መስቀልና ደመራ

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

መስቀል እግዚአብሔርን ለሚፈሩና በመስቀሉ ኀይል ለሚታመኑ ሁሉ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ መዳኛ፣ የጠላትን ሐሳብ ማክሸፊያ፣ ከማንኛውም ክፉ ነገር መሰወሪያና ማምለጫ ምልክት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት፤ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ”(መዝ.፶፱፥፬) በማለት ትእምርተ መስቀል፤ የመስቀል ምልክት ከሚወረወርብን ከጠላት ጦር ማምለጫ(መመከቻ) መንፈሳዊ ትጥቅ እንደሆነ ጠቅሶታል፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች መስቀል ኀይላችን፣ መመኪያችን፣ ጠላትን ማሸነፊያችን ስለሆነ በብዙ አይነት መልኩ የመስቀልን ምልክት እንጠቀማለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡- በመስቀል ምልክት ማማተብ፣ በአንገታችን ማሠር፣ በግንባራችን መነቀስ፣ ነጠላን መስቀልኛ አጣፍቶ (አመሳቅሎ) መልበስ፣ ማዕድ በመስቀል ምልክት መባረክ፣ ማንኛውንም ነገር ከመጀመር በፊት እና ሠርተን ከፈጸምን በኋላ በመስቀል ምልክት ማማተብና የመስቀሉን ኀይል መማጸን በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ  የማይታጣ ምልክት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ስለሆነ ለቅዱስ መስቀሉ ያላት አክብሮትና ፍቅር ታላቅ ነው፡፡ በተለይም በወር መስከረም በዓለ መስቀሉ በተከታታይ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም ማለት ሁልጊዜም ቢሆን በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ልብ ታትሞ የሚኖር ሲሆን  በእነዚህ ዕለታት በተለይም መስከረም ፲ ቀን ተቀጸል ጽጌ በሚል፣ መስከረም ፲፮ ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓት፣ መስከረም ፲፯ ቀን በጢሱ አመልካችነት ቁፋሮው የተጀመረበትና በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያኑ ታንጾ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት፣ መስከረም ፳፩ ቀን ቅዱስ መስቀሉ በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በግሸን ደብረ ከርቤ ያረፈበት ቀን እና ከመስከረም ፲፯ ቀን እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት በቅዱስ ያሬድ የዝማሬ ሥርዓት መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ዘመነ መስቀል በመባል ይከበራል፡፡

ከላይ እንደ ጠቀስነው የደመራ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን ነው፡፡ የደመራ በዓል በዚህ ዕለት የሚከበረው ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ሥፍራ ለመለየት ደመራ አስደምራ ዕጣን አስጨምራ፣ በእሳት አስለኩሳ የደመራው ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ በመመለስ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት ሥፍራ ላይ ያረፈበት/የጠቆመበት/ ዕለት ነው፡፡

ቅድስት ዕሌኒ በብዙ ድካም ቅዱስ መስቀሉ ያለበትን ሥፍራ በማወቋ ከሕዝበ ክርስቲያኑና ከሠራዊቶቿ ጋር ደስታዋን የገለጠችበት ዕለት በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥነ ሥርዓት በእልታና በዝማሬ በዐደባባይ ታከብረዋለች፡፡

ይህንንም ለአብነት ያህል ብንመለከት በዚሁ በመስከረም ፲፮ ቀን የመስቀል የደመራ በዓል በየዓመቱ በመስቀል አደባባይ አስቀድሞ ደመራ ይደመራል፡፡ ከዚያም ከየአድባራቱ የተወጣጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እጅግ በሚያምሩና በተዋቡ አልባሳት አሸብርቀው ምእመናንም ለመስቀሉ ክብር የሚገባውን ነጫጭ ልብስ በተለይም በባሕላዊ ልብሶች አሸብርቀው በቦታው ላይ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ ለበዓሉ የመደበለት ቃለ እግዚአብሔር በሊቃውንቱ ከቀረበ በኋላ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራንም ያሬዳዊ ዝማሬ ይቀርባል፡፡ በዓሉ የሚከበርበትን ምክንያት የሚያወሳ ታሪክና ልዩ ልዩ ትርኢቶችም ይቀርባሉ፡፡ የደመራውን በዓልና ቅዱስ መስቀሉን አስመልክቶም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና መምህራን ትምህርተ ወንጌል ከተሰጠ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ ደመራው ይለኮሳል፡፡

በዚህ መልኩ በዓሉ በመስቀል አደባባይ ከተከበረ በኋላ በየአጥቢያው ባሉ አድባራትና ገዳማትም እንዲሁ በየደብሩ ካህናትና መዘምራን ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ይከብራል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ቅድስት ዕሌኒ ደመራ አስደምራ በእሳት አስለኩሳ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ በሚያርፈው ጢስ መስቀሉ ያለበትን ሥፍራ ማወቋን በማዘከር ነው፡፡

ነገር ግን አሁን አሁን በአንዳንድ አጥቢያዎች የደመራውን በዓል በየአካባቢው ለማክበር በወጣቶች አስተባባሪነት ገንዘብ እየተለመነና ቅዱሳት ሥዕላት ተይዞ እየተለመነ የሚደረገው የመንደር የደመራ በዓል አከባበር መንፈሳዊ ይዘቱን እየለቀቀ መሆኑ ሁላችን የምንታዘበው ሐቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት ሥዕላት ተይዞ እየተዞረ መለመኑ አንዱ ሃይኖማትን የሚያስነቅፍ ሲሆን እንደዚያ ተለምኖ ደመራው ተደምሮ የሚደረገው የአከባበር ሥርዓትም ጥንቃቄ የጎደለው መሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ትምህርተ ወንጌል ለመስጠት የሚሰየሙት ሰዎች ማንነት ላይ ጥንቃቄ ስለማይደረግ ሾልከው በመግባት የምንፍቅና ትምህርታቸውን ለማስተላለፍ ለመናፍቃኑ በር የሚከፍት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደመራ መለኮስ በኋላ ወጣቶቹ ከወጪ በቀረውና በተረፈው ገንዘብም ይሁን በሌላ መንገድ የአልኮል መጠጦች መጠጣት ይጀምራሉ፡፡ የዝማሬውም መንፈስ ወደ ዘፈንና ጭፈራ ተቀይሮ ለሌላ የርኩሰት ሥራ ራስን ወደ መጋበዝ የማምራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ ከዚህ አልፎ በደመራው በዓል ምክንያት እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ በመጠጥና በጭፈራ ሰፈሩን በማወክ ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ ይታያልና ሁላችንም ለችግሩ የመፍትሔ አካል መሆን ይጠበቅብናል፡፡

እግዚአብሔር ከቅዱስ መስቀሉ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያድለን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *