት ጎዳና ወጥቶ በጽኑዕ ደዌ ሲሰቃይ ነበረ በሽተኛ ተሸክማው የኖረችውን አልጋ እሱም በተራው እንዲሸከማት ዕድሉን የሰጠውን አምላክ ወንጀለኛ ነው ብሎ ጻድቁን ለመክሰስና ለመመስከር ከከሳሾች ጋር መተባበር የልቡና መታወር ነው፡፡ ልቡናቸው ብሩህ የሆነላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ የከፈለውን ዋጋ ቤዛነቱን ለመመስከር የኤሁድ ዛቻና ማስፈራሪያ አልገደባቸውም፡፡ያዩትን፣የሰሙትን፣የተደረገላቸውን በአጠቃላይ ለሰው ልጅ የተከፈለለትን ዋጋ ከመመስከር የተሳለ ሰይፍ ፣የሚንበለበል እሳት፣ግርፋትና ስቅላት ፣ስደትና እርዛት መጠማትና ረሃብ አላስቀራቸውም፡፡ይልቁንስ እውነትን በመመስከራቸው በሚገጥማቸው መከራ ደስ እያላቸው ምስክርነታቸውን ሰጡ እንጂ፡፡ ‹‹ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን በዐይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን››(፩ኛዮሐ.፩፥፩) እንዲል፡፡
መጻጉዕ ግን ስለተደረገለት ምህረት እየመሰከረ እግዚአብሔርን ማክበር ሲገባው ቀና ብሎ እንዲራመድ ከወደቀበት ያነሣውን ክርስቶስን ለመቃወም ደፈረ፡፡ ‹‹የበላበትን ወጪት ሰባሪ›› ማለት እንዲህ ነው፡፡ ጌታችን ክርስቶስ መጻጉዕን በቤተ መቅደስ እንዳገኘው ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ ብሎት ነበር፡፡ እሱ ግን በበደል ላይ በደል ጨመረ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ውብ አድርጎ ቢሠራውም ከንቱ ነገርን እንደሚመስል ያውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ለቸርነቱ ወሰን ለምህረቱ ገደብ የሌለው አምላክ ነውና ሰውን በፍቅሩ ጥላ ሥር እንዲያርፍ አድርጎታል፡፡
ቀድሞውኑ ሰው አታድርግ የተባለውን በማድረግ የማይገባውን በመመኘት ፈጣሪውን የበደለ፣ ከጸጋ እግዚአብሔር የተራቆተ፣ከገነት የተሰደደ፣ከክብር ያነሰ ሆኖ ቢገኝም የጠፋውን ሊፈግና ሊያድን ጌታችን ክርስቶስ በዓለም ተገለጠ፡፡ ሰው ሕግ አፍራሽ ሆኖ ሳለ ሠራኤ ሕግ ክርስቶስ ሕግን ሁሉ ፈጸመ፡፡ በደለኛው አዳም ካሳ ተከፈለለት፡፡ የሰው ልጅ የሚወደድ ሥራ ሳይኖረው በፍጹም ፍቅሩ ወደደውና ወደ ቀድሞ ርስቱ መለሰው፡፡ በዚህ ሁሉ የወደደን አምላካችን ልዑል እገዚአብሔር ከፍጹም ፍቅሩ የተነሣ ነውና ምሕረቱን ከእኛ ያላራቀብን ምስጋና ይድረሰው፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!