‹‹የምንጾመው ለምንድን ነው?›› የጾም ጥቅም፣ ዓላማና አስፈላጊነት

ለሜሳ ጉተታ

ጾም፣ ጸሎትና የንስሐ ሕይወት የማይነጣጠሉ የክርስትና ሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ ጾም በሃይማኖትና በምግባር ለመጽናት ከክፉ አሳብና ምኞት እንዲሁም ተግባር ለመጠበቅ የምግባር ፍሬንም ለማፍራት ይረዳል፡፡ ጾም ፍትወተ ሥጋን፣ የዓለምን ሀሳብ፣ ምኞትና ተግባሩን ለመጥላት የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት ከሥጋ ፍሬ ራስን ለመጠበቅ መንግሥቱን ለመውረስ የእርሱ ጥበቃን ለማግኘት ይረዳል፡፡ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን፣ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት ይረዳል፤ ምሥጢር እንዲገለጥልንም ያደርጋል፡፡ ጾም የመንፈሳዊ ተግባራትና የበጎ ሥራዎች ሁሉ መነሻ መሠረት/መገኛና መጀመሪያ ነው፡፡

ጾም ሥጋን ለመንፈስ ለማስገዛት፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት ለመበርታት ለመጽናት፣ ለእግዚአብሔርም ለመገዛት ይረዳል፡፡  ያለ ጾም በመደዳ መብላትና መጠጣት፣ ያለ ልክና አግባብ ሥጋን ያበረታል፤ በአንጻሩ መንፈስን ደግሞ ያዳክማል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ኃጢአትና በደልን ክፋትን ያሠራል፤ ለዓለምና ለሥጋ ሀሳብ ፍላጎትና አምሮትም ያስገዛል ፍላጎታችን ፤ ሥጋችን እና አሳባችን በነፍሳችን ላይ እንዲሠለጥን ያደርጋል፡፡ ጾም ከዚህ ሁሉ ይጠብቃል፡፡ ጾም ለትሩፋት ያተጋል፡፡ አብዝቶ መብላትና መጠጣት ለፍትወት ያነሣሣል፡፡ ይህ ደግሞ የሰው መልአካዊና ሰማያዊ ብሎም መንፈሳዊ ማንነቱን ንጽሕናና የቅድስና ሕይወቱን ለማቆሸሽ ይዳርጋል፡፡ ክርስቲያን ሕይወቱን በጾም በጸሎትና በንስሐ የሚመራ መንፈሳዊ ሰው መሆን አለበት፡፡ ሮሜ.7፡1፡፡          

ይህ እየታወቀ ግን አሁንም ትውልዱ ‹‹ለምን እንጾማለን?›› በሚል ጥያቄ ተወጥሯል፡፡ ያለንበት ወቅት እና የምንኖርባት ዓለም በልዩ ልዩ ጥያቄዎች የተሞላች ምድር ናት፡፡ ደግነትም ክፋትም የሚንጸበረቅባት ዓለም ናት፡፡ ክርስቲያን  ሁሉን የማወቅ የመመርመር መልካሙን እና ክፉዉንም የመለየት መልካሙንም የመምራጥ ግዴታ እና ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥም መጠየቅ ከክፋት ራስን ለመጠበቅ ብሎም በጎዉን ለመሥራት ይረዳል፡፡ ለዚህ ነዉ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም መርምሩ መልካሙንም ያዙ’’ የሚለን (1ተሰ.5፥20-21)፡፡

አይታይ፣ አይጨበጥ፣ አይዳሰስ፣ አይነገር፣ አይተረክ የነበረው ይህ ዓለም ለምን እንዲታይ እንዲዳሰስ እንዲተረክ ሆነ ብሎ መጠየቅ  አላዋቂ አያሰኝም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የፍጥረተ ዓለምን ዓላማ  ለመረዳት፣ ተረድቶም ድርሻን ለመወጣት እስከሆነ ድረስ ተገቢ ነውና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለምን እንደሚጾም ለሚጠይቅ ሰውም ግልጽ ማብራርያ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡- ጾም ለክርስቲያኖች  መንፈሳዊ ተግባር እና ግዴታ መሆኑን፣ መንፈሰዊ ሰው እንደሚያደርግ፣ ከፈተና እንደሚጠብቅ፣ በሃይማኖት እና በምግባርም እንደሚያጸና፣ ለአገልግሎት እንደሚያተጋ፣ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ራስንም ከኃጢአት ከክፋት ከደበል ለመጠበቅም እንደሚረዳ፣ ከፈቃደ ሥጋ፣ ከተግባረ ዓለም፣ ከከንቱ ምኞት እና ሃሳብም እንደሚጠብቅ፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችንም እንድናፈራ እንደሚያግዘን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ጾም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፡፡ ጾም ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ተግባርና ሕግ እንዲሁም ግዴታቸውም ጭምር ነው፡፡ ያለጾም ክርስቲያንና መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም የሃይማኖት መገለጫ እና መሠረት ነው፡፡ ጾም ለግል ሕይወት ለሀገር ለቤተ ክርስቲያን ለቤተሰብ ብሎም ለዓለም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

እናም በአጭሩ፡-

  1. ጾም ሥጋን ለነፍስ ለማስገዛት ይረዳል፡፡

ሥጋችን ሁሉ ጊዜ ምቾትና ድሎትን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሥጋ ከመንፈስና ከነፍስ በላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሥጋ ሲሠለጥንብን የመንፈስ ተግባርን መሥራት ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን መወጣት መተግበር ንስሐ መግባት፤ ምሥጢራት ላይ መሳተፍ በጎና መልካም ሥራን መሥራት ቃለ እግዚአብሔርን መማር፤ መተግበር ያዳግተዋል፡፡ ይህ በተራው ነፍስንና መንፈስን ያቀጭጫል፤ ሕይወትንም ያሳጣል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለመዳን ጾም ትልቅ ልጓም በመሆን ያገለግላል፡፡ ጾም ሥጋን ለነፍስ ያስገዛል፡፡ ሁልጊዜ ስለነገረ እግዚአብሔር፣ ስለ መንፈሳዊነት እንድናስብ፣ ስለ ሕይወትና ሞት፣ ስለመልካም ሥራ፣ ስለ ቅድስና እና ስለ በረከት እንድናስብ ያደርጋል፡፡ ንስሐ እንድንገባ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን ሁሉ ሕይወቱን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት አለበት፡፡ ገላ.5፡16-17፣ ሮሜ.8፡5-6፡፡

የሥጋ ፈቃድ እና ተግባርን የሚፈጽሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይችሉም፡፡ ከዚህ ለመውጣት መንግሥቱን ለመውረስ ደግሞ ሕይወትን በጾም መምራት ያስፈልጋል፡፡ ሕይታቸውን ያለ ጾም ጸሎት እና ንስሐ የሚመሩ ሰዎች  የእነሱ ሕይወት መጨረሻው የዘለዓለም ሞት ነው፡፡ እናም ራስን ለመጠበቅ እናም መንግሥቱን ለመውስ መጾም ይኖርብናል፡፡

  1. ጾም ከእግዚአብሔር የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ ይረዳል፡፡

ክርስቲያን ያለ ጾም  ሕይወቱ ባዶ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር የምንፈልጋቸው ነገሮችን ለማግኘት እርሱን በጾም እንማጸናለን፡፡ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ ይቅርታን፤ ጤናን፤ በረከትን፤ የእርሱን ጠብቆቱን እንለምንበታለን፡፡ ከኃጢአት እንዲጠብቀን፣ በሃይማኖት እንዲያጸናን፣ በምግባር፤ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት፤ በምግባር እንዲያበረታን እርሱን እንማጸናለን፡፡ የሳሙኤል እናት ሐና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሰውን የሚያክብር፣ ታማኝ ታዛዥ ቅን ትሁት የሆነ ልጅን ያገኘችው በጾምና በጸሎት ሕይወት ነው፡፡ በቤቱ በመመላለስ ደጅ በመጥናት ሳትሰለች፣ ተስፋም ሳትቆርጥ በጽናት በእምነት በመለመን ነው፡፡ እኛም ከእርሱ የምንፈልገውን ነገር ማግኘት የምንችለው ያለ ትዕቢት በትዕግሥት በመለመን፣ በጽናትና በተስፋ በቤቱ በመጽናት ስንለምን ብቻ ነው 1ኛ.ሳሙ.2፡1፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የሆነውን ታቦትን የተቀበለው ከዐርባ ቀናት የጾምና የጸሎት ሕይወት በኋላ ነው፡፡ ዘጸ.34፡1-31፡፡ እኛም ዛሬ ለብዙ ችግሮቻችን ከእርሱ መልስን ለማግኘት ሕይወታችንን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት ይኖርብናል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ እና ዳንኤል ሃይማኖትን በምግባር ገልጸው ከሞት ባሕር የተሻገሩት ሕይወታቸውን በጾምና በጸሎት፣ እግዚአብሔርንም በመፍራት ይመሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬም እኛ ከማናውቃቸው ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ ሕይወትን በጾምና በጸሎት መምራት ያስፈልጋል፡፡

ጾም የልባችንን መሻት ለእግዚአብሔር ለመግለጽ ይረዳል፡፡ ስናውቅም ሆነ ሳናውቅ የምንሠራው ኃጢአት ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ከረድኤተ እግዚአብሔር፣ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያራቁታል፡፡ ስለዚህም ለምሕረት፣ ለቸርነት እና ለይቅርታ ማልቀስ ይኖርብናል፡፡ ጾም ከበደልና ከኃጢአት እንመለስ ዘንድ ንስሐን በመግባት ከእግዚአብሔር ምሕረት፤ ቸርነትና ይቅርታን ለማግኘት የምንፈጽመው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ ጾም በሃይማኖት ያበረታል፤ ከመከራ ሥጋና ነፍስም ያሻግራል፤ በጎ ምግባርንም ለመሥራት ያተጋል፡፡

ማጠቃለያ ፡-

የጾም መሠረታዊ ዓላማ ከምግብ ዓይነት መቆጠብ ከመመገብ እና ካለመመገብ ጋር የሚያያዝ ብቻ ሣይሆን ከምግብ በመራቅ በሚገኘው ውጤት ላይ ነው፡፡ ውጤቱም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ መንፈሳውያን መላእክትን  መስሎ መኖር ወይንም መሆን ነው፡፡ እንዲሁም ራስን፣ ዓለምን፣ ክፉ ሃሳብ፣ ተግባር እና ምኞትን በማሸነፍ መንፈሳዊ መሆን፣ ራስንም ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡

ከጾም ዋጋን ለማግኘት በዋናነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾማችንንም በፍቅር፣ በምግባር፣ በሃይማኖት እና በእምነት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ ለተራቡት ማሰብ፣ ለተጨነቁት መድረስ፣ ተሰፋ ላጡትም ተሰፋ መሆን ይኖርብናል፡፡ ጾማችንንም በንሰሐ ሕይወትና በጸሎት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ፣ ይልቁንም ከትዕቢት በመራቅ፣ ትሕትናንም ገንዘብ በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ ጾሙን ጹመን ለመንግሥቱ እንዲያበቃን ከክፉ ነገርም እንዲጠብቀን  የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *