ቆይታ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ጋር
ክፍል አንድ
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ካለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በማስተማርና በማስመረቅ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ዘመኑ የዋጀ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን በመስጠት ተመራቂዎች ሀገራቸውንና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ እንዲሆኑ በትጋት ይሠራል፡፡ በየዓመቱም በርካቶች በተማሩት ትምህርት ውጤታማ ሆነው ዋንጫና ሜዳልያ ተሻላሚዎች ሆነዋል፡፡ “ለዚህ ውጤት እንድንበቃ ማኅበረ ቅዱሳን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል” በማለት ዋንጫና ሜዳልያቸውንም ለማኅበሩ ሲያበረክቱ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡
በ፳፻፲፭ ዓ.ም የቤተ ክርስቲያንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት ውስጥ በርካቶች የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ስለ ቆይታቸውና ስለ ውጤታማነታቸው አነጋግረናቸዋል ቀጥለን እናቀርብላችኋለን፡፡
“እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ እንደሚያደርገኝ አልተጠራጠርኩም” (ውብነሽ ለማ)
ውብነሽ ለማ ከ፳፻፲፭ ዓ.ም የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጅነሪኒንግ ትምህርት ክፍል ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ዘጠኝ (3.99) አጠቃላይ ውጤት በማምጣት የዩኒቨርሲቲው ዋንጫ እና ሁለት ሜዳልያዎች ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡
ዝግጅት ክፍላችንም ስለ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እና ግቢ ጉባኤ ቆይታዋ አነጋግረናታል፡፡
ውብነሽ ቆይታዋን ስትገልጽ “ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድቤ ስሄድ ቦታው ገና አዲስ ስለ ነበር ፍርሃትና ግራ መጋባትም ገጥሞኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ዓላማዬን ለማሳካት ምን ማድረግ አለብኝ ለሚለውና በኅሊናዬ ለሚመላለሰው ጥያቄ መልስ የሆነኝ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖርን ነው፡፡ እንደ ዓላማም አድርጌ የገባሁት ራሴን ውጤታማ ሆኜ መውጣትን ነው፡፡ እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫም እንደሚያደርገኝ አልተጠራጠርኩም፡፡ ለዚህም መሸሸጊያ ያደረግሁት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡ ቦንጋ ስደርስም በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው የሄድኩት፡፡” በማለት ትውስታዋን አጋርታናለች፡፡
ጊዜ አጠቃቀሟን በተመለከተ ስትገልጽም፡- “ጊዜዬን በትምህርቴ፣ በጥናቴና በቤተ ክርስቲያን እንዲወሰን ማድረግ ቻልኩ፡፡ ቀድሞም በአካባቢዬ ባለው ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አገለግል ስለነበር ሕይወቴን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ማቆራኘት አልከበደኝም፤ ሌላም የሕይወት ተሞክሮ አልነበረኝም፡፡ በቅድመ ግቢ ጉባኤም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረ ቅዱሳን በሚሰጠው የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በሰንበት ትምህርት ቤታችን ስንሸኝም የተመከርነው ምክር ስንቅ ሆኖኛል” ብላለች፡፡
ጊዜዋን በአግባቡ መወጣት እንዳለባት ራሷን በማሳመን በዕቅድ በመመራት በተግባርም እንደፈጸመችው የምትገልጸው ውብነሽ ስለ ጊዜ እንዲህ ትላለች፡፡ “ጊዜን በተመለከተ ከቤተሰብ እንደመለየታችን መጠን በራሳችን ላይ የምንወስነው እኛው ብቻ ስለሆንን ነጻነት ይሰማናል፡፡ ብዙዎችም ለመዝናናትና ለማይጠቅሙ ነገሮች ጊዜያቸውን ስለሚያባክኑ ውጤታቸው ላይ ደካማ ሆነው ይገኛሉ፡፡ እኔ ግን ከትምህርቴ በኋላ ከቀኑ ፲ ሰዓት ጀምሮ የምገኘው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ አጋጣሚ አስቸኳይ ነገር ሲገጥመኝ ግን በሌሊቱ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሜ እመለሳለሁ፡፡ በነበረኝ ቆይታዬም ቤተ ክርስቲያን ሳልደርስ የቀረሁበት ጊዜ የለም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የተለየ ሕይወት ስለሌለኝ መብቴ ብቻ ሳይሆን ግዴታዬም አድርጌ ነው የቆየሁት፡፡ ከትምህርቴ፣ ከጥናት እና ከቤተ ክርስቲያን ውጪ የማሳልፈው ጊዜ ኖሮኝ አያውቅም፡፡
ስለ ጓደኛ ተጽእኖ ላቀረብንላት ጥያቄም “በአጋጣሚ ዓላማችን ተመሳሳይ የነበረ ዐራት ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞችና እኅቶች ነበርን የተገናኘነው፡፡ በጣም ደስ የሚል ቅርበት ስለነበረን እንደጋገፋለን፣ አንዱ የሚያውቀውን ለሌላው ለማካፈል አይሰስትም፡፡ በጓደኛ ደረጃ ተሳክቶልኛል ማለት እችላለሁ፡፡ ያም ሆኖ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ የመጀመሪያ ዓመት ላይ በርካታ ዓይኖች ይፈትኑኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት ሁሉን አለፍኩት፡፡ ለዚህም ራሴን በሦስት ነገሮች መጥመዴ ጠቅሞኛል፡፡ በትምህርቴ፣ በቤተ ክርስቲያን(ግቢ ጉባኤ) እና ጥናቴ፡፡
በመማር ላይ ላሉና ወደፊት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች ባስተላለፈችው መልእክትም “ዓላማቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ በኦርቶዶክሳዊነታቸውና በውጤታማነታቸው ከራሳቸው አልፈው የቤተሰቦቻቸው እና የቤተ ክርስቲያን ኩራት እንደሚሆኑ መገንዘብ አለባቸው፡፡ ማንኛውንም አስቸጋሪም ይሁን መልካም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢገጥማቸው መሸሸጊያቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ማሰብ፣ በሯን ከፍታም እንደምትቀበላቸው አምነው መጠለል ይገባቸዋል፡፡ ክርስቲያን ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ምን ሕይወት አለው? ስለዚህ ተስፋ በመቁረጥ እንዳይዘናጉ፣ ከግል ጥረት ጋር እግዚአብሔርን መመኪያ አድርጎ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል” በማለት ከተሞክሮዋ አካፍላናለች፡፡
በቀጣይ በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ የሌሎችን ኦርቶድክሳውያን ውጤታማ ተመራቂዎች ተሞክሮዎችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!