ምኵራብ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንትን ምኵራብ ብላ ትጠራዋለች። ምኵራብ ሰቀላ መሰል አዳራሽ፣ የአይሁድ የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁድ በኢየሩሳሌም ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት ቤተ መቅደስ ነበር፡፡ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን    በመውረር ቤተ መቅደሳቸውን አፍርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን ካፈለሰ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ምኵራብ መሥራት እንደ ጀመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትይገልጻል፡፡

አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግና የነቢያት መጻሕፍትን (የብራና ጥቅሎች) በአንድ ሣጥን ውስጥ በማስቀመጥ የጸሎት ስፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባዓ ለመስጠትም ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኦሪትንና ነቢያትን ልሽራቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አመልመጣሁም፡፡” እንዲል ሕግ ሊፈጽም ወደ ቤተ መቅደስ ይሄድ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ብቻ ሳይሆን በምኵራብ እየተገኘም ያስተምር ነበር፡፡ “ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፡፡” (ሉቃ. ፲፱፥፵፯)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ በሚያስተምርበት ወቅት ነጋዴዎች በመሸጥና በመለወጥ ቤተ መቅደሱን ያውኩ ስለነበር ቤተ መቅደሱን ለማስከበር ሲል በዚያ ያሉትን ሻጮችንና ለዋጮችን እየገረፈ፣ የሚሸጡትንም እየገለበጠ አስወጥቷቸዋል፡፡ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ፤ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም “በቤተ መቅደስም በሬዎችና በጎችን፣ ርግቦችን የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም ‘ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ፡፡” በማለት አስወጣቸው፡፡ (ዮሐ. ፪፥፲፬-፲፮) በዚህም መሠረት የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኵራብ ተብሏል፡፡

ዛሬም በዘመናችን የእግዚአብሔርን የቅድስና ስፍራ የሚዳፈሩ፣ ለሙስና እና ለራስ ወዳድነት ያደሩ ከአገልጋዮች እስከ ምእመናን ድረስ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በደሙ የዋጃትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት’ እያለ ዛሬም የእግዚአብሔር ድምፅ ይጣራል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በመንደር፣ … በመከፋፈል ለቃለ እግዚአብሔር ባለመታመን ኃጢአት የምንሠራና የግል ፍላጎታችንን ለማሟላት የምንሮጥ ብዙዎች ነን፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት በመጠበቅ በንስሓ ሕይወት በመመላለስ ከማገልገል ይልቅ ግላዊ ፍላጎትን ለማሟላት የምንሮጥ ሁሉ ራሳችንን መመርመር፣ ከክፉ ተግባራችንም መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ካልሆነ እግዚአብሔር ምሕረቱ የበዛ አምላክ እንደ መሆኑ መጠን ክፉ ሥራችን በበዛ ቁጥር የቁጣ በትሩን ማሳረፉ አይቀርምና በዚህ በዐቢይ ጾም በተሰበረ ልብ ሆነን በይቅርታው ይጎበኘን ዘንድ ዘወትር ያለመታከት ልንማጸን፣ ልንጸልይ  ይገባል፡፡

በዕለቱ የሚነበቡ መልእክታት፣ ምስባክ እና ወንጌል

መልእክታት፡-  

የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት፡- “እንግዲህ በመብልም ቢሆን በመጠጥም ቢሆን በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን በመባቻም ቢሆን በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት በሥርና በጅማትም በሚስማማበት በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት፣ በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡

ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ፣ ይህን አትንካ፣ ይህንም አትቅመስ፣ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት፣ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡” (ቆላስ. ፪፥፲፮-፳፫)

የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት፡- “ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን ወይም ከእኅቶቻችን የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ ከእናንተም አንዱ ‘በሰላም ሂዱ እሳት ሙቁ ትጠግባላችሁም’ ቢላቸው ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡ …”

ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራው ትረዳው እንደ ነበር፣ በሥራውም እምነቱ እንደመላችና ፍጽምት እንደሆነችም ታያለህን? መጽሐፍ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፣ ጽድቅ ሆኖም ተቆጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻ እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጉበኞችን ተቀብላ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡” (ያዕ. ፪፥፲፰-፳፮)

የሐዋርያት ሥራ፡- “በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝብም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ፡- “ቆርኔሌዎስ ሆይ” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና “አቤቱ ምንድነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፡- “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጧል፡፡ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት፣ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ፡፡ ነገሩንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካቸው፡፡” (የሐዋ. ፲፥፩-፱)

ወንጌል

የዮሐንስ ወንጌል፡- “ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ ከወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፣ ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን፣ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፣ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጪዎችንም “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡ …” (ዮሐ. ፪፥፲፪-፳፭)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *