በዓለ መስቀል
በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው (ከአሜሪካ )
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል የምታከብረው መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀን ነው። እነዚህም አይሁድ በክፋት ቀብረው ሠውረውት የነበረውን መስቀል ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት እና መስቀሉ የተገኘበት ዕለታት ናቸው። ክቡር መስቀሉ ከክርስቲያኖች ተሰውሮ የኖረው ለሦስት መቶ ዓመታት ነው።
ክቡር መስቀሉ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር፦ በክፋት የተመሉ አይሁድ፥ በጌታ መስቀል እና መቃብር ምክንያት ይፈጸሙ የነበሩትን አያሌ ተአምራት አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውን ይተርካል። አይሁድ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ እስከ ፷፬ ዓ.ም ድረስ ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ከ፷፬ ዓ.ም በኋላ ግን ራሳቸውን ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ዓመጽ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ተቈጣጠሩ።
በዚህን ጊዜ ክርስቲያኖቹን ወደ ጌታ መስቀል እና መቃብር እንዳይቀርቡ ከልክለው ቦታውን የቆሻሻ መድፊያ አደረጉት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥፍራው ትልቅ ጉብታ ሆኖ ከቦታው ጋር ተመሳሳለ። ከዚህም ጋር እስራኤል በየጊዜው ይማርኩ ስለነበር፥ ከምርኮ ሲመለሱም የከተማዪቱ መልክ ስለሚለዋወጥባቸው መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ጉብታ መለየት አልተቻለም። በተለይም ከ፻፴፪ – ፻፴፭ ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ጠፍታ ነበር። ዳግመኛም ንጉሥ ሐድርያን በ፻፴፭ ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በአዲስ ፕላን በመሥራቱና በጎልጎታ የቬነስን መቅደስ በመገንባቱ ክርስቲያኖቹ ምንም ማድረግ አልተቻላቸውም ነበር። ያን ጊዜ ጎልጎታ ከከተማዋ ውጪ ነበር፥ ዛሬ ግን በአሮጌዋ የኢየሩሳሌም ከተማ ክልል ይገኛል።
መስቀሉ እንዴት ሊገኝ ቻለ?
ክቡር መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ናት። ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች ሙሉ ነፃነት የሰጠ ደገኛው የሮም ንጉሥ ነበር። ከዚያ በፊት ምንም ነፃነት አልነበራቸውም።ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የሰጣቸው መብት፦
፩ኛ ቤተ ክርስቲያንን ከግብር ነፃ አደረጋት።
፪ኛ፦ ከመንግሥት ገቢ ለቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ድርሻ ሰጣት።
፫ኛ፦ ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች የበዓል ቀን በመሆኗ በግዛቱ ሥራ እንዳይሠራ በ፫፻፳፩ ዓ.ም አወጀ።
፬ኛ፦ ለቤተ ክርስቲያን ኑዛዜ የመቀበልና ውርስ የመውረስ መብት ሰጣት።
፭ኛ በክርስቲያኖች መካከል ለሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባት፥ ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ለኤጲስ ቆጳሳት የዳኝነት ሥልጣን ሰጣቸው።
፮ኛ፦ ክርስትና የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ።
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የመዳን መልእክት እያወጀች ሐዋርያዊ ጉዞዋን እንድትቀጥል ያደረገ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ነው። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ይህን ያደረገበት ምክንያትም በመስቀል ምልክት የተደረገለት ተአምር ነበር። ይኸውም የሮምን የምዕራቡን ክፍል ይገዛ የነበረው ማክሴንዲዮስ የጦር ኃይሉን ባዘመተበተት ጊዜ፥ እርሱም በበኩሉ «ምታ ነጋሪት፥ ክተት ሠራዊት»ብሎ ለጦርነት ተዘጋጀ። ገና በዝግጅት ላይ እንዳለም፦ «በዚህ ድል ታደርጋለህ፤» የሚል በመስቀል ቅርጽ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈረ ሰማይ አየ። በዚህን ጊዜ፦ ሠራዊቱ በፈረሱ አንገት፥ በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ እንዲያደርግ አወጀ።
ሮምን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መግዛት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር ።ከዚያ በፊት ለአርባ ዓመታት ለአራት ተከፍላ በኋላም ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር። ጦርነቱም በመስቀሉ ኃይል ጠላቶቹን ድል አድርጎ ተመለሰ እናቱ ንግሥት ዕሌኒ በልጇ ዘመን የተገ ኘውን የክርስትና ነፃነት ተጠቅማ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክቡር መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። በዚያም ጉብታ የሆነውን ሥፍራ ሁሉ በማስቆፈር ብዙ ብትደክምም መስቀሉን ለማግ ኘት አልቻለችም። በዚህን ጊዜ ኪራኮስ የተባለው አረጋዊ፦ «ደመራ አስደምረሽ፥ ዕጣን አፍስሰሽ፥ ብታቀጣጥዪው ጢሱ ይመራሻል፤» ባላት መሠረት ሳትጠራጠር አደረገችው። የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ እንደ ቀስተ ደመና ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመለከታት።
ቁፋሮ ውም መስከረም ፲፯ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ተፈጸመ። የተገኙት ሦስት መስቀሎች ስለነበሩ የክርስቶስን መስቀል በተአምራቱ ለዩት። ዕውር አበራ፥ አንካሳ አረታ፥ ለምጽ አነጻ፥ ሙት አስነሣ። ንግሥቲቱም ያን ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ መስቀል የከበረ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ በክብር እንዲቀመጥ አደረገች።
መስቀል፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ተላልፎ በመሰጠት ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፥ ክቡር ደሙንም ያፈሰሰበት ነውና ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው። መሰቀል ድኅነታችን የተፈጸመበት (መዳናችን የተረጋገጠበት) ነው «ኢየሱስም ሆምጣጣውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ፥ አለ»ይላል (ዮሐ፲፱፥፴) በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን (መዳናችን) ነው። ይኸውም የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው(ሉቃ. ፩፥፴፩)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፥ ኃጢአታችንም ተሠረየልን።» ብሏል። መድኃኒት ከድንግል ማርያም መወለዱን ለእረኞች አስቀድመው የሰበኩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው(ሉቃ. ፪፥፲፩)መርገመ ሥጋ መርገም ነፍስን የተወገደበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተወገደበት ነው አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው የወደቀባቸው የሥጋና የነፍስ መርገም ለሰው ልጅ በጠቅላላ ተርፎት ነበር። «ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደ ሉትንም ሞት ገዛቸው።» ይላል( ሮሜ ፭፥፲፬) ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በኦሪቱ እንደተጻፈው በእንጨት ተሰቅለው የሚሞቱ ርጉማን ነበሩ( ዘዳ.፳፩፥ ፳፫)
ይህንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፥ ተብሎ ተጽፎአልና፤ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ያመጣብንን ኃጢአት ለመደምሰስ ተላልፎ በመሠዋት) ከሕግ እርግማን ዋጀን።» በማለት ገልጦታል (ገላ. ፫፥፲፫) ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።»ብሏል (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፳፬)
ዲያብሎስ የተሸነፈበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል፤ ዲያብሎስ የተሸነፈበት ነው ጥንተ ጠላታችንን (ገነትን ያህል ርስት፥ እግዚአብሔርን ያህል አባት ያሳጣንን ዲያብሎስን) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገልን በመስቀሉ ነው።«ጥልን በመስቀሉ ገደል፤» ይላልና። (ኤፌ.፪፥፲፮) ጥል የተባለው ለሰውና ለእግዚአ ብሔር መጣላት ምክንያት የሆነ ዲያብሎስ ነው። እኛም በኃይለ መስቀሉ ድል እያደረግነው የምንኖር ሆነናል።
የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ቅዱስ መስቀል
መሰቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤የጥል ግድግዳ የተባለው ኃጢአት ነው። እርሱም ሰውና እግዚአብሔ ርን ለያይቷቸው ኖሯል። «በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሠውሮታል።» ይላል (ኢሳ.፶፱፥፪) ይህ ከእግዚአብሔር ለያይቶን እግዚአብሔርን ሰውሮብን የኖረ የጥል ግድግዳ (በዲያብሎስ ምክር የተሠራ ኃጢአት) የፈረሰው በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። «በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ፤» እንዲል (ኤፌ ፪፥፲፭)
ዕርቅ የተፈጸመበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል ዕርቅ የተፈጸመበት ፣ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በመስቀል ላይ በተፈጸመ ካሳ ነው። ሰውና እግዚአብሔር በመታረቃቸው ነፍስና ሥጋ፣ሰውና መላእ ክት፣ሕዝብና አሕዛብም ታርቀዋል። እኛ በበደልን እርሱ ክሶ (የደም ካሣ ከፍሎ ) ታርቆናል።«ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።»ይላልና (ሮሜ ፭፥፲፣፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፰፣ኤፌ.፪፥፲፮)በሌላ በኩል ደግሞ «ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ።» የሚልም አለ (ቈላ. ፩፥፳)
አምላካዊ ይቅርታ የተገኘበት ነው፤«አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።» በማለት ገር ፈው የሰቀሉትን በቃሉ ይቅር ብሎአቸዋልና (ሉቃ.፳፫፥፴፬) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦በሞቱ የሰውን ዘር በጠቅላላው ይቅር እንዳለው ሲናገር፦«አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።»ብሏል (ቈላ.፩፥፳፪)
አምላካዊ ሰላም የተሰጠበት የተገኘበት ቅዱስ መስቀል
ነቢዩ ኢሳይያስ፦«ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።»በማለት ትንቢት የተናገረለት አምላክ ፍጹም ሰላምን የሰጠን በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት ነው።(ኢሳ.፱፥፯) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦«መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።» ብሏል( ኤፌ ፩፥፲፯)
የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው። ጌታችን የማታ ተማሪ የነበረውን ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፦ «እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤»ብሎታል።( ዮሐ.፫፥፲፮) ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የጻፈውን የጌታችን ትምህርት መሠረት አድርጎ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፥ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥ እርሱ ወደደን እንጂ እኛ የወደድነው አይደለንም፥ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።»ብሏል (፩ኛ ዮሐ ፬፥፱-፲፩)
የገነት በር የተከፈተበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የገነት በር የተከፈተበት ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው፥ ድኅነተ ምእመናንንም በመስቀል ላይ የፈጸመው ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነትን ለመክፈት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፥ በቀኙ ተሰቅሎ፥ «አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ»እያለ ሲማጸነው የነበረውን ወንበዴ፦«እውነት እልሃልሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ» ብሎታል(ሉቃ. ፳፫፥፵፪-፵፫)
የምንመካበት ቅዱስ መስቀል
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦«ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት (ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት የሆነበት)፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት (እኔም በዓለም ዘንድ ሙት የሆንኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ፤»ብሏል፡፡(ገላ. ፮፥፲፬)
በመሆኑም ዓለምና ቅዱስ ጳውሎስ በጌታ ደም ላይ በተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን እና በደሙ በጸናች ወንጌል ምክንያት ተለያይተዋል። አንዳቸው ለአንዳቸው ሙት ናቸው። ዓለም ሕያው የሆነችልን፥ እኛም ሕያው የሆንላት የሚመስለን የዓለም ፈቃድ ፈጻሚዎች ከቅዱስ ጳውሎስ ልንማር ይገባል። ዓለም ታልፋለች፥ እኛም ከእሷ እንለያለንና።
ከአጋንንት የምንድንበት ቅዱስ መስቀል
በክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ከአጋንንት ጦር እንድናለን ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፦ «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት (ከአጋንንት ጦር) ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህም እንዲድኑ።» ያለው ስለ መስቀል ነው። (መዝ.፶፱፥፬) በመሆኑም በመስቀል ምልክት አማትበን፥ ከአጋንንት ፈተና እንድናለን። መስቀል ኃይላችን ነው መስቀልን በእጅ መጨበጥ፥ በአንገት ማንጠልጠል፥ መሳለም በዓለም ዘንድ ሞኝነት ነው ለእኛ ለክርስቲያኖች ግን ድኅነት የተረጋገጠበት ነው። ለዚህም ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና» በማለት ያስተማረን ፡፡(፩ኛቆሮ.፩፥፲፰)
በመሆኑም በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር እስከ ዘለዓለሙ አይለየንም። በመሆኑም ለቅዱስ መስቀሉ እንሰግዳለን። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።» በአለው መሠረት የጌታችን እግሮች በመስቀል ላይ፥ ያውም በቀኖት ላይ ስለቆሙ ለመስቀሉ እንሰግዳለን። መስቀሉን በደሙ ቀድሶታልና፥ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። እግዚአብሔር በረድኤት በደብረ ሲና ራስ በቆመ ጊዜ፥ «ወደዚህ አትቅረብ፥ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤» በማለት ሙሴን አስተምሮታል፡፡(ዘዳ.፫፥፭)
እንኳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ይቅርና የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የቆመበትን መሬት፥ የተቀደሰ በመሆኑ፦«አንተ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ።» በማለት ኢያሱን ሲያዘው እርሱም የታዘዘውን እንዲደረግ ተረድተናል (ኢያ.፭፥፲፭) እንግዲህ መሬቱን፥ አፈሩን የቀደሰ አምላክ ፦ ሥጋውን የቆረሰበትን፥ ደሙን ያፈሰሰበትን፥ ነፍሱንም አሳልፎ የሰጠበትን መስቀል አልቀደሰውም ለማለት እንዴት ይቻላል? ፈጽሞ አይቻለም።ንግሥት ዕሌኒ በብዙ ድካም ከወርቅ ዙፏኗ ወርዳ ከአፈር ላይ ተቀምጣ፥ቆፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታለች።ዛሬ በእኛ ዘመን የተቀበረው ዳግም በመስቀሉ ያ የተገኘው ፍቅርና ሰላም ነው።
ፍቅር በጥላቻ፥ሰላም በጦርነት፥አንድነት በመለያየት፥እምነት በክሕደት፥ መንፈሳዊነት በሥጋዊነት የሕዝቦች ውሕደት በዘረኝነት ቆሻሻ ተቀብሮአል።ይህንን ቆፍረን ካወጣን ያን ጊዜ የዘመኑ ዕሌኒዎች እንሆናለን። መስቀሉን ተሸክመን በጥላቻና በዘረኝነት ቆሻሻ የተቀበርንም በቅድሚያ ራሳችንን ቆፍረን እናውጣ፥ ለብዙዎችም እንቅፋት አንሁን።ዘመኑን ከተቀበርንበት የምንወጣበት ያድርግልን።
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የመስቀሉ በረከት አይለየን፥ አሜን።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!