ጾመ ፍልሰታ
በሳሙኤል ደመቀ
ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት በትንቢት ተናግሯል፡- “ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ” በማለት (መኃ. ፪÷፲)፡፡ ፍልሰት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ መወሰድ፣ መሰደድ፣ መፍለስ የሚል ፍቺ ይኖረዋል፡፡ ፍልሰታ ቃሉ የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴ ሴማኒ ዕፀ ሕይወት ወደአለበት ወደ ገነት፤ ኋላም ከዕፀ ሕይወት ሥር መነሣቱን የሚያመለክት ነው፡፡
የፍልሰታ ለማርያም ጾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ድረስ የምንጾመው ጾም ሲሆን ጀማሪዎቹም ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ የጌታችን እናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት ያዩ ዘንድ ጾመውታልና፡፡ የእመቤታችን ፍቅር እንዲበዛልን ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበረከቷ እንዲከፍለን፣ በዓለም ካለ መከራና ችግር በአማላጅነቷ ጥላ ከልሎ እንዲያሳልፈን ስለምንማጸንበት መምጣቱን በፍቅር የምንጠባበቀው የጾም ጊዜ ነው የፍልሰታ ለማርያም ጾም፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኵሉ፤ ሞትስ ለሚሞት ይገባዋል፤ የማርያም ሞት ግን ከሁሉ ያስደንቃል” በማለት እንዳመሰገነው እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ የምትከብር ከሁሉ ከፍ ያለች ብትሆንም በተፈጥሮ ከሰው ወገን ናትና እንደ ሰው ትሞትን ትቀምስ ዘንድ ስለሚገባ ቅዱሳን እያመሰገኗት በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች።
ቅዱሳን ሐዋርያትም አስቀድሞ ሞቷ በመንፈስ ቅዱስ ስለተገለጸላቸው ከያሉበት ተሰባስበው የተቀደሰ ሥጋዋን ገንዘው ለመቅበር ወደ ጌቴሴማኒ ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇ ሞተ፣ ሞትንም ድል አድርጎ ተነሣ ይላሉ፤ አሁን ደግሞ እናቱ ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያስቸግሩን አስከሬኗን በእሳት እናቃጥለው” በማለት በክፋት ተነሡ፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ከሞት መነሣትና ማረግ በዓለም ሁሉ እየታመነበት ስለመጣ እርሷም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ያስተምራሉ በሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ከአይሁድ ወገን የሆነ ታውፋንያ የተባለ ብርቱ ሰው የእመቤታችን የተቀደሰ ሥጋዋ ያረፈበትን ቃሬዛ ከቅዱሳን ሐዋርያት ለመንጠቅ ሲሞክር መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾ በእሳት ሰይፍ እጆቹን ቆረጣቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም ወደ እመቤታችን ቢለምን በእመቤታችን አማላጅነት የታውፋንያ እጆቹ እንደነበሩ ተመልሰውለታል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችን በመላእክት ዝማሬ ታጅባ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ይህንንም ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ በቀር ለሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው አልተገለጠላቸውም ነበር። ቅዱሳን ሐዋርያትም ለእመቤታችን ካላቸው ፍቅር የተነሣ ለምን አልቀበርናትም? ለምንስ የሥጋዋ ምሥጢር ለቅዱስ ዮሐንስ ተገልጾ ለእኛ ይሰወረናል? በማለት መንፈሳዊ ቅናት እየቀኑና እያዘኑ ቆይተው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ በጾምና በጸሎት ቆይተው ነሐሴ ፲፬ ቀን ሥጋዋ ተሰጥቷቸው በታላቅ ክብርና ምስጋና በጌቴሴማኒ ቀበሯት። በ፫ኛውም ቀን ነሐሴ ፲፮ በልጇ ሥልጣን ከተቀበረችበት ተነሥታ በታላቅ ክብር ዐርጋለች።
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን በተባለ ድርሰቱ እመቤታችንን በከበሩ ደንጊያዎች እየመሰለ የሚያመሰግንበት ክፍል አለው፡፡ በዚህ ምስጋናው በምሳሌ እመቤታችንን ካመሰገነበት የደንጊያ ዓይነቶች አንደኛው የደወል ደንጊያ ነው፡፡ ለምን የደወል ደንጊያ እንዳላት ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡- “አንዲት በምጥ የተያዘች ሴት የደወል ደንጊያ ሲመታ ብትሰማ ልቡናዋ በድምጹ ውበት ስለሚመሰጥ ምጧን እንደምትረሳና እስከምትወልድ ድረስ ሕመሙ አይሰማትም” በማለት ጠቅሶ ሰማዕታትም ከእመቤታችን ፍቅር በመነጨ የሚደርስባቸውን መከራና ሕማም እንደሚዘነጉት ይገልጻል፡፡ በፍልሰታም እንደዚሁ ነው፡፡ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ያሉ ወንዶችም ሴቶችም ለእመቤታችን ካላቸው ፍቅር በመነጨ ረኀቡና ጥሙ ሳይታወቃቸው ሳይመረሩ በደስታ ይጾሙታል፡፡
የጾሙ ጣዕም የመብልን አምሮት የሚያስንቅ ነው፡፡ መንፈሳዊነት በሰውነታችን እንዲሰለጥን ያደርጋል፡፡ ይኸውም የእመቤታችን በረከት ውጤት ነው፡፡ ጾሞ ለመጠቀም ያብቃን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!