የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክረምት ምን ይጠበቅባቸዋል?

አሸናፊ ሰውነት

ግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በዓለማዊና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በታማኝነት ያገለግሉ ዘንድ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበትና ክርስትናን በተግባር የሚገልጹበት ቦታ ነው።

ወጣትነት የምንለው ደግሞ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከሃያ እስከ ዐርባ ዓመት ያለው ዕድሜ ነው፡፡ይህ የዕድሜ ክልል የእሳትነት ባሕርይ ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ሲሆን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከራስ አልፎ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናውን መልካም ፍሬን ማፍራት የሚቻልበት ወርቃማ ጊዜ ነው። ነገር ግን በተቃራኒው የወጣትነት ዕድሜን በመልካም መንገድ መምራት ካልተቻለ ከራስ አልፎ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን መጉዳትን ያስከትላል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ግን የመንፈሳዊ ሕይወትን ጉዞ ጀምረዋልና ከራሳቸው አልፈው ለሌላው በመኖር እነርሱ የጀመሩትን መንፈሳዊ ሕይወት ጓደኞቻቸውም እንዲጀምሩና የክርስቶስ የፍቅሩን ጣዕም እንዲቀምሱ በማድረግ ኦርቶዶክሳዊና ማኅበራዊ ግዴታቸውን መወጣት ይገባቸዋል። እነዚህ የሩቅ መንገደኞች በክረምት ወቅት መደበኛ ትምህርታቸው ለዕረፍት በመዘጋቱ በዚህ ወቅት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? ስንል ከሚጠበቅባቸው ተግባራት ውስጥ ሁለቱን እንመለከታለን።

. መማር፡- እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዐዋቂ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ዕለት ዕለት በሚያደርገው እንቅስቃሴም አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ፣ ክፉውንና ደጉን የመለየት ነፃነት ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ይህንን ስጦታ የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በጎውን በመተው ክፋትንም በማድረግ ኃጢአትን በራስ ላይ በማንገሥ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል” እንዲል እስራኤላውያን ለተለያዩ የኃጢአት ሥራዎች ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው እግዚአብሔር በነቢዩ ሆሴዕ ላይ አድሮ ገሥጿቸዋል፡፡ (ሆሴ.፬፥፮) አባቶቻችንም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” በማለት እንደሚናገሩት በዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሚፈትናት ነገር አንዱ የምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው ለመማር የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ መሆን ነው፡፡

ለመማር ጥረት የሚያደርግ ትውልድ ያውቃል፣ የሚያውቅ ደግሞ በቀላሉ ለክፉ ሥራ አይጋለጥም፤ ዘወትር ለመልካም ሥራ ይተጋል እንጂ፡፡ ስለዚህ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዚህ ዘመን በፍጥነት እየተለዋወጠች ባለች ዓለም ላይ እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ የድርሻን ለመወጣት በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መንገዱን ማሳየትና ማሳወቅ  እንደ ግዴታ ሊቆጥሩት ይገባል። የማወቂያ አንዱ መንገድ ደግሞ መማር ሲሆን ዕውቀት ደግሞ ስለ አንድ ነገር ያለን መረዳት ወይም ግንዛቤ ነው፤ ዕውቀት ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል።

መንፈሳዊ ዕውቀትን ስንመለከት ለማገልገልም ሆነ ለመገልገል አስፈላጊ ነው። ከሐዋርያትም ታሪክ የምንማረው ይህንኑ ነው። በቅድሚያ ከጌታችን እግር ሥር ተማሩ፤ የተማሩትን ደግሞ   በቃልና በተግባር ፈጸሙት። የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም በግቢ ቆይታቸው የተማሩትን መንፈሳዊ   ትምህርት ለማጠናከር በደረጃቸውና እንደ አካባቢያቸው ምቹ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶችን ጊዜ ሰጥቶ መማር ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሆነ በመነሻችን ላይ እንደ ጠቀስነው በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆነው ለመውጣት የሚያደርጉትን ሩጫ ያቀልላቸዋል።

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን ከስሜታዊነት ርቀው ዕውቀትን ፍለጋ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከሐሰተኛ ትርክቶችና የምዕራባውያን አእምሮ በራዥ ትምህርቶች በመራቅ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ላይ ሊገነቡ ይገባል፡፡ የቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ታሪክ የሚነግረን ዕውቀትና ጥበብን አጥብቆ ፈላጊዎች መሆናቸውን ስለሆነ እነርሱን አርአያ በማድረግ የወደፊት የሕይወት አቅጣጫቸውን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ላይ መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከላይ የተነሡት መሠረታዊ ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለመቀየር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ችግሮች አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- ስሜታዊነት፣ የዓላማ አለመኖር፣ የሚያስፈልጋቸውን   አለማወቅ፣ ቁርጥ ውሳኔ አለመወሰን፣ ነገሮችን በሥጋዊ ዓይን ብቻ ማየት፣ የአብነት ትምህርትን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ብቻ ነው ብሎ ማሰብና ሌላ ጊዜ እደርስበታለሁ ብሎ መዘናጋት፣ …  ተጠቃሾች ናቸው። የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዚህ ክረምት እነዚህንና ሌሎችም ከመንፈሳዊ ጉዟቸው ሊያደናቅፉ ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ ለዕውቀት ልዩ ትኩረት በመስጠት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ሊያንጹ ይገባል፡፡

. ማገልገል፡- አገልግሎት እግዚአብሔርን የመውደዳችን አንዱ መገለጫ ነው። ማገልገል ስንል የግድ ሰንበት ትምህርት ቤት ገብተን አልያም ዐውደ ምሕረት ላይ አትሮንስ ተዘርግቶ ብቻ ላይሆን ይችላል። ቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎትን “ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት መልካምን ነገር እናስባለንና” በማለት ገልጦታል፡፡ (፪ኛቆሮ. ፰፥፳-፳፩) ስለዚህ ጊዜና ቦታ መርጠን ሳይሆን የትም ቢሆን መቼም የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በሥርዓትና በአግባቡ ማድረግ ተገቢ ነው።

ይህም ማለት መንፈሳዊ አገልጋይ በመንፈሳዊና በማኅበራዊ ሕይወቱ ራሱን በመጠበቅ ለሰዎች እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ድርጊቶችም በመራቅ ሊኖር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ክርስትና በቃልም፣ በተግባርም የሚገልጥ ነውና፡፡ አገልጋይ ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር የተሞላ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር መልካም እንደሆነ ቀምሶ ያየና ሌሎችንም ወደዚህ ሕይወት እንዲመጡ የሚጋብዝ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ቀጠሮ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የመዳን ቀን አሁን ነውና።

በአገልግሎት ውስጥ ያለ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳይመላለስና አገልግሎቱንም በትጋት እንዳይፈጽም ከራሱ፣ ከሰይጣንና ከአካባቢ በሚመነጭ ፈተና ሊፈተን ይችላል፡፡ አንድ ክርስቲያን እነዚህ ሁሉ የግድ ሊጠብቃቸው የሚገቡ ናቸው እንጂ አገልግሎት አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል። ያ ቢሆን ኖሮ ቅዱሳን ሐዋርያት በመቀጠልም ሰማዕታት ብሎም ሐዋርያነ አበው ያ ሁሉ መከራና ሥቃይ ባለደረሰባቸውም ነበር።

ስለዚህ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ለአገልግሎት ያላቸውን አመለካከት በማስተካከልና ነገ አገለግላለሁ ከማለት ወጥተው በቅንነት ሊያገለግሉ ይገባል። ስለሚበሉት፣ ስለሚጠጡት፣ ስለሚለብሱት፣ ነገ ስለሚኖራቸው መኖሪያ ቤት፣ ስለሚይዙት መኪና፣ ስለ ሥልጣንና መሰል ነገሮች በማሰብ ቁሳዊ ብቻ መሆን ሳይሆን ለራሳቸውና ለሌሎች ድኅነት ሊተጉ ይገባል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አገልግሎት ስላለን አንታክትም” በማለት እንዳስተማረው (፪ኛቆሮ.፬፥፩) እንደ አባቶቻችን ዕለት ዕለት መጨነቅ የሚገባው ስለ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ መሆን አለበት። ለአንድም ሰው ቢሆን የድኅነትን መንገድ ማሳየትና መምራት ዋጋ ስላለው መድከም፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይም መሠማራት፤ የእግዚአብሔርን ቃል መናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ አካሄዳችሁንም አይተው የማን ፍሬ እንደሆናችሁ ያውቃሉና እንደተባለው።

በመጨረሻ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክረምት ወቅት ማድረግ ስላለባቸው ጉዳዮች በተመለከተ መማርና ማገልገልን የሚሉትን ነጥቦች አነሣን እንጂ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይጠብቋቸዋል፡፡ እነዚህንም በማከናወን ሂደት ውስጥ ዓላማና ግብ ያላቸውን ዕቅዶች በማውጣት ለተግባራዊነቱም ቁርጥ ውሳኔና ጥረት በማድረግ፣ እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅና አገልግሎቱም ፍሬ ያፈራ ዘንድ በመትጋት ክረምቱን በመንፈሳዊ አገልግሎት ማሳለፍ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *