መንፈሳዊ ወጣት

በእንዳለ ደምስስ

የሰው ልጅ ሕይወት በዐራቱ የዕድሜ ክልል ይከፋፈላል፡፡ ይኸውም የሕፃንነት፣ የወጣትነት፣ የጎልማሳነትና የእርግና ዘመናት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የወጣትነት የዕድሜ ክልል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሠረት ከሃያ እስከ ዐርባ ዓመት ያለውን ዕድሜ የያዘ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እነዚህን የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርያት በአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም በነፋስ፤ በእሳት፤ በውኃና በመሬት ሲመስሏቸው አምስተኛ ነፍስን ጨምሮ በአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ላይ ሲንጸባረቁ ይኖራሉ፡፡ የመሬት መሠረቷ ጽናቷ ነፋስ ነው፡፡ የእኛም ከላይ ሥጋችን መሬት ነው፡፡ መሬትም በውኃ ላይ ናት ይህም ውኃው ደማችን ነው፡፡ የእኛም ሥጋችን በደማችን ነውና የሚጸናው፤ የውኃ ሕይወት ነፋስ ነው፡፡

ከሃያ እስከ ዐርባ ያለው የዕድሜ ክልል የእሳትነት ባሕርይ ጎልቶ የሚታይበት በመሆኑ ዘመነ እሳት ወይም ምግበ እሳት ይባላል፡፡ እሳት ያገኘውን እንደሚያቃጥል እና እንደሚፈጅ ሁሉ ወጣትነትም በመንፈሳዊ ሕይወት ካልተገራ ሁሉን ልጨብጥ፣ ሁሉን ላድርግ የሚል ስሜታዊነት ጎልቶ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥፋትና ለርኵሰት አሳልፎ ይሰጣል፡፡

ይህንን የእሳትነት ዘመን በሰከነና ማስተዋል በተሞላበት ሁኔታ ለማለፍ ሕይወትን በመንፈሳዊነት መምራት ይገባል፡፡ ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ላይ ማሠልጠን፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እንዲሁም በልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ ምግባራት በማነጽ ዓለምን ማሸነፍ ከወጣቶች ይጠበቃል፡፡

በቅድሚያ ወጣቶችን ከመንፈሳዊ ሕይወት ሊያስወጡ ይችላሉ የምንላቸውን ነጥቦች ቅዱሳት መጻሕፍትን መነሻ በማድረግ ጥቂቶቹን እንመልከት፡-

ስሜታዊነት፡-

ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው ከሌሎቹ የዕድሜ ዘመናት በተለየ ሁኔታ በወጣቶች ላይ ቅጽበታዊ ውሳኔዎችና ድርጊቶችን ለመፈጸም የሚሽቀዳደሙበት ጊዜ ነው፡፡ “ሁሉን ነገር አሁን ካላደረግሁ” የሚል ስሜት ሲነዳቸው እናስተውላለን፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ቃየልን መመልክት እንችላለን፡፡

ቃየል በወንድሙ በአቤል ላይ በቅናት መንፈስ በመነሣሣት ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት ወንድሙን እስከ መግደል አድርሶታል፡፡ ቃየል ምድርን የሚያርስ አራሽ ሆነ፤ አቤልም በግ ጠባቂ ሆነ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፡፡ አቤል ከሚጠብቃቸው በጎች ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጸጉሩ ያላረረውን የአንድ ዓመት ጠቦት ሲያቀርብ፣ ቃየል ግን አርሶ ካከማቸው ስንዴ እግዚአብሔር አይበላው፣ ምን ያደርግለታል በሚል በንዝህላልነት እንክርዳዱን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤል መሥዋዕት ተመለከተ፤ ከሰማይም እሳት ወርዶ በላው፤ ቃየልም ተበሳጨ በወንድሙም ላይ በጠላትነት ተነሣ፡፡ ይገድለውም ዘንድ ወደ ሜዳ ይዞት ወጣ፡፡ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው፤ በሜዳም ሳሉ ቃየል በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም” (ዘፍ.፬፥፰) በምድርም ላይ ተቅበዝባዥ ሆኖ ኖረ፡፡ ይህንን ስንመለከት ቃየል በቅናት መንፈስ መነሣቱንና ስሜታዊነት አይሎበት ነገሮችን ለማመዛዘን ጊዜ ሳይወስድ የከፋውን ኃጢአት እስከ መሥራት አደረሰው፡፡

የዝሙት ጾር፡-

በወጣትነት የዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ከሚፈተኑበት አንዱ ጉዳይ ራሳቸውን ለዝሙት መንፈስ አሳልፈው መስጠታቸው ነው፡፡ በወጣትነት ዘመን ለተቃራኒ ጾታ ያላቸው ስሜት እጅግ የሚያይልበት እና በመንፈሳዊ ሕይወት ባለመቃኘቱ ምክንያት ከሐሳብ አልፎ ወደ ድርጊት መጣደፍ ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡

ወጣቱ የዳዊት ልጅ አምኖን በእኅቱ ትዕማር ፍቅር ተነደፈ፡፡ የታመመ መስሎም ተኝቶ እኅቱ ትዕማር እንድትንከባከበው በጓደኛው በተንኮል አመንጪነት ተነሣስቶ አባቱን አስፈቀደ፡፡ ነገር ግን ትዕማር ወንድሟን ልትንከባከበው በመጣች ጊዜ “እኅቴ ሆይ ነዪ ከእኔ ጋር ተኚ፤ አላት፡፡ እርስዋም አለችው፡- ወንድሜ ሆይ አታዋርደኝ፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና ይህን ነውረኛ ሥራ አታድርግ” ብላ ለመነችው፡፡ እርሱ ግን ምክሯን አልሰማም፡፡ ለስሜታዊነት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷልና እኅቱን አስነወራት፡፡ በእግዚአብሔርም ፊት ኃጢአትን ሠራ፡፡ (፪ኛ ሳሙ. ፲፫፥፩-፲፱)፡፡

ዓለምን መውደድ፡-

ሌላው ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት መካከል ወጣቱ ዴማስ ነው፡፡ ዴማስ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ፣ በሄደበት የሚሄድ፣ ባደረበት የሚያድር ሆኖ ሳለ ብልጭልጩ የተሎንቄ ከተማ (ዓለም) አታለለው፡፡ ከመንፈሳዊው ዓለም ይልቅ ሥጋዊው ሕይወቱን ለማስደሰት ሲል ወደ ከተማው ኮበለለ፡፡ ዓለምም ውጣው ቀረች፡፡ በዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዘን “ዴማስ ይህን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔንም ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” በማለት ገልጿል፡፡

በወጣትነት ዘመን ከመንፈሳዊ ሕይወት የሚለዩ ጉዳዮች መካከል እንደ ምሳሌ ከላይ ጥቂቶቹን ተመለከትን እንጂ ዘርዝረን ልንጨርሳቸው አንችልም፡፡

ወጣቶች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጸኑ የሚያደርጓቸውን ጉዳዮችን በጥቂቱ ስንመለከት ደግሞ፡-

ራስን መግዛት፡-

በእሳት በተመሰለው ወጣትነት ዘመን ራስን መግዛት መቻል ትልቅ ሰማዕትነት ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” (መክ. ፲፪፥፩) እንዲል በወጣትነት ዘመን በመንፈሳዊ ሕይወት መትጋት፣ እንደ እግዚአብሔርም ፈቃድ መጓዝ በመጨረሻ በእግዚአብር ፊት ለክብር የሚያበቃ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ሰው ራሱ በገዛ ምኞቱ ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” (፩ኛ ያዕ. ፩፥፲፬) ላይ በማለት እንዳስተማረን፤ በወጣትነት ዘመን የሚገኝ ምኞት ከመጠን በላይ ወደ ጥፋት የሚስብና የሚያታልል ነው፡፡ በተለይም ሰው በገዛ ምኞቱ ሲሳብ በወጣትነት ዘመን ምንም አእምሮው የበሰለ ቢሆንም እንኳ ራሱን መግዛት ካልቻለ በብዙ ነገር ይፈተናል፡፡

ራስን ከመግዛት ጋር እንደ ምሳሌ ከምናነሣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መካከል አንዱ የዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ታሪክ ነው፡፡ በወንድሞቹ ተንኮልና ምቀኝነት ከተጣለበት ጉድጓድ አውጥተው ወደ ባዕድ ሀገር (ግብጽ) ሸጡት፡፡ ዮሴፍ የፈርዖን ጃንደረባ የመጋቢዎቹም አለቃ የሚሆን የግብጽ ሰው ጲጢፋራ ወደ ግብጽ ካወረዱት ከይስማኤላውያን እጅ ገዛው፡፡ “እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታው ቤትም ተሾመ፡፡” እንዲል ለባርነት የተሸጠው ዮሴፍ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ከፍ ከፍ አደረገው፡፡ (ዘፍ. ፴፱፥፩-፲፰)፡፡

ነገር ግን የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን በመጣሏ ከእርሷም ጋር እንዲተኛ ጠየቀችው፡፡ ዮሴፍ ግን “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” (ዘፍ. ፴፱፥፱) በማለት የቀረበለትን ጥሪ እምቢ አለ፡፡ ታገለችውም፤ ልብሱንም በእጇ ትቶላት ሸሸ፡፡ በዚህም ምክንያት ለእሥር በመዳረግ፣ መከራም እስከ መቀበል ድረስ ጸና፡፡ ይህም በቀላሉ የተገኘ ድል አልነበረም፤ ራሱንም በመግዛት ከክፉ ጋር ባለመተባበር ሰውነቱንም ከርኩሰት ጠበቀ፡፡ ዮሴፍ ወጣት ነው፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ክብር፣ ጠባቂነቱም እንደማይለየው በማመን እምቢ ማለትን መረጠ፡፡ በዘመኑም እንደነበሩት ወጣቶች ከኃጢአት ጋር አልተባበረም፡፡ እግዚአብሔርም በግብጽ ምድር አዛዥ አደረገው፤ በክብርም ላይ ክብርን አጎናጸፈው፡፡

እግዚአብሔርን መፍራት፡-

“ልጆቼ ኑ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ” (መዝ. ፴፫፥፲፩) በማለት ነቢየ እግዚአብሔር እንደተናገረው ወጣቶች እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በፊቱም መልካምን በማድረግ እንደ ቃሉ መመላለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣት ነኝና በዚህ ዕድዬ ማየት ያለብኝን ሁሉ ማየት አለብኝ በማለት ተፈትቶ እንደተለቀቀ እምቦሳ ፈቃደ ሥጋቸውን ለማስደሰት መሮጥ አይገባቸውም፡፡ እግዚአብሔርን በመፍራት ቢኖሩ ከላይ እንዳየነው እንደ ዮሴፍ “በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን አልሥራም” በማለት ክፉን በመጠየፍ የወጣትነት ዘመናቸውን በመንፈሳዊ ሕይወት ማነጽ አስፈላጊ ነው፡፡ ለክብር የሚያበቃው እርሱ ነውና፡፡

ጻድቁ ኢዮብ በዲያብሎስ በተፈተነና በተለያዩ መንገዶች እግዚአብሔርን ይክድ ዘንድ ሲፈትነው ሦስቱ ጓደኞቹ በማይገባ ምክር እግዚአብሔርን ይክድ ዘንድ ተከራክረውታል፡፡ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት ጽኑ ነውና “ሰውንም፡- እነሆ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፉ መራቅም ማስተዋል ነው” ሲል መልሶላቸዋል፡፡ (ኢዮ. ፳፰፥፳፰) እግዚአብሔርን በመፍራት መኖርም ለበለጠ ክብር እንደሚያበቃ ከጻድቁ ኢዮብ መማር ተገቢ ነው፡፡

ዕውቀትን መፈለግ፡-

ዕውቀት ሁሉ ወደ መልካም መንገድ ይመራል ማለት አይቻልም፡፡ መልካሙንና ክፉውን መመርመርና ወደ ቀናውም መንገድ ለመጓዝ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ፣ በመምህራንም መታገዝ ይገባል፡፡ በቃል የተነገረ፣ በመጽሐፍ የሰፈረ ሁሉ ዕውቀት ልንለው አንችልም፤ ወደ ጠማማው መንገድ የሚመሩ፣ እግዚአብሔርንም ከማወቅ የሚለዩ አሉና ጥንቃቄን ይሻል፡፡ “እነሆ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አበዛሁ፤ ልቤንም ለጥበብና ለዕውቀት ሰጠሁ፡፡” በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው በወጣትነት ዘመን በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት የተቃኘ ጥበብንና ዕውቀትን መፈለግ ተገቢ ነው፡፡ (መክ. ፩፥፲፮)

በተለይም ወጣቶች አባቶቻችን እግዚአብሔር ገልጾላቸው በእምነት ጸንተው የመረመሩትና ለትውልድ ያስተላለፉትን መንፈሳዊ ዕውቀት መገብየት፣ መጻሕፍትን መመርመር በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው እንዲወጡ ያስችላቸዋል፡፡ “ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፣ አባቶችንም በየወገናቸው በትጋት መርመምር” ሲል ጻድቁ ኢዮብ እንደተናገረው ለሕይወት ጠቃሚና መንፈሳዊነትን የሚጨምረውን ዕውቀትና ጥበብ መፈለግ፣ እርሱንም አጥብቆ መያዝና እንደ ቃሉም መጓዝ ከወጣቶች ይጠበቃል፡፡ (ኢዮ. ፰፥፰)

መንፈሳዊ ምግባራትን መፈጸም፡-

ጾም ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ምግባራት ከወጣቶች ሕይወት ጋር የተቆራኘ ሊሆን ይገባዋል፡፡ መንፈሳዊ ምግባራትን ይዞ የተገኘ ወጣት የኑፋቄ ትምህርቶች እንደ ወጀብ ቢወርዱ እንኳን አይደናገጥም፡፡ ዲያብሎስ መንፈሳውያን ወጣቶችን ለማሰናከል በዙሪያቸው ይዞራልና እነዚህን ምግባራት በመፈጸም ድል መንሣት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ የጴጥሮስ በመልእክቱ “እንግዲህ አዋቆች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” (፩ኛጴጥ. ፭፥፰) በማለት እንደነገረን መንፈሳዊ ትጥቅ የሆኑትን በጎ   ምግባራት በመፈጸም ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡

በንስሓ ሕይወት መመላለስ፣ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን በመቀበል መንፈሳዊ ሕይወትን ማጽናት ከአንድ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ይጠበቃል፡፡ በየጊዜው ዲያብሎስ አቅጣጫውንና ዓይነቱን እየለዋወጠ ለሚያመጣቸው ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች ባለመደናገጥ መንፈሳዊውን ጋሻ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ” እንዲል ወጣቶች ለመንፈሳዊ ምግባራት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዲያብሎስ የሚያመጣውን ፈተና ድል መንሣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ኤፌ. ፮፥፲፫)

በአጠቃላይ መንፈሳዊ ወጣቶች በኦርቶዶክሳዊ አኗኗር የተቃኙ፣ ራሳቸውንም የሚያንጹ እና የሚመጡባቸውን ፈተናዎች ሁሉ በመንፈሳዊ መንጽር በመቃኘት እንዳይወድቁም እየተጠነቀቁ መንፈሳዊውን ጎዳና መጓዝ ይገባቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፤ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ፡፡ ከዚህም ሁሉ የሚንበለበሉ የክፉ ፍላጻዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡ … ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” በማለት ለኤፌሶን ሰዎች እንዳስተማረው ወጣቶች ቃለ እግዚአብሔርን እውነተኛ ጋሻቸው ማድረግ፣ በዲያብሎስም ላይ በመሠልጠን ድል መንሣት ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *