ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ቁልፍ
በመ/ር ተመስገን ዘገዬ
እግዚአብሔር ሰውን ሕያው ሁኖ እንዲኖር በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮታል፡፡ ይህ ማለት ግን ሰው:- ኃጢአት የማይሠራ፣ ሞትም የማይስማማው፣ ባሕርይው ድካም የሌለበት እንደሆነ መናገር አይደለም፡፡
እግዚአብሔር ሰውን አእምሮ ሰጥቶ እንደ መላእክት ሕያው ሆኖ እንዲኖር ከፈጠረውና የጸጋ አምላክነትን ደርቦ ከአከበረው ኃጢአት ላለመሥራትና ትእዛዘ እግዚአብሔርን ባለመተላለፍ መጽናት ነበረበት፡፡ ነገር ግን አዳም ሕግን ተላለፈ፣ ቅጣትንም አስተናገደ፡፡ በዐዋቂ አእምሮው የፈጠረውን የአምላኩን ትእዛዝ መተላለፉን፣ መበደሉንና የሞት ሞትም እንደሚሞት በተረዳ ጊዜ ተፀፀተ፣ የንስሓ ዕንባም አነባ፡፡ እግዚአብሔርም በምሕረት ዐይኑ ተመልክቶትና ንስሓውን ተቀብሎ ከልጅ ልጁ ተወልዶ ወደ ቀደመ ክብሩ እንደሚመልሰው ቃል ኪዳን ገባለት፡፡
ለመሆኑ ንስሓ ምንድነው?
ንስሓ የቃሉ ፍቺን በተመለከተ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት “ሐዘን፣ ፀፀፀት፣ ቁጭት፣ ምላሽ፣ መቀጮ፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡
ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሓ የሚገባ ሰው ከሠራው ኃጢአት በሙሉ ልቡ ይመለስ ዘንድ ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነውና ወደ እርሱ ለሚመለሱት ሁሉ ይቅር ባይ ነው፡፡ አይሁድን “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፣ እርሷንም አልጠበቃችሁም፡፡ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፡፡” (ሚል. ፫፥፯) በማለት ከበደላቸው ይነጹ፣ በይቅርታውም ይጎበኙ ዘንድ ይጠራቸዋል፡፡
ቅዱስ ያዕቆብም “ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” በማለት ኃጢአት የነፍስ ሞት፣ ንስሓ ደግሞ ሕይወት መሆኑን አስተምሯል፡፡ (ያዕ. ፭፥፳) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም “እኛ … ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን” በማለት ምስክርነቱን ገልጧል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፬)
ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ባስተማረው በሁለተኛው መልእክቱ ከበደላቸው ርቀው፣ ንስሓ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቁ ዘንድ ሲያመለክታቸው ” … ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን” በማለት ተናግሯቸዋል፡፡ (፪ኛ ቆሮ.፭፥፳)
ንስሓ ከኃጢአት ባርነት ነፃ መውጣት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው፡፡ ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም … እንግዲህ ልጁ (ወልደ እግዚአብሔር) አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ” (ዮሐ. ፰፥፴፬—፴፮) በማለት ከኃጢአት ባርነት መውጣት የሚቻለው ከእግዚአብሔር በተሰጠች ንስሓ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሰው በፍጹም ልቡ ካልተመለሰ ስለ ኃጢአቱ እያዘነ ሊያለቅስ አይችልም፡፡ንስሓ ስለ አለፈው ስህተት(ኃጢአት) አብዝቶ ማልቀስ፣ ያለፈውንም የኃጢአት ኑሮ ማውገዝና መኰነን መሆኑን መረዳት ይገባል። ነቢዩ ኢዩኤል “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት የሚመክረን ለዚህ ነው፡፡ (ኢዩ. ፪፥፲፪)
ንስሓ ፍጹም የሆነ የሕይወት ለውጥ እንጂ ጊዜያዊ ስሜት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል ንስሓ ፍጹም ወደሆነ የሕይወት ለውጥ (ከኃጢአት ወደ ጽድቅ) የምንመለስበት እንጂ በጊዜያዊ ስሜት ላይ ተመሠርተን የምንፈጽመው አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፪)
ንስሓ ኃጢአት ሲሠሩ ከመኖር ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን (መምረጥ) ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚወደውንና የሚደስበትን፣ ጽድቅ የሚገኝበትን፣ መልካም ምግባርና ትሩፋት በመሥራት እርሱን በማምለክና በማገልገል መኖርን መምረጥ ነው፡። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ለእኔስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ምርጫውን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጓል፡፡ (መዝ. ፸፫፥፳፰)
ንስሓ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያስችል ወደ መንግሥተ እግዚአብሔርም የሚያስገባ ቁልፍ ነው፡። ስለዚህ ንስሓ ከሚመጣው መከራና ሐዘን መዳኛ ወይም ማምለጫ መንገድ ነው፡። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የነነዌ ሰዎች ከኃጢአታቸው የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ እንደመጣባቸው በነቢዩ ዮናስ አማካኝነት በተሰበከላቸው ጊዜ ሊወርድ ከነበረው የእሳት ዝናብ ለመዳን የቻሉት በንስሓ እና በልቅሶ ነው፡፡ (ዮና. ፫፥፲) በነቢዩ ኤርምያስም “አሁንም መንገዳችሁን፣ ሥራችሁን አሳምሩ፣ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተወዋል፡፡” (ኤር. ፳፮፥፲፫) በማለት የገለጸው ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡
ንስሓ ለዕርቅ የተዘረጋ የእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን የቀደመ ኃጢአት ይቅር የሚልበትና የሚያጥብበት መንፈሳዊ ምሥጢር ነው፡፡ ሰው በንስሓ የታጠበ እንደሆነ ከበረዶ ይልቅ ይነጻል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፤ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ … በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” እንዲል (መዝ. ፶፥፪-፯)
ንስሓ የሰማያዊም የምድራዊም ደስታ ምንጭ ነው። አንድ ኃጢአተኛ ንስሓ ቢገባ በሰማይ ደስታ እንደሚደረግ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል፡፡ … ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል” በማለት እንደተገለጸው፡፡ (ሉቃ. ፲፭፥፯-፲)
ንስሓ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚሰጥበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የሚታየው አገልግሎት የተነሣሒው ፀፀትና ኑዛዜ፣ የቄሱ የንስሓ ጸሎት ሲሆን፤ የማይታየው ጸጋ ደግሞ ተነሳሒው የሚያገኘው ስርየተ ኃጢአት ነው፡፡ በአጠቃላይ ንስሓ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የድኅነት ቁልፍ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!