በመከራም ተስፋ ይገኛል፡፡ (ሮሜ.፭፥፬)
በእንዳለ ደምስስ
መከራ የሚለውን ቃል አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ “ፈተና፣ ጭንቅ፣ ለተቀባዩ ምክር የሚሰጥ” በማለት ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘው መጽሐፋቸው ይፈቱታል፡፡ (ገጽ 7፻፸፡፡ መከራ በሁለት ዓይነት መንገድ ሊደርስብን ይችላል፡፡ በሥጋም በነፍስም፡፡
በሥጋ ሊደርስ የሚችለውን መከራ “ረኀብ፣ ጥም፣ ሕመም፣ እስራት፣ ግርፋት፣ ስቅላት”፣ መከራ ነፍስን ደግም “ኵነኔ፣ ሲኦል፣ ገሃነም” በማለት ይገልጹታል፡፡ የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት መከራ ሊገጥመው ይችላል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ዓይኖቼ በመከራ ፈዘዙ፣ አቤቱ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፣ እጆቼም ወደ አንተ ዘረጋሁ” (መዝ.7.9) እንዲል መከራ በገጠመው ጊዜ እግዚአብሔር ያስወግድለት ዘንድ ይማጸናል፡፡ ስለዚህ ሰው መከራ ሲደርስበት በሥጋዊ ጥበቡ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ማስወገድ የሚችለው ሳይሆን በእግዚአብሔር ርዳታና ፈቃድ እንደሚከናወን ያመለክተናል፡፡
ቅዱስ ዳዊት በዘመኑ ከታናሽነቱ አንሥቶ እስራኤልን ይመራ ዘንድ የመረጠው፣ በክብር ዙፋን ላይ ያስቀመጠው ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን በደለ፤ በበደሉ ምክንያትም ለመከራ ተላልፎ መሰጠቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ከዙፋኑ ወርዶ፣ ትቢያ ለብሶ፣ አመድ ነስንሶ በልቀሶና በዋይታ በትዕግሥት እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ በተማጸነ ጊዜ የልቡናው መሻት ተፈጽሞለታል፡፡ መከራውም አልፎ ተስፋ ያደረገውን የሕሊና ሰላም እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ለመሆኑ ተስፋ ምንድነው?
ተስፋ “አለኝታ፣ ወደፊት አገኛለሁ የማለት ጽኑዕ እምነት” በማለት አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ይገልጹታል፡፡ ይህንንም ጽኑ እምነት ለአባታችን አብርሃም እንደተፈጸመለት ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ቃል ኪዳኑን በሁለቱ መካካል እንደሚያደርግና እጅግም እንደሚያበዛው ለአሕዛብም አባት እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቶታል፡፡ “አብርሃም “ዘርህ እንዲህ ይሆናል” ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ፡፡” (ሮሜ ፬.፳-፩) እንዲል፡፡
መከራ ለምን እንቀበላለን?
አዳም ምድርን ይንከባከባት፣ በውስጥዋም ያሉትን ሁሉ ይገዛ፣ ይነዳ ዘንድ እግዚአብሔር ሁሉን አመቻችቶ ቢሰጠውም ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ፈጣሪውን እግዚአብሔርን በበደለ ጊዜ ከገነት ተባረረ፡፡ ነገር ግን አዳም ተጸጽቶ ወደ እግዚአብሔር ባለቀሰ ጊዜ አዘነለት፡፡ ቃል ኪዳንም ገባለት፣ እንዲህ ሲል “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ እምርሃለሁ፣ ይቅርታም አደርግልሃለሁ፣ በወገንህም ከርሥ አድራለሁ፣ ይህ ሁሉ ስለ አንተ ድኅነት ይሆናል” (ቀሌ.፫..፲9) እንዲል፡፡ ቅዱሳን ነቢያት ይህንን ተስፋ በማድረግ፣ የክርስቶስን መወለድ ሲጠባበቁ ኖሩ፡፡ የነገሥታቱን ክሕደትና ጨካኝነት ተቃውመው ተስፋ የሚያደርጉትን እግዚአብሔርን አምነው፣ የሚደርስባቸውንም መከራ ታግሠው እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆኑ፡፡
አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመንም ሲፈጸም፣ “እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጣቸው ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኃኒት አድርጎ ኢየሱስን ሰጣቸው” እንዲል (ሐዋ.፫.፳፫) ጊዜው ሲደርስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነስቶ ተወለደ፡፡ በዲያብሎስ ተፈትኖ ድል ነሳ፣ በአይሁዳውያን በሐሰት ተከሰሰ፣ ተገረፈ፣ ተሰለቀ፣ ሞተ፣ በሞቱ ሞትን ሻረ፣ ሲኦልንም በዘበዛት በሲኦል ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ነፃ አወጣ፡፡ ሞትንም ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፣ ትንሣኤውንም አወጀ፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እንዳለው ነቢያት ተስፋ ሲያደርጉት የነበረውን ድኅነት ተፈጸመላቸው፣ ለሚመጣውም ትውልድ እስከ ዓለም ፍጻሜ በስሙ ቢታመኑ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ታግሠው በጽናት ወደ እርሱ ለሚጮኹት ርስት መንግሥተ ሰማያትን ሰጣቸው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፣ እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል” (2ጢሞ.፬.7) በማለት እንደተናገረው በሃይማኖት ብንጸና፣ የሚደርስብንን፣ ዲያብሎስ ያዘጋጀውን መከራና ፈተና ሁሉ እስከ ሞትም በመታገሥ ተስፋ ያደረግነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ መከራን ብንታገሥ፣ እግዚአብሔርንም በማመን በተስፋ ብንጸና ይህ ሁሉ ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ መከራ ለምን እንቀበላልን ስንል “በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፣ ከመከራቸውም አዳናቸው” እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት (መዝ.፻፮.፲9) ተስፋ ያደረግነውን መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡
ቅዱሳን መከራ ሲቀበሉ ለምን ደስ ይላቸዋል?
ቅዱሳን ስለ ሰማያዊው ክብር ሲሉ በምድር እያሉ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ደስ እያላቸው ሳይሳቀቁ በተጋድሎ በመጽናት ይቀበላሉ፡፡ ግባቸው መንግሥተ ሰማያት ስለሆነ በዓለም እያሉ ዲያብሎስ ሥጋቸውን እንጂ ነፍሳቸውን መውሰድ አይቻለውምና ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ ወደ ወኅኒ በተወረወሩ ጊዜ በዝማሬ ማመስገናቸውን ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ “በመንፈቀ ሌሊትም ጳውሎስና ሲላስ ጸለዩ፣ እግዚአብሔርንም በዜማ አመሰገኑት” እንዲል (ሐዋ.፲፮.፳፭)፡፡ በሥጋ ሥቃይ እየደረሰባቸው፣ ዓይናቸው እየፈረጠ፣ አንገታቸው በሰይፍ እየተቀላ፣ ቆዳቸው እየተገፈፈ፣ እጅ እግራቸው እየተቆረጠ፣ በድንጋይ እየተወገሩ በጽናት ስለ ሃይማኖታቸው መስክረው ደስ እያላቸው በሰማዕትነት ለማረፍ ይቸኩላሉ፡፡ “በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፣ ነገር ግን ጽኑ፣ እኔ ዓለሙን ድል ነስቼዋለሁና” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳስተማራቸው በተግባር መስክረው አልፈዋል፡፡
ቅዱስ ዳዊት “ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና፤ ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ” በማለት እንደተናገረው መከራ ሲመጣ በፍርሃትና በክሕደት መሸሽ ሳይሆን ለእግዚአብሔር በመታመን እንደ ቃሉም መኖር ይገባል፡፡ አበው መከራ በራቀላቸው ጊዜ ‘ምነው አምላኬ ሆይ ረሳኸኝ’ እያሉ መከራን ሲናፍቁ እንመለከታለን፡፡ በሃይማኖት ምክንያት የሚደርስ መከራ የጽድቅ መንገድ ነውና፡፡ (መዝ.፻፲፰.$)፡፡ በሀገራችንም በዐፄ ሱስንዮስ የንግሥና ዘመን ሃይማኖቱን ለውጦ እናንተም ለውጡ በማለት ባወጀው አዋጅ ምክንያት በኦርቶዶክሳውያን ላይ በተደረገ ዘመቻ አባቶቻችን “ሃይማኖታችንን አንክድም፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” እያሉ ወደ እሳት እየዘለሉ በመግባት ዓለምን ድል እንደነሱ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ “በመከራ መካከል እንኳ ብሔድ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፣ በጠላቶቼ ቁጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፣ ቀኝህም ታድነኛለች” እንዳለው (መዝ.፻፴፯.7)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል ተማርኮ ወደ ባቢሎን በተወሰደና በጉድጓድ ውስጥ ለተራቡ አንበሶች በተጣለ ጊዜ እግዚአብሔርን እያመሰገነ በመገኘቱ የተራቡ አንበሶች የእግሩ ትቢያ ምግብ ሆኗቸው በምላሳቸው እየላሱ፣ በትንፋሻቸው እያሞቁት ተገኝተዋል እንጂ ሊበሉት አልተዳፈሩም፡፡ ናቡከደነጾር ሠለስቱ ደቂቅን ወደሚነደው እሳት እንዲጣሉ ሲያደርግ እግዚአብሔርን ታምነው “እግዚአብሔር ከሚነደው እሳት ያድነናል፣ ባያድነንም አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም” በማለት በመጽናታቸው የፀጉራቸው ጫፍ እንኳን ሳይነካ ከእሳቱ ወጥተዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ቆዳው ተገፎ፣ ሥጋውን እንዲቆራርጠው ጨው ነስንሰው ቆዳውን እንደ ስልቻ አሸክመው አሠቃይተውታል፡፡ ነገር ግን መከራውን ሳይሳቀቅ ተጋድሏል፡፡ በሥጋም በነፍስም ታምኖ መገኘት በተስፋ ለምንናፍቀው መንግሥተ ሰማያት ያበቃልና፡፡
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ዘመናቸውን በተጋድሎ አሳልፈው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን ዓለም ያደረሳባቸውን መከራ ታግሠው በሰማዕትነት ወደማያልፈው ዘለዓለማዊ መንግሥተ ሰማያት ተሸጋግረዋል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መከራን መታገሣቸው ለዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ለመብቃታቸው ድልድይ ሆኗቸዋልና መከራውን በደስታ ተቀብለውታል፡፡
ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስም ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በስም የምናውቃቸውና የማናውቃቸው ቅዱሳን ፃድቃን ሰማዕታትን አፍርታለች፡፡ በቅዱሳን ጸሎትና ቃል ኪዳን ተጠብቃ ያለች፣ ወደፊትም የምትኖር ናት፡፡
በየዘመናቱ በተለይም በታሪክ ከሚታወቁት ውስጥ ዮዲት ጉዲት፣ ዐፄ ሱስንዮስ፣ አሕመድ ግራኝ እና ሌሎችም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳረፉት ጠባሳ እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም በዓለት ላይ ተመሥርታለችና የሲኦል ደጆች አይችሏትም እንደተባለው ለጥፋት የተነሡት ሲያልፉ እርሷ ግን ዛሬም በቅዱሳን፣ ጻድቃን ሰማዕታት ደም አብባና አጊጣ ታበራለች፣ ወደፊትም ትቀጥላለች፡፡
በዘመናችን ካለፉት ዐርባ ዓመታት ወዲህ የተነሡና እግዚአብሔርን የማያውቁ፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር የራቁ መሪዎች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿ የመከራ ገፈት ሲቀምሱ ኖረዋል፡፡ ሀገርን የመሠረተችና ያጸናች፣ ለአንድነትም የቆመች ሆና ሳለ፣ ፊደል ቀርጻ፣ ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ የትምህርትን ብርሃን ለትውልድ በመስጠት በሥነ ምግባር አንፃ እንዳላኖረች ዛሬ ዛሬ ለውለታዋ ምላሽ የሌላትን ስም እየሰጡ አብያተ ክርስቲያናትን ለእሳት፣ ልጆቻን ለጥይትና ለሰይፍ እየዳረጓት ይገኛሉ፡፡
በየጊዜው የሞት ድግስ ደግሰው፣ ነጋሪት ጎስመው በግልጽም በሥውርም የጥፋታቸው ሰለባ እየሆነች ነው፡፡ ሳውል የተባለው ጳውሎስ ለአይሁድ እምነት ታማኝ በመሆን ክርስቲያኖችን ለማሰደድ ከሊቀ ካህናቱ ደብዳቤ ጠይቆ በወጣበት ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማስቆ ላይ ገልጦ “ሳውል፣ ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “አንተ ማነህ?” በማለት ነበር ጥያቄውን በጥያቄ የመለሰው፡፡ ጌታችንም “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስብሃል” ነው የተባለው፡፡ ገዳዮች በሥጋ ገደልን ሊሉ ይችላሉ ነገር ግን እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችን በሥጋም በነፍስም ሲቀጣ፣ ሰማዕታትን ለክብር ለመንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፤ “መኖሪያችን በሰማይ” ነው እንደተባለ፡፡ በእግዚአብሔር የሚታመኑት መከራውን በመታገሥ ሰማያዊውን መንግሥት በተስፋ ሲጠብቁ ገዳዮች ግን ምድራዊውን ብቻ ይመለከታሉ፡፡ (ሐዋ.9.፩-፮)፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የመንግሥትን መለወጥ መነሻ አድርገው ቀስቶቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿ ያነጣጠሩና የተወረወሩ ቢሆንም ብዙዎች ለሰማዕትነት በቅተዋል፡፡ ታርደዋል፣ ሥጋቸው ለአሞራ ተሰጥቷል፣ መሬት ለመሬት ተጎትተዋል፣ ቤት ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ተሰደው ለሥቃይ ተዳርገዋል፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱም ተጠልለው እጆቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው፣ ዕንባቸውን ወደ ሰማያት እየረጩ ይገኛሉ፡፡
ዛሬም በተለያዩ ቦታዎች ብልጭ ድርግም የሚሉ ጥቃቶች በኦርቶዶክሳውያን ላይ እየደረሱ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ክፉ ላደረጉብኝ ክፉ ልመልስ ሳትል ከልጆቿ አልፋ በጠላትነት ለተነሡባት ጭምር እየጸለየች ትገኛለች፡፡ “ክፉን በክፉ አትመልሱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ እንጂ” እንደተባለ፡፡
ትላንት አልፏል ዛሬ ከትላንት ጠባሳ ተሻግረን ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ይኖረን ዘንድ ተግተን መጸለይ ከኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ይጠበቃል፡፡ ጠላት ተኝቶ ባያደርም፣ ክፉን ለመሥራት ቢያደባም ሁሉን ለሚችል አሳልፎ በመስጠት በተስፋ ልንጸና ይገባል፡፡ ቀድሞ የእነ ዮዲት ጉዲት፣ የአሕመድ ግራኝና የመሰሎቹን ጦር የሰበረ እግዚአብሔር ይታደገናል፡፡ “ባያድነን እንኳን….” በማለት ወደ እሳቱ ጥልቅ የተወረወሩትን ሠለስቱ ደቂቅን እናስብ፡፡ እግዚአብሔር አባታችን አድኖ አሳይቶናልና፡፡ “በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፣ መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፣ በመከራም ተስፋ ይገኛል፣ ተስፋም አያሳፍርም፣ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቷልና” (ሮሜ ፭.፬-፭) እንዲል እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ እንጽና፡፡
ያለፉት ዓመታት የመከራ ዝናብ በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ቢወርድም እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ መከራውን በመታገሥ አልፈነዋል፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስና ሕሊና ሆነን በጎ ዘመን፣ የአንድነትና የሰላም ዘመን እንዲመጣ ተስፋ ሰንቀን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ “የሙት ልጆች ትሆኑ ዘንድ አልተዋችሁም፣ ወደ እናንተ እመጣለሁ፣ … ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አምላካችን የሚሠጠንን ሰላም መጠበቅ ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ በመከራም ተስፋ ይገኛልና እግዚአብሔር አምላካችን መከራውን አሳልፎ በጎውን ተስፋ በማድረግ ሰላምን እናገኝ ዘንድ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!