ደብረ ዘይት

መ/ር በትረ ማርያም አበባው

ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ፣ የወይራ ዛፍ የሚበዛበት ተራራ ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ሲሰጥ አምስተኛውን እሑድ ደብረ ዘይት ብሎታል። በዚህም ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱና ምልክቶቹ ለቅዱሳን ሐዋርያት ነግሯቸዋል።

በዚህ የዐቢይ ጾም አምስተኛው እሑድ ላይ በስፋት የሚነገረውና በሥርዓተ ማኅሌቱም የሚቆመው ዳግም ምጽአትን የሚያወሳ ጉዳይ ነው። “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ እንተ ባሕቲቶሙ ወይቤልዎ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንት ተአምሪሁ ለምጽአትከ ወለኅልቀተ ዓለም፤ ያን ጊዜ ጌታ በደብረ ዘይት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፡- ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠይቀውታል። (ማቴ. ፳፬፣፫)

 ምጽአት ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ የትርጓሜ ስልት ምጽአት እንደ ጊዜ ግብሩ ይተረጎማል፡፡ ለምሳሌ፡- “እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ” (መዝ. ፵፱፣፩) የሚለውን ብንመለከት በሦስት መንገድ ሲተረጎም እናገኘወለን፡፡ አንደኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል ረድኤት ይሰጣል ተብሎ ይተረጎማል። ሁለተኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል የማይታየው ረቂቁ አምላክ ሥጋን ተዋሕዶ ይታያል ማለት ነው። ሦስተኛው እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል ሲል ዓለምን ለማሳለፍ በኃጥኣን ሊፈርድባቸው ለጻድቃን ሊፈርድላቸው ይመጣል ማለት ነው።

ከምጽአት በፊት የሚታዩ ምልክቶች

. ብዙዎች በሐሰት እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉ (ማቴ. ፳፬፭ )፡-

ይህን የመሰለ በዓፄ ዘድንግል ዘመነ መንግሥት በአማራ ሳይንት እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበር። ንጉሡም “እስመ ይትነሥኡ ሐሳውያነ መሲሕ፣ ወሐሳውያነ ነቢያት፣ ወይገብሩ ተአምራተ ወመንክራተ ዐበይተ ለአስሕቶ፤ ሐሳውያን ነቢያት፣ ሐሳውያን መምህራን ይነሳሉ፤ ሰውን ያስቱ ዘንድ ጽኑ ጽኑ ተአምራትን ያደርጋሉ።” እንዲል (ማቴ. ፳፬፣፳፬) ድፍረት የተሞላበትን ትምህርቱንና ሐሳዊነቱን ተረድተው አስገድለውታል፡፡

ተአምርን ኃጥኣንም ጻድቃንም ሊያደርጉት ይችላሉ። በሙሴ ዘመን የነበሩ ጠንቋዮችም ተአምር ሠርተዋል። ሊቀ ነቢያት ሙሴም ተአምር ሠርቷል።

ስለዚህ ተአምር ብቻ ዓይተን አንከተልም። መንፈሳዊ ሕይወቱ በምልአት ተጠንቶ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ ከሆነ አስተምህሮውም ትክክል ከሆነ እንጂ ተአምር ብቻ ስላደረገ አንድ ሰው ትክክል ነው አይባልም። እንግዲህ በድፍረት እኔ ክርስቶስ ነኝ የሚል ሐሳዊ መሲሕ እንደሚመጣ፣ የክርስቶስ ያልሆኑ ነገር ግን የክርስቶስ ነን ብለው የሚመጡ ሐሰተኛ መምህራንም እንደሚነሡ ይነግረናል።

. ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል (ማቴ. ፳፬፯)፡-

አንዱ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ ይጠላዋል፤ አንዱ መንግሥት ሌላውን መንግሥት ይጠላዋል። ይህማ ቀድሞስ ነበረ አይደለምን ቢሉ በዝቶ ይደረጋል ማለት ነው።

. ረኀብ፣ ቸነፈር ይመጣል (ማቴ. ፳፬፱)፡-

ያን ጊዜ ለጸዋትወ መከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገርፏችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ ይጠሏችኋል። በእኔ ስም ስላመናችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ይህ ለጊዜው ለቅዱሳን ሐዋርያት የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው ግን እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ክርስቲያኖች ነው።

. ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይስታሉ (ማቴ. ፳፬፲)፡-

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “ሃይማኖት አንዲት ናት” (ኤፌ. ፬፣፬)፡፡  ይህ ሆኖ ሳለ ግን ሰይጣን በዘራው ኑፋቄ፣ ከመጻሕፍት ያላገኙትን፣ ከመምህር ያልተማሩትን፣ በልብ ወለድና በመሰለኝ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል እንደ ቃሉ ሳይሆን ለራሳቸው ስሜት እንዲስማማ እየተረጎሙ ብዙዎች ከአንዲቱና ርትዕት ከሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል። ብዙዎች በሃይማኖታቸው ይስታሉ በማለት በሃይማኖት የሚጸኑት ጥቂቶች መሆናቸውን ይነግረናል።

. ፍቅር ትቀዘቅዛለች (ማቴ. ፳፬፲፪)፡-

የሕገ እግዚአብሔር ፍጻሜው ፍቅር ነው። ሕግጋት በሙሉ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ተብለው ይከፈላሉ። የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫው ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅ ነው። “ዘያፈቅረኒ ይዕቀብ ቃልየ፤ የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቅ” ብሏል (ዮሐ. ፲፬፣፳፪)፡፡ የፍቅረ ቢጽ መገለጫው ደግሞ ሊደረግብን የማንፈልገውን እና ለእኛ የማንመኘውን በሌላው አለማድረግና አለመመኘት ሲሆን ለእኛ ሊደረግልን የምንፈንገውንና የምንመኘውን ደግሞ ለሌላውም ማድረግና መመኘት ነው። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ዘሌ.፲፱፣፲፰ ይላልና”።

በመጨረሻው ዘመን ግን ፍቅር ትቀዘቅዛለች። ራስ ወዳድነት ይበዛል ማለት ነው። “ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት። ወይከውኑ ሰብእ መፍቀርያነ ርእሶሙ ባሕቲቶሙ ወመፍቀርያነ ፈጊዕ ወንዋይ፤ በመጨረሻው ዘመን ክፉ ዘመናት እንደሚመጡ ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ ይሆናሉ። ገንዘብን ወዳጅ ይሆናሉ” ተብሏል። (፪ኛ ጢሞ .፫፣፩-፫)፡፡

ምጽአት መቼ ይሆናል?

ዳግም ምጽአት መቼ እንደሚሆን አይታወቅም። ምጽአት መቼ እንደሚሆን የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ “ወበእንተሰ ይእቲ ዕለት ወኪያሃ ሰዓት አልቦ ዘየአምራ፤ ያችን ሰዓት ያችን ዕለት የሚያውቃት የለም፡፡” (ማቴ. ፳፬፣፴፮) እንዲል የሰው ልጅ ምጽአት መቼ እንደሚሆን ሰለማያውቅ መልካም ሥራን እየሠራ ተግቶ እንዲጠብቅ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ በኋላም “ድልዋኒክሙ ሀልው፤ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ብሎናል። ስለዚህ ንስሓ ገብተን፣ ሥጋውን ደሙን እየተቀበልን መልካም ሥራን እየሠራን ፈጣሪያችንን እንጠብቀው።

ፍርድ በምጽአት

መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በምጽአት “ለሁሉ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ” (መዝ. ፷፪፥፲፪)  ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባው እንደ ሥራው ፍርድ የሚሰጥ ያን ጊዜ ነው። “አሜሃ ይብሎሙ ንጉሥ ለእለ በየማኑ ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ ለአቡየ ትረሱ መንግሥተ ሰማያት ዘድልው ለክሙ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም፤ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥተ ሰማያትን ውረሱ” በማለት መልካም ሥራ የሠሩትን በቀኙ ያቆማቸዋል። (ማቴ. ፳፭፣፴፬)።

ሕይወታቸውን በከንቱ ያሳለፉ፣ ከመልካም ሥራ ርቀው ሲቀጥፉና ሲበድሉ፣ ለክፉም ሲተባበሩ ለነበሩት ኃጥኣን ደግሞ “ሑሩ እምኔየ ርጉማን ውስተ እሳት ዘለዓለም ዘድልው ለሰይጣን ወለመላእክቲሁ፤ እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደተዘጋጀው የዘለዓለም እሳት ሒዱ” ይላቸዋል፤ በግራውም ያቆማቸዋል።

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለእያንዳንዱ የዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ሰጥታ የምታስተምር ሲሆን አምስተኛውን የዐቢይ ጾም ሰንበት ደብረ ዘይት (ዕለተ ምጽአት) በማለት ሰይማዋለች፡፡ በዕለቱም ከዋዜማው ጀምሮ የሚዜመው ዜማ፣ የሚነበቡት ምንባባት፣ የሚሰበከው ስብከት ሁሉ ዕለቱን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *