በዓለ ጰራቅሊጦስ
በዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ
በዓለ ጰራቅሊጦስ ከዘጠኙ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው። ጰራቅሊጦስ ማለት ከአብ እና ከወልድ ጋር ለምንሰግድለት የዘለዓለም አምላክ ለሆነው ለሚያነጻ፣ ሊሚያጽናና እና ለሚቀድስ ለመንፈስ ቅዱስ የመጠሪያ ስም ነው፡፡ በዚህም በዓለ መንፈስ ቅዱስ ለማለት በዓለ ጰራቅሊጦስ ብለን እንጠራዋለን፡፡
ይህ ታላቅ በዓል የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ቀን ነው፡፡ ይህም ስለ ምነው ቢሉ ቤተ ክርስቲያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዘመኑ በተነሡ ገዢዎችና እናውቃለን፣ እንመራመራለን በሚሉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በሚያደርሱት አድርገው ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ስትፈተን ብትኖርም ሳትጠፋ ፈተናውን ሁሉ እያለፈች ከዛሬ የደረሰችው መሳሪያዋ ጠላት የማያከሽፈው፣ ዲያብሎስ የማይችለው፣ ዘመን የማይሽረው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህች ዕለት ሲናገር “ዛሬ ከበረከት ሁሉ ጫፍ ላይ ደርሰናል፤ ጌታችን የገባልንን የተስፋ ቃል ፍሬውን አግኝተናልና” ብሏል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ሊሰጥ የሚችለውን የመጨረሻውን ስጦታ በምልዓት ሰጥቶናል፤ ይህም ስጦታ ምንድን ነው ቢሉ መንፈስ ቅዱስ ነው ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህችን ቀን “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብሏታል፡፡ (ሃይማኖተ አበው)
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ቅዱስ ሉቃስ በዚህ በዓል ዕለት የተደረገውን በተመለከተ ሲገልጽ “በዓለ ኀምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፤ ተቀምጠውም የነበሩበትን ቤት ሁሉ ሞላው፤ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩዋቸው በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፤ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር፡፡” በማለት ጽፏል(ሐዋ. ፪ ፥ ፩ – ፬)፡፡
መንፈስ ቅዱስ በጌታችን ጥምቀት ጊዜ በርግብ አምሳል እንደታየ አሁን ደግሞ ዓለሙን ሁሉ ሊለውጥ ቤተ ክርስቲያንም ልትተከል ባለበት ዕለት በአምሳለ እሳት ታየ፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው በቁሙ ነፋስ ሳይሆን እንደ ዐውሎ ነፋስ በማለት ረቂቅ አመጣጡን የገለጸው፡፡
ድንገትም እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ ያለውም መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡ ይህም ስለ ምን ነው ቢሉ ነፋስ ረቅቅ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና ፤ ነፋስ ኃያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኃያል ነውና፤ ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና፤ ነፋስ በምልዓት ሳለ አይታወቅም መንፈስ ቅዱስም በምልዓት ሳለ አይታወቅም፤ ነፋስ ባሕር ሲገስጽ ዛፍ ሲያናውጥ ነው እንጂ አይታወቅም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ /ልሳን/ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም ነው እንጂ አይታወቅም፤ ነፋስ መዓዛ ያመጣል መንፈስ ቅዱስም መዓዛ ቅድስና ያመጣልና፡፡
በእሳት አምሳል መውረዱም እንዲሁ እሳት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም “ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ወበእሳት፤ እርሱ ግን በመንፈስ እና በእሳት ያጠምቃችኋል” በሚለው ቃለ ወንጌል ይታወቃል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፩)
በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው ማለቱ በእነርሱ አድሮ ሳይለያቸው ቤቱ ማደሪያው አደረጋቸው ማለት ነው፡፡ ተቀመጠባቸው የሚለው ማደር፣ ከዚያው ሳይለዩ መቀጠልን እና አለ መለየትን ያሳያልና፡፡
፩. ሐዋርያት ይህንን ታላቅ ጸጋ ያገኙ ዘንድ ብቁ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
ሀ. በእምነት እና በትዕግሥት መጠበቃቸው(ሉቃ.፳፬፥፵፱)
ለ. ትዕዛዙን መፈጸማቸው(ሐዋ. ፭፥፳፱)
ሐ. በአንድ ልብ ሆነው ስለተጉ ነው
፪. ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን በመቀበላቸው ምን አገኙ?
ሀ. ኃይልን፣ብርታትን፣ቆራጥነትን እና ጽናትን አገኙ፡- መንፈስ ቅዱስ ኃይል ባይሰጣቸው ኖሮ መከራውን ሁሉ ተሸክመው ይጸኑ ዘንድ አይችሉም ነበር፡፡ ለዚህም ነው በጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን በፍጹም ፈቃዱ በአይሁድ እጅ በተያዘ ጊዜ ከዮሐንስ እና ከጴጥሮስ በቀር ሁሉም ፈርተው የተበታተኑት፡፡ አልክድህም ከአንተ ጋር እሞታለሁ ሲል የነበረው ጴጥሮስም በአንድ ምሽት ውስጥ ሦስት ጊዜ ነው የካደው፡፡ ተስፋ አድርጎ የተናገረውን ከመፈጸም ወደ ኋላ የማይል እግዚአብሔር በተስፋው መሠረት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ጽናትን እና የማይዝል ብርታትን አግኝተዋል፡፡
ለ. ዕውቀትንና ማስተዋልን አገኙ፡- በዚህ ዕለት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት አእምሮአቸው ብዙ ምሥጢር ለመስማት እና ለመሸከም የማይችል እንደ ሕፃን አእምሮ ነበር፡፡ ጌታችን እንዲህ ሲል እንደ ተናገራቸው “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፤ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡”(ዮሐ. ፲፮፥፲፪-፲፫) በተስፋ ቃሉ መሠረት መንፈስ ቅዱስን ሲልክላቸው ከእነርሱ ጋር በአካል ሳለ ያስተማራቸው እና የነገራቸው ሁሉ ግልጽ ሆነላቸው አዕምሮአቸውም የእግዚአብሔርን ድንቅ እና ረቂቅ ምሥጢር የሚረዳ እና የሚያስታውል ሆነ፡፡
ሐ. በአስተሳሰባቸው ከምድራዊነት ወደ ሰማያዊነት ተሸጋገሩ፡- ዓላማቸው ሁሉ የክርስቶስን ክብር መንገር ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ሆነ፡፡ በዚህ ዓለም የሚያስጨንቃቸው እንዴት ሀብት ንብረት እንደሚያገኙ እና እንደሚሾሙ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ነገር ብቻ ሆነ፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፩-፳፰)
እንግዲህ የሐዋርያት መባረክ እና ጸጋን ማግኘት ይህን ከመሰለ እኛም በጥምቀት የምንቀበለው ጸጋ እነርሱ የተቀበሉትን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህ የተቀበልነውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ የእርሱ ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በኃጢአት እንዳናቆሽሽ እና እንዳናሳዝነው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ “ለቤዛ ቀን የታተማችኁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” (ኤፌ. ፬፥፴) እንደተባልን ሰው ከመሆን የተነሣ ውድቀቶች ቢገጥሙንም በንስሓ እናስወግዳቸው፡፡ ሐዋርያትን ያጸና አምላክ እኛንም እንዲያጸናን ክብሩን ለመውረስ እንዲያበቃን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!