የደረጃ ሦስት መምህራን ሥልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ ተሠጠ

በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል የደረጃ ሦስት የግቢ ጉባኤያት መምህራን ሥልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥቅምት ፱ እስከ ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም መስጠቱን አስታወቀ፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን አዳራሽ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ባፈራቻቸው መምህራን ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ በቆየው ሥልጠምና ዐርባ የግቢ ጉባኤያት መምህራን የተሳተፉ ሲሆን፤  ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ድኅነት፣ አንፃራዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የመጻሕፍት ትርጓሜያት አጠናን ስልት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ትምህርት አበው በሃይማኖተ አበው እና አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት በሚሉ ርእሶች ላይ በማተኮር ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይህ የደረጃ ሦስት መምህራን ሥልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ እንደመሆኑ መጠን የቡድን ውይይት፣ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥም አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎት ላይ ተሰማርተው እያገለገሉ እንደመገኘታቸው ሳምንቱን ሙሉ ምሽቱን በአገልግሎት ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው መምህራን እየተገኙ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

ሥልጠናውን በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል የተዘጋጀ ሲሆን፤ ደረጃ አንድ የመምህራን ሥልጠና በማእከላት፣ ደረጃ ሁለት ደግሞ በማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች አማካይነት ይሰጣሉ፡፡ ፣ ደረጃ ሦስትን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋናው ማእከል የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ እንዲሰጥ በተወሰነው መሠረት ሥልጠናው ተካሂዷል፡፡

በዚህ ሥልጠናም ሠልጣኞች ሰፋ ያለ ትምህርት እና ልምድ መቅሰማቸውን በመግለጽ በሚሄዱበት ሁሉ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *