የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች

በመ/ር ተመስገን ዘገየ

ክፍል ፩

ፈተና በቤተ ክርስቲያናችን እምነት፣ ሥርዓት፣ ቀኖናና ትውፊት መሠረት በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞ ውስጥ ዓላማችንን ለማደናቀፍ ከተለያዩ አካላትና አቅጣጫ የሚገጥመን መሰናክል ወይም እንቅፋት ነው፡፡

ፈተና ከየትም አቅጣጫና አካባቢ ወይም ምክንያት ይምጣ በውስጡ ግን ዓላማ ይኖረዋል።ቅዱስ ያዕቆብ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፡፡ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና፡፡ ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል“ ብሏል (ያዕ. ፩፥፲፪-፲፬)፡፡ ትልቁ ነገር የፈተናው መምጣት ሳይሆን ፈተናውን ለማለፍ መንፈሳዊ ትጥቅን በመታጠቅ ድል መንሣትን እናገኝ ዘንድ ዝግጁና ብቁ ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው።

ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” ተብሎ ተጽፏል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፥፲፫)

በትምህርት ዓለም ሳለን ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች ለየት የሚሉ ፈተናዎች የሚያጋጥሙን ገና ከተመረቅን ማግሥት ጀምሮ ነው፡፡ እኛ የሕይወት ለውጥ ባደረግን ቁጥር ፈተናውም እንዲሁ   ይለዋወጣልና ለዚህም ደግሞ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ከምረቃ በኋላ ከሚያጋጥሙ ችግሮችና ፈተናዎች መካከል

፩. እንደ ተመረቁ ሥራ አለመያዝ

በዚህ ዘመን አንዱ መሠረታዊ ችግር ከብዙ ድካም የትምህርት ጊዜና ውጣ ውረድ ቀጥሎ ያለው ፈተና ሥራ አለማግኘት ነው፡፡ ሥራ ቶሎ ባለማግኘቱም የተመረቁበትን የትምህርት መስክ ማጥላላትና የሌላውን ማድነቅ ይጀመራል፡፡ ወደ ተስፋ መቁረጥና አልባሌ ተግባራት  የሚሄዱም ብዙዎች  ናቸው፡፡ ሥራ  የፈታ አእምሮ ምን ጊዜም “የሰይጣን  ቤተ ሙከራ“ ነው፡፡]

ብዙዎቻችን ደግሞ ለሥራ ያለን አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ የተሳሳተ አመለካካት የሚመነጨው ደግሞ ከመንግሥት ተቋማት ተቀጥረን ቢሮ ይዘን ካልሠራን ሥራ የሠራን ስለማይመስለንና ሥራ ፈጥረን ስለማንሠራ ነው፡፡ አንዳንዶችም የአካባቢው ወሬና አሉባልታ በመፍራት ያልሆነ ምርጫ ሲመርጡ ይታያሉ፡፡ “እስከ አሁን ሥራ እንዴት አልያዝክም?” የሚል ጥያቄን ይሸሹታል፡

ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ዘመን ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለመወለድ   ጊዜ አለው፣ ለሞሞትም ጊዜ አለው፣ ለመትከል ጊዜ አለው፣ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፡፡ … ለሠራተኛ የድካሙ ትርፉ ምንድር ነው?” (መክ. ፫፥፩-፰) ብለን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡ ሁሉም ነገር ያልፋል ነገር ግን የሚያልፈው ጊዜና ችግር በሕይወታችን ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ እንዳይሄድ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ በዚህም የወጣትነት ጊዜ ለነፍሳችን የሚጠቅም ሥራን ለመሥራት መሽቀዳደም (መሯሯጥ) ብልህነት ነው፡፡

፪. አለመረጋጋት፦

አለመረጋጋት ብዙ ተመራቂዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደተመረቁ የሚያጋጥማቸው ፈተና ነው፡፡ ብዙዎች ከመመረቃቸው በፊት ያስቡት የነበረውን ሁሉ ለማሟላት አቅም ሲያንሳቸው መረጋጋት ይጎድላቸዋል፡፡ እንደ ተመረቁ ሁሉም ነገር በአንድ   ጊዜ እንደማይሟላ ዐውቆ ፍላጎትን መግታት የግድ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ”… ኑሮዬ ይበቃኛል፤ ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፡፡   ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል፤ ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችንም በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ፤ ገንዘብን መውድድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና” ይላል (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፮-፲) ባገኘነው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማመስገን ይኖርብናል፡፡ ኑሮአችንም በመጠን አድርገን መኖር መቻል አለብን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “… በመጠን ኑሩ፣ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱን ፍጹማን ያደርጋችኋል፣ ያጸናችሁማል፣ ያበረታችሁማል …” (፩ኛ ጴጥ. ፮፥፰-፲፩) ሕይወት የሚጣፍጠው ታግለው በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈው ሲያገኙት ነው፡፡ ስለዚህ በመጠን ፍላጎትን ቀንሶ መኖር መለማመድ ያስፈልገናል፡፡

የአንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራቂ መቼና የትም ቢሆን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደሆነ ካላመነ በሕይወቱ መረጋጋትና ማስተዋል ሊኖረው አይችልም፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች መሠረታዊ ችግር ይህ ነው፡፡ ሥራ የት ቦታ እንደሚመደቡ እያሰቡ ይጨነቃሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “… እንግዲህ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?  ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና፡፡ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህ ሁሉ ይጨመርላችኋል፡፡ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” ብሎናል፡፡ (ማቴ. ፮፥፴፩-፴፬)

፫. መወሰን፦

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከሚያስፈልጉት ነገሮች ትልቁና ዋነኛው መወሰን መቻል ነው፡፡ በራስ ላይ መወሰን ካልተቻለ ሌሎች (ቤተሰብ፣ ዘመድ) እንዲወስኑ ፈቀድንላቸው ማለት ነው፡፡ ዕቅድ፣ ሂደትና ግብ ሊኖር ይገባናል፡፡ የዕቅድ ዐቀበት የለውም ፈተናው ክንውኑ ስለሆነ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ውሳኔዎቻቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ሊወስኑ ይገባል፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *