ቅድስት ሥላሴ
የሁሉ ፈጣሪ የዓለም ገዢ አምላካችን እግዚአብሔር ለስሙ ክብር ይግባውና በሐምሌ ፯ ቀን ወደ ጻድቁ አብርሃም ቤት በመግባት በአንድነትና በሦስትነት ክብሩ ተገለጠለት፡፡ በዚህች በከበረችም ቀን አብርሃም በደጃፉ ሆኖ ዓይኖቹን አንሥቶ ሲመለከት ሦስት አረጋውያንን አየ፤ ሮጦ ሄዶም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁን እንጠባችሁ፡፡ ከዛፉም ሥር ዕረፉ፤ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ ከአረፋችሁ በኋላ፥ ወደ አሰባችሁት ትሄዳላችሁ›› አላቸው፡፡
‹‹እንደምታየን ሽማግሌዎች ነን፤ የመጣነው ደግሞ ከሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ አዝለህ ወደ ድንኳንህ አስገባን›› አሉት፡፡ አንደኛውን አዝሎ ወደ ድንኳን ሲያስገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ገብተው ተገኙ፡፡ አብርሃምም ነገሩ እየረቀቀበት ሲሄድ በጓዳ ለነበረችው ለሚስቱ ሣራ ‹‹ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፡፡
ሚስቱ ሣራም እንዳዘዛት አድርጋ ጋግራ አቀረበች፤ እርሱም ቤት ለነበረ አንድ ብላቴና ወይፈኑን አርዶ አወራርዶ እንዲያመጣለት ካዘዘው በኋላ ከወተትና ማር ጋር አብሮ አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም አብርሃምን ደስ ለማሰኘት በሉ፤ መብላታቸውም እሳት ቅቤ በላ እንደ ማለት ነው፤ በግብር አምላካዊ ነውና አይመረመረም፡፡ ከዚያም የታረደውና የተወራረደው ወይፈንም ተነሥቶ በድንኳኑ ደጃፍ ‹‹ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ ሥላሴን አመሰገነ፡፡
አብርሃም ደነገጠ፡፡ ‹‹እንግዳ ከመጣልህ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና ሆነህ ተቀበል፤ እንግዳ ካልመጣ ጾምህን አትደር፤›› አሉት፤ ከዚያም ስለ ይስሐቅ አበሠሩት፡፡ (ዘፍ. ፲፰፥፩-፰፣አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፰)
ጻድቁ አባታችን አብርሃም አምላኩን ለማወቅ ሽቶ በእምነትና በሃይማኖት ጽናት ሥላሴን በአንድነትና በሦስትነት ለማየት በቅቷል፡፡ በእርሱም የጽድቅ ሥራ ለብዙዎች ድኅነት ከመሆን አልፎ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹የአብርሃሙ ሥላሴ›› በማለት አብርሃምን ታመሰግነዋለች፡፡ ቅድስት ሥላሴ የሁሉ ፈጣሪ በመሆናቸው ክርስቲያን የሆነ ሁሉም የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ሊያውቅ ይገባል፡፡
በ ‹‹ምሥጢረ ሥላሴ›› ትምህርት እንደምንረዳው ቅድስት ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ ‹‹ሥላሴ›› የሚለው ቃል ‹‹ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ (መጽሐፍ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፷፱)
ቅድስት ሥላሴ ስንልም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/ ይጠራል፤ ‹‹ቅድስት›› እና ‹‹ልዩ ሦስት›› የሚባልበትም ሃይማኖታዊ ምሥጢር፡-
፩. ቅድስት
ሥላሴ ‹‹ቅድስት›› ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ሴት /እናት/ ልጅዋን መውለዷን እንደማትጠረጥረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም መፍጠራቸውን ስለማይጠረጥሩ ነው፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣ ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት ወይም እናት ልጅዋ ቢታመምባት እንዲሞትባት አትሻም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ እንኳን በጠላት ዲያብሎስ እንዲገዛባቸው አይፈቅዱም፡፡ ሴት ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን እንደምትመግበው ሥላሴም በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ ስለሚመግቡ ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እያልን እንጠራቸዋለን፡፡
፪. ልዩ ሦስትነት
በትምህርተ ሃይማኖት ሥላሴ በቅድምና፣ በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በመመስገን፣ በክብር፣ በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
ሀ. በስም
የቅድስት ሥላሴ የስም ሦስነትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተብለው መጠራታቸው ነው፡፡ አብ በራሱ ስም አብ ይባላል እንጂ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ይባላል እንጂ አብ ወይንም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወይም ወልድ አይባልም፤ ስማቸው ፈጽሞ የማይፋለስ ነውና፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት በአንጾኪያ ተሹሞ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹አብሂ ውእቱ አብ ወኢኮነ ወልደ ወኢ መንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ ውእቱ ወልድ ወኢኮነ አበ ወኢ መንፈሰ ቅዱሰ፣ ወመንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ ኢኮነ አበ ወኢ ወልደ፣ ኢይፈልስ አብ ለከዊነ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢ ወልድ ለከዊነ አብ ወወልድ፤ ወኢ መንፈስ ቅዱስ ለከዊነ አብ ወወልድ፤ አብም አብ ነው እንጂ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፤ ወልድም ወልድ ነው እንጂ አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፤ ወልድም አብን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፤ መንፈስ ቅዱስም አብን ወልድን ወደመሆን አይለወጥም›› ብሏል፡፡ (ሃይ. አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. ፲፩. ገጽ. ፴፯)
የቅድስት ሥላሴ ስማቸው ከአካላቸው፣ አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡ (መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. ፴፪)
ስለዚህም ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ‹‹ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት፡፡ ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱ… ወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም አይደለም፡፡ ባሕርዩ ነው እንጂ የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ ናቸው እንጂ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ (ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ፲፫፥፬-፰ ገጽ ፵)
ለ. በአካል
የቅድስት ሥላሴ የአካል ሦስትነታቸው ደግሞ አብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ሊቁ አቡሊዲስ ስለ ሥላሴ የአካል ሦስትነት ሲገልጽ ‹‹ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ መለኮቶሙ ዘበአማን፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣ በአካል ፍጹማን እንደሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› ብሏል፡፡ (ሃይ. አበ. ዘአቡሊዲስ ምዕ. ፴፱፥፫ ገጽ ፻፴፯)
ሐ. በግብር
የቅድስት ሥላሴ የግብር ሦስትነታቸው ሲተረጎም የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረፅ ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርፇልና፡፡ የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረፅ ነው፤ ከአብ ሠርፇልና፡፡
አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርፅም፡፡ ወልድ ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርፅም፤ አያሠርፅም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቢሠርፅ እንጂ አይወለድም፤ አያሠርፅም፤ በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ተብለው ይጠራሉ፡፡
በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መርምሮ መረዳት ለማንም ቢሆን አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ ጥምቀት ተገልጧል፡፡ እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ በቀናች ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡
ምንጭ፡– ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ፣ መጽሐፍ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት በአለቃ ኪዳነ ወልድ፣ ሃይማኖተ አበው (ዘቅዱስ አግናጥዮስ፣ ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ
መንክራት፣ዘአቡሊደስ) እና መንገደ ሰማይ–በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!