“መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሀ በሰው ፊት ይብራ((ማቴ፭፥፲፮)
መ/ር ቢትወድድ ወርቁ
ክርስቲያኖች በዓለም ስንኖር ሌሎችን ወደ ሃይማኖት ሊያመጣ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርብ የሚችል የሚገባ መልካም አኗኗር ሊኖረን እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ተግባራዊ የክርስትና ሕይወት በቃል ከምንመሰክረው በላይ በሌሎች አርአያነት ተጽዕኖ አለውና፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን የተራራው ስብከቱ ለጊዜው ለቅዱሳን ሐዋርያቱ በፍጻሜው እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡ ክርስቲያኖች ሊኖረን ከሚገባን አኗኗር አንጻር ክርስቲያኖችን በአራት ነገሮች መስሎ አስተምሯል፡፡
ሀ. የምድር ጨው ናችሁ (ማቴ፭፥፲፫)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ”እናንተ የምድር ጨው ናችሁ ጨው አልጫ ቢሆን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም‘ በማለት እንደተናገረው ጨው የገባበት ነገር ሁሉ ይጣፍጣል፡፡ክርስቲያኖች ይልቁንም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም እንዲሁ የዓለሙን ሕይወት የሚያጣፍጡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ሲያስተምር ”የምድር ጨው ናችሁ‘ አለ፡፡ ጌታችን ” እናንተ የምድር ጨው ናችሁ‘ ብሎ መናገሩ የሰው ልጅ በሙሉ ከኃጢአቱ የተነሣ ጣዕም አጥቶ አልጫ ሆኖ እንደነበር ሲያስገነዝብ ነውና፡፡
ስለዚህ እንደዚህ በኃጢአት ምክንያትም አልጫና ጣዕም አልባ የሆነውን የሰውን ልጅ መምራት ይቻላቸው ዘንድ እንዲህ ያሉ ምግባራትን ከደቀ መዛሙርቱ (ከክርስቲያኖች) እንደ ግዴታና ቅድሚያ እንደሚፈለግባቸው እንረዳለን፡፡ አስቀድሞ የዋህና ለጋሽ የሆነ የሚምር ስለ ጽድቅ የሚራብና የሚጠማ ሰው እነዚህን ደገኛ ምግባራት ለሌሎች ሰዎችም እንደ ጅረት ውኃ ይፈስሱ ዘንድ ያደርጋቸዋል እንጂ መልካም ምግባራትን ”ለእኔ ብቻ‘ አይልምና፡፡ ዳግመኛም በልቡ ንጹሕ የሆነ፣ የሚያስታርቅ፣ ስለ እውነት ብሎም የሚሰደድ ሰው ሕይወቱን በአግባቡ የሚመራው ለሌሎች ጭምር ነው፡፡
ጨው ባይጣፍጥ አልጫ ቢሆን ምን ያደርጋል ? ቢክቡት ይናዳል ቢንተራሱት ራስ ይቆርቁራል፡፡ ከተክል ቦታ ቢያደርጉት ተክል ያደርቃል ብለው ሰዎች እንደሚጥሉት እንደሚረግጡትም ክርስቲያኖችም ለሌሎች አብነት ካልሆንን ማን ይሆንላቸዋል? ለሌሎች አብነት መሆን ካልቻልንም ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አንጠቅምምና፡፡ጨው ካልጣፈጠ ወደ ውጭ እንደሚጣል እኛንም ሌሎች ከልቡናቸው አውጥተው ይጥሉናል፡፡በክፉ አኗኗራችን ሌሎች ሰዎችን በማሰናከላችን እግዚአብሔር ከመንግሥተ ሰማያት ውጭ ያደርገናል፡፡
ጨው ሦስት ተግባራት አሉት፡፡ ያጣፍጣል፣ቁስል ያደርቃል፤እንዲሁም ሥጋን እንዳይፈርስ አንዳይተላ ይጠብቃል፡፡ ክርስቲያኖችም የሌሎችን ሕይወት ማምረር ሳይሆን በመልካምነት ማጣፈጥ አለብንና ጌታችን ይህን አስተማረን፡፡ ጨው ቁስል እንደሚያደርቅ ክርስቲያኖችም በኃጢአትና በርኲሰት ተስፋ በመቁረጥና በክሕደት የቆሰለ ዓለምን በወንጌል የተገለጠ መልካም አኗኗርን ገንዘብ በማድረግ ቁስሉን እንድንፈውስለት ጌታችን አስተማረን፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያቱ ክርስቶሳዊነትንና አርአያ ክህነትን ይዘዋልና “ጌታችን እስከምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናል፡፡” በማለት ያስተማሩትንና የሰሙትን ሆነው በመገኘት በተግባር አሳይተው በቃልም መሰከሩ፡፡ ጨው ሥጋን እንዳይተላና እንዳይፈርስ እንደሚጠብቅ ክርስቲያኖችም ይህ ዓለም በእኩይ ምግባር እንዳይፈርስ በዚህም በትል የተመሰሉ አጋንንት እንዳይሠለጥኑበት በአርአያነት አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት ሳይሆን በመጾም፤ አብዝቶ በመቀባጠርና ነገረ ዘርቅ በማብዛት ሳይሆን በአርምሞና አብዝቶ በመጸለይ የአጋንንትን ኃይላቸውን የማድከም ጸጋና ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ (ማር. ፱፥፵፫)
ለ . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ (ማቴ.፭፥፲፬)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” በማለት ያስተማረው ትምህርት ክርስቲያኖች በዓለም ሊኖራቸው የሚገባውን የምሳሌነት (የአርአያነት) ሚናና ድርሻ በሚገባ ያመለክታል፡፡ ክርስቲያኖች አኗኗራችን የክርስትናውን ሚዛን በሳተ ከወንጌል መንገድም ባፈነገጠ ልክ የዓለሙም የበጎነትና የመልካምነት ነገር መስመር ይስታል፡፡ብርሃን ሲጠፋ ጨለማ እንደሚነግሥ በብርሃን የተመሰሉ ክርስቲያኖችም ጨለማ በተባለ ክፉ ሥራ በተዘፈቅን ቁጥር ኃጢአት፣ የፈሪሐ እግዚአብሔር መታጣት፣ ሕገ ወጥነትና ሌሎች እኩይ ምግባራት ይሠለጥናሉ፡፡
ሰዎች ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከመምጣት ይልቅ ወደ አምልኮ ባዕድ፤ ወደ ጽድቅ ከማዘንበል ይልቅ ወደ ኃጢአት፣ ወደ ንስሓ ከመቅረብ ይልቅ ወደ ዓመፅ ይተማሉ፡፡ ይህ በሆነ ቁጥርም ዓለም የጭንቀትና የኃዘን የጦርነትና የሁከት ዋሻና መድረክ ትሆናለች፡፡የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን አብነትነታቸው በብዙ ወገን ነው፡፡ ስካር፣ ዝሙት፣ ሴሰኝነት፣ ጉቦ መቀበል፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ሰዎችን ወደ ጨለማ የሚወስዱ የጨለማ ሥራዎች እንደሆኑ በጎ ሥራዎችም ሰዎችን አማናዊ ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ የሚያመጡ የብርሃን ሥራዎች ናቸው፡፡ስለሆነም ጌታችን ለክርስቲያኖች በሙሉ ይልቁንም በየደረጃው ላሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እነርሱ የሚሠሩት በጎ ሥራ ሌሎች ገንዘብ ያደረጉትን ጨለማ የሆነ ክፉ አሳብ፣ ንግግርና ተግባራቸውን የሚያጠፋ ብርሃን መሆኑን አስተማራቸው (ሮሜ፲፫፥፰-፲፫) ፡፡
ሐ. በተራራ ያለች ከተማና መቅረዝ (ማቴ፭፥፲፬–፲፭)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖችን ”በተራራ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም፡፡ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፡፡ በቤቱም ላሉ ሁሉ ያበራል‘ ብሎ በተራራ ባለች ከተማና በመቅረዝ ላይ በተቀመጠ መብራት መስሏቸዋል፡፡ ይህ የጌታችን ትምህርት ክርስቲያኖች ምንም ጊዜ በሰዎች ሁሉ ፊትና በዓለም የትርኢት ቦታ ላይ እንደቆምን ሆነን በማሰብ ልንመላለስ እንደሚገባን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በመዋዕለ ሥጋዌው ክፉ ለሆኑትም ጭምር ልንጠነቀቅ እንደሚገባን አስተምሮናል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን የወንጌል ትርጓሜ እንደሚያስተምረን በቃና ዘገሊላ በሠርጉ ቤት እመቤታችን ድንግል ማርያም ልጅዋን ”የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም‘ ባለችው ጊዜ ”ጊዜዬ ገና አልደረሰም‘ ብሎ ለጥቂትም ቢሆን ተአምራቱን ካዘገየባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የይሁዳ በዚያ ቅጽበት በስፍራው አለመኖር ነው፡፡
እንደዚሁም ወደ ታቦር ተራራ ሲወጣ ዘጠኙን በተራራው ግርጌ ትቶ ሦስቱን ብቻ ወደ ተራራው ራስ ይዞ መውጣቱም በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ ይሁዳ ከቀድሞውም በክፉ አሳብ መያዙንና አሳልፎ እንደሚሰጠው እያወቀ ከደቀ መዛሙርቱ አልለየውም፡፡ ቢለየው ኖሮ ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠቱ ”ከተአምራቱ፣ ከምሥጢራቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት‘ የሚል የመሰናከያ ምክንያት ያገኝ ነበርና፡፡
አይሁድ ጌታችንን ለመክሰስ ብሎም የመሰናከያ ነገርን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ጥረዋል፡፡ ለምሳሌም ”መምህር ሆይ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ ?‘ ብለው የቀረቡት ለምን እንደነበር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሲነግረን ”የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት እንዲህ አሉ‘ ብሎናል (ዮሐ፰፥፬-፮)፡፡
ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ”ተዉአት አትውገሯት‘ ቢላቸው ”ሕግንና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም‘ ይላል ነገር ግን ደግሞ ይኽው የሙሴን ሕግ ይሽራል ሊሉት፤ ውገሯት ቢላቸውም ደግሞ ለኃጢአተኞች መጣሁ ይላል ነገር ግን ደግሞ አይራራላቸውም ብለው ሊከሱት አስበው መሆኑ በተረዳ ነገር የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም ውገሯትም፣ አትውገሯትም ሳይላቸው ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ከጻፈ በኋላ ”ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት‘ አላቸው፡፡ እነርሱም የሚከሱበትንና የሚሰናከሉበትን ነገር አጥተው ሕሊናቸው ወቅሷቸው አንድ በአንድ እየወጡ ሄደዋል፡፡ የማያሰናክልና ለክስ የማይመች አኗኗርን ብንከተል እንኳን ዓለም ክርስቲያኖችን ለመክሰስ የሚያስችለውን ነገር ከመፈለግ ወደ ኋላ እንደማትል ይህ ታሪክ ምስክር ነው፡፡
እንኳን ክፉ ነገር ተፈልጎብን፤ ሳይፈለግብንም በክፋት የተሞላን ሰዎች ልንመለስና አኗኗራችንን ልናስተካክል ምንኛ ይገባን ይሆን ? በብሉይ ኪዳን በናቡከደነጾር ቤተ መንግሥት ይኖሩ የነበሩ አለቆችና መሳፍንቱ በነቢዩ ዳንኤል ላይ በቅንአት ተነሣስተውበት ሊከሱትና ሊያስገድሉት ክፉ ምክንያት ይፈልጉ ነበር፡፡ መጽሐፍ ይህን ሲነግረን ”የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፥ ነገር ግን የታመነ ነበረና ስሕተትና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም እነዚያ ሰዎች ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ ይለናል (ዳን.፮፥፬-፮)፡፡
ቀደምት አባቶቻችን ለሌላው እንቅፋትና የጥፋት መሰናክል ላለመሆን እንዲህ ተጠንቅቀው ኖረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች ይልቁንም ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ”ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን ብለውም አስተምረውናል ‘(፩ኛጴጥ.፪፥፲፪)
የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ረድኤት አይለይን!!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!