በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ (መዝ.፩፻፳፭:፭)

በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ

ክፍል አንድ                                      

ይህ የቅዱስ ደዊት መዝሙር የመዓርግ መዝሙሮች ከሚባሉት መካከል የሚመደብ ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግረ ሥጋ ወደ ኢየሩሳሌም፣ በእግረ ሕሊና/ነፍስ/ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ሲወጡ ይዘምሯቸው ስለነበር ይህን ስያሜ አግኝተዋል፡፡ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጠው በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ የምናገኛቸው ቁም ነገሮች እግዚአብሔር በምናውቀውና በምንረዳው በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ምሳሌነት ገልጦልናል፡፡ ዛሬም በእግረ ሥጋ ብቻ ለምንመላለሰውና አንዱንም ላልያዝነው ሰዎች የሚያስተምረን ቁም ነገር አለ፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው የፀደዩን ክፍለ ዘመን /ወቅት/ ተከትሎ የሚመጣው የክረምት ወቅት ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ነው፡፡ ይህ ወቅት በርካታ ተፈጥሯዊ ክስተቶች የሚስተናገዱበት ከመሆኑም በላይ የሰብዓዊ ፍጥረት የኑሮ መሠረት የሆነው የግብርና ሥራ ሌት ተቀን የሚከናወንበት ጊዜ ነው፡፡ አሮጌው ዓመት ፋይሉን ዘግቶ ለአዲስ ዓመት የሚያስረክብበት የርክክብ ጊዜ ነው፡፡ በጥቅሉ ክረምት ሁለት እጁ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ዝናብና ነፋስ የሚበረታበት ላዩ ውኃ ታቹ ውኃ /ጭቃማና ድጥ/ የሚሆንበት፣ ተራራውና ሸንተረሩ በጉም ተጨፍኖ የሚከርምበት፣ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት በደመና ተጋርደው የሚቆዩበት፣ ውኃዎች የሚደፈርሱበት፣ ጎርፍ መሬትን የሚሸረሽርበት፣ ማዕበል ከፍ ከፍ የሚልበት ሲሆን፤ አንድ እጁ ማለትም የክረምቱ ጫፍ መስከረም ደግሞ ሰማዩ ወለል የሚልበት፣ ጨለማው ተወግዶ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት መግቦታቸውን በጠራ ሰማይ ላይ የሚቀጥሉበት፣ ውኆች ከድፍርስነታቸው የሚጠሩበት፣ ምድር በልምላሜና በአበቦች የምታጌጥበት፣ አእዋፍ በዝማሬ የሚደምቁበት፣ የአበቦች መዐዛ የሚያውድበት፣ ቆሻሻውና ደለሉ ተወግዶ ያረገረገው መሬት የሚጠብቅበትና ክረምት ያልተመቻቸው ወይን በለስና እምቧጮ የመሳሰሉት ዕፅዋት የሚለመልሙበት እንዲሁም በልቅሶ የዘሩ ሰዎች ያማረ ቡቃያን ከመልካሙ አበባ ጋር በማየት ደስታን መጥገብ የሚጀምሩበት ጊዜ ነው፡፡

ለመሆኑ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ትእይንቶች ይህ ክፍለ ዘመን /ክረምት/ ምን ሊያስተምረን ይችላል? ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ሁሉ እግዚአብሔር በተፈጥሮ መስተጋብር ውስጥ ብዙ ነገር የሚያሳየን አንድ ቀን እንድንማርበትም ነው፡፡ ይህም በሥጋና በነፍስ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳ ለአእምሮ የቀረበ /የተረዳ/ ጉዳይ ነው፡፡ የክረምት ሰፋ ያለ  የመጀመሪያው ንዑስ ክፍል የሁላችንንም የጨለመ፣ የደፈረሰና የተሸረሸረ ውጣ ውረድ የበዛበትና ያረገረገ /ላላ/ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት የሚጠቁም ነው፡፡  በብልሹ አሠራር በዘረኝነት፣ በሙስና እና በሕገወጥነት ዳኝነት የተመረዘውን ሥጋዊና መንፈሳዊ አስተዳደርም ሆነ በእነዚሁ ጠንቅ የተሽመደመደውን የግልና የጋራ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚጠቁም መልእክት የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በሁለተኛ ንዑስ ክፍል ደግሞ ከጠቀስነው የተበላሸ ሕይወት ወዴትና እንዴት መሸጋገር እንደሚገባን ያሳየናል፡፡

በዓመቱ ውስጥ በሥጋ ፍሬዎች /በኃጢአት/ በመመላለስ ያዳጎስነውን ቡራቡሬ ወይም ጥቁር ፋይል እንዴት ለአዲስ ዓመት ማስረከብ እንዳለብንም ያመለክተናል፡፡ ተፈጥሮ እንኳን አዲሱን ዓመት አስተካክላና አስወባ ለሚኖሩባት ፍጥረታት ካቀረበች እኛ ደግሞ ምን ያህል ሰውነታችንን አስተካክለን ለአዲሱ ዕቅድ ሥራና ሕይወት ማዘጋጀት ይገባን ይሆን? በኃጢአት የጨለመ ሰውነታችንን በንስሓ ብርሃን አብርተን የተዝረከረከና የደፈረሰ ሥነ ምግባራችንን በቁርጠኝነት አጥርተን የዘረኝነት ደለል አስወግደን የውስጥ ጎርፍ የናደውን ሕይወት በሃይማኖትና በምግባር አድሰን ሰውነታችንና ቤተ ክርስቲያናችን በቅድስና መዓዛ እንድታውድ ልንነሣ ይገባል፡፡ ያልረጋ /የላላ/ መንፈሳዊ ሕይወታችንና የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር እግዚአብሔር ጠብቆ የጠወለጉ የፍቅርና የሰላም ዛፎች አብበው እንዲታዩ ወርኃ ክረምትን አብነት አድረገን እንትጋ፡፡

ካለፉት ዓመታ በቅብብሎሽ መጥቶ በ፳፻፲፫ ዓ.ም ደግሞ የዕዳ ደብዳቤዎች ተደርቶ የተከማቸውን ፋይላችን የኃጢአት ቆሻሻ ደለል እንደተሸከመ እንዳሸጋገር ብርቱ ጥረት ማድረግ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለውን ሁሉ የሚመለከት ወቅታዊ ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ነው በልቅሶና በመከራ መከፈል ያለበትን መሥዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይጠበቅብናል፡፡ የመንፈስ ፍሬዎች በደስታ መሰብሰብና በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ሁላችንም በገነት መንግሥተ ሰማያት መሰብሰብ የምንችለው ያኔ ነው፡፡

ነቢዩ ዳዊት በኃይለ ቃሉ ውስጥ በቀጥታ በልቅሶ የሚዘሩ ሲል፡-

፩ኛ. ከላይ በዘረዘርናቸው አስቸጋሪ የክረምት ተፈጥሯዊ ክስተት ውስጥ ራስን አሳልፎ በመስጠት መከራውን ሳይሰቀቁ አርሶ አደሮች የሚቀበሉትን የውዴታ ግዴታ ስቃይ መግለጽ ነው፡፡

፪ኛ. የከረመው እህል ከጎተራ አልቆ /ተሟጦ/ መሶቡ ጎድሎ እያለ በመጨከን ዘር ቋጥሮ ለመሬት አደራ የሚሰጥበትንና አንጀትን አሥሮ እየተራቡ የሚሠራበትን እልህ አስጨራሽ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ገበሬው በዚህ ወቅት ከእርሻ ጀምሮ የሚታወቁትንና ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርጋቸውን ግብግብ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው ልቅሶ በማለት የጠራው ይህንን ወቅት ነው፡፡ /መክ.፫፤፬/ አርሶ አደሩ ይህንን መሥዋዕትነት ወድዶ ፈቅዶ የሚቀበለው በመከራ ጊዜ የሚያገኘውን እጥፍ ድርብ ምርት /ደስታ/ በማስብ ነው፡፡ በኋላ ተስፋ ስለሚያደርገው ጥጋቡ በክረምት ይራባል፣ ደስ እያለው ፍሬውን ሊሰበስብ በታላቅ መከራ ውስጥ ይዘራል፡፡ ከዚህ ተጨባጭ ክስተት መማር ካልቻልን በእውነት ከምን ልንማር እንችላልን፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ይህን አጠቃሎ ሲያስቀምጠው “በሄዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሠማሩ በተመለሱ ጊዜ ነዶዋቸውን ተሸክመው ደስ እያለቸው ይመጣሉ” ይላል፡፡ /መዝ.፩፻፭፤፮/፡፡ በኋላ ስለሚመጣውና ስለ ዘለዓለማዊው ደስታ ዛሬ በጊዜያዊው ዓለም ውሰጥ የሃይማኖትንና የምግባርን ዘር በልቅሶና በፈተና እንዝራ፤ ሁላችንም በምናውቀው በዚህ እውነት ውስጥ እግዚአብሔር የሚያስተምረን ብዙ ነገር በቅዱስ ዳዊት አድሮ በርእሰ ጉዳያችን ያነሣነውን ኃይለ ቃል ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል፡፡ እነዚህ በተራ በተራ እያነሣን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

ሀ. ስላለፈው ዘመን ተናግሮታል፡-

ነቢዩ ዳዊት ከእርሱ ዘመን በፊት ስለነበረው የእስራኤላውያን መንፈሳዊ ሕይወት የተናገረውን የሚያመለክት ነው፡፡ ሁለቱን ዐበይት ክንውኖች መነሻ አድርገን የተናገረውን እንመልከት፡-

፩ኛ. የግብፅ የባርነት ሕይወት፡- ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ወንድሞቹ የሸጡት፣ ግብፅም ይባስ ብሎ የጲጢፋራ ሚስት በሐሰት ከሳው ወደ ወኅኒ ቤት የወረደው በዕንባና በታላቅ ልቅሶ ሲሆን የልቅሶ አዝመራውን የሰበሰበው ግን በቤተ መንግሥት በደስታ ነበር፡፡ /ዘፍ.፴፯፤፴፱፤ ፵፥፵፩/፡፡ አባቱ ያዕቆብና ቤተሰቡ ሁሉ ወደ ግብፅ እህል ፍለጋ የወረዱት በረሃብና በመከራ በታላቅ ልቅሶም ነው፡፡ በባዕድ ምድር የተወሰኑት አንጻራዊ የዕረፍት ዓመታት ቢኖሩም ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ፈርኦን ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የነበረው የግብፅ ኑሮዋቸው የልቅሶና የሰቆቃ ሲሆን ኪዳነ አብርሃም፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ያልዘነጋው አምላከችን እግዚአብሔር በጸናች እጁ፣ በተዘረጋች ክንዱ ከግብፅ የመለሳቸው /ያወጣቸው/ ደግሞ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ በልቅሶና በመከራ ውስጥ የዘሩት ዕንባና የተቀበሉት ግፍ የደስታ ፍሬ ሲያሳፍሳቸው እንመለከታለን፡፡ በዘር የተመሰለ ተስፋ /ኪዳን/ አበውን ተሸክመውና እግዚአብሔር እንደማይተዋቸው ተማምነው እያለቀሱ ግብፅ ወረዱ፡፡

የአባቶቻቸው አምላክም አብሮአቸው በረድኤት ግብፅ ወረደ፡፡ በተመለሱ ጊዜም በነዶ የተመሰለ ተአምራት ተደርጎላቸውና ነፃነት ተጎናጽፈው ጭቃ፣ ጡብ፣ ድንጋይና የመሳሰሉትን ያለ ርኅራሄ እያሰቃየ ላሰቃዩአቸው የነበሩ ግብፃውያንን በተራቸው መሸከም የማችሉት ውኃ አሸክመው “ንሴብሖ፣ እናመስግነው” እያሉ በደስታ ወደ ምድራቸው ከነዓን ተሰበሰቡ፡፡ ባለቅኔው “አይተርፍ ግፍዕ ለዘዕድሜሁ ጎንድየ፤ አስራኤል ለፈርኦን እስመ አጸርዎ ማየ፤ የግፍ ጊዜ ቢረዝም አይቀርም እስራኤል ፈርኦንን ውኃ አሸክመውታልና” ያለውን ይህን ታሪክ ጠቅልሎ አስውቦ ያቀረበበት ምሥጢር ነው፡፡ ታሪኩ በዮሴፍ ዓይነት ሕይወት በሐሰተኛ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ለመከራና ለሰቆቃ የተሸጡ፣ እየተሸጡ ያሉና የሚሸጡ አልፎ ተርፎም ታሪክ ተዘግቶባቸው እንኳን ሊሠሩት አስበውትም የማያውቁት ጉዳይ የመከራ እንጀራ እንዲበሉ የተፈረደባቸው ወገኖቻችን አንድ ቀን የእውነት አምላክ በደስታ እንደሚያወጣቸው ያስተምረናል፡፡

ትጋታቸውን፣ የለውጥ ርእያቸውን፣ ቅን አስተሳሰባቸውን እና ንጽሕናቸውን የማያውቁ፣ ሊያውቁ የማይወዱና እያወቁም ሰይጣናዊ ቅንዓት በልቡናቸውን ያነጹ ናቸው፡፡ አሰሪዎች አለቆች በሚፈጥሩት መሰናክል በግድ ተጠልፈው የወደቁ ብዙ ወገኖቻችን ልቅሶና ዋይታ ወደ አሸናፊ እግዚአብሔርም በተስፋ ደጅ የሚጠኑትን ልጆቹን ዕንባ የሚያብስበትንና ጠላቶቻቸውን የሚያደቅበት ጊዜ አለው፡፡ /መዝ.፻፵፮፤፲/፡፡ የዘገየ ቢመስለንም እንኳን በተሰጣቸው ጊዜ ከክፋታቸው እስኪመለሱ ወይም ኃጢአታቸውን ፈጽመው እስኪሠሯት ድረስ እየጠበቀችው እንደሆነ መሆኑን አውቆ በትዕግሥት መጽናት ከዮሴፍና ከእስራኤላውያን የምንማረው ቁም ነገር ነው፡፡

፪ኛ. የባቢሎን የምርኮ ሕይወት ማርና ወተት የምታፈሰውን ተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ከወረሰ በኋላ ዘወትር እንዲያስታውሱትና እንዳይረሱት የተናገራቸውን የአባቶቻቸውን መከራና የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ፣ የተሰጣቸውንም ትእዛዝ ዘንግተው ፈጣሪያቸውን በማሳዘናቸው እስራኤላውያን ሌላ የመከራ ዘመን ገጠማቸው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ደጋግሞ ቢያስጠነቅቃቸውም ሊሰሙ ባለመፈለጋቸውና በነቢዩም ላይ በክፋት በመነሣታቸው ባቢሎናውያን ጓዝ፣ ትብትብ አሸክመው ምድራቸውን አጥፍተው እነርሱን በመማረክ ባቢሎን አወረዷቸው፡፡ ዘር ተስፋ ሚጠትን /መመለስን/ ተሸክመው እያለቀሱ ወረዱ፡፡ በታላቅ ግዞት ቀንበር ሥር ወድቀው በሰቆቃ ሰባ ዓመታትን ከኖሩ በኋላ የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር አስቀድሞ “በልቅሶ ወጡ፣ እኔም በመጽናናት አመጣቸዋለሁ” /ኤር.፴፩፥፱/ በማለት እንዳናገረው በደስታ ሰበሰባቸው፡፡

እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባው የብዙዎቻችን ድክመት ያለፈውን የመከራም ሆነ የደስታ ጊዜ መዘንጋትና ካለፈው ጥሩም ሆነ መጥፎ ድርጊት መማር አለመቻላችን ነው፡፡ ክረምት ላይ በጋን፣ በጋም ላይ ክረምትን እንረሳለን፣ ወይም አናስብም፡፡ በክረምት እያፈሰሰ ያስቸገረን የቤት ጣሪያ /ቆርቆሮ/ የምናስታውሰው ሌላኛው ክርምት ሲመጣ ነው፡፡ በበጋ ችግራችንን ሁሉ ረስተን በሌላ ጉዳይ ላይ እንጠመዳለን፡፡ በተደላደልንበት ወቅት የተቸገርንበትን፣ በጠገብንበት ወቅት የተራብንበትን፣ ባለ ሥራ በሆንበት ሰዓት ሥራ አጥ የነበርንበትን፣ በሣቅንበት ጊዜ ያለቀስንበትን … ማሰብ ካልቻልን በሌላ የመከራ ድግስ ዋዜማ መሆናችንንና በተስፋ ለመጽናትም እንደምንቸገር ያስረዳናል፡፡ አንዳንዶቻችን ለሌሎች ወገኖቻችን የማንራረውና በሚያለቅስ ዐይናቸው በርበሬ፣ በቁስላቸውም ውስጥ እንጨት የምንጨምረው የራሳችም ያለፈውን የመከራ ጉዞአችንን መለስ ብለን ለማየት ባለመፈለጋችን ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተጠራቅመው ወደተለየና ወደ ባሰ የመከራ አዘቅት ያወርዱናል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ ግን ከሰው ግፍና ኃጢአት ይልቅ ሊነገር በማይችል መጠን ስለሚበልጥ በመከራቸው ውስጥ ሆነው በእምነት የፀፀት ዕንባቸውን ለሚረጩትና የተስፋ እጃቸውን ለሚዘረጉት ሁሉ እርሱም የቸርነት እጁን ልኮ ያወጣቸዋል፡፡ ከባቢሎን ምርኮኞች ሕይወት ያየነው ይህንን ነው፡፡

በኃጢአታቸው ምክንያት እያለቀሱ ቢወርዱም ነዶ ሚጠትን /ነፃነትን/ ተሸክመው ደስ እያላቸው ወደ ምድራቸው ተመልሰዋል፡፡ አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚቀጣ ተቆጥቶ ቢቀጣም አምላካችን የልጆቹን የመከራ ዕንባ እያየ የሚጨክን ልብ /ባሕሪ/ የለውም፡፡ የደረሰውን መከራ እያበላለጡ ብቻ ሳይሆን ይበልጡንም ፈጣሪያችንን በደልነው፣ አሳዘንነው እያሉ በመጸጸት የሚያለቅሱ ምእመናን የእግዚአብሔርን የይቅርታ ድምጽ ለመስማትና በምሕረት እጆቹም ለመዳሰስ የቀረቡ ናቸው፡፡ “አልቦ ካልዕ ሕሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጠአቱ፤ ለአዳም ስለ ኃጢአቱ ከማልቀስ በስተቀር ሌላ ሐሳብ የለውም” ተብሎ ለአዳም እንደተነገረ በመከራችን ውስጥ ኃጢአታችንን እያሰብን ወደ አምላካችን ልናንጋጥጥ ያስፈልጋል፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *